አምባሳደሮች ዓለም አቀፋዊ አዝማሚያዎችን በመረዳት ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ ውስጥ በሪፖርት ሳይሆን በውጤት የሚለካ ትርፍ ማምጣት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጠው አቅጣጫ ትክክለኛ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የአምባሳደርነት ምደባ ጡረታ መውጫ፣ ጤና ሲጓደል መታከሚያና ከፖለቲካ ማግልያ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እራሱን በማሻሻል እንደገና ተዋቅሯል፡፡ ለብዙ ዓመታት ተልከው የተረሱ ዲፕሎማቶችን በመጥራት ጭምር አስተካክሏል፡፡ ባለሙያዎች ከበፊቱ በተሻለ መድቧል፡፡ በዲፕሎማሲ ሙያ ራሳቸውን ያሳደጉና ሥራውን በደንብ የሚያውቁት ባለሙያዎች ገብተዋል፡፡ በቀጣይም እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ቅድሚያ የሚሰጠው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ነው ያሉት አቶ መላኩ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪስትን መሳብ፣ ንግድን ማቀላጠፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀዳሚ አቅጣጫ ተብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከምንም በላይ ከሪፖርት ወጥተው በውጤት እንደሚመዘኑ መቀመጡ ዲፕሎማቶቹ እንዲያርፉ ሳይሆን ነቅተው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው፡፡
ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዲፕሎማቶች በትኩረት እንዲሰሩት ያስቀመጡት በዳያስፖራዎች ዙሪያ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዲፕሎማቶችና በዳያስፖራዎች መካከል አለመግባባት ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጡ በኋላ ይህ ተቀይሯል፡፡ አሁን በአምባሳደሮቹ እንዲሰሩ የተሰጠው አቅጣጫ በውጭ አገር ያለውን የዜጎችን እውቀትና ሀብት ለመጠቀም መስራት እንዳለባቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ያለውን ሁኔታ በማሳወቅ በሁሉም መስክ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡
አሁን ከተደረገው የመዋቅር ማሻሻያ በተጨማሪም የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲው ክፍተት ስለሚታይበት ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያበረከት ስላለው ቱሪዝም ምንም የሚያስቀምጠው ነገር የለም፡፡ ከጎረቤት አገራት ስላለው ድንበርም በግልጽ የሚያስቀምጠው ነገር የለም፡፡ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ አገራትም የተዘነጉ እንዳሉ በማንሳት በፖሊሲው ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ክፍተቶችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና ስትራቴጂክ ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰይፈ ኃይሉ፤ ቀደም ሲል የነበረው የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማሻሻያ ሳይደረግ ተቋሙን ማሻሻያ ማድረግና አምባሳደሮችን መመደብ የተለየ ውጤት እንደማያመጣ ይናገራሉ፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ምንም እንኳ ግልፅ የሆነ የፖሊሲ ለውጥ ባይደረግም በአዲሱ አመራር ቀደም ሲል ከነበረው ፖሊሲ በተለይ የአተገባበር ለውጦች አሉ፡፡ ይህን የተግባር ለውጥ፣ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በመተንተን የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ወደ ሥራ መገባት አለበትም ይላሉ፡፡
ቀደም ሲል የነበረው ፖሊሲ የውስጥ ኃይል ከተጠናከረ የውጭ ተፅዕኖን መቋቋም ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም በአገራዊ በኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማ ሥራ ቢሰራም በዴሞክራታይዜሽንና አገራዊ አንድነት በማስፈን ጉድለት አለ፡፡ የጎረቤትና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችም ተቀይረዋል፡፡ ምንም እንኳ ሙሉ ለሙሉ ፈር ይዟል ባይባልም ባለፉት ዓመታት በጠላትነት የፈረጅናቸው እንደ ኤርትራ ያሉ አገራት፤ ጠላትም ወዳጅም ያልነበሩት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት በወዳጅነት ካርታ ውስጥ ገብተዋል፡፡
የጎረቤትም ሆነ የውጭ አገራት ተጽዕኖ ቀድሞ ከነበረው በአካባቢያችን ጠንክሯል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ ፖሊሲ መነሻነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተተንትኖ በግልጽ አቅጣጫ ተቀምጦ መንግሥት ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ በተረፈ ግን አምባሳደሮችን መመደብ በፊትም ያለ ነው፤ አሁንም የተለየ ነገር የሌለው መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
መንግሥት ፖሊሲውን መከለስ አለበት ብሎ እምነት ይዞ ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መውጣት አለበት፡፡ አሁን ግን መንግሥት በተግባር ከበፊቱ ፖሊሲ አንዳንድ ጉዳዮች በተለየ መንገድ እየሄደ ነው፡፡ የሚወስዳቸው የተግባር እርምጃዎች አንዳንዶቹ መልካም ቢሆኑም ገዥ ፖሊሲ ሆኖ ወጥቶ በጠንካራ ቁጥጥርና ሥርዓት መመራት አለበት፡፡ ይህን የሚፈጽሙ ባለሙያዎችና መዋቅር መዘርጋት ተገቢነት እንዳለው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰይፈ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ሲሳይ አሰምሬ በበኩላቸው፣ ፖሊሲው አንዳንድ ትናንሽ ማሻሻያዎች ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም መሰረታዊ ችግሩ የፖሊሲ አይደለም፡፡ ዋናው የውጭ ጉዳይ የአፈጻጸም ችግር ነው፡፡ የሚመደቡት አምባሳደሮች በሙያው ያልሰለጠኑ ሹመኞች መሆናቸው ነው፡፡ አዲሱ አመራር የተቋሙን መዋቅር ማስተካከሉና በሙያው የተማሩና ልምድ ያላቸው አምባሳደሮችን እንዲመጡ ማድረጉ የውጭ ግንኙነት ያሳልጣል በማለት ከረዳት ፕሮፌሰሩ የተለየ ሀሳብ ያራምዳሉ፡፡
አዲሱ አመራር ለውጭ ግንኙነት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ከዳያስፖራዎችና ከውጭው ዓለም መልካም ግንኙነትና ተቀባይነት አትርፏል፡፡ ይህን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ አገሪቱ እንድትጠቀም በእውቀት የሚያገለግሉና ብቁ ባለሙያዎችን ከዋናው መሥሪያ ቤት እስከ ሚሲዮኖች መመደብ ተገቢነት ያለው ነው፡፡
ኢትዮጵያ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ያላትን እውቅና ያክል በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስኬታማ አይደለችም፡፡ በፖለቲካ ያለውን እውቅና በኢኮኖሚ ለመድገም አሁን የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይገባል፡፡ የአገሪቱ የዲፕሎማሲ መዋቅር ጠባብ በመሆኑ የአገሪቱን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አገራት ላይ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎችን መክፈት ይገባል፡፡ በአፍሪካ ያለውን ግንኙነት በተለይም በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማስፋት እንደሚገባ መምህሩ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ‹‹አም ባሳደሮች ሲሾሙ ድግስ ነው፡፡ የሚመደቡበት ቦታ ሲያውቁ ግን ጸብና ጭቅጭቅ ይመጣል፡፡ ይህም የሆነው አምባሳደርነት የጡረታ፣ የመዝናኛ፣ ጥቅም የማግኛና የመጨረሻ አድርጎ ስለሚወሰድ ነው፡፡ አምባሳደርነት በሚመች ቦታ ብቻ ሳይሆን በማይመች ቦታ ኢትዮጵያን ነግዶ ትርፋማ ማድረግ ነው›› ብለዋል፡፡
አምባሳደር የሚሄደው ለግሉ ሳይሆን ለአገር ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ትርፋማ ለማድረግ ነው፡፡ ሥራውንም ሲሰራ የግል ምቾትና ጥቅም ሁለተኛ አድርጎ መወሰድ አለበት፡፡ አምባሳደር ስብሰባ አደረግሁ ብሎ ሪፖርት ማድረግ ሳይሆን ምን ያህል ባለሃብት አገር ቤት አምጥቶ ልማት ላይ እንዳሳተፈና በሌሎች ሥራዎች ውጤት ነው መለካት ያለበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት አገሪቱ ያላትን አማራጭ ለዓለም ገበያ በመሸጥ ቦታ እንዲኖራት ማድረግ ነው፡፡ አገሪቱ በትክክል የሚያቀርብ አምባሳደር ከሌላት በዓለም ገበያ ቦታ አይኖራትም፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ጥንካሬ ላይ በመቆም የአገሪቱን ፍላጎት ለዓለም ገበያ መሸጥ የሚያስችል ብቃት በመያዝ ለአገራቸው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አምባሳደሮች በተመደቡበት አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብት በማስከበር፣ ኢትዮጵያዊነት ክብር መሆኑን ማሳየት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ኤምባሲዎችንም ለዜጎች በደስታ፣በኀዘንና በንግድ ሥራ ለሁሉም ኢትዮጵያዊው ክፍት ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡ በተለይም አፍሪካውያን በማስተባበር ለጥቅማቸው እንዲቆሙ በማድረግ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመመስረትና በሰላም ማስከበር የደመቀ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡
ይህ የኢትዮጵያ የደመቀ የዲፕሎማሲ ታሪክ ይቀጥልና ይሰፋ ዘንድ አሁንም ፖሊስን በማሻሻልም ሆነ መዋቀር በመለወጥ ወይም የሚሰማሩ ባለሙ ያዎችን በማሳተፍ ሰፊ ሥራ መከናወን ይገባዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ