የመጀመሪያዋ የሴት ዲፕሎማት፣ የሴቶች መብት ተሟጋች ፣ ጀግናና ፀረ-ፋሺስት አርበኛ ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ የመጽሐፍ ደራሲና የመጀመሪያዋ የሴት ፓርላማ አባል ክብርት ዶክተር ስንዱ ገብሩ በ93 ዓመታቸው ያረፉት ከ11 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም ነበር።
ስንዱ ገብሩ በሸዋ ክፍለ ሀገር በመናገሻ አውራጃ በአዲስ ዓለም ከተማ ጥር 6 ቀን 1908 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸው ታዋቂው ዲፕሎማት፣ የመጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ፤ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ከወጡ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፤ በዳግማዊ ምኒልክ ሹመትም የመጀመሪያው የጎንደር ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት ከንቲባ ገብሩ ደስታ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ ካሣዬ ኤሌምቱ ይባላሉ። ታዋቂዋ የረቂቅ ሙዚቃ ደራሲ የውብዳር ገብሩ (እማሆይ ጽጌ ማርያም) ታናሽ እህታቸው ናቸው።
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰበት ወቅት ቤታቸው አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የአማርኛን ትምህረት ከፊደል መቁጠር እስከ ዳዊት መድገም ተምረዋል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትለዋል።
ከንቲባ ገብሩ ወጣቷን ስንዱን እያስከተሉ ቤተ መንግሥትም ሆነ ሌላ ሥፍራዎች ይወስዷት እንደነበረና ከጊዜው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጋር እንዳስተዋወቋት ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። ከዕለታት አንድ ቀን ታዳጊዋ ስንዱ አንዲት የድብ አሻንጉሊት ይዛ እጅ ለመንሳት ወደ ቤተ-መንግሥት ሄደች። ወደ አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ፊት ቀርባም ‹‹ይቺ አሻንጉሊት ከተሠራችበት አገር ለትምህርት ይላኩኝ›› ብላ ጠየቀቻቸው። አልጋ ወራሹም ፈገግ ብለው አሻንጉሊቷን ተቀብለው አገላብጠው ተመለከቷት። አሻንጉሊቷ የስዊዝ ስሪት ነበረች። አልጋ ወራሹ ‹‹እሺ እልክሻለሁ›› ብለው መለሱላት። ስንዱም ‹‹አማርኛ እንዳልረሳ አንዷ እህቴ አብራኝ ትሂድ›› ብላ ፈቃድ ጠየቀች።
አልጋ ወራሹም የወጣቷን ብልሀትና ትጋት በማድነቅ ወደ ፈረንጅ አገር ተልከው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ባዘዙት መሠረት ስንዱ እና ታናሽ እህቷ የውዳብር ገብሩ በ1921 ዓ.ም ውጭ ሄዱ። ከንቲባ ገብሩ ደስታ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለኖረው ማርቲን ፍላድ ለተባለው ጀርመናዊ ‹‹ልጆቼን ተከታተልልኝ፤ ወኪል አባት ሁንልኝ፤ እንደእኔ ሆነህ ወደ ትምህርት ገበታቸው ስደድልኝ›› ብለው መልዕክት ላኩበት። ማርቲን ፍላድም እነስንዱን ተቀብሎ የቤተሰቡ አባል እንዲሆኑ አደረጋቸው። አባታቸው ከንቲባ ገብሩ ለሥራ ጉዳይ ወደ አውሮፓ በሚያመሩበት ወቅትም ልጆቻቸውን ይጠይቋቸው ነበር።
ስንዱ ገብሩ ስዊዝ ከደረሱ በኋላ ኑሮው ስላልተመቻቸውና ትምህርት ይሰጥበት የነበረውን የጀርመንኛ ቋንቋ ስላልወደዱት ወደ ፈረንሳይ አቅንተው ትምህርታቸውን ቀጠለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል። ውጭ አገር ቆይተው የሕግ ትምህርት መማር ጀምረው የነበረ ቢሆንም ፍላጎታቸው ወደ ሥነጽሑፍ በማዘንበሉ ሌላ ትምህርት ቤት ገብተው የሥርዓተ ትምህርት ጥናትና ሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም ፈረንሣይኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አጥንተው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። አገር ቤት ከገቡ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው ቅዱስጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ውስጥ ፈረንሳይኛ ቋንቋን ፣ ቁጥርንና የአማርኛ ድርሰት አጻጻፍን አስተምረዋል።
ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ስንዱ ገብሩ ሆለታ ውስጥ ከሚገኙ የጦር መኮንኖች ጋር ተቀላቅለው ፋሺስቶችን ለመፋለም ወደ ቦሬ ሲያቀኑ በፋሽስት እጅ ከመውደቅ ለጥቂት ተርፈው ጎሬ ከሰፈረው ከልዑል ራስ እምሩ ጦር ጋር ተቀላቅለዋል። በዚያም ሳሉ በጦርነቱ የሚጎዱ አርበኞችን ለማከም የሚሆን ቀይ መስቀል ለማቋቋም መፈለጋቸውን ለራስ እምሩ ሲያማክሯቸው 500 ብር ስለሰጧቸው ቀይ መስቀል አቋቁመው አርበኞችን መርዳት ጀመሩ። ወዲያው ግን እርሳቸው ተቀላቅለውት የነበረው የ “ጥቁር አንበሳ” ጦር በጣሊያን ጦር በመመታቱ ተማርከው በእስር ወደ አዲስ አበባ ተወስደው የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ተደረገ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ወንድማቸው መሸሻ ገብሩ አሉበት በመባል ይታሰሱ ስለነበር ወንድማቸውን ከአደጋ ለማዳን ሲሞክሩ በድጋሚ በፋሺስቶች እጅ ወደቀው ግራዚያኒ ይኖርበት የነበረው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ ታሰሩ። ቀጥሎም ወደ አሥመራ ከዚያም ወደ ምጽዋ ተወሰዱ። ከምጽዋ ወደብ ከህታቸው እማሆይ ጽጌ ማሪያምና ከሌሎች 306 አስረኞች ጋር በመርከብ “አዚናራ” ወደተባለች የጣሊያን እስር ቤት ተወስደው ዘጠኝ ወራት ታስረዋል። ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእንደዚህ ያለ ተግባር ላይ እንዳይሰማሩ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ማስጠንቀቂያወን ከምንም ሳይቆጥሩ አርበኞችን በግጥምና በወኔ ቀስቃሽ ጽሑፎች በማበረታታት ፤ መረጃ በማቀበልና መሣሪያ በማዳረስ የአርበኝነት ተግባር ፈጽመዋል።
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ ስንዱ ለሁለት ዓመታት ደሴ ከተማ የሚገኘው የወይዘሮ ስኂን ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነትና በርዕሰ መምህርነት ሠርተዋል።
ስንዱ ገብሩ ከ1948 ዓ.ም እስከ 1952 ዓ.ም ድረስ የመጀመሪያዋ የሴት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባልና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር በመሆን አገልግለዋል። የምክር ቤቱ አባል በነበሩበት ወቅት የሴቶች እኩልነት በማይከበርበት ዘመን የሴቶችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበርና እኩልነትን በሕግ ለማረጋገጥ ብዙ የታገሉ ጀግኒት ነበሩ።
የፍትሐ ብሔር ሕግ ሲረቀቅ የሴቶችን የቤተሰብ ስም በተመለከተ የሕጉ አርቃቂዎች የውጭውን ሕግ እንዳለ ገልብጠው አምጥተውት ነበር። በዚህ ረቂቅ ሕግ መሠረት “ሴት ባል ስታገባ በባሏ ስም ትጠራ” የሚል ድንጋጌ ነበረው። ወይዘሮ ስንዱ ይህን አንቀጽ ተቃውመው ሴት ልጅ መጠራት ያለባት በራሷ ቤተ-ዘመድ ስም እንጅ በባሏ ስም መሆን የለበትም ብለው በጽኑ ተከራከሩ። ሃሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶም የ1952 የኢትዮጵያ ፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 40 ላይ ያገባች ሴት በራሷ ቤተ-ዘመድ ስም ትጠራለች ተብሎ አንቀጹ ተስተካክሎ ታወጀ።
የፍትሐ ብሔር ሕጉ ቤተሰብን በተመለከተም ወይዘሮ ስንዱ ጉዳዩን በማንሳታቸው ብዙ ክርክር ተደርጎበት ነበር። ከዚህ መካከል ባል ምን ያክል ብድር መበደር ይችላል የሚለው አንዱ ነበር። ወይዘሮ ስንዱ “ባል ከሚስቱ እውቀት ውጪ ከአምስት መቶ ብር በላይ እንዳይበደር“ የሚል ሃሳብ አቀረቡ። ከብዙ ክርክር በኋላ ጉዳዩ ከቁም ነገር ውስጥ ገብቶ በሕግ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በዚህ መሠረት የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 658 ላይ “ከተጋቢዎች አንዱ (ባል/ሚስት) ሌላኛው ተጋቢ ሳያውቅ/ሳይስማማ ከአንድ መቶ ብር በላይ መበደር አይችልም” ተብሎ ተደንግጓል። በ1992 ዓ.ም የተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ ይህን ድንጋጌ ሃሳቡን በመውሰድ የገንዘቡን መጠን ከፍ አድርጎ ባል/ሚስት ሁለቱም ስምምነት ሳያደርጉ ከአምስት መቶ ብር በላይ መበደር አይችሉም ብሎ በአንቀጽ 68(1)(መ) ሥር አስቀምጦታል።
ወይዘሮ ስንዱ ከፍ ያለ ተቃውሞ አቅርበውባቸው የተረቱባቸው ጉዳዮችም ነበሩ። በወቅቱ የሕግ መምሪያ ም/ቤት አባል የነበሩት ፊታውራሪ አመዴ ለማ ባል/ሚስት በትዳራቸው ላይ ስለሚኖራቸው ሥልጣን ክርክር በተደረገበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ተርከውታል።
ሹም ባል ይሆናል። ሚስት ለባሏ ታዛዥ መሆን አለባት። እንዲህ እንዲህ የሚል ሴቶችን የሚጫኑ አንቀጾች አሉ። ይሄንን ወይዘሮ ስንዱ የዚያን ጊዜ ቀደም ብለው የነቁ ስለነበረ “እንዴ! ለምን አንድ ጊዜ እኛን ንጉሠ ነገሥቱ እኩል ናችሁ ካሉን በኋላ በእራሳችን ስምምነት እንጂ በሕግ ሴቶችን የሚጨቁን ሕግ መግባት የለበትም” ብለው ተከራከሩ። እሺ ድምፅ ይሰጥበት ሲባል አንድ ሰው ብቻ ደገፋቸው። ተናደዱ። “እናንተ እዚህ ምክር ቤት የመጣችሁ ወንዶች፤ ስትመረጡ ሴትና ወንደ ነበር የመረጣችሁ፣ ግን ልትመክሩ የመጣችሁት ለወንዶች እንጂ ለሴቶች እንዳልሆነ ታዝቤአችኋለሁ። ይህ ዛሬ እናንተ የሰጣችሁት ውሳኔ፣ ከአንድ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ብዙ ሴቶች ገብተው ይገለብጡታል እና ዘለቄታ የለውም።” እነዚህ ክርክሮች በወንዶች የበላይነት አስተሳሰብ ሕግ ሆነው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 635 እና 641 ተደንግገው ይገኛሉ። እነዚህ ድንጋጌዎች ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ብቻቸውን ተከራክረው በድምፅ ተሸንፈው /ታፍነው ማለት ይሻላል/ የተረቱባቸው ድንጋጌዎች ናቸው። የቤተሰብ ሕጉ በ1992 ዓ.ም ሲሻሻል ግን ባል እና ሚስት ቤታቸውን እኩል የማስተዳደር መብት በሕግ ተረጋገጦ የወይዘሮ ስንዱ ትንቢታዊ ንግግር ተፈጽሟል።
ከ1966 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ ወይዘሮ ስንዱ ሙሉ ጊዜያቸውን ያዋሉት በሥነ-ጽሑፍ ሥራ ላይ ነበር። ብዙ የተውኔት እና የታሪክ መጽሐፍትን ፅፈው በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መጽሐፍት እንዲቀመጡ አድርገዋል። ከ1966 ዓ.ም በኋላ ከፃፏቸው መካከል ‹‹ራስ መኰንን ከአረጋዊ መካር ጋር›› ፣ ‹‹ጥቁር አንበሳ››፣ ‹‹ሰገሌ የመንግሥት ለውጥ››፣ ‹‹የጥቁር አንበሳ ትግል በምዕራብ ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ጃንሆይ በእንግሊዝ አገር››፣ ‹‹ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ እንዲነግሡ ሲጠየቁ›› የሚሉት ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ።
ቀደም ብሎም ‹‹የኢትዮጵያ ትግል››፣ ‹‹ዓድዋ››፣ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹የታጋዮች ስሜት ከግራዚያኒ ንግግር በኋላ››፣ ‹‹ኮከብህ ያው’ና ያበራል ገና››፣ ‹‹በግራዚያኒ ጊዜ የየካቲት ቀኖች››፣ ‹‹ከማይጨው መልስ››፣ ‹‹የኔሮ ስህተት››፣ ‹‹የልቤ መጽሐፍ››፣ ‹‹የታደለች ሕልም››፣ ‹‹ርዕስ የሌለው ትዳር››፣ እንዲሁም ‹‹ፊታውራሪ ረታ አዳሙ›› የተሰኙ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችንና ሌሎች የጽሑፍ ሥራዎችን አበርክተዋል።
ስንዱ ገብሩ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ፕሬዚዳንት ፣ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ዋና ፀሐፊነትና አስተዳዳሪነት ፣ በመምህርነት፣ በአርበኝነት፣ በፖለቲካና በአስተዳደር ፣ በሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ተግባራት ላበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች የወርቅ ሜዳሊያ፣ የንግሥት ሣባ የወርቅ ኒሻን ፣ የቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
የትናየት ፈሩ