በአዲስ አበባ በሚገኙ በነባር ሰፈሮች ህይወት እንደ ቀድሞ እየፈሰሰች ነው። ምንም እንዳልተፈጠረ በዓሉን እንደቀድሞው ተሰባስበው በፌሽታ ያከበሩ ብዙዎች ናቸው። ፈጣሪን ማረን ፤ አድነን የምንለው ለወረርሽኙ ተመቻችተን ነው። በየሚዲያው የሚለፈፈው ለእርሱ ሳይሆን ለሌላ ቸልተኛ ሰው የሚመስለው ፣ ራሱን ጠንቃቃ አድርጎ የሚያስብ ግዴለሽ ብዙ ነው።
በየዕለቱ “የጉዞ ታሪክ ያለውና የሌለው” እየተባለ በኮሮና ስለተያዙ ሰዎች የሚቀርበው ረፖርት የመዘናጊያ ምክንያት እየሆነ ያለ ይመስለኛል። በሽታውን የሚያስተላልፍ ሰው የጉዞ ታሪክ ያለው ብቻ እንደሆነ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ አለ። ጎረቤት ፣ ጓደኛ ፣ የሥራ ባልደረባና የሚያውቁት ሰው በኮሮና የሚጠቃ የማይመስላቸው ሰዎች ቁጥር ጥቂት አለመሆኑን ለመገንዘብ ላፍታ አኗኗራችንን ማጤን በቂ ነው።
ወትሮም ቢሆን ገበያ የሚወጣ ሰው ሃሳቡ የሚፈልገውን ነገር በቅናሽ ማግኘት ላይ ብቻ አድርጎ ኪሱን ነቅቶ ካልጠበቀ ሌባ ጉድ ይሠራዋል። ዘንድሮ ግን ኪሱን ብቻ መጠበቁ ትርጉም የለውም። እርቀቱን ካልጠበቀ ገንዘቡን ሳይሆን ሕይወቱን የሚሰርቀው ቀማኛ መጥቶበታል። በበዓሉ ምክንያት የበሽታው ስርጭት እንዳይጨምር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲነገር ቢቆይም ገበያተኛው ለበሽታው በሚያጋልጥ መልኩ ሲገበያይ ውሏል። ለበዓል ሸመታ ወጥቶ ኮሮናን የሸመተው ምን ያህሉ ይሆን ? ለሸመታ ያወጡት ውድ ዋጋ ርቀት መጠበቅን አስረስቷቸው የገዙትን በግና ዶሮ አቅፈው ውር ውር ሲሉ የነበሩትን መንገድ ይቁጠራቸው። ምን አለፋችሁ ደጁ ድረስ እየሄድን “እንኳን አደረሰህ ኮሮና” ስንለው ነው የዋልነው።
አንዳንዶች ገበያተኛ ሳይባዛ ቀደም ብለው የበዓል ሸመታቸውን አጠናቀዋል። ለበዓሉ የሚያርዱትን በግ ቀድመው ገዝተው ለ14 ቀናት ኳራንቲን አድርገው የትኩሳት መጠኑንና አተነፋፈሱን እየለኩ የቆዩም አሉ። 15 ዕንቁላሎችን ለ14 ቀናት ኳራንቲ አደርጋለሁ ብሎ አስሩ ጫጩት ሆነውበት ያለዕቅድ ዶሮ አርቢ የሆነም አይጠፋም።
አንዳንድ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ህብረተሰቡ በንክኪ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድሉ እንዲቀንስ የተዘጋጁ የበግና የዶሮ
ስጋዎችን በስፋት ለገበያ እንደሚያቀርቡ አስቀድመው ገልጸው ነበር። ዳሩ ባህሉ ለስጋ ብቻ ሳይሆን ለሳውንድ ትራኩም ከፍ ያለ ዋጋ ስለሚሰጥ “ኩኩሉ” ብሎ ያልጮኸን ዶሮና “በእእእ” ያላለን በግ እሺ ብሎ አያኝክም። ሥራን የሚያቀል የተበለተ ዶሮ ሱፐር ማርኬት ውስጥ 200 ብር እየተሸጠ ፣ ነፍስ ያለው ዶሮ በ900 ብር ለመግዛት የገበያ ትርምስ ውስጥ የሚገባው የሚበዛው ለዚህ ነው።
የተዘጋጀ ዶሮን ከሱፐር ማርኬት ለመግዛት አለመፈለግን ከመሰልጠንና ካለማሰልጠን ጋር እንዳታያይዘው። እንዴ ምን ነካህ ? ወግ ፣ ልማድና ባህል የሚባል ነገር እኮ አለ። ዶሮ ቢያንስ ከመታረዱ አንድ ቀን ቀድሞ ግቢ ውስጥ አሊያም በረንዳ ላይ መታሰር አለበት። ከዚያም የታሰረበት ገመድ በፈቀደለት መጠን እየተንቀሳቀሰ ሊንጎራደድ ግድ ነው። በግም ቢሆን ግቢ ውስጥ ታስሮ ጥቂት ጊዜ ሳር መንጨት አለበት። ይህ ሲሆን ነው ስጋቸው የሚጣፍጠው።
በየበዓሉ ለሚፈጽሙት እርድ የተለያየ ቀለም ያላቸውን የእርድ እንስሳት የሚመርጡ ዜጎች ቁጥር ጥቂት እንዳይመስልህ። ከሱፐር ማርኬት የምትገዛው የዶሮና የበግ ስጋ ላይ ደግሞ ከእርድ በፊት ምን ዓይነት ቀለም እንደነበራቸው አይጻፍም። በዚያ ላይ “ቤት ውስጥ ደም ሲፈስ ጥሩ ነው” የሚል እምነት አለ። ይህ ብቻ አይደለም ዕድል ከቀናህ ካረድከው ዶሮ ሆድ በሚገኝ ወርቅ ዓውድ ዓመትህ ይበልጥ ሊደምቅ ይችላል። አራጆች፣ ሞረድና ቢለዋ ሠሪዎችም ቤት ውስጥ እርድ ሲፈጸም ነው የሥራ ዕድል የሚያገኙት። አየህ ከሱፐር ማርኬት የዶሮና የበግ ስጋ መግዛት ይህን ሁሉ በረከት ያሳጣል።
የበዓል የመዝናኛ ዝግጅቶች ላይም ኮሮና ጥላውን አጥልቷል። በርካታ ተመልካቾች ባሉት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ኮሜዲያን ገበያ ውስጥ ላገኘው በግ በአራት እግሮቹ ላይ የእጅ ጓንት አድርጎለት የፊት ማስክ ሲያለብሰው ታይቷል። እነዚህን መገልገያዎች የህክምና ባለሙያዎች እንኳን በበቂ መጠን እያገኙ እንዳልሆነ በሚነገርበት አገር በዚህ መልኩ እንዲባክኑ መደረጉ ያሳዝናል። የህክምና ባለሙያዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጣ አዘል ቅሬታ አሰምተዋል። ቴሌቪዥን ጣቢያው እንዲህ ያለ ድርጊትን ማስተላለፍ አልነበረበትም። አንዳንድ ጊዜ ሳቅ ለማጫር የሚደረጉ ያልተጠኑ እንቅስቃሴዎች እሳት ሊጭሩ እንደሚችሉ የሚያሳይ ክስተት ሆኖ አልፏል።
በተላለፈው ዝግጅት የተበሳጨ አንድ ግለሰብ በማህበራዊ ድረገጹ ስለድርጊቱ ስሜቱን ሲገልጽ “ቀልዱ አልታየኝም፤ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክትም አልገባኝም ፤ ኮሜዲያኑ የትኛው ፤ በጉ የትኛው እንደሆነ አልተረዳውም።” ብሏል። አንዳንዶች ደግሞ “ድሮስ እዚህ አገር አሳቃቂ እንጂ አሳቂ የት አለ” እስከ ማለት ደርሰዋል። ኮሜዲያኑ የፈጸመው ተግባር ተገቢ ባይሆንም በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎችን ለማንቃት ድንቅ በሆነ አቀራረብ መልዕክት በማስተላለፍ የሚታወቁትን የኢትዮጵያ ኮሜዲያንን በጅምላ ለማውገዝ መጋበዝ አይገባም።
በዚሁ ዕለት በርከት ያሉ ኮሜዲያን ሰብሰብ ብለው በአንድ አዝናኝ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቆይታ ዜጎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ አዝናኝ በሆነ መንገድ መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር። እኔን አንዲት ሴት ኮሜዲያን ስለኮሮና የቀለደችው ቀልድ አንከትክቶኛል። አንዱ “ስልኬ በአሻራዬ ነበር የሚከፈተው። በሳኒታይዘር ደጋግሜ ከመታጠቤ የተነሳ አሻራዬ ስለለቀቀ ስልኬን መክፈት አልቻልኩም” ብሎ ይቀልዳል። በዚህ ጊዜ አንዷ “ሂድ ጣቶቼ ላይ ባሉት ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች ነበር አትልም” ብላው እርፍ አለች።
በዓሉ የእንኳን አደረሳችሁ ሃይ ማኖታዊ መልዕክቶች “ከኮሮና ቫይረስ እንጠንቀቅ” ከሚል መልዕክት ጋር ተጣምረው ኔትወርክ ያጨናነቁበት ነበር። በበዓል ቀናት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶችን በመላክ የሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮምም መልዕክቱን ከወቅቱ ወረርሽኝ ጋር አያይዞ ለደንበኞቹ ልኳል። መልዕክቱ “ሁላችንም ባስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፍን እንደመሆናችን በዚህ ቀን በእግዚአብሔር ፍቅርና በመስቀል ላይ ለኛ ባደረገው ነገር ተስፋ እንድታደርጉ እናበረታችኋለን። እርሱ ከዚህ ጨለማ ውስጥ እንድንወጣ ደግሞ ይረዳናል።
መልካም ፋሲካ ! “ ይላል። ይህ መልዕክት “የኢትዮ ቴሌኮም ገለልተኛነትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ባሉ አንዳንድ ወገኖች ተቃውሞ ገጥሞታል። በርግጥም “ለክርስትና እምነት ተከታዮች” የሚል ሐረግ ያልያዘና ተቋሙንም የእምነቱ ተከታይ አድርጎ ያቀረበ መልዕክት በመሆኑ ክፍተት አለበት። ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ ተግባሩ ትምህርት ወስዶ መሰል ስህተቶችን ከመሥራት ይቆጠባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አበቃሁ !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
የትናየት ፈሩ