ለስምንት ዓመታት በዱባይ በቤት ሠራተኝነት ትሠራ የነበረችዋ አዳነች ወርቁ፣ ወርሐዊ ደመወዟን ለዓመታት ለቤተሰቦቿ ስትልክ ቆይታለች። ቤተሰቦቿ ድካሟን ስለሚረዱ ላቧን መና አላስቀሩባትም። ‹‹ለእኛ›› ብለው ያማራቸውን ለብሰውና አሸብርቀው፤ የፈለጉትን ዕቃ ገዝተው እና ቤታቸውን አሳድሰው፤ ጮማ እየቆረጡ በአዳነች ገንዘብ ድግስ አልደገሱም። ይልቁኑ ‹‹ቅርስ ያስፈልጋታል›› ብለው የላከችውን ገንዘብ ሲያጠራቅሙ ዓመታትን አሳልፈው ቤት ለመግዛት ማጠያየቅ ተያያዙ።
ነገር ግን ያጠራቀሙት ገንዘብ በአዲስ አበባ ቤት ለመግዛት የሚበቃ አልነበረም። ከአዲስ አበባ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ግን የተሻላ ዕድል መኖሩን ሰሙ። ነገር ግን ብዙ ቢዞሩም የፈለጉትን አላገኙም። አንድ ዕሁድ ደላላ ለአቶ ወርቁ ስልክ ደውሎ አጣደፋቸው። አንድ በጣም የተቸገረ እና በአስቸኳይ ቤቱን መሸጥ የሚፈልግ ሰው እንዳለ ነገራቸው። ቤቱ አዲስ ዓለም አካባቢ በመሆኑ አቶ ወርቁ ባለቤታቸውን ይዘው ወደዚያው አመሩ። የተገኘው ቤት ዋጋውም ሆነ የግቢው ስፋት ለልጃቸው የሚፈልጉት ዓይነት ሆኖ አገኙት።
የአዳነች አባት ጉጉታቸው ልጃቸውን የቤት ባለቤት ማድረግ ላይ በመሆኑ ብዙም ሳያስተውሉ፤ ልጃቸውን ወክለው ግዢውን በእማኞች ፊት ፈፀሙ። ሻጭ ትዳር ይኑረው አይኑረው ማስረጃ አላቀረበላቸውም። እንዲሁ በቃል ሚስት እንደሌለው ገልፆላቸው በአመኔታ ቤቱን ገዝተው ማደስ ሲጀምሩ እንቅፋት አጋጠመ። ‹‹የሻጭ ሚስት ነኝ›› የምትል ሴት ‹‹ያለኔ ፈቃድ ቤቴን ማን ቆርጦት ይኖርበታል›› ስትል የማደስ ሥራው እንዳይከናወን ችግር ፈጠረች። አቶ ወርቁ ግራ ተጋቡ፤ ሴትየዋ እግድ አወጣች፤ ክስ መሰረተች። አዳነች ትኖርበት ከነበረበት አገር መጣች። ቤተሰቦቿ ገንዘቧን ቆጥበው ለእርሷ ቤት መግዛታቸው እጅግ ቢያስደስታትም፤ የተፈጠረው ችግር አስጨነቃት። እግድ ማስነሳት፤ የክስ ሂደቱን መከታተል ጀመረች። ትኖርበት የነበረው አገር ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የማህበረሰቡ የአኗኗር ልዩነት፣ በንግግርም ሆነ በአስተሳሰብ ከዘመዶቿም ጋር አለመግባባቷን ልትቋቋመው አልቻለችም። ለአባቷ ውክልና ሰጥታ ተመልሳ ወደ መጣችበት ዱባይ አመራች።
አቶ ወርቁ እነርሱን እና የገዛ ባሏን የከሰሰችውን ‹‹የሻጭ ሚስት ነኝ›› ባይዋን ለማስማማትና ክስ እንድታነሳላቸው ብዙ ጥረት አደረጉ። ፍርድ ቤት መመላለሱና መንገላታቱ የሚያቆም ስላልመሰላቸው፤ የሻጭ ሚስት ‹‹ካሳ እንክፈልሽ›› ብለው ሽማግሌ በመላክ አሳመኗት። በመጨረሻም አዳነች የሠራችበትን ገንዘብ እየላከች የተወሰነ ገንዘብ በማጠራቀም እና ከዘመድ አዝማድ በመበደር ለሻጭ ሚስት ካሳ ከፍለው ክሷን እንድታቋርጥ ማድረግ ቻሉ።
አዳነች አሁን ከዱባይ መጥታ በቤቱ ውስጥ ትኖራለች። ‹‹አባቴ ጠንካራ በመሆኑ ይህንን ለእኔ አደረገ። አሁን ቤት አከራያለሁ። በዚያው ግቢ ለሱቅ የሚሆን ቤት ሠርቼ የሸቀጥ ዕቃዎችን እሸጣለሁ። መዋያ አላጣሁም፤ ራሴን ችያለሁ። የቤት ግዢው በአባቴ ባይከናወን፤ በተለይ የከሳሽ ባለቤት ክስና ክርክር ተስፋ አስቆርጦኝ የሥምንት ዓመት ልፋቴ ገደል ይገባ ነበር›› ትላለች።
ሌላው በቤት ግዢ ወቅት ምንም እንኳ ትልቅ ጥንቃቄ ቢያደርጉም ከባድ ፈተና አጋጥሟቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ መላኩ ደምመላሽ ናቸው። እርሳቸው ባለአንድ መቶ አምስት ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሰፈረ ቤታቸውን ሽጠው ለማትረፍ፤ ቢቻል የተሻለ የመሬት ስፋት ለማግኘት ሲሉ ቤታቸውን ለመሸጥ ወሰኑ። የተሻለ ቤት ለማፈላለግ ከአንድ ዓመት ያላነሰ ጊዜ ፈጅቶባቸዋል። እርሳቸው ቡራዩ አካባቢ ያላቸውን መሬት ሽጠው ሌላ ቤት ለመግዛት ያልዞሩበት የለም። አዲሱ ገበያ፣ ሱሉልታ፣ ፈረንሳይ፣ ኮተቤ፣ ካራቆሬ፣ ለገጣፎ፣ ጎሮ፣ የሺ ደበሌ፣ ወለቴ፣ ኮልፌ፣ አሸዋሜዳ፣ ኬኒተሪ እና ሌሎችም አካባቢዎች ከደላላዎች ጋር እግራቸው እስኪቀጥን ዞረዋል።
‹‹ይህንን ሁሉ የተንከራተትኩት ገዢ በማግኘቴ የተሻለ ቤት ለመግዛት ነበር። ›› የሚሉት አቶ መላኩ፤ ነገር ግን በዋጋም ሆነ በይዞታ ስፋት እንዲሁም በመሬት አቀማመጥ ብዙም የሚያስደስታቸውን ባለማግኘታቸው ከገዢያቸው ላይ ገንዘብ አለመውሰዳቸው ጠቅሟቸው የመሸጥ ሃሳባቸውን ሰረዙ። ገዢው ግን በማንኛውም ጊዜ ለመሸጥ ሲፈልጉ እንዲያሳውቁት ነግሯቸው ተለያቸው።
አቶ መላኩ ደላሎች ለእርሳቸው የሚስማማ ምርጥ ቤት እንዳገኙላቸው ሲገልጹላቸው፤ የተባለውን ቤት አይተው እውነትም እንደሚፈልጉት ዓይነት መሆኑን አረጋገጡ። ካርታው ህጋዊ እና የጀርባ ማህተብ ያለው መሆኑ፤ የጋብቻ ወረቀት መኖሩን አረጋግጠው ለመግዛት ተስማሙ።
የእርሳቸውን ቤት ለመግዛት የተስማማውን ሰው በፊት ከገመተበት ስድሳ ሺህ ብር ጨምሮ ይገዛ እንደሆነ ጠይቀው ተስማምተው ቀጠሩት። ቀጠሯቸው ከእርሱ ጋር ብቻ አልነበረም። ሁለቱንም እርሳቸው የሚሸጡለትንም ሆነ እርሳቸው የሚገዟቸውን ሰዎች ወዲያው እጅ በእጅ ሽያጭ እና ግዢውን ለመፈፀም በተመሳሳይ ሰዓት በውል እና ማስረጃ ቀጥረው ቀድመው ሽያጩን ፈፀሙ። መሸጣቸው ግን እንደመግዛታቸው ቀላል አልሆነም። ሻጮች ውልና ማስረጃ ከገቡ በኋላ ካሉት ገንዘብ በላይ ‹‹አንድ መቶ ሺህ ብር ጨምር፤ ያለበለዚያ ሽያጩን አንፈፅምም›› አሏቸው።
‹‹በወቅቱ ተናደድኩ፤ ራሴንም መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር። ተረጋግቼ ለማነጋገር ብሞክርም በተለይ የሻጭ ሚስት ‹ሞቼ ልገኝ ያለበለዚያ አንሸጥም፤ አለመሸጥ ደግሞ መብታችን ነው› አለች። ›› የሚሉት አቶ መላኩ፤ በወቁቱ ከስድሳ ሺህ ብሩ ውጪ ሊጨምሩት የሚችሉት ገንዘብ ባለመኖሩ ጭራሽ ጠብ ውስጥ ገብተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ሳቢያ ስምምነታቸው በመፍረሱ የፈለጉትን ቤት መግዛት ሳይችሉ ቀሩ።
ገንዘቡን እንዳያጠፉ በመስጋታቸው ቀደም ሲል ካዩዋቸው መካከል የተሻለ የመሰላቸውን ገዙ። በጨረሻም አቶ መላኩ ‹‹የያዙትን መሸጥ ቀላል ሊሆን ይችላል። ቤት መግዛት ግን እጅግ ከባድ ነው። የይዞታውን ህጋዊነት ለማረጋገጥ ዕውቀቱ እና ጥንቃቄው ቢኖርም ማንኛውንም ‹ብልህ ነኝ› ያለ ሰው፤ ብልጣብልጥ ደላሎች እና ያልታመነ ሻጭ ገደል ሊከቱት ይችላሉ። መጨረሻ ላይ የሚያጋጥመውን መገመት እጅግ ከባድ ነው፤ አይታወቅም›› ይላሉ።
በቤት ሽያጭ የድለላ ሥራ ላይ የተሰማራው አቶ ተሰማ ኮይራ እንደሚናገረው፤ የአቶ ወርቁም ሆነ የአቶ መላኩ አጋጣሚዎች እንዲያውም ቀላል ናቸው። በቤት ሽያጭ ላይ ከፍተኛ ውንብድና አለ። ከውንብድናዎቹ መካከል በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያለው የቤት ሽያጭ እጅግ በጣም የተወሳሰበ፣ አንዳንዶችን ባዶ የሚያስቀር፤ ብዙዎችን የሚያከስር እና አልፎ አልፎም እስከመገዳደል የሚያደርስ ይሆናል።
ለአንድ መሬት ሁለት ሦስት ካርታ የተሰጠበት ሁኔታ በመኖሩ አንዳንዶች ‹‹ቤት ገዛሁ›› ብለው ሌላ ‹‹የቤቱ ባለቤት ነኝ›› ባይ ይመጣባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ቤት ሳይሆን መሬት ከአርሶ አደር ላይ ይገዛሉ። ተሯሩጠው ካርታ አውጥተው አነስተኛ ቤት ከሠሩ በኋላ የገዙትን በውድ ዋጋ ይሸጡታል። መጀመሪያ መሬቱን እያረሰ ሲጠቀምበት የነበረው አርሶ አደር ቤቱ የተሸጠበትን ዋጋ ሲሰማ ይበሳጫል። ‹‹መሬቱ የኔ ነው፤ እንደገና ከኔ መሬቱን መግዛት አለብህ›› እያለ አርሶ አደሩ አዲሱን ገዢ ያሰቃያል።
በአዲስ አበባ ደግሞ በስፋት የሚታየው የውርስ ቤቶች ሲገዙ የሚያጋጥመው ችግር ተጠቃሽ ነው። የሰነዶች ማረጋገጫ የውርስ ቤት የተለያዩ ሰዎች የወረሱት ቢሆንም፤ ‹‹ሽያጭ መፈፀም ያለበት ለአንድ ሰው ውክልና በመስጠት ነው›› ብሎ ያስገድዳል። ነገር ግን አንዳንዶቹ ውክልና ከሰጡ በኋላ በሽያጩ ገንዘብ አይስማሙም።
በሌላ በኩል ወራሾች በሙሉ ሳይሟሉ የውርስ ቤቶች በተወሰኑ ሰዎች የውርስ ሰነድ ሳይረጋገጥ የሚሸጥበት ሁኔታ ያጋጥማል። በዚያ ጊዜ ውርሱ ላይ ያልተካተተ ሰው ክስ ይጀምራል። ‹‹ስለዚህ ገዢው እንደገና ለሌላ እንግልት ይጋለጣል። ›› በማለት የሚናገረው አሻሻጭ ተሰማ፤ ከሁሉም በአሁኑ ወቅት በተለይ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ሽያጭ ላይ እያጋጠመ ያለው ሚስት ወይም ባል እያላቸው በማታለል ‹‹ብቸኛ ነን›› እያሉ የሚሸጡበት ሁኔታ በስፋት የሚስተዋል መሆኑን ይገልጻል።
በእነርሱ በኩል በተቻለ አቅም ህጋዊ ካርታ እንዲኖር፤ ገዢም ሻጭም በመሃል ያሉት ደላሎችም ሁሉም እንደሚታሰበው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢፈልጉም አንዳንዴ ሻጮች ብዙ ጊዜ ደግሞ ገዢዎች እጅግ ከባድ ኪሳራ ውስጥ የሚገቡ መሆናቸውን በመግለፅ ደላላው ተሰማ ሃሳቡን ይደመድማል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
ምህረት ሞገስ