መንደርደሪያ፤
“ኮሙዩኒኬሽን” ለሚለው ቃል ብዙዎቹ የተለያየ የአማርኛ ፍቺ ቢሰጡትም ተዘውትረው በአቻ ትርጉምነት የሚደመጡት ግን “ግንኙነት” እና “ተግባቦት” የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው። በግሌ ሁለቱም የአማርኛ ፍቺዎች “ኮሚዩኒኬሽን” ለሚለው ሰፊ ጽንሰ ሃሳብ ምሉዕ ይዘቱን በሚገባ የመወከል አቅማቸው የሳሳ ስለሆነ “ኮሚዩኒኬሽን” የሚለውን ቃል እንዳለ መጠቀሙ ተመራጭ እንደሆነ አምናለሁ። ሙያዊ ትንተናው ሰፋ ስለሚል አልነካካውም።
“ኮሙዩኒኬሽን” የሚለው ቃል እንደ ብዙኃኑ የባዕድ ቃላት ለባህላችንና ለቋንቋዎቻችን ቤትኛ ከሆነ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለይም ረጅም ዕድሜን ካስቆጠረው የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ጋር ተያይዞ ከሕፃን እስከ አዛውንት በዕለት ተዕለት ንግግራችን ውስጥ ሳይጠቀስ ስለማያልፍ ባዕድ ነው ለማለት ያዳግታል። ይህ መሠረቱን ላቲን ያደረገው ፅንሰ ሃሳብ (Commu¬nis) ከሚለው የቋንቋው ሥረወ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም “የጋራ የሆነን ጉዳይ በእኩልነት መጋራትና የጠለቀ ስሜታዊ ትስስር መፍጠር” የሚል ጽንሰ ሃሳብ የያዘ ነው።
ይሄው ጽንሰ ሃሳብ በዘመናዊው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥም መሠረታዊ ፍቺውን ሳይለቅ ቅርንጫፎች እየተመዘዙለት በርካታ ቃላት ተፈጥረውለታል። በቅርንጫፍነት በተዘረጉት በሁሉም የእንግሊዝኛ ቃላት ውስጥ የሚንጸባረቀው መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ ግንኙነት (Relationship) የሚለው ዋና ሃሳብ ሲሆን፤ ይህ የግንኙነት ትስስር የሚያመለክተው የሰብዓዊያንን የእርስ በእርስና የቡድን ተዳምሮ ሲሆን የሰውን ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት የሚለየውም ይሄው ጠንካራ ግንኙነቱና መናበቡ ነው። ስለዚህም ነው “የኮሚዩኒኬሽን” የእውቀት ዘርፍ የሰብዓዊያን ተቀዳሚ ጉዳይ ነው የሚባለው።
በመሠረቱ የኮሚዩኒኬሽን ዕውቀት ለእኛ ለሰው ልጆች ከፈጣሪ ዘንድ ተለግሶን ባህርያችን የሆነው በምራቂነትና በድጎማ ስጦታነት ሳይሆን ሰብዕናችን ራሱ የተገነባው በኮሚዩኒኬሽን ስለሆነ ነው።
ይህ የኮሚዩኒኬሽን የዕውቀት ዘርፍ በሳይንሳዊ ሥልጠና ዳብሮና በእውቀት ተደግፎ አገልግሎት ላይ ሲውል ምን ያህል አቅም እንደሚኖረው ማክስዌል የተባሉ የሥነ አመራር (Leadership) ተጠባቢ የገለጹት እንዲህ በማለት ነበር። “የዘርፈ ብዙ ዕውቀት ባለቤት የሆኑ በርካታ ባለሙያዎች አንድን ቀላል ጉዳይ በመምዘዝ ውስብስብ ባህርይ እንዲኖረው የማድረግ ጥበብን ተክነዋል። የኮሚዩኒኬሽን እውቀቱ ከፍ ያለ ባለሙያ ግን አንድን የተወሳሰበ ችግር መፍትሔ በማመላከት ውል አልባውን እንቆቅልሽ በቀላሉ ፈትቶ የማግባባት ልዩ ችሎታን ታድሏል።” (በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የጻፍኩትን “የአመራር ጥበብ” መጽሐፍ ከገጽ 135 -163 ማንበብ ይቻላል።)
ተቋሞቻችን ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎታቸው አንጻር ሲቃኙ፤
በከፍተኛዎቹ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ተቋማትም ውስጥም ሆነ በመለስተኞቹና በአነስተኛዎቹ ድርጅቶች ውስጥ “የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፣ የኮሚዩኒኬሽን መምሪያ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሥራዎች የቡድን መሪ፣ አልፎ አልፎም የሕዝብ ግንኙት ወዘተ…” የሚሉ መዋቅሮች የተለመዱ መሆናቸውን እግራችንና ጉዳያችን ባደረሰን መ/ቤቶች ውስጥ ሁሉ የቢሮዎቹ ስያሜ በጉልህ ተጽፎ ሳናነብ የቀረን አይመስለኝም። መቼም የሀገራችን ችግር “ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል” ተብሎ እንደሚተረተው የሚሟጠጥ ሳይሆን “ሁሉን በመጻፋችን ብዕራችን የሃሳብ ድሃ” ስለማይሆን በዚህኛው ጽሑፌ በተለይ በከፍተኞቹ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ተቋማት (ሚኒስቴር መ/ቤቶች) መዋቅር ውስጥ ያሉትን “የኮሚዩኒኬሽን” ሹመኞችና ባለሙያዎች በተመለከተ አንዳንድ ትዝብቶቼን ለማጋራት እሞክራለሁ።
እንደ አንድ ዜጋ በግል ግርድፍ ምልከታዬ የሀገሬን ሚኒስቴር መ/ቤቶች የምመድባቸው እንደሚከተለው ከፋፍዬ ነው። አንዳንድ ሚኒስቴር መ/ቤቶቻችን እንደ ማቱሳላ በዕድሜ ፀጋ ተባርከው፣ በስምና በዘመን ርዝመት ገዝፈው፣ እንደየሥርዓተ መንግሥታቱ ስማቸው ቢለዋወጥም ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የመጀመሪያዎቹን ሚኒስትሮች ከሾሙበት ከጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም ጀምሮ አንቱ እየተባሉ የዘለቁ ናቸው። ማስታወስ ካስፈለገ የፍርድ ሚኒስቴር (ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ)፣ የጦር ሚኒስቴር (መከላከያ ሚኒስቴር)፣ የገንዘብ ሚኒስቴር (የገንዘብና የኢኮኖሚ ሚኒስቴር)፣ የንግድ ሚኒስቴር (የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስያሜው ለ102 ዓመታት እንደነበረ የቀጠለ)፣ የርሻና የመሥሪያ ሚኒስቴር (የግብርና ሚኒስቴር)፣ የሥራ ሚኒስቴር (የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር)፣ የትምህርት ሚኒስቴር (ስሙን ይዞ የቀጠለ)፣ እና በኋላ የተፈጠረው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እነዚህ ከ110 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ጎምቱ ተቋማት በሙሉ ያለጥርጥር “የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት” የሚባል መዋቅር እንዳላቸው ይታወቃል። ዳይሬክቶሬቶቹ ሥራና ተግባራቸውን እንዴት እየሠሩ ነው? ምን ያህልስ ሕዝቡ ስለተቋማቱ ተገቢና አስፈላጊ መረጃ እየተሰጠው ነው? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች አንባቢው እያሰላሰለ እንዲቆይ በመጠየቅ ለአጠቃላዩ የግል ትዝብቴ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ።
በሁለተኛነት የማነሳቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች በአፍቅሮተ ፖለቲካ ውሳኔ ሳይታሰብበት በሆይ ሆይታ ተጸንሰው በጨቅላነታቸው የጨነገፉትን እንደ “የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት” (በሚኒስቴር ማዕረግ መሆኑን ልብ ይሏል) ዓይነት ተቋማትን ነው። አንባቢው አጽንኦት እንዲሰጥልኝ የምፈልገው ከሕዝብ ይልቅ “የመንግሥት ጉዳዮች” የሚለውን ሀረግና “የኮሚዩኒኬሽንን” ስም ተሸክሞ ገና በማለዳው መጨንገፉን ማሰቡ ለግርምትም ለትዝብትም ይዳርጋል። በጨቅላነቱ የተቀጨው የዚህ ተቋም ጎምቱ ፖለቲከኞችና ሹመኞች በተሰጣቸው ኃላፊነት ምን ሲሠሩ እንደኖሩ “የእከሌ ልጆች” እየተባሉ ይቆላመጡ የነበሩት “የኮሚዩኒኬሽን ሙያተኞች” ቢመልሱት ይሻል ነበር። ዕጣው እኛ ላይ ከወደቀ አይቀር ግን ግንዱ እንኳ ቢቀር ከቅርንጫፍ ችግሮቹ መካከል አንድ ሁለቱን ዘለላ ብቻ ጠቅሶ ማለፉ አይገድም።
ሦስተኞቹ የሚኒስቴር መ/ቤቶቻችን በችግር ወቅት ተፈጥረው በችግር ውስጥ እየተፍገመገሙ ያሉትን ተቋማት ይመለከታል። ለአብነትም የሰላም ሚኒስቴርና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤቶችን ይመለከታል። ሁለቱም ተቋማት የተፈጠሩት ሀገራዊ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይህቺን መከረኛ ምድራችንን እንደ ሱናሚ ከወዲያ ወዲህ በሚያላጓት ወቅት መፍትሔ ያመጣሉ ተብለው አንዱ በበኩር ሃሳብነት አንዱ ከትምህርት ሚኒስቴር ተፋትቶ ሰሞኑን የተፈጠሩ ናቸው። ለእነዚህም ተቋማት የፈረደበት “የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት” እንደተመረቀላቸው አይዘነጋም።
እነዚሁ በሦስተኛነት የፈረጅኳቸው የሚኒስቴር መ/ቤቶች የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ቁጥርና ብዙ ጊዜያትም የተቋማቱ መሪዎች ወንበሩ ተመችቷቸው ማንጎላጀጅ ሲጀምሩ አንዴ የስም ለውጥ፣ አንዳንዴም ደባል ተቋማት እየተደረቡላቸው፣ ሲከፋም ተግባራቸውም ስማቸውም ከሚኒስቴርነት እየተሰረዘ ሲታጠፉ፣ አንዳንዴም አለቆቻቸው ቸር ሲሆኑ ስማቸውን እየለወጡ ሲያነሷቸውና ሲጥሏቸው እነርሱም አቧራውን እያረገፉና እንደ ገና እየተንከባለሉ ሲገላበጡ የኖሩ ተቋማት ናቸው። እነዚህኞቹ ሚኒስቴር መ/ቤቶች ቁጥራቸው ብዙ ስለሆነ ለመዘርዘር ያዳግታል። ለአብነት ይጠቀስ ከተባለም አንዴ ከማስታወቂያ፣ አንዴ ከወጣቶች፣ አንዴ ከስፖርት አሁን ደግሞ ከቱሪዝም ጋር እየተፋታና እየተጋባ የኖረውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን መጥቀስ ይቻላል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም እንዲሁ ልክ እንደ ስሙ ስያሜውና ተግባሩ አልጣጣም ብሎ “እንደ ገበቴ ውሃ” ሲዋልል የኖረ ተቋም ነው።
አሁን ግን የረጋ የተረጋጋ ይመስላል። ምናልባትም የህዳሴው ግድባችን ጉዳይ ጫንቃው ላይ በመውደቁ ሊሆን ይችላል። በጋብቻና ፍቺ የደለበ ታሪክ ያላቸው እነዚህን መሰል ተቋማትም ግብሩ እንኳ ቢቀር “የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት” የሚል ስም የተጎናጸፈ መዋቅር እንዳላቸው ልብ ይሏል። አንዳንድ የሚኒስቴር መ/ቤቶችም “የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት” የሚለው ፋሽን በሕንፃቸው ውስጥ ስሙ ጎልቶ ቢታይም ምን እየሠሩ እንዳሉ ሕዝቡ በቂ መረጃ ስለማያገኝ “አሉ ወይንስ የሉም” እየተባሉ “ቶማሳዊ ጥርጣሬ” ላይ ጥለውን ለሃሜት በራቸውን ከፍተውልናል።
የየተቋማቱን የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ኳራንቲን አስገብቶ ድምፃቸው እንዲጠፋ የተጠናወታቸው የወረርሽኝ በሽታ መነሻው ምን ይሆን? ደመቅና ረገጥ አድርገን በውስጣችን የሚብላላውን እባጭ ማፍረጡ ለሚመለከታቸው ፈውስ፣ ለእኛ የሩቅ ቅርብ ተመልካቾች ከህሊናና ከሙያ ወቀሳ ያድን ይመስለኛል።
የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ በጅምላ ምልከታ የአንድ ተቋም የገጽታ ደጀንና የመረጃ ምንጭ እንደሆነ የዘርፉ ጥናት ያመለክታል። ለሙያው ሥነ ምግባር የሚገዛ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ተግባሩን የሚፈጽመው ተወስኖ በተሰጠው የስምንት ሰዓታት የዕለት ውሎው ብቻ ሳይሆን ውሎ አዳሩን “ተቋሙን በልቡና በመንፈሱ እንደተሸከመ ነው” የሚል የተዘወተረ አባባል አለ። “አራት ዓይናማ” እና “ጆሮው ከዝሆን የገዘፈ” የሚሉት አባባሎችም የአንድ ውጤታማ ኮሚዩኒኬተር መገለጫዎች ናቸው።
የኮሚዩኒኬሽን ሙያ አርትም ሳይንስም ነው። የአርት (የሥነ/ኪነ ጥበባት) ባህርይ ትጋትን፣ የፈጠራ ብቃትን፣ ብልሐትና ዘዴን፣ ስሜት መማረክን ወዘተ… ያካትታል። በሥነ/ኪነ ጥበብ ውስጥ ሥነ ሥዕል፣ ኪነ ሕንፃ፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ ሌሎችም ብጤ የጥበብ ሥራዎች እንደሚካተቱ ይታወቃል።
እነዚህ የጥበብ ጎራዎች በመጀመሪያ የሚማርኩት ስሜትን ነው። በተገለጹት የጥበብ ውጤቶች ያልተገለጸው የሰው ልጅ ውስጠት ይመረመራል። ኮሚዩኒኬሽን አርት ነው የሚባለውም ይህንን መሰሉን የጥበብ ባህርይ ስለሚጋራ ነው። በአንጻሩም ኮሚዩኒኬሽን በትምህርት የሚዳብር የራሱ ዲስፕሊንና የአሠራር ቅደም ተከተል ስላለው ሳይንስም ነው። ስለዚህም ነው እንደ ሥነ አዕምሮ (ሳይኮሎጂ) እውቀት አዕምሮን የመማረክ ሚናው ላቅ የሚለው።
በቀደምት ጊዜያትም ሆነ ዘንድሮ ብዙዎቹ የጠቃቀስኳቸው ተቋማት የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች እንኳንስ የተመደቡበትን ይህንን ግዙፍ ተግባር ለመከወን ቀርቶ ከመዋቅራቸው ውጪ እስትንፋሳቸው ራሱ ህልው ስለመሆኑ እያጠረጠረን ነው። የብዙ ተቋማት የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች የድርጅቱን ብሮሹርና በራሪ ወረቀቶች ከማዘጋጀትና ከማሳተም፣ በሚመለከታቸውም ይሁን በማይመለከታቸው ስብሰባዎች የፊት ወንበር ይዞ ከመታየት፣ በጨረታዎች ውስብስብ ጨዋታዎች ውስጥ በንቃት ከመሳተፍ (በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል)፣ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሚገኙበት ቦታዎች ማጀብና ቀድሞ መታየት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ስለ ተቋማቸው መረጃ ሲጠይቋቸው “እርሳቸውን አናግሬ መልስ እሰጣለሁ” የሚል መልስ በመስጠት በረኛ ከመሆን የዘለለ ተግባር እየፈጸሙ ስለመሆናቸው ለመመስከር ያዳግታል።
እንደ ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያና እንደ ማኅበራዊ ሃያሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባሩና ስሙ የመከነ እንደ ኮሚዩኒኬሽን ያለ ሙያ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ከጥቂት ዓመታት በፊት የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያነት የሚመዘነው ለፖለቲካውና ለፖለቲከኞች ባለው ቅርበትና ፍቅር እንጂ በውጤት እንዳልነበረ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ዛሬም ይሄው ልማድ በእጅጉ ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል። የታወቀ የወቅቱን ፖለቲከኛ ስም ይዞ “የእከሌ ልጆች” የመባል የጡት ልጅነቱ ቀርቶ ካልሆነ በስተቀር የሀገሬ የኮሚዩኒኬሽን ሙያና ፖለቲካ እየተጠላለፉ ስማቸውና ግብራቸው ተደበላልቆ ተሳክሯል። በየትኛውም መሥሪያ ቤት “እሽ አትበሉን የሹም ዶሮዎች ነን” ባይ ይፈለግ ከተባለ ለኮሚዩኒኬሽ ባለሙያዎች የሚቀርብ ሌላ ሙያ ስለመኖሩ በግሌ እጠራጠራለሁ።
እንደ አንድ የዘርፉ ተማሪ የባለሙያዎቹ የግል ብቃትና ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ የኮሚዩኒኬሽኑን ሙያ አካል ጉዳተኛ ያደረገው የፖለቲካው እርግጫ ብቻ ሳይሆን ሹማምንቱ ራሳቸው ተጠያቂ ከመሆን የሚዘሉ አይመስለኝም። እንዴታውን ላብራራው። አንዳንድ ከፍተኛ የየተቋማቱ ሹመኞች በትንሽ በትልቁ ሚዲያ ፊት መቅረብ ያለባቸውና ስለ ተቋማቸው መረጃ መስጠት የሚገባቸው እነርሱ ብቻ እንደሆኑ ስለሚያምኑ ለኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ዕድል አይሰጡም። ምክንያቱ አንድም በባለሙያዎቻቸው ስለማያምኑ ይሆናል ወይንም የእነርሱን ውጤታማነት ለሾማቸው ክፍል ለማሳየት ሊሆንም ይችላል። ባለሙያዎቹም “በሙያ አምላክ” እናንተ የምትሠሯቸው አብዛኞቹ ሥራዎች የእኛ ድርሻ ስለሆኑ ጣልቃ ገብታችሁ አታግልሉን የማለት አቅሙን የተላበሱ አይመስልም። እንዲያውም አንዳንድ ሚኒስትሮች በትንሹም በትልቁም ስለ ተቋማቸው መግለጫ ለመስጠት ከሚዲያ ላይ ስለማይጠፉ የተቋማቸውን የኮሚዩኒኬሽን ሙያ ደርበው የሚሠሩ እስከ መምሰል ደርሰዋል። ይህ ማለት ሚኒስትሮች ምን ሲደረግ መግለጫ ሰጡ ለማለት ሳይሆን በአግባቡና በውጉ ይሁን ለማለት ነው። ሰሞኑን የምናስተውለው ይህንኑ አይደል?
ለዚህ ጉዳይ ማረጋገጫ ለመፈለግ አጭሩ መፍትሔ ካሉን የሚኒስቴር መ/ቤቶች መካከል ስለ ተቋማቸው አዘውትረው መረጃ ለሕዝብ የሚያደረሱትንና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሚሰጡትን የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መፈተሹ ይቀላል። ስማቸውና መልካቸውማ ባዕድነቱ የተለመደ ነው።
አይደለም ስለ ሥራቸውና ስለተቋማቸው በቂ እውቀትና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ቀርቶ በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ እንኳ ሥማቸውና ስልካቸው እንደሌለ ባደረግሁት መለስተኛ ቅኝት ለማረጋገጥ ችያለሁ። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ስማቸውና ስልካቸው ይፋ የሆኑትም እንኳ መረጃና ማብራሪያ ሲጠየቁ ወይ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ አለያም ዕረፍት ላይ ናቸው፣ ጠንከር ሲልም ክቡርነታቸውን/ክብርትነታቸውን ጠይቀን መልስ እንሰጣለን በሚል ማምለጫ የኮሚዩኒኬሽን ሙያተኞች በዘዴ እንደሚሾልኩ ብልሐታቸው ፀሐይ ከሞቀው ውሎ አድሯል።
መቼም ተረት የማይጠፋለት የፈረንሳዩ ንጉሥ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ (1769-1821) እንዲህ አደረገ ይባላል:: በአንድ የተፋፋመ ጦርነት መካከል የእርሱ የሆነ ወታደር በፍርሐት ሲሸሽ ከሩቅ ተመልከቶት ስለነበር ከወታደሮቹ መካከል አንዱን ልኮ ያንን ፈሪ ይዘው እንዲመጡ በማዘዙ ትዕዛዙን ፈጽመው እያዋከቡ ከፊቱ አምጥተው ገተሩለት ይባላል። ናፖሊዮን ምንም የቁጣ ስሜት ሳይታይበት ፈሪውን ወታደር “ስምህ ማነው?” በማለት ጠየቀው ይባላል። ያም ወታደር እየተንቀጠቀጠ “ጌታዬ ስሜ ናፖሊዮን ይባላል!” ብሎ መለሰለት። ንጉሥ ናፖሊዮንም ምንም የቁጣ ፊት ሳያሳይ እንዲህ ሲል ድጋሚ ወታደሩን ጠየቀው፤ “ወይ ስሜን መልስ፣ አለያም እንደ ናፖሊዮን ጀግና ሁን።” አዲዮስ። ምሳሌውን ልዋስና እኔም አንድ ሁሉት ነጥቦች ላክል።
አንድ፤ የሀገሬ የየተቋማቱ “ባለሥልጣኖች ሆይ!” ወይ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎቻችሁን አምናችሁ የነጠቃችኋቸውን የሙያውን ግብር ፈጥናችሁ መልሱላቸው፤ አለያም ከተቋማችሁ መዋቅር ላይ “የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት” የሚለውን የሥራ ክፍል ሰርዛችሁ አሰናብቷቸው። ልክ የብልፅግናው አመራር የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትን እንደዘጋው ማለት ነው። ሁለት፤ የሀገሬ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ሆይ በተሾማችሁበት መደብ ሳይሆን በሰለጠናችሁበት የኮሚዩኒኬሽን ሙያ ወይ ሥሩበት አለያም ላሰለጠናችሁ ተቋም ወረቀታችሁን መልሱ፤ አለያም የምትሠሩበትን ሌላ መስክ ለመፈለግ ጨክኑ። ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)