ሰዎች በከተማ ለመኖር የሚያስችላቸውን ሥነ ልቦና ሰንቀው የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ፋይዳው በርካታ ነው። አኗኗራቸው የግብር ውጣ እንዳይሆን ተጠንቅቀውና የሚኖሩበት ከተማ የሚጠይቀውን ሥርዓት ተከትለው የሚወጡና የሚገቡም ከሆነ ለከተማው ውበት ከመሆኑም በላይ ለራሳቸው ለነዋሪዎቹ ጤና ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ስልጡን የሆነ የከተማ አኗኗሩ የአንድ ከተማ ከተማነትን ስለሚያሳይ እንደ አንድ ቁልፍ ጉዳይ ይወሰዳል።
ይሁንና የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ ሌሎቹም ከተሞች የከተሜነት መመዘኛን ያሳያሉ ወይ ተብሎ ሲጠየቅ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች የሚነገረው ምንም የከተሜነት መገለጫ እንደሌላቸው ነው። በከተማ ፕላንም ሆነ በከተማ ጽዳት እንዲሁም በሌላውም ገና ወደስልጣኔው አለመገባቱም ነው በተለያየ ጊዜ ሲጠቀስ የቆየው። ከተማ የሚጠይቀው የከተሜነት መለኪያ ከሆነው መካከል እንደ ዋንኛ ሳይሆን እንደ አንዱ ከሚጠቀሰው የህዝብ ብዛት ካልሆነ በስተቀር አገሪቱ ገና የከተሜነትን መገለጫዎች ያልተገበረች እንደሆነች እየተነገረ ነው።
በዚህና ተያያዥ ጉዳዮችን በማስመልከት በህንፃ ኮሌጅ መምህርና ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር የሆኑትን ፕሮፌሰር ኃይሉ ወርቁን አነጋግረናል፤ በሳቸው አተያይ በኢትዮጵያ ያሉ ከተሞች ስንቶቹ አቅደው ወይም በባለሙያዎች አማካይነት በሙያው ሥነ ምግባር ላይ ተመስርተው እየተሰሩ ነው ቢባል ወጥ የሆነ ሥራ የለም። በጉዳዩ ዙሪያ ጥናቶች እዚህም እዚያም ይጠናሉ፤ ነገር ግን ተቀናጅተው ሲሰራባቸው አይታይም። ለህብረተሰቡ በሚጠቅም መልኩ ሥራ ላይ እየዋሉም አይደለም። ለከተማ የተሰጠው ትኩረት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ማወቅ የሚቻለው በሀገሪቱ ያሉ ከተሞች በተሰራለት ማስተር ፕላን መሰረት የተገነቡ /እየተገነቡ / አይደሉም። (ለዛውም ማስተር ፕላን ላላቸው ማለት ነው)። አብዛኞቹ ላይ ትክክል የሆነ ነገር የለም፤ ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ብዙ ነው። ለምሳሌ በከተማ መኖር አለባቸው ተብሎ የሚያዙ አርንጓዴ ቦታችዎች እንዲሁም መናፈሻ ሊሆኑ የሚችሉ በሙሉ የተበላሹ ናቸው ›› ይላሉ።
ከተማን ከተማ የሚያሰኘው ህንፃው ብቻ አይደለም። አረንጓዴ አካባቢዎች እንዲሁም ክፍት ቦታዎች የተባሉትም በሥነ ሥርዓት ተቀናጅተው መመራት ያለባቸው ናቸው። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ሲታይ ይህን ይዞ እየመራ ያለ ከተማ ማነው ተብሎ ቢጠየቅ አንድም አይገኝም። በምሳሌነት እንኳ ሊጠቀስ የሚችል እርሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ የለም። እንዲያውም ኢትዮጵያ ለከተሜነት ያላተዘጋጀች መሆኗን አሳባቂዎች ናቸው።
‹‹ላለፉት አስራ ሁለት ዓመት ያህል በከፍተኛ የትምህርት ተቋሙ ቆይቻለሁ። ከዛ በፊት ደግሞ የከተማ ፕላንን በተመለከተ ሥራና ከተማ ልማት ነበር እስራ የነበረው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ሆኜ በመሥራቴ ስለ አዲስ አበባ በሚገባ አውቃለሁ›› የሚሉት ፕሮፌሰር ኃይሉ፣ ኢትዮጵያ ለከተሜነት ያላት ሁኔታ እና እንቅስቃሴ ገና ነው ቢባል እንደሚቀል ነው የሚያስረዱት።
ይህ ደግሞ በተለያየ መልክ ይገለፃል። ለምሳሌ በከተማ ፕላን ሥራ ላይ በተለይ በዘርፉ የሰለጠኑ አካላትም የሚሰሩት በሰለጠኑበትም ሙያ አይደለም። እርሳቸው በሚያስተምሩበት ህንፃ ኮሌጅ ይማራሉ፤ ነገር ግን ሥራ አያገኙም። ምክንያቱም ፕላን የሚደረግ ከተማ ጠፍቶ ሳይሆን አገሪቷ ባለመዘጋጀቷ ነው። በእርግጥ እነዚህን ባለሙያዎች የሚፈልግ ከተማ ጠፍቶ ሳይሆን መንግሥት ራሱ ለዛ ባለመዘጋጀቱ ነው። ግማሹ በተቋሙ የከተማ ፕላን አጥንቶ ሄዶ ግን በየከተሞቹ ውልና ማስረጃ ውስጥ ጋብቻ የሚያፈራርም ሆኖ ነው የሚቀረው።
ፕሮፌሰር ኃይሉ እንደሚሉት፤ በዘርፉ የተማሩ አካላት በተማሩበት ዘርፍ ሥራ አይሠሩም፤ ፕላኑ መሠራቱ የማይቀር ቢሆንም ከተሞችም በወጣላቸው የከተማ ፕላን መሠረት አይተገበሩም። ምክንያቱ በዋናነት ያለው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በትንንሽ ከተሞች ሕገ ወጥ ግንባታ አለ። ይህን የሚቆጣጠር አካል የለም። ለምሳሌ ለአረንጓዴ ቦታ ተብሎ የተቀመጠው መሬት ውድቅት ላይ የጨረቃ ቤት ይሰራበታል። ቀስ እያለ ይጎለብትና ለማፍረስ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ይደርሳል። ለማፍረስ ሲታሰብ ደግሞ ጫጫታ የበዛበት ሂደት ይሆናል። ስለዚህ አብዛኛው ጊዜ ከማስተር ፕላኑ ይልቅ ከተማን የሚቆጣጠረው ሕገ ወጥነት ነው። በማስተር ፕላኑ አሊያም በልማቱ መመራቱ ቀርቶ ሕገ ወጥ ግንባታው አስቀድሞ ሄዶ ከተማውን ይመራዋል። ይህ ድርጊት በየትኛውም ከተማ የሚታይ ነው፤ ብዙ ማስረጃም የሚያስፈልገው አይደለም።
ሌላው በሙስና የሚገለፀው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው። ከሙስና ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለው ችግር ከሌሎች አገሮች የተለየ አይደለም። በአገሪቱ ከሚገኘው ከሌላው ዘርፍም እንዲሁ የተለየ ነው ማለት አይቻልም። በኢኮኖሚውም ሆነ በሌላው ማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁ መሰል ችግሮች አሉ። በሁሉም ዘርፍ ሰው በሙያው ሲመደብ እምብዛም አይታይም። ምደባም የሚካሄደው አብዛኛውን ጊዜ ችሎታ ኖረም አልኖረም በፖለቲካ ወገንተኝነት ነው።
ተመዳቢው አካል ደግሞ የሚያስበው እስካለበት ጊዜ ድረስ የሆነ ነገር ተጠቅሞ መሄድን እንጂ ከተማዋን አሊያም አገሪቷን ወደፊት የማራመድ ሐሳብን አይተገብርም። ከተሾመ መቼ እንደሚነሳ ስለማያውቅ እስከዛው ድረስ ያጠፋውንም አጥፍቶ የተጠቀመውንም ተጠቅሞ መሄድን ነው የሚያልመው። ‹ከተማዋን አሻሽዬ ጥሩ ነገር አስመዘግባለሁ› የሚሉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ተማሪዎቻቸው ሆነው ብዙ ጊዜ ያገኟቸዋል። ብዙዎቹም በጥቅም የሚጠላለፉ ናቸው።
እዚህ አገር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ፈቀቅ ማለት ያልቻለው ለምንድን ነው? መንግሥት ዘርፉ እንዲያድግ በእጅጉ ቢፈልግም እልፍ ማለት ግን አለመቻሉን የሚገልፁት ፕሮፌሰር ኃይሉ፣ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ነው የሚናገሩት። የመጀመሪያው ብቁ የሆነና ጉዳዩን ወደፊት ማራመድ የሚችል የሰው ኃይል አለመኖሩ ነው። ቢኖርም ደግሞ አብዛኛው ባለሙያ የሚሰራው ቀደም ሲል እንደጠቀሱት ለራሱ እንጂ ለአገሪቱ አለመሆኑ ነው። እናም እነዚህን መሰል ችግሮች በከተማ ዘርፍም ይታያል። ለምሳሌ በከተማ አስተዳዳሪነት የሚመደብ ከንቲባ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስበው እንዴት አድርጌ ዘመዶቼንና ጓደኞቼን ልጥቀም ነው። የጌጠኛ ድንጋይ ለማስነጠፍ እንኳ በመጀመሪያ የሚደረገው ‹እንዴት አድርገን ከኮንትራክተሩ ጋር ተመሳጥረን እንብላ› የሚለው ነው።
በከተማ ዘርፍ ላይ የሚመደበው ጥቂት የማይባል ባለሙያተኛ እንዴት አድርጌ ዘመዶቼን ልጥቀም በሚል ነገር ሲጠመድ ይስተዋላል። ይህን ለማስጣልና ከተሜነትን በሚፈለገው ልክ ለማሳደግ መንግሥት ቆራጥ የሆነ እርምጃ መውሰድ አለበት። በየጊዜው ለውጥ ለውጥ ቢባልም የጠገበው ሄዶ የተራበው ስለሚመጣ የባሰ ችግር መኖሩን ነው የሚያመለክቱት።
‹‹ለዚህ ሁሉ ዋና ችግር የሆነው አገሪቱ የምትመራበት ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል›› ሲሉ ጠቅሰው፤ የከተማ ልማት ዘርፉን ብቻ ነጥሎ ችግሩ ያለው እሱ ዘንድ ነው ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ። መንግሥት ቁርጠኛ መሆን ሲኖርበት ይህ ችግር ይስተካከላል። በተለይ ሙስና ላይ የጠገበው ሄዶ በላተኛው እንዳይመጣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥራ ሊኖር የግድ ይላል።
በብዙዎች ዘንድ ከለውጡ ወዲህ ሙስና ይቀንሳል የሚል እምነት ነበር። ሁኔታው ግን ብሶበታል የሚያስብል ነው። ይህም የአገሪቱ የሥርዓት ችግር ነው። የከተማ ልማት ዘርፉን ብቻ ነጥሎ እሱ ብቻ በዚህ በኩል ይሂድ ማለት ሳይሆን እንደ አገር በጥቅሉ ሥርዓቱ ተስተካክሎ ብቁና ቁርጠኛ የሆነ የሰው ኃይል እንዲኖር ለማድረግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል። ጎን ለጎን ደግሞ አንድ ሰው ለሠራው ሥራ ተጠያቂም ተሸላሚም የሚሆንበት ሥርዓት ሊኖር ያስፈልጋል።
‹‹ይህን ስል ዝም ብሎ ለመተቸት አይደለም፤ ነገር ግን የመንግሥት ቁርጠኝነት ካለ እንደሚሻሻል ለመጥቀስ ነው። መንግሥት ሙስናን የማይታገስ መሆን አለበት። ይህንን ለማምጣት ደግሞ ውይይት ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን አንዱን አንስቶ ሌላውን መተካት በራሱ ትርጉም አይኖረውም።
ከተሜነት የሚያካትታቸው ነገሮች አሊያም አንድ ከተማ ከተማ ነው ሊያስብለው የሚችል ነገር ምንድን ነው ሲባል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪ በእርሻ የማይተዳደር ህዝብ ሲኖርበት ነው ተብሎ ይነገራል። ሌላው ብያኔ ደግሞ ከተማ ማለት ከሁለት ሺህ ሰው በላይ የሚኖርበት ስብስብ ነው ሲባል ይደመጣል። ይሁንና የከተማ ብያኔ ግን በዚህ ብቻ የሚለካ አይደለም። ዋናው ነገር የነዋሪው የሥልጣኔው ደረጃ ምን ያህል ነው የሚለውም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው የሚሉት ለዚህ ነው፤ ይህ ከተማን ለመጠበቀም ሆነ ለማስተዳደር የሚያግዝ ነው።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ህዝቡ ራሱ የገጠር ባህሪ ያለቀቀው ነው። ሚዲያችንም ስለሌላ ሌላ እንጂ ስለከተማ የአኗኗር ንቃተ ህሊና የሚያስጨብጡት መረጃ የለም። ነዋሪው ‹እዚህ አካባቢ መሽናት ክልክል ነው› የሚል ማስታወቂያ ኖረም አልኖረም ዞር ብሎ ሲሸና ይታያል። የሙዝ ልጣጭን በተገቢው ማስወገጃ ማስወገድ ሲገባ ሰለጠኑ የሚባሉትም የተሽከርካሪያቸውን መስታወት ዝቅ በማድረግ ሲጥሉ ይስተዋላሉ። ጽዳትን በተመለከተ ይህኛው የአኗኗር ዘይቤ መቀየር መቻል አለበት። ከተማ ሲባል ከተማ የሚፈልገው አይነት ስልጣኔም ሊኖር የግድ ነውና።
‹‹አንዱ ዛፍ ሲተከል ሌላው ቀጥፎ መፋቂያ የሚያደርግ ጊዜ ላይ ነን። ጥቂት የማይባለው ደግሞ ለከተማ ውበት ተብሎ አበባ ሲተከል ወደቤቱ ያስገባዋል። ስለዚህም ከተማን ከተማ ለማድረግ የሚያስችል የሥነ ልቦና ዝግጅቱ በራሱ ገና የዳበረ አይደለም። በዚህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ ሌላውም ሚዲያ ስለጉዳዩ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይጠበቅበታል። ነገር ግን በተለይ ሬዲዮ ሲከፈት ከዚህ እና መሰል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ይልቅ ምናልባት ከአስር ሚዲያ ውስጥ ስድስቱ ስለውጭ አገር ስፖርቱ ሳይታክቱ ሲያወሩ ይደመጣሉ። አንድ ሦስት ያህሉ ደግሞ ስለዘፈንና አርቲስቶች መረጃ ሲያቀብሉ ይውላሉ። ስለማኑፋክቸሪንግ፣ ስለከተማ ልማትና ስለሌሎችም ጉዳዮች የህዝብን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ምን ያህሉ ነው እየሠራ ያለው ቢባል በጣም ኢሚንት ሚዲያ ነው።
ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹የከተማነት ምልክት ከሆኑት መካከል አንዱ የከተማነት ንፅህና ሆኖ ሳለ ከተሞቻችንን ስናይ ግን ይህ አይንፀባረቅባቸውም። ነዋሪው ቆሻሻን አውጥቶ በአዩኝ አላዩኝ ያልተገባ ቦታ ሲጥል ይስተዋላል፡ ዝናብ ጠብ ሲል የመፀዳጃ ቤቱን ትቦ ወደውጭ በማውጣት ያለውን ቆሻሻ ሁሉ መንገድ ላይ ሲደፋ ምንም አይመስለውም። ጽዳትን ለመጠበቅ የግድ ሀብታም ከተማ መሆን አይጠበቅም፤ ደሃ ሆነው በጣም ንፁህ ከተሞች አሉ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ሚዲያው ባለመሥራቱ ተወቃሽ ነው›› ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ከዛ ውጭ ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችም እዚህ ላይ መንቀሳቀስ አለባቸው። የየከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤቶችም የየራሳቸውን የቤት ሥራ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። በአዲስ አበባም እንዲሁ ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር የበኩላቸውን ግንዛቤ ለመፍጠር የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው። እርሳቸው ወጥተው በየጊዜው ካላፀዱ በስተቀር በህዝብ ሲቀጥል አይታይም። ይህ ነገር ከምን የመነጨ ነው ሲባል የህዝብ ግንዛቤ አለመኖር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ተረድተው የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚወጡበት ጊዜ ብቻ ህዝቡ ወጥቶ ሽር ጉድ ከማለት ውጭ መሪውን ተከትለው ሲያስቀጥሉ አይታዩም። በመሆኑም ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጽዳቱ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ስለዚህ ጽዳቱ የዘመቻ ሳይሆን ሥርዓት ተበጅቶለት ቀጣይ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነታቸውንም ሊወጡ ይገባል።
ዋናው ነገር በኢኮኖሚ መበልፀግ ብቻ አይደለም፤ የአመለካከት ለውጥም ማምጣትም ጭምር ነው። ማህበራዊ ልማቱ ላይ መሠራት አለበት። ህዝቡ ስልጣኔውን ከራሱ ጋር ማዋሃድ አለበት። ህዝቡ የስልጣኔ ደረጃው አደገ ማለት ደግሞ ለፖለቲካውም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ምክንያቱም ያወቀና የሰለጠነ ህዝብ ፖለቲከኛው ሲያናግረው ይሰማዋል። ያወቀን ህዝብ ለማስተዳደርም በጣም ቀላል ይሆናል። ስለዚህ ማህበራዊ ልማቱ ላይ መሠራት እንዳለበት ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
አስቴር ኤልያስ