ሠራተኞች በሥራ ወቅት በደህንነት ጉድለት ምክንያት የተለያዩ አደጋዎች እና ጉዳቶች ሲያጋጥሟቸው ይስተዋላል። ይህንንም ችግር ለመቀነስ የተለያዩ የሕግ፣ የህብረተሰብ ጤና እና ማህበራዊ ግንዛቤ ሥራዎች ሲሞከሩ ይታያል። በተለይም እ.ኤ.አ ከ1919 ዓ.ም ጀምሮ የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት መቋቋምን ተከትሎ በርካታ ከሠራተኛ የሥራ ደህንነት ጋር የተያያዙ መርሆዎች እያደጉ መምጣታቸው አይዘነጋም።
እንደ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ሪፖርት ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በግንባታ ወቅት ቢያንስ 60ሺህ ሠራተኞች ከደህንነት ጉደለት ጋር በተያየዘ ለሞት የሚዳርጉ ወይም ከባድ የአካል ጉዳት አደጋዎች እንዳሚያጋጥማቸው ይጠቁማል። ይህም ማለት በየአስር ደቂቃው ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ይደርሳል እንደማለት ነው። ሪፖርቱም በተለይ ከአጠቃላይ የሥራ ላይ አደጋዎች ውስጥ 17 በመቶ ይህም ከስድስት አደጋዎች ውስጥ አንዱ የሚሆነው ገዳይ አደጋ በግንባታ ዘርፍ እንደሆነ ያትታል። የግንባታ ደህንነትን በተመለከተም በ2005 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የኮንስትራክሽን ሥራ ደህንነት ጉዳይ ከኢንዱስትሪው ዕድገት ጋር ተያይዞ በትይዩ ትኩረት የሚሠጠው ቁልፍ ሥራ መሆን እንዳለበት ይናገራል።
የግንባታ ደህንነት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ያለው ይዞታ
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የግንባታ ደህንነትን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ አልወጣም። ሆኖም ግን ከሥራ ጋር በተያያዘ እንደ ሠራተኞቹ የቅጥር ግንኙነት የተለያዩና የተበታተኑ ሕጎች ይታያሉ። ለምሳሌ በ1952 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 25/48 ላይ አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው አካላዊ ደህንነት ተገቢ የሆነ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው በቀደምትነት ይደነግጋል። በእርግጥ የሥራ ግንኙነትን የተመለከተው የፍትሐብሔር ሕግ ተፈፃሚነቱ ውስን የሆነበትን ሁኔታ መጠቆም ይቻላል።
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 አንቀጽ 92-93 የግንባታ ሥራን ጨምሮ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የደህንነት ጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቀምጧል። በእርግጥ አብዛኛውን ጊዜ የግንባታ ሥራ ሠራተኞች በጊዜያዊነት ከመቀጠራቸው ጋር ተያይዞ የጥንቃቄ እርምጃዎች በአግባቡ ሲተገበሩ አይስተዋልም። ሆኖም ግን የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ የሥራ ላይ ደህንነት የአሠሪዎች አንዱ ግዴታ መሆኑን በአንቀጽ 12 (4) ላይ በማያሻማ መልኩ አስቀምጧል። ይህንን ግዴታም ተላልፎ የተገኘ አሠሪ የወንጀል ሕግ ላይ ያሉ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቀ ሆኖ በመቀጮ ይቀጣል።
በ2001 ዓ.ም የወጣው የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624 ከመግቢያው ጀምሮ በርካታ የግንባታ ላይ ደህንነትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ይዟል። በተለይም የሕንፃ አዋጅ ተቀዳሚ ዓላማ ህንፃ በሚገነባበት ወይም በሚታደስበት ጊዜ የሕዝብ ደህንነት እንዲጠበቅ ብሔራዊ ዝቅተኛ መመዘኛዎችን በመደንገግ ነው። በዚህ ረገድ የግንባታ ላይ ሠራተኞች የሂደቱ መሪ ተዋንያን በመሆናቸው በቂ ጥበቃ ሊደርግላቸው ይገባል። በተለይም የሕንፃ አዋጁ በአንቀጽ 31 (1) ላይ ስለ ግንባታ ደህንነት ጉዳዩን የሚያቀምጠው ‹‹ማንኛውም ግንባታ በግንባታው አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን፣ የግንባታ ሠራተኞችን፣ የሌሎች ግንባታዎችን ወይም ንብረቶችን ደህንነት በማያሰጋ መንገድ ዲዛይን መደረግና መገንባት ይኖርበታል።›› ብሎ አስቀምጧል:: ሲል ነው።
የሥራ ቦታ ደህንነት መጠበቅ
ተገቢ የሆነ እንደመሰላል ያለ ለግንባታ ሥራ የሚያግዝ መወጣጫና መሰላል መሥራት፣ በአግባቡ የተተከሉ እንዲሁም የሚሠሩ የዕቃ ማንሻ እና ማቀበያ መሣሪያዎች መጠቀም፣ በግንባታው አካባቢ ያለውን የአካባቢ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሳይገድቡ ተገቢ የሆኑ ማሽኖች፣ ማጓጓዣ መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች መጠቀም፣ የሠራተኞችን የሥራ ብቃት መለኪያ መርሆችን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚተከሉ ማሽኖችን እና በተግባር የተሞከሩ መሣሪያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል::
የከፍታ ላይ ሥራዎች በተለይ ገመድ መሰል መቋጠሪያ በመታጠቅ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሠራተኛው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተገቢ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የቁፋሮ ሥራዎች፣ የጉድጓድ፣ የከርሰ-ምድር እንዲሁም የዋሻ ሥራዎች በሚከናወኑበት ጊዜ አንድም ከፍርስራሽ አደጋዎች ለመጠበቅ ተገቢ ድጋፍና ከለላ የሚያደርግ መሣሪያ መጠቀም አሊያም በቂ የሆነ አየር እንዲኖር የሚያስችሉ፤ ከድንገተኛ የተፈጥሮ ጋዝ እና ውሃ መታፈን ለመከላከል የሚያስችሉ ነገሮችን ማድረግ፣ የድልድይና ትላልቅ የከርሰ-ምድር ግንባታዎች በሚሠራበት ወቅት የውሃ ማገቻ መሣሪያ እና ውሃ ሳይገባ ሳጥን መሰል የውሃ አጥር በመገንባት ጥንቃቄ በተሞላው መልኩ ሥራውን ማከናወን፣ ከውሃ በላይ በሚሠሩ ግንባታዎች እንዲሁም የነበረ ግንባታ በሚፈርስበት ወቅት ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
እንደ አስፈላጊነቱ ተንቀሳቃሽ የሆነ የመብራት፣ የኤሌትሪክ ሃይል እንዲሁም ለእሳት አደጋ መከላከያ የሚሆኑ መሣሪዎችን በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋል፣ በመጨረሻም አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች የግል ደህንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች እንደ የደህንነት ኮፍያ መጠቀም፣ አደጋ በደረሰ ጊዜም የመጀመሪያ የህክምና አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ የምግብ አቅርቦት ተያያዥ ማህበራዊ መድህን እንዲኖር ያስፈልጋል።
በእርግጥ የግንባታ ሥራ ደህንነት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በውስጡ ያለተፈቱ እና ቅቡል ያልሆኑ ጉዳዮችን ጥቅል በሆነ መልኩ ያስቀመጠበትን ሁኔታ እናገኛለን። ዳሩ ግን ከላይ ከተቀመጡት እርምጃዎች የግንባታ ሥራ ደህንነትን ጽንሰ ሃሳብን በመጠኑም ቢሆን ለመረዳት ያግዛሉ። እንዲሁም ስምምነቱ የማዕቀፍ ስምምነት እንደመሆኑ መጠን አገራት ይህንኑ እንደ መነሻ በመውሰድ የተሻሉ ዝርዝር የደህንነት ሕግጋት ማውጣት አለባቸው። ሌላው ጉዳይ ከላይ የተዘረዘሩት የግንባታ ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደግንባታዎቹ መጠን፣ ዓይነት እና ጊዜ አተገባበራቸው ሊለያይ ይችላል። ይህ ዓለም አቀፍ ሕግ እስከዛሬ ድረስ 31 አገራት በመፈረም እና በማጽደቅ የህጋቸው አካል አድርገውታል። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ግን የዚህ ስምምነት ፈራሚ አገር አይደለችም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
መርድ ክፍሉ