በአራት ኮንትራት ተከፍሎ ግንባታው እየተካሄደ የሚገኘው የሞጆ ሃዋሳ ዘመናዊ የፍጥነት መንገድ 32 ሜትር ስፋት ያለውና 90 ሜትር የመንገድ ወሰን ማስከበር ክልልን ያካተተ መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። መንገዱ በአጠቃላይ አራት መኪኖችን በአንድ ጊዜ በግራና ቀኝ በኩል ለማስተናገድ በሚያስችል መልኩ እየተገነባ ሲሆን፣ በአንድ አቅጣጫ ሁለት መኪናዎችን የሚያስተናግደው የመንገዱ ክፍል 3 ነጥብ 65 ሜትር ስፋት በ9 ሜትር ሚዲያን የመንገድ አካፋይ ያካተተና ከ1 ነጥብ 75 እስከ 2 ነጥብ 25 ሜትር የመንገድ ትከሻ ስፋትን የያዘ።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በታሰበለት ጊዜ ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም፤ መንገዱ የሚሠራባቸውንና የግንባታ ግብአት ማምረቻ ቦታዎችን በቶሎ አለመያዝ ለመዘግየቱ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው። በተጨማሪም የዲዛይን ለውጦች፣ መንገዱ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ የመብራት ምሰሶዎች በቶሎ አለመነሳት፣ የመሬት ባለቤትነት ሰርተፊኬት በቶሎ አለማግኘት፣ የወረዳው ለኪና ታማኝ ኮሚቴዎች በፕሮጀከቱ ሙሉ ተሳታፊ ሆነው አለመሥራትና አብዛኛዎቹ በብድር ያሉ የጠጠርና እና የአሸዋ ሀብቶች በአካባቢው በተደራጁ ወጣቶች መያዝና በሌሎችም ምክንያቶችም መዘግየቱ ይነገራል።
ይሁን እንጂ በባለስልጣኑ በኩል አብዛኛዎቹ ችግሮች በመፈታታቸው እና ቀደም ሲል የመንገዱ ግንባታ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ይገጥሙ የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ መምጣታቸውን ተከትሎ ኮንትራክተሮች የመንገዱን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በኮንትራት አንድ የሞጆ መቂ የመንገድ ግንባታ የቻይና ሬል ዌይ ሰቨን ግሩፕ ፕሮጀክት ማናጀር ዋንግ ጉዋንግ እንደሚገልጹት፤ የመንገድ ግንባታው 56 ነጥብ 4 ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቦለታል። ለግንባታው የሚውለውን ወጪም 58 ነጥብ አንድ ከመቶውን የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ እንዲሁም 41 ነጥብ 9 በመቶውን የኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፍኑታል።
የመንገዱ ግንባታ በህዳር ወር 2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ እስከአሁን 88 ከመቶ ያህሉ ተከናውኗል። በኪሎ ሜትር ደግሞ 48 ነጥብ 5 ያህሉ ተከናውኗል። የመንገድ ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅም አጥር የማጠር፣ የድልድይና ከአዳማው የፍጥነት መንገድ ጋር የማገናኘት ሥራዎች ብቻ ይቀራሉ። እስከአሁንም የአስፓልት፣ የመንገድ ምልክት፣ ቀሪ የአጥር ሥራዎች ተከናውነዋል። በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2020 ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።
በኮንትራት ሁለት የመቂ ዝዋይ የመንገድ ግንባታ የኮሪያው ዴዎ ኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ኩባንያ ፕሮጀክት ማናጀር ጆንግ ሂዮክ እንደሚገልጹት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ 37 ኪሎ ሜትር የሚራዝምና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ሲሆን፣ ለግንባታው የሚውለው ወጪ ሙሉ በሙሉ በኮሪያው ኤግዚም ባንክ ብድር ይሸፈናል። ግንባታውም በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ 79 ከመቶ ያህል የመንገዱ ፕሮጅክት ተከናውኗል፤ ይህም 29 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ያህሉ የመንገዱ ፕሮጀክት ተከናውኗል ማለት ነው። ፕሮጀክቱ በዚህ ፍጥነቱ የሚቀጥል ከሆነም እ.ኤ.አ መጋቢት 2021 እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል።
በኮንትራት ሦስት የዝዋይ አርሲ ነገሌ የመንገድ ግንባታ የሲውዘርላንዱ ኤስ.ቢ.አይ ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ፕሮጀክት ማኔጀር አሌክሳንደር ጎንዶሽ እንደሚሉት፤ መንገዱ 57 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው። ከ 3 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር በላይ ተይዞለትም ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል። ግንባታውም ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር የሚሸፈን ይሆናል።
የመንገዱ ግንባታ የተጀመረው በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ሲሆን፣ ለግንባታውም የተያዘው ጊዜ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ነው። እስከአሁንም ሰባት ከመቶ የሚሆነው ብቻ የመንገዱ ግንባታ ወይም ደግሞ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ተከናውኗል። ይህም አፈፃፀሙ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል።
ፕሮጀክቱ በሦስት ዓመታት ውስጥ ያልቃል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም የመንገድ ፕሮጀክቱ አስቀድሞ በርካታ ውስብስብ ውጣውረዶች በተለይም ከመሬት ወሰን ማስከበር፣ ከማህበራዊና ከደህንነት ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች የገጠሙት በመሆኑ ለመዘግየቱ ምክንያት ሆኗል። የመንገዱ በልዩ ልዩ ምክንያት መዘግየቱን ተከትሎም ግንባታውን ለማጠናቀቀ ተጨማሪ ዓመታትን ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የመንገድ ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና ከአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን እየተሠራ ይገኛል።
በኮንትራት አራት የአርሲ ነገሌ ሃዋሳ የመንገድ ግንባታ የቻይና ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ፕሮጀክት ማኔጀር ሉሆንግ ቦ እንደሚናገሩት፤ የመንገድ ፕሮጀክቱ 52 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ከ4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ከፍ ያለ በጀት ተይዞለታል። ለግንባታው የሚውለው ወጪ 85 በመቶ ያህሉ ባቻይና ኤግዚም ባንክ ብድር እንዲሁም ቀሪው 15 በመቶው በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፣ ለግንባታው የተሰጠው ጊዜ እስከ ሦስት ዓመት ተኩል ያህል ቢሆንም፤ እስከአሁን ባለው ሂደት መንገዱ የተከናወነው 10 ነጥብ 1 በመቶ ብቻ ነው። በዚህ ሂደትም የአንድ ድልድይ ግንባታና ሌሎች ሥራዎች ተጀምሯል። በኪሎ ሜትር ደግሞ 5 ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር ተከናውኗል። በዚህ ፕሮጀክት በቀጣይ ሰባት የዋና መንገድና ሰባት ተሸጋሪ ድልድይ ሥራዎች የሚከናወኑም ይሆናል።
የመሬት ካሳ ጥያቄዎችና ከደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮች ፕሮጀክቱ በታሰበለት ጊዜ እንዳይጀመር እንቅፋት ሆነዋል። ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮች በመፈታታቸው በተቻለ አቅም የመንገድ ፕሮጅክቱን በፍጥነት ለማስኬድ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የመንገድ ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቅበት ዋናው የኮንትራት ስምምነቱ እ.ኤ.አ በመስከረም ወር 2021 ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆኑም፤ ፕሮጀክቱ በገጠሙት ችግሮች ምክንያት የመጠናቀቂያ ጊዜው ይራዘማል ተብሎ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
አስናቀ ፀጋዬ