አርክቴክት ጋሻው አበራ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በከተማ ትራንስፖርት ፕላን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከተማ ፕላን እና አስተዳደር ከደቡብ ኮርያ አግኝተዋል። አሁን ዋናው ቢሮው ኒውዮርክ የሆነው የአይቲ ዲፒ የአፍሪካ ቢሮ ትራንስፖርት አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ። በከተሞች ልማት፤ በ10ኛው ማስተር ፕላን፤ በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- ከትምህርት በኋላ የት የት ሠሩ?
አርክቴክት ጋሻው፡- መጀመሪያ የሠራሁት አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ቢሮ ነው። ለ5 ዓመት የትራንስፖርትና መንገድ ጥናትን በተመለከተ የትራንስፖርት ፕላኒንግ ቡድን መሪ ሆኜ ሠርቻለሁ። ሁለተኛ ድግሪዬን ሠርቼ ከውጭ እንደተመለስኩ በበርካታ አገራት ቢሮዎች ላሉት አይ ቲ ዲ ፒ የሚባል መሰረቱን ኒውዮርክ ላይ ያደረገ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ እየሠራሁ ነው። ድርጅቱ የትራንስፖርት ፕላኒንግ ላይ ይሠራል።
ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ እየሠራሁ በሌሎችም ብዙ ፕሮጀክቶች ተሳትፌያለሁ። በተለይ የሽሬ ከተማ ማስተር ፕላንን እዚያው ድረስ በመሄድ ታደሰ ኮንሰልቲግ ከሚባል ተቋም ጋር ሠርቻለሁ። ማክቶ ከሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በትራንስፖርት ዙሪያም ሠርቻለሁ። ሀብታሙ ኮንሰልቲንግ በሚባል ድርጅት ውስጥ የጅማን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠርቻለሁ። ስታድያ ኮንሰልቲንግ የሚባል ትልቅ የመንገድ ዲዛይን ተቋም አለ። ከእነርሱ ጋርም ሁለት ፓኬጅ መንገዶች ሠርቻለሁ። ከዋይ ቲ ኤች ኮንሰልቲንግ ጋር የወላይታ ዩኒቨርሲቲ ማስተር ፕላንን ሠርቻለሁ። የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ዩኒቨርሲቲ ማስተር ፕላን ላይም ተሳትፌያለሁ። ሌሎችም በትርፍ ጊዜ የሠራኋቸው ብዙ ሥራዎች ይኖራሉ።
አዲስ ዘመን፡- የሙያ መስክዎ አንደኛው የከተማ ፕላን ሲሆን ሌላው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው። ለኢትዮጵያ ሁለቱም ወሳኝ ናቸው። እስቲ ስለ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ከተማ አመሰራረት ታሪክ ይንገሩን?
አርክቴክት ጋሻው፡- የማውቀውን ለማጋራት ያህል አዲስ አበባ አመሰራረቷ ከእቴጌ ጣይቱ ጊዜ ጀምሮ ሆኖ እንደ መጀመሪያው ማስተር ፕላን ተደርጎ የሚወሰደው የሰፈራ ፕላን ነው። በመቀጠል የተለያዩ የከተማ ፕላኖች በተለያዩ የውጭ ዜጎች ተሠርተዋል። በአጠቃላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ 9 ማስተር ፕላኖች ነበሩ። ከዘጠነኛውና ከአስረኛው ማስተር ፕላኖች ውጪ ሌሎቹ በፈረንሳዮችና በጣሊያኖች በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ ናቸው። የመጀመርያው የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን የእቴጌ ጣይቱ ነው። የሴትልመንት (የሰፈራ) ፕላን የሚባለው ማለት ነው።
የዘመኑ ሹሞች እንደየስልጣን ደረጃቸውና ለንጉሡ ባላቸው ቅርበት በንጉሡ አካባቢ ይሰፍሩ ነበር። ከእንጦጦ ተነስተው ፍልውሃ ድረስ በመውረድ የመጀመሪያው ከተማ እየሰፋ ሄዷል። ከእቴጌ ጣይቱ የሰፈራ ፕላን ቀጥሎ የተለያዩ ደረጃዎች ነበሩ። ለምሳሌ የሲኒማ ቦታዎች፤ የንግድ ቦታዎች፤ የመድሃኒት መሸጫ ቦታዎች፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በሚል ቁጥር እየተሰጠ ተሠርቶ ነበር። ያኔ ከተማዋም በጣም ትንሽ ነበረች። ብዙ ሰው አልነበረባትም። ከዚያ በኋላ ኩዲ እና ቪሊ የሚባሉ የኢጣሊያ መሐንዲሶች የሠሩት የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን አለ። አቨርኮቪ በሚባል ፈረንሳዊ መሐንዲስ የተሠራ ሌላ የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንም አለ። 9 ኛው ማስተር ፕላን ላይ የደረስነው በሂደት ነው። እኔ የማውቀው ዘጠነኛውንና አስረኛውን የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ከሁለተኛው እስከ ስምንተኛው ድረስ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላኖች በኢጣሊያና በፈረንሳውያን መሐንዲሶች የተሠሩ ናቸው። ከእነሱ ውጪ ሌሎች የተሳተፉ የውጭ አገራት ዜጎች ነበሩ?
አርክቴክት ጋሻው፡- ማስተር ፕላን የሚሠራው በየአስር ዓመቱ ነው። በተለያየ ጊዜ ተሠርተዋል። ስምንተኛውም የኢጣሊያን ማስተር ፕላን ነው። በኢትዮጵያውያን የተሠራው ዘጠነኛውና አስረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ሲሆን፤ እኛ ደግሞ የሠራነው የአሁኑን አስረኛውን ማስተር ፕላን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከበፊቶቹ ጋር ሲነጻጸር በእኛ ሰዎች የተሠራውን የተለየ የሚያደርገው ምንድነው ?
አርክትኬት ጋሻው፡- ለውጡ የሚመጣው ከሕዝብ እድገት መጨመርና ከአገልግሎቶች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ነው። በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው እጅግ በጣም ትንሽ ሕዝብ ነበር። አንድ ማስተር ፕላን በዋናነት የመሬት አጠቃቀም ጥናት ይኖረዋል። በሁለተኛ ደረጃ የትራንስፖርትና መንገድ ጥናት አለ፤ ይሄ የሚካሄደው በአንድ ላይ ነው። ሌላው ደግሞ የሕንፃ ከፍታ የሚባል አለ። ከዚያ የአረንጓዴ ስፍራዎች አሉት። ለእነዚህ የወንዝ ዳርቻው፤ የተጠበቀ ደን የሚባለውንና አጎራባች ፓርኮችን ጨምሮ ራሱን የቻለ አንድ የጥናት ቡድን አለው። የሚጠኑት በቡድን በቡድን ነው።
የመጀመሪያው የመሬት አጠቃቀም ቡድን የሚባል አለ። በወቅቱ ምን ምን ዓይነት የመሬት አጠቃቀሞች ነበሩ፤ አሉ የሚለው ብዙ ዝርዝሮች አሉት። አንደኛው የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ነው። (ሆስፒታል፤የቀብር ቦታዎች፤ትምህርት ቤቶች ወዘተ) ፕላኑ ላይ የሚወከሉት በአንድ ቀለም ነው። ኮድ ይኖራቸዋል። ለእነዚህ የምንጠቀመው ሰማያዊ ቀለም ይሆናል። የመኖሪያ ቦታዎች ሲሆኑ በቢጫ ይመላከታሉ። አረንጓዴ ቦታዎች ሲሆን በአረንጓዴ፤ የትራንስፖርት መናኸሪያ የአገልግሎት መስጫዎች፤ የአውሮፕላን መናኸሪያዎች የንግድ ቦታዎች አሉ። የኢንዱስትሪ ቦታዎች ሲሆኑ በሃምራዊ ቀለም ይወከላሉ። በዚህ መልኩ ካርታው ላይ በመሬት አጠቃቀሙ ውስጥ መለያ እንዲሆኑ በቀለሞች ተወክለው ሰፍረው ይቀመጣሉ ማለት ነው።
ዘጠነኛው መሪ የከተማ ፕላን (ማስተር ፕላን) ላይ የነበሩት የተለያዩ የመሬት አጠቃቀሞች፤ የትራንስፖርት፣ የሕንፃ ከፍታዎችን ካስቀመጠ ከ10 ዓመት በኋላ እንደገና መታየት ስለነበረበት በ2013 ዓ.ም አስረኛው የማስተር ፕላን ጥናት ተጀመረ። የቀደመው ታይቶ አገልግሎቱም አበቃ። 10ኛውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በሥራ አስኪያጅነት በዋናነት የመሩት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አርክቴክትና ፕላነር ማቲዎስ አስፋው ናቸው። የከተሞችን ፕላን መመሪያ ያወጡትም እርሳቸው ናቸው። አሁን ያሉት በጣሊያን አገር ነው። አስረኛው ማስተር ፕላን ዘጠነኛው ላይ የነበሩ ክፍተቶች ምን ምን ነበሩ ብሎ በመለየትና በማየት የጎደሉትን ለመሙላት የተሻለ ለማድረግ ጥረት የተደረገበት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ዘጠነኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ምን ምን ክፍተቶች ነበሩት ?
አርክቴክት ጋሻው፡- በዘጠነኛው ማስተር ፕላን ከነበሩት ክፍተቶች መካከል አንደኛው የቅይጥ መሬት አጠቃቀም የሚባለው ነው። አንድ አካባቢ ሙሉ በሙሉ የመኖሪያ ቤት አካባቢ መሆን የለበትም የሚል ነው። የተለያዩ የሚመጣጠኑ አገልግሎቶች ተያይዘው መምጣት አለባቸው። ለምሳሌ መኖሪያ ቤት አድርገን ኢንዱስትሪ አናስቀምጥም። ከመኖሪያ ቤቶች ጋር ግን የንግድ ቦታዎች፤ ድምፅ የማይበክሉ፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን አብረው እንዲኖሩ ማድረግ ይገባል። የተጨመረውን የሕዝብ ብዛት ያማከለ መሆንም ነበረበት።
ለምሳሌ በአዲስ አበባ የቤት አቅርቦት ችግር አለ። አዲስ አበባ አጠቃላይ የቆዳ ስፋቷ 54 ሺ ሔክታር ነው። አስረኛው የከተማዋ ማስተር ፕላን ጥናት ሲጀመር በ54 ሺ ሔክታር መሬት ላይ አዲስ አበባ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሕዝብ ነበራት። ይህ የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ ነው። እንጦጦ፣ አንቆርጫ፤ የካ አባዶን ጨምሮ ለመኖሪያ አመቺ ያልሆኑ ቦታዎች አሉ። ከዚያ ውጪ አረንጓዴ ቦታዎች ክፍትና እንደ አድዋ ፓርክ ዓይነቶች ሰፋፊ ሆነው ለልማት የማይሆኑ ቦታዎች አሉ።
መገንባት የሚቻልባቸው ቦታዎችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ከተሞች ፕላን ውስጥ የተቀመጡ መመሪያዎች አሉ። አንድ የከተማ ዲዛይን ሲሠራ ግንባታ የሚያርፍበት አርባ በመቶ ብቻ ነው ይላል። 30 በመቶ ለመንገድና ትራንስፖርት ይሆናል። የቀረው 30 በመቶ ደግሞ ለአረንጓዴ ቦታ ይውላል። ይሄ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያወጣው የከተሞች ፕላን መመሪያና መረጃ አለ። እዚያ ላይ በቁጥር ተቀምጠዋል። ከተሞች ማስተር ፕላናቸውን ሲያዘጋጁ የሚከተሉት እርሱን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለዋናው ማስተር ፕላን ቢነግሩን?
አርክቴኬት ጋሻው፡- አሁን ባለው ዝንባሌ ዘመናዊ የከተማ ፕላኒንግ ላይ በፊት የነበረውን ፎርም ተከትለን ባለችው ጠባብ መሬት ልማቱን ማምጣት ከባድ ነው። የተገመተ የሕዝብ ቁጥር እድገት ትንበያ አለ። 4 ሚሊዮን አካባቢ የሚል ነበር። የ2007 ዓ.ም መረጃ ስለሆነ አሁን ላይ ትክክለኛ አይሆንም። የሚጠበቀው ከዚያ በላይ የሕዝብ ብዛት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ትክክለኛ ቆጠራ ባይካሄድም አዲስ አበባ 7 እና 8 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል፤ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት ያለባት ከተማ ነች የሚሉ አሉ። እንዴት ያዩታል ?
አርክትኬት ጋሻው፡- የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ እንደዚያ አይደለም። ዩኤንዲፒና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ያስቀመጡትን ቁጥር ለመጠቀም ሞክረናል። ሰፋ አድርጎ የሕዝብ ብዛትን በታሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የመያዝና የምናስቀምጣቸውን አገልግሎቶችንና የመኖሪያ ቦታዎችን አብሮ ለማየት ተሞክሯል።
አንድ የተወሰነች ቦታ ላይ ግለሰብ ሲያለማ ብዙ ቦታዎችን ይወስዳል። በዚህ መልኩ ሌላ ዓለም ላይ እየተሠራ ችግር እየፈጠረ ነው። ለምሳሌ ሀይ ዴንሲቲ (ከፍተኛ ጥግግት) የሚባል ጽንሰ ሃሳብ አለ። አሁን የተዘጋጀው ማስተር ፕላን ከፍተኛ ጥግግትን ያበረታታል። በከተማ ማዕከልና በትራንስፖርት ኮሪደሮች ላይ የሕንፃ ከፍታውን የመጨመር፤ እያንዳንዳቸው የሚገነቡት ሕንፃዎች ደግሞ 60 በመቶ ለመኖሪያ አገልግሎት እንዲውሉ ማስገደድ በሚል የመኖሪያ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ያለመ ነው።
አሁን እንዳሉት ዓይነት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሠራን መቀጠል አንችልም። ጂ 3 እና ጂ 4 ስለሆኑ ያላቸው ጥግግት ዝቅተኛ ነው። እነዚህ የሚመጣውን ትውልድ ለመሸከም ለማስተናገድ አያገለግሉም። ያለው አማራጭ ከፍተኛ ጥግግት ነው። ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ሕንፃዎች በተወሰነ መሬት ላይ ወደላይ በመገንባት ብዙ ሕዝብ እንዲይዙ ማድረግ ነው። የሕዝብ ትራንስፖርት የምንላቸው አማራጮቻችን አሁን ባለው የአምበሳ አውቶቡስ የሀይገር ኮንቬንሽናል ባሶች በምንላቸው መቀጠል አይቻልም። ዘመናዊ ፈጣን የአውቶቡስ ትራንስፖርት ዘዴ ቢ አር ቲ መጠቀም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ቢ አር ቲ ትራንስፖርት ምንድ ነው?
አርክቴክት ጋሻው፡- ባስ ራፒድ ትራንዚት (ቢ አር ቲ) ፈጣን የአውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ማለት ነው። እንደ ባቡር መስመር አገልግሎት መሀል ላይ የሚኖር ቦታ አለ። ቢአርቲን በአዲስ አበባ ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል። አዋጭነቱ ስለታመነበት አሁን ጨረታ ተገብቶ ሁለት ኮሪደሮች ሊሠሩ ነው። አንደኛው ከዊንጌት ፓስተር፤ ከፓስተር አውቶቡስ ተራ፤ ከአውቶቡስ ተራ ዲ አፍሪክ፤ ከዲ አፍሪክ ሜክሲኮ፤ ከሜክሲኮ ቄራ፤ ከቄራ ቀጥሎ የሚሄድ አንድ ትልቅ ኮሪደር አለ። 16 ነጥብ 4 ኪሎሜትር ይሸፍናል።
አዲስ ዘመን፡- የሚሆነው አውቶቡስ ብቻ ነው? ወይስ ምንድነው?
አርክቴክት ጋሻው፡- በዋና ዋና መንገዶች መሀል ላይ 7 ሜትር መጠባበቂያ ይያዝለታል። በሁለት መንገድ ግራና ቀኝ 3 ነጥብ 5 ሜትር ለየብቻ ይኖረዋል። በአጠቃላይ 7 ሜትር ማለት ነው። አንዱ የአውቶቡሱ መሄጃ ሌላኛው መመለሻ ነው። ከአፍሪካ ውስጥ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ታንዛኒያ ነች። ከላቲን አሜሪካ አገራት ኮሎምቢያ ቦጎታና የብራዚል ኩርቲባ ከተሞች ናቸው። እዚያም ሄደን ዓይተን ነበር። የተጨናነቀውን ቅይጥ ትራፊክ (ሁሉም ዓይነት መኪኖች ከሚተራመሱበት ወጣ ብለን ለብቻው አውቶቡስን ለማንቀሳቀስ ብቻ የምንጠቀምበት መንገድ ነው። የቢአርቲ (ባስ ራፒድ ትራንዚት) ዋና ዋና ባሕርያት አንደኛ ፈጣን ትራንስፖርትን ያመጣል። መጨናነቅን ያስወግዳል። ሁለተኛው ምቾት ያለው ትራንስፖርት ይሆናል። ሦስተኛው የማሕበረሰቡን አቅም ያማከለ ነው።
15 የፈጣን አውቶቡስ መስመሮች ዝርጋታ በ10ኛው የከተማ መሪ ፕላን ውስጥ ተቀምጧል። ቀደም ብሎ የሚሠራው የምንገለገልባቸውን የአውቶቡስ መስመሮችን ተከትሎ ነው። ከሌላው የመንገዱ አካል ተለይቶ ኮንክሪት ይሞላና የአውቶቡስ መሄጃ ብቻ ይሆናል። በዚሁ የቢአርቲ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት በቅርቡ ታንዛኒያ ነበርኩ። ሌጎስም እየተሠራ ነው።
በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የመጀመሪያው ኮሪደር ከዊንጌት ጀምሮ ያለው ይሠራል። የሚታወቁት የቀላል ባቡር መስመሮች ከጦር ኃይሎች እስከ አያት፤ ከጊዮርጊስ እስከ ቃሊቲ የሚሄዱትን ተከትሎ ይሠራል።
አዲስ ዘመን፡- ለመጀመር የታሰበው መቼ ነው? ፈንድ ተገኝቶለታል?
አርክቴክት ጋሻው፡- ኢኮኖሚክ ፕላን የሚባል አለ። ራሱን የቻለ ነው። የኢኮኖሚ ጥናቱ በኢኮኖሚስቶች የሚያዝ ነው። ውይይት የሚካሄድበት ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ውይይት እንደማይካሄድ እየተገለጸ ነው። የተነሳው ሃሳብ ማይክሮ ስኬልን የሚያራምደው ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ሌላ ኢንዱስትሪን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ አማራጮችን ማምጣት አለብን የሚል ነው። ኢኮኖሚውን እንዴት ማሳደግ ይቻላል የሚለውን በተመለከተ ማስተር ፕላኑ አማራጮችን አስቀምጧል። ቱሪዝምና የተለያዩ ዘርፎች አሉ። የታሰበው አሁን ባለው ሁኔታ ሳይሆን በትልቅ ደረጃ ነው። የቀረበው አማራጭ መንግሥት ብቻውን ከሚያለማ የግሉን ዘርፉም እየደገፈ ጥቅሙንና ጉዳቱን መካፈል የሚችልበት አማራጮች ናቸው።
ከአስፈላጊነቱ አንጻር እነዚህ ቦታዎች ላይ የሚገነቡት ሕንፃዎች ከፍታቸው ይሄን ያህል መሆን አለበት ተብሎ የተወሰነው ቢያንስ ስሌቱ ላይ የሆነች ቦታ በመውሰድ ነው። ሁሉም ቦታ ላይ ከፍተኛ ጥግግት ይሆናል ማለት አይደለም። የሕንፃው ከፍታ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ኮሪደሮች ላይ ከፍተኛ ጥግግት ይሆናል። ከጂ 19 በላይ 20 ወለል ይሆናል ማለት ነው። ሌሎች ቦታዎች ላይ እያነሰ ይመጣል።
በዋነኛነት የወሰድነው የቀለበት መንገዱ አለ። በፊት ቀለበት መንገዱ የተሠራው እንደ ከተማ ዳርቻ ተቆጥሮ ነበር። በዘጠነኛው ማስተር ፕላን ላይ አንድ ክፍተት አገኘን ማለት ነው። አሁን ባለው የከተማ ስፋት እነ አያት፤ የካ አባዶ፣ ኮዬፈጬ፣ ጀሞ እና ዊንጌት በአምስቱም አቅጣጫዎች እስከ አስኮና ከታ ድረስ ሰፊ ሰፈራዎች አሉ። እነሱን ተጭኖ በትናንሽ ነገሮች የሚለማበትን ሁኔታ ይዞ ከተማው መቀጠል አይችልም። በምሳሌነት የሚጠሩት ያደጉ አገራት ኒውዮርክን የመሰሉ በሕዝብ ብዛት እነ ቶኪዮ ጃፓን፤ ደቡብ ኮርያ ሶል፤ የኤሽያ ከተሞች ኢንዶኔዥያ ጃካርታ፤ ፔሩ ሊማ ላይም ከፍተኛ የሕዝብ ጥግግት አላቸው። ይሄን የሚያደርጉት ያለ ምክንያት አይደለም።
አብዛኛው አርባናይዜሽን (የከተማ እድገት) በተመለከተ ሁሉም ትኩረቱ አዲስ አበባ ላይ ነው። ሁለተኛ ከተሞች የሚባሉትም ያን ያህል እያደጉ እየለሙ አይደለም። አብዛኛው ገጠር ወይንም ሌሎች ከተሞች ያለው ሕዝብ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። ይህ መጥፎ ጎን አለው።
ከተሞች ጥግ ጥግ ያሉ ቦታዎች እየለሙ ሲሄዱ ወሰኑ (ድንበሩ) ገደብ የለሽ ይሆናል፤ አይታወቅም። ሁለት ዓይነት ወሰኖች አሉ። አንደኛው አስተዳደራዊ ወሰን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ፕላኒንግ ባውንደሪ ( የፕላን ወሰን) የሚባል ነው።
በተለምዶ ወሰን የሚደረገው በወንዞች፣ ተራራዎች በተፈጥሮ ምልክቶች ነው። ለእድገት የተወሰነ አጥር አይሠራም። አብሮ የሚሠራበት ሁኔታ ቢመቻች ለእድገቱ ይጠቅማል። ፕራይሜሲ (ቅድሚያ) የሚባል ሌላ ጽንሰ ሃሳብ አለ። አንድ ከተማ ብቻውን እያደገ ሲመጣ ጫና ይበዛበታል። የመንገድ መጨናነቅ፤ የአየር መበከል፤ የአገልግሎት እጥረት፤ የውሃ የመብራት የመሳሰሉት ችግር ያጋጥማሉ። እነዚህን ለመቅረፍ በጋራ የመሥራቱ ሁኔታ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የትራንስፖርት ችግሩን እንመልከት። ከፍተኛ የሕዝብ ብዛትና መጨ ናነቅ በየጊዜው እየጨመረ ባለበት ሁኔታ የትራን ስፖርት ችግሩ ከአቅም በላይ ሆኗል። ችግሩን ማስታገስ እንጂ መፍታት አልተቻለም። እንደ ሙያ ተኛ ይሄ ችግር የሚፈ ታው እንዴት ነው ብለው ያስ ባሉ ?
አርክቴክት ጋሻው፡- ዘመናዊ የፕላኒንግ ጽንሰ ሃሳቦች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ሁኔታ የቤት መኪና አማራጭ አይደለም። ሌሎችም ሀገራት አቅጣጫቸውን እየለወጡ ነው። ብዙ መኪናዎች ነበራ ቸው። በ1980ዎቹ ኢንዱስትሪ ላይ ባተኮረው የከተማ ልማት (አርባናይዜሽን) መሰረት መኪና ላይ በከፍተኛ ደረጃ ያተኮረ እንቅስቃሴ ነበራቸው። ሁሉም የመኪና ጥገኛ ነበሩ። አሁን በኢትዮጵያም ይህ እየሆነ ነው።
ብዙ መሰረተ ልማት ለመገንባት ሲቻል ለመንገድ ሥራ ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ወጣ። የተለያዩ ቀለበት መንገዶች ተሠሩ። አደጋው እየጨመረ መጣ። አሁን ከሚታዩት የተለያዩ በሽታዎች የበለጠ የመኪና አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው። ከዚህ ውጪ ሃያ የሚሆኑ የቤት መኪናዎችን መንገድ ላይ የሚጠቀሙ ሰዎች ስታዩ በአማካይ በውስጣቸው ሁለት ሰው ቢይዙ ሌላ ደግሞ አንድ አውቶቡስ በዚያ መስመር ላይ ቢያልፍ ተመሳሳይ ሰዎችን መያዝ ይቻላል። ስለዚህ የሕዝብ ማመላለሻዎችን (ፐብሊክ ትራንስፖርት) በማበረታታት ቢአርቲ (ባስ ራፒድ ትራንስፖርትን) ማራመዱ የሚጠቅመው ለዚህ ነው። መንገድ አይዘጋጋም። ለአውቶቡሱ ብቻ የሚሆን የራስ መስመር አለ። ምቾት አለው። መገናኛና መለያያ ቦታዎች ላይ ቅድሚያ ይሰጣል። ተከፍሎ የሚገባው አውቶቡስ ውስጥ አይደለም፤ ውጪ ነው። ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። በቢ አር ቲ የፕሮጀክት መንገድ ከተቀመጡት ውስጥ ትራንስፖርት ቢሮው ወስዶ አንደኛውን በፈረንሳይ ዕርዳታ ድርጅት የተወሰነውን ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ይከወናል። አብሬያቸው የምሠራው ፕሮጀክት እሱን ነው። ዲዛይኑን ጨርሰን ወደ ትግበራ የምንገባበትን ጨረታ እያዘጋጀን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የግል መኪናዎች እንዴት ይሆናሉ?
አርክቴክት ጋሻው፡- የግልመኪና መጨመሩ ሰው መግዛቱ አይቀርም። ሌላው የእኛ ሀገር ችግር መኪናን የሚወስደው እንደ ደረጃ(አቅም) ማሳያ ነው። ሌሎች ያደጉ አገራት ከመኪና ይልቅ ብስክሌቶችን መጠቀም በእግር መሄድ (መጓዝ) አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ያዘወትራሉ። ያደጉ አገራት የግል መኪናን አያበረታቱም። ለመግዛት የሚከለክል የለም። እኛ መኪናን በተመለከተ ከፍተኛ የታክስ ሲስተም ነበረን። ያ ይገድበው ነበር። እንደገና ከሌላው አገር አንፃር ሲታይ እኛ ሀገር የመኪና ባለቤትነት በጣም ዝቅተኛ ነው። ከናይሮቢ ጋር እንኳን ቢነጻፀር እዚያ በመኪና ብዛት የተነሳ መንቀሳቀስ አይቻልም። አሁን የራይድ ኦፕሬተሮች ዲጂታል ታክሲዎች ሲጨመሩ እየበዛ ይመጣል። የግሉም እንደዚያው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከተማዋ ልታስተናግደው የምትችለው እንዴት ነው?
አርክቴክት ጋሻው፡- አንዱ የሚገታው የታክስ ስርዓቱ ነበር። ይጨምር ይቀንስ አናውቅም። ሌሎች አማራጮች አሉ። አንደኛው እንግሊዝን በምሳሌነት ብንወስድ ለንደን መሀል ከተማ ላይ መኪናህን ይዘህ ከመጣህ ለፓርኪንግ ከፍተኛ ገንዘብ ብዙ ፓውንድ የመክፈል ግዴታ አለብህ። በጣም ሀብታም ወይንም ግዴለሽ ካልሆንክ በስተቀር የግል መኪናህን ይዘህ መሀል ከተማ አትገባም።
ሌሎች አገራትም ይሄን ልምድ ወስደው መጠቀም ጀምረዋል። ቤጂንግ (ቻይና) ላይ ደግሞ ጎዶሎና ሙሉ ቁጥሮች ያላቸውን መኪኖች በተለያየ ጊዜ እንዲወጡ አድርገዋል። አንዳንዶቹ ሀብታሞች ስለሆኑ ሁልጊዜ ለመንቀሳቀስ እንዲችሉ ሙሉና ጎዶሎ ቁጥር ያላቸው መኪኖች ይገዛሉ። ሌላው ችግሩን ለማለዘብ እየሠራንበት ያለ አለ። በአጭር ርቀቶች ብስክሌትን እንዲጠቀሙ ማበረታታት ነው። አንድ ፓይለት ፕሮጀክት ከጀሞ ለቡ የሚል ነበረን። እንደዚያ እያጠናን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለብስክሌቶች ብቻውን መንገድ ይኖራል ማለት ነው?
አርክቴክት ጋሻው፡- አይደለም። እንደ አውቶቡሱ ሆኖ ከእግረኛው መሄጃ መስመር ቀጥሎ የሚሆነው ነው። 20 ሴንቲሜትር ስፋት ያላት የምትሆን ኮንክሪት የምትሞላ ከመደበኛው ትራፊክ መለያ መስመር ትኖራለች። እንደሱ ተደርጎ የብስክሌት መንገዶችን ከተማው ላይ የመሥራት የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል። ዓላማው ሰው በብዛት ብስክሌትን እንዲጠቀም ማበረታት ነው።
ሴፍ ሳይክሊንግ ፕሮጀክት የሚባል አንድ ዓመት የፈጀ አንድ ፕሮጀክት ነበረ። እርሱም ላይ ብዙ ጉዳዮች ተነስተዋል። ለምሳሌ ሕንድ ላይ ይሄን ፕሮጀክት የሚሠራው በዋናነት ጂአይዜድ ነበር። እኛ አገርም ወደ 200 ሺህ ዩሮ ተገኝቶ ብስክሌትን ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጎ ነበር። የደህንነት (ሴፍቲ) ጉዳይ መጣ። አሁንም የመኪና አደጋዎችና ያነሳኋቸው የቶፖግራፊ (የመሬት አቀማመጥ) ጉዳዮች ይኖራሉ። አዲስ አበባን ወደጎን የሚቆርጠው ከታች ከአቃቂ ወይ ከቃሊቲ ወደ ጊዮርጊስ ከፍተኛ የከፍታ ልዩነት አለ።
አብዛኞቹ መንገዶች ከከፍታው በተጻራሪ ስለሚሠሩ ያን ያህል የደረጃ ልዩነት የላቸውም። ሌላ ደግሞ ኤሌክትሮኒክ ብስክሌት የሚባል ተራራ ላይ ጭምር የሚወጣባቸው የተለያዩ ዓይነቶች አሉ። በእነሱም መጠቀም ይቻላል። ከእኛ የባሰ የመሬት አቀማመጥ ያላቸው ሀገሮች አሉ። የኖርኩበት ሲኦል(ኮርያ) ተራራ አላት። በይበልጥ ብስክሌት ተጠቃሚዎች አሉበት።
ለምሳሌ ከአዲሱ ገበያ ወደላይ ወደሚያስወጣው መንገድ ለመሄድ መንገዶቹ ሲቋረጡ ዚግዛግ እየተደረጉ መሄድ ይቻላል። ቀጥ ተብሎ አይወጣም። እንጦጦ ላይም በፓርኩ ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሠራ የተደረገ መንገድ አለ።
ሌላው የከባቢ አየር ሁኔታን በምክንያትነት ይጠቀሳል። አዲስ አበባ በጣም ሞቃታማ ነች። ዝናብ ሲመጣስ የሚሆነው እንዴት ነው ብለው ሲጠይቁ ያልተረዱት ወይንም ያላወቁት ነገር በረዶ የሚዘንብባቸው ሀገራት በብስክሌት ትልቅ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ነው። ኔዘርላንድ 13 ሚሊዮን ሕዝብና 26 ሚሊዮን ብስክሌት አላት። ፐብሊክ ትራንስፖርት ነው ማለት ነው። የግል መኪና የሚጠቀም በጣም ጥቂት ነው። ኔዘርላንድ ብስክሌትን በመጠቀም ለዓለም ጥሩ ምሳሌ የምትሆን ሀገር ነች። የእሷን ፈለግ ተከትለው ያደጉና የበለጸጉ ሀገራት ሥራ ላይ እያዋሉት ነው።
የእኛ ቢሮ ያለባቸው በአሜሪካም ሆነ በቻይና እነሱም በየከተሞቻቸው ብስክሌት ተጠቃሚነትን እያስፋፉ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ከመጣው ኮቪድ 19 በሽታ ጋር የብስክሌት ተጠቃሚነትን እያበረታቱ ነው። ኡጋንዳ በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ብስክሌት ማምረት (ሳይክል ማኒፋክቸሪነግ) ልትጀምር ነው። የግለሰብ ትራንስፖርት ስለሆነ ብዙ ንክኪ የለውም። በቻይና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ ፐብሊክ ትራንስፖርት እየቀነሰ ነው። ፐብሊክ ትራንስፖርት እየተጠቀምን ቢሆንም ብስክሌትም ሌላው አማራጭ ነው። እንደውም በዚህ ዓይነት ወቅት የተሻለ አማራጭ ነው።
ይሄን በተመለከተ የብስክሌት ትራንስፖርትን ተጠቃሚነት ለማበረታታት በከተማ አስተዳደሩ በኩል የአዲስ አበባ ትራንስፖርት የሚሠራበት ሰነድ ተዘጋጅቷል። እኔም አለሁበት። ብስክሌትን በእግር ጉዞ መጠቀምን የማበረታታት ሥራ ይሠራል። የመንገድ መገጣጠሚያዎች ላይ ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ 22 እና መገናኛ አካባቢ እያሻሻሉት ነው። እሱም ከሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ የወጣ ነው።
በተጨማሪ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የእግረኛ መንገድ ማሻሻያ የሚባሉ ፕሮጀክቶች አሉ። ይሄንንም በሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂው እየሠሩበት ነው። ማንዋሉን አዘጋጅተን መሄድ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም ሲደወሉ ለሚሠሩት መንገዶች ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ ምክር እንሰጣለን። በዚህ መሰረት አዲስ አበባን አሁን ባለችበት ሁኔታም ደረጃዋን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግና ማሻሻል መለወጥ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ቃለምልልስ እናመሰግናለን።
አርክቴክት ጋሻው አበራ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2012
ወንድወሰን መኮንን