የበለጠ ትኩረት ለትምህርት ሥርዓቱ ስብራት!

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ሲገለጽ “መርዶ” ሆኖ የሚከርመው የተማሪዎች ውጤት ጉዳይ ነው ።ችግሩ ለምን በየዓመቱ አነጋጋሪ ይሆናል ? ውጤት ሲወጣ ብቻ ለምን ችግሩን ጮክ ብለን አንነጋገርበታለን።

ከችግሩ ስፋት እና ጥልቀት ፣ እያስከተለ ካለው እና ሊያስከትም ከሚችለው ሀገራዊ አደጋ አኳያ ፣ ችግሩ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፈተናዎችን ይዞ መምጣቱ ተገማች ነው። ከዚህ የተነሳም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለጉ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ አይደለም።

የተማሪዎች ውጤት ማጣት ውድቀቱ የዛ ወይም የዛች ተማሪ ብቻ ነው እንዴ? አይደለም !። እንደ ሀገር ስናየው የወደቀው ሀገር ነው። እንደመምህር ስናየው የወደቀው ስንት ዓመት ሙሉ “ሲያስተምር የከረመው” መምህር ነው።

የወደቀው ስንት ዓመት ሙሉ መከራውን ሲያይ ፣ ከሌላው ገንዘብ ከፍሎ ልብስ አልብሶ ፣ ቀለብ ሰፍሮ፣ ጎንበስ ቀና ብሎ አሳድጎና አስተምሮ የልጁን ውጤት የሚጠብቀው ወላጅ ነው። የወደቀው ምንም ተማሪ ሳያሳልፍ የቀረው ትምህርት ቤት ነው። የወደቀው 12 ዓመት ሙሉ የደከመበት ልፋቱ በማይሆን ውጤት የደመደመው ተማሪ ነው።

የተማሪዎች መውደቅ ላይ ድርሻ የሌለው የለም ብል በድፍረት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ለተማሪዎች የትምህርት ላይ ቆይታ በርካታ አሻራቸውን ያኖሩና የሚያኖሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በርካታ ናቸው። ስለዚህ ውድቀቱ የሁሉም ነው። እናም አሁን ምን ይሁን ? ተማሪዎችን ወደ ውጤታማነት እንዴት እንመልስ በሚለው ዙሪያ ላይ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም ?

አሁን ለተማሪዎች ውጤት በዚህ ልክ ማሽቆልቆል ምክንያት መደርደር ጊዜው አይደለም። ጊዜው እንዴት አድርገን የትምህርት ጥራትን እናስጠብቅ በሚለው ዙሪያ ላይ መምከር ነው። ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት። ተማሪው ደብተር ይዞ ትምህርት ቤት ስለዋለ ብቻ ተ ምሯል ማለት አይደለም።

መማር ያለበትንና በትምህርት ደረጃው ማወቅ የሚገባውን እውቀት ጨብጧል ወይ የሚለውን መመለስ ያለበት ራሱ ተማሪው ነው። ከመምህሩ ያገኘውን እውቀት በሚገባው ልክ አጥንቶና ተረድቶ ገብቶታል ወይም ነገ ለሚቀመጥበት ፈተና ብቁ ዝግጅት እያደረገ ነወይ ብሎ ራሱን መጠየቅ ያለበት ተማሪው ነው።

ተማሪ የትኛውም ትምህርት ቤት ቢገባ የትኛውም አዋቂ የተባለ መምህር ቢያስተምረው የራሱ ቆራጥነትና ጥረት ካልታከለበት ውጤት ያመጣል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ለተማሪው ውጤታማ መሆን ደግሞ ተማሪው ብቻ ወሳኝ እንዳልሆነም መረዳት ያስፈልጋል።

ሥራውን በኃላፊነት ስሜት የሚሰራ መምህርነት ሥራ(ደመወዝ ማግኛ) ሳይሆን ሙያ ነው፤ ተማሪ መቅረጽ ነው ብሎ በእውነት ስለእውነት ለተማሪ ውጤት የሚሰራ መምህር ሊኖረን ይገባል። አሁን አሁን የሚታዩ አብዛኛው መምህራን ሙያውን የደመወዝ ማግኛ ብቻ ያደረጉ የሚመስሉ ናቸው፤ብዙም ሙያዊ ኃላፊነት ሲሰማቸው አይታዩም።

ሲመቻቸው ክፍል ይገባሉ፤ ገብተውም ተማሪ ይወቅ አይወቅ ፣ ትምህርቱን ይከታተል አይከታተል ጉዳያቸው ሳይመስላቸው የቆይታቸውን ክፍለ ጊዜ በዋዛ ፈዛዛ አሳልፈው ይወጣሉ። በማይመለከታቸው ፖለቲካ ውስጥ የሚዳክሩ አይጠፉም።

የተጠራቀመ ትምህርት በአንድና በሁለት ክፍለ ጊዜ አካክሰው ብታውቁ እወቁ የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በዚህ ሁኔታ ያስተማረ መምህርና በዚህ ሁኔታ ሊማር ክፍል የተገኘ ተማሪ የምንጠብቀውን ውጤት ያመጣል ብሎ ማሰብ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደሚባለው ነው ።

መምህር የቀለም አባት ነው። በቀለምም በስነምግባርም ተማሪን ማረቅና ማሳወቅ ይጠበቅበታል። የሚቀርጸው ተማሪ የነገው ሀገር ተረካቢ መሆኑን መረዳት አለበት። መምህርነት ከደመወዝ በላይ መሆኑን አምኖ መስራት አለበት። ፈቅዶና ወዶ የተሰማራበት ሙያ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት።

በተማሪዎቹ ላይ የሚገለጸው ውጤት የእሱ የሥራ ውጤት መሆኑን መረዳት ይጠበቅበታል። ጥሩ ውጤት ሲመጣ የልፋቱና የጥረቱ ውጤት በመሆኑ መደሰት፤ የተማሪ ውድቀትም የእሱ አስተዋጽኦ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ውጤት ሲመጣ ማዘን ግን በራሱ ብቻውን ዋጋ የለውምና ለቀጣዩ ሥራ መጠንከር በቆራጥነት መንቀሳቀስ ነው ወሳኙ። ዛሬ ዓለም አንድ ሆኗል። ቴክኖሎጂው ፣ ቋንቋውም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ተወዳድሮ ማሸነፍን ይጠይቃል። ዘመኑ የውድድር ነው። ለዚህ ብቁ የሆነ ዜጋ ማፍራት የሚጠበቀው ከመምህሩ ነው።

አሁንም የተማሪዎች ውጤት መውረድ የተማሪው ፣ የመምህሩ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ይሆናል። ምክንያቱም ተማሪው በሰዓቱ ወደ ትምህርት ቤት ሄዶና ተመልሶ ምን እየሰራ ነው? ትምህርት ቤት ሄዶስ ምን ተምሮ መጣ ? ብሎ መከታተልና መቆጣጠር ያለበት ወላጅ ነው።

አንዳንድ ወላጅ ልጁን ውድ ክፍያ የሚከፈልበት ትምህርት ቤት ስላስገባውና አስጠኚ ስለቀጠረለት ብቻ ልጁን ያስተማረ ይመስለዋል። ግን አይደለም ልጁ በወጪው ልክ እየተማረ ነወይ? በሚጠበቅበት ልክ እውቀት ጨብጧል ወይ? ብሎ ክትትል ማድረግ የወላጅ ግዴታ ነው።

ወላጅ ያልተከታተለውን ልጅ መምህር ብቻ ያበቃዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ብዙ ገንዘብ ስላወጡ ብቻ ልጆቼን አስተምሬያለሁ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በወራጅ ውሃ ላይ ገንዘብን እንደመነስነስ ይቆጠራል። ሌላው ቀርቶ ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል የአካባቢ ማህበረሰብ ጭምር ተጠያቂነት አለበት።

ተማሪዎች ትምህርት ቤት ብለው ወጥተው በምን አይነት ቦታ በምን አይነት ስነምግባር ውስጥ እያሳለፉ ናቸው የሚለው መጠየቅ አለበት። ምንም አይነት ጉዳይ ከማህበረሰብ እይታ ውጪ ሊሆን አይችልም። ዩኒፎርም የለበሱ ልጆች በየመዝናኛ ፣ በየመጠጥ ቤቱ ፣በየፑል ቤቱ፣ በየሲኒማ ቤቱ ፣ በየስፖርት ውድድር ቤቶች… ይታያሉ።

ሕግ አስከባሪ የሚባለው አካል ጭምር አይቶ እንዳላየ ያልፋል። በእነዚህና በሌሎችም ተደራራቢ ምክንያቶች የተማሪዎች ውጤት ያሽቆለቁላል። ተማሪው ተማሪ መሆኑ ቀርቶ ከስነምግባር ያፈነገጠ ፣ ዋልጌ ይሆናል።

“ከ1300 በላይ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላሳለፉም” ሲባል ይሄ እንደ ጀግንነት ጆሮ ሰጥተን የምንሰማው ዜና መሆን የለበትም። በጣም አስደንጋጭ እንደ ሀገርም ቆም ብለን የትምህርት ፖሊሲያችንን፣ መምህራኖቻችንን፣ተማሪዎቻችንን ፣ ትምህርት ቤቶቻችንን አይናችንን ከፍተን እንድናይ የሚያስገድደን ይሆናል። ትልቅ ውሳኔንም ይጠይቃል።

ተማሪው እስካሁን ድረስ ክፍል ቆጥሮ እዚህ ደረጃ የደረሰው በኩረጃ ነበር ? በመምህራን ያልሰሩት ውጤት እየተሰጣቸው ነበር? ሌሎች ከክፍል ወደ ክፍል የማዛወሪያ መንገዶች ነበሩ ማለት ነው ብለን እንድንፈትሽ እንገደዳለን። አሁንም በዚህ ውስጥ ተማሪው፣ መምህሩ፣ ወላጅ፣ የትምህርት ቤቱ አስተዳደሮችና የትምህርት ፖሊሲው ሁሉ ይነሳሉ። ይብጠለጠላሉ።

በግለሰብ ደረጃ ድክመት ሊኖር ይችላል። በእዚህን ያህል ትምህርት ቤቶች የተፈተኑ ተማሪዎች በሙሉ ወድቀዋል ማለት ግን ከባድ ነገር ነው። በእኛ ሀገር አልተለመደም እንጂ ይህን ውጤት የሰማና ያየ የሥራ ኃላፊ ፣ መምህር፣ የትምህርት ማህበረሰብ ሥራውን መልቀቅ ነበረበት።

ዘርፉን በኃላፊነት የሚመራው የመንግሥት አካልም አስተማሪ እርምጃ መውሰድ፤ የተጠያቂነት ሥርዓት መፍጠር ይጠበቅበታል። ችግሩ የአንድ ወገን /የተማሪው ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ። ለችግሩ ሁላችንም ባለድርሻ ነን። አሁን ከመወቃቀስ ወጥተን የትምህርት ሥርዓቱን ስብራት እንዴት እንጠግን፤ሀገር እና ትውልድን ከዚህ ችግር እንዴት እንታደግ ለሚለው ትኩረት ሰጥተን በጋራ ልንቀሳቀስ ይገባል።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን መስከረም 9/2017 ዓ.ም

Recommended For You