ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዝግጅቶች አንዳንድ የፖለቲካ እንከኖችን በአጠቃላይና የኢትዮጵያን ደግሞ በተለይ ለማየት ሞክረናል። በዚህ ዝግጅት ውስጥ ደግሞ ለሀገራችን የፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ ፍለጋ ይረዳሉ ተብለው የታመኑባቸው መንደርደሪያ ሐሳቦችን ለማንሳት እንሞክራለን። በኢትዮጵያ በደካማ አስተሳሰብና በጭቆና ሥርዓት ምክንያት ሕይወትንና ዕድገትን የተሻለ ማድረግ የሚያስችል ግዙፍ አቅም ባክኖአል፤ ዛሬም እየባከነ ነው። ችግሩ ግልጽ ቢሆንም መፍትሔው እንደራቀን ነው። በእርግጥ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ማግኘት ይሳናቸዋል ተብሎ አይገመትም። ይሁን እንጂ በተግባር ከግምት በታች ሆነናል። በአእምሮአችንና በእጆቻችን የፈጠርናቸውን የፖለቲካ ችግሮች በራሳችን ጥረት መፍታት አለመቻላችን አሳንሶናል፤ መሆን የምንፈልገውን እንዳንሆንና መድረስ ከነበረብን እንዳንደርስ አድርጎናል። ሁልጊዜ ጊዜያዊ እሳት ማጥፋት እንጂ ችግሮችን ከሥረ-መሠረታቸው ነቅለን መጣል አልቻልንም።
ይህን የውድቀት ታሪክ ለመለወጥ በራስ አቅም መነሳሳት ያስፈልጋል። ሀገራዊ ጉዳይን ከመሠረቱ ለመቀየር ከራስ መጀመር ተመራጭ ነው። በመጀመሪያ ራስን በበጎ ፈቃድና ቅንነት መሙላት ይጠቅማል። ከነበረብን የጉግማንጉግ ፖለቲካ ራሳችንን ነፃ ማድረግ አማራጭ የማይገኝለት ታሪካዊ ሥራ ነው። ይህ ማለት በግለሰብ፤ በማሕረሰብ፤ በቡድን፤ በፓርቲ፤ በተቋምና በሀገር ደረጃ ያሉብንን መልካም ያልሆኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ማስወገድ ማለት ነው። ይህን ማድረግ ሀገርን፤ ሕዝብን፤ ትውልድንና ራስን መታደግ ነው። በስሕተት ወይም ባለማወቅ የተፈጠረን ችግር መፍታት ብዙ ላያስቸግር ይችላል። ሆን ተብሎ በክፋት የተፈጠረን ችግር መፍታት ግን ይከብዳል። በጎ ፈቃድና ቅንነት ካለ ግን የሚከብደው ችግር ራሱ ቀላል ይሆናል። የሀገርን ችግር ለመፍታት የመጀመሪያ እርምጃ የችግርዋ አካል አለመሆን ነው። እንችላለን ብለን ከተነሳን ያለመቻል መንፈስን እናሸንፋለን።
ለሀገር፤ ለወገንና ለራሱ ጉዳይ ሲል ቅን መሆን የማይፈልግና የማይችል ወገን ካለ ሰብአዊ ፍጡርነቱን መጠራጠር አለበት። እኛ ኢትዮጵያውያን ለፈጠርናቸው ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል ቅንነት የሚጎድለን ከሆነ ኢትዮጵያዊነታችንን መጠራጠር አለብን። በየትኛውም አቅጣጫ ኢትዮጵያን ለመታደግ የማያገለግል ኢትዮጵያዊነት ደግሞ እንደ ዜግነት ኢትዮጵያን አይመጥናትም። እስካሁን ከነበረን የጉግማንጉግ ታሪክ በመላቀቅ የሰላምና የልማት፤ የፍቅርና የክብር ታሪክ ለመስራት ቅንነት የሚያንሰን ከሆነ የአስተሳሰብ ድህነት ሰለባ መሆናችንን መረዳት አለብን። ይህ ደግሞ ከችግሩ እንጂ ከመፍትሔው አካል አያደርገንም።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተማረ ባይሆንም ከሕይወት ልምዱ ባገኘው ግንዛቤ የሚበጅንና የማይበጅን፤ የሚጠቅምንና የሚጎዳን በሚገባ የሚረዳ ነው። አብሮነቱን የሚፈልግና የሚያከብር፤ ለሀገሩ ዳር ድንበርና ነፃነት ቀናኢ ነው። በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ግን እጅግ ሲቸገርና ሲቸጋገር ኖሮአል። ሁልገዜ በሴራ፤ በተንኮልና በጠለፋ በተገማመዱ አሠራሮች ወደ ሥልጣን የዘለቁ ሊህቃን አቅም ሲያሳጡት ቆይተዋል። ይህ ትላንት የነበረ እውነት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ያለ ኩነት ነው። የሊህቃኑ የፖለቲካ ቅኝት ዛሬም እንደ ድሮና ትላንቱ ነው። አሁንም የምናወራው ለዓመታት ስለአወራናቸው ጥላቻ፤ አሉባልታ፤ ውሸት፤ ማደናገር፤ ሸፍጥ፤ ማጠልሸት፤ መኮነንና ማጋነን ነው። እነዚህ የሕዝቡን ውስጠ-ሕይወትና ግንኙነት መርዘዋል፤ እየመረዙም ነው። ችግሮች ካንዱ ወደሌላው እየተንከባለሉ፤ በዓይነት እየተወሳሰቡና በመጠን እየገዘፉ መጥተው ዛሬ ሀገርንና ሕዝብን ከአደጋ አፋፍ ላይ አድርሰዋል። የጥላቻ መረቦች እንዳሉ ሆነው ወደፊት መሄድ ጭራሽ አይታሰብም።
ውስብስብ ችግሮች ቢኖሩብንም ተስፋን የሚያለመልሙ በርካታ ነገሮች እንዳሉን መገንዘብም ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያ ለልማትና ዕድገት፤ ለውበትና ድምቀት፤ ለፍቅርና ሰላም፤ ለኃይልና ሀብት ፈጠራ የሚመቹ ብዙ ነገሮች አሏት። ብዙ የተፈጥሮ አካባቢዎች፤ ወንዞች፤ ሀይቆች፤ የየብስና የከርሰ-ምድር ማዕድናት እንዳሏት ይታወቃል። የበለፀጉ ሀገሮች የዳበረ ሀብት አላቸው። ኢትዮጵያ ደግሞ ሊበለፅግ የሚችል ያልበለፀገ ሀብት አላት። በተለያዩ ኬሚካሎችና መርዛማ ነገሮች ያልተበከለ የአየር ሁኔታ ያላት መሆኑ ለብዙ ነገሮች ተመራጭ ያደርጋታል። የደን ሀብትን በማልማት ብቻ ያለ ብዙ ድካምና ወጭ ባጭር ጊዜ ውስጥ የባከኑ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችን መመለስ ይቻላል። የውኃ ሀብትን ከነዳጅ ሀብት ባልተናነሰ መንገድ መጠቀም ብንችል ድህነትን ታሪክ ማድረግ ሩቅ አይሆንም።
ሀገራችን እንደበለፀጉ ሀገሮች ከተፈጥሮ ሥርዓት ርቃ አለመሄዷ ራሱ በመልካም አጋጣሚነት ሊወሰድ የሚችል ነው። በፖለቲካ ምክንያት በሚፈለገው መጠንና መልክ ዳብሮ ችግሮችን የመቋቋም አቅም ባይፈጥርላትም፤ ኢትዮጵያ ተሳስበውና ተቻችለው፤ ተረዳድተውና ተዛዝነው የሚኖሩ ሕዝቦች ሀገር መሆኗ ራሱ ትልቅ ዕድል ነው። ሕዝቦቻችን በቋንቋ፤ በሃይማኖት፤ በነገድ፤ በባሕልና በመሳሰሉት መለያየታቸው ለገዢዎች የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምቹ ሆኖ መቆየቱ ጉዳት ቢሆንም ለሀገሪቱ የውበትና ድምቀት፤ የሀብትና ጉልበት ምንጭ መሆን የሚችል ፀጋ ነው። የሀገራችን ዋነኛ ችግር የፖለቲካ ችግር ነው። ላሉት የፖለቲካ ችግሮች መፍትሔ ማስገኘት ከተቻለ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተአምር መስራት የሚያስችል አቅም በሀገራችን ውስጥ አለ።
የሚፈለግ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ነው? ሁሉም ሰው፤ ሕዝብና ሀገር መርካት የሚገባው ፍላጎት አለው። ፍላጎቶች መርካት የሚችሉት የተፈለጉ ነገሮች መገኘት ሲችሉ ነው። የሰላምና የሥርዓት፤ የህግና የደንብ መኖር የግለሰብ፤ የሕዝብ፤ የተቋማት ወዘተ ፍላጎት ነው። እነዚህ ሁሉ ሰላምና ፍቅርን የሚያስከብር፤ ዕድገትና ልማትን የሚያመጣ፤ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን የሚያስጠብቅ፤ የሕግ የበላይነትንና የሀገር ልዕልናን የሚያሰፍን የፖለቲካ ሥርዓት ይፈልጋሉ። ባጭሩ ይህን ማርካት የሚስችል ሥልጣን ወይም አቅም ያለው ተቋም መፈጠር የተገልጋይ ፍላጎት ነው። ሥልጣን ይዞ ሀገርን መምራት የፖለቲከኛ ፍላጎት ነው። ሁለቱም ፍላጎቶች የሚረኩት የሚፈለገው የፖለቲካ ሥርዓት ሲፈጠር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝባችን የፖለቲካ ፍላጎቱን የሚያረካ የፖለቲካ ሥርዓት አግኝቶ አያውቅም። በመሠረቱ የኢትዮጵያና የሕዝብዋ ፍላጎትና ጥቅም፤ ክብርና ልዕልና ከማናቸውም ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎትና ጥቅም በላይ ነው። የኢትዮጵያ ፍላጎት ወደ አንድ ግለሰብ፤ ቡድን ወይም ፓርቲ ፍላጎት የሚጨፈለቅ አይደለም። ሀገሪቱ እጅግ በጣም ሰፊና ውስብስብ ፍላጎት አላት።
ዛሬ ለኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ሕዝብና መንግሥት ለመቀጠልና ለማደግ መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ አስፈላጊ ነው። ይህ አማራጭ የማይገኝለት ብቸኛ መንገድ ነው። አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በትንሽ እውነትና በትላልቅ ውሸቶች መካከል መከራዋን ስታይ ኖራለች። ሊያድኑአት በሚታገሉና ሊያጠፏት በሚያሴሩ ወገኖች መካከል ሆና አበሳዋን አይታለች። በላይዋ ላይ ሰፍኖ የቆየው የጉግማንጉግ ሥርዓት ዕድገቱን ከጨረሰ ብዙ ጊዜ ቢሆነውም በተፈጠሩት ውስብስብ መዋቅሮችና ተግዳሮቶች ምክንያት ሙሉ በሙሉ አልተወገደም። አሁን ያለው ትውልድ ከሞላ ጎደል ጨቋኝ ሥርዓቶች መወገድ እንዳለባቸው የተረዳ፤ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓተ-መንግሥት አንደሚያስፈልግ የተገነዘበ፤ ይህ መምጣት የሚችለው ሰላማዊ በሆነ የሕዝብ ድምፅ መሆኑን የሚገነዘብና ይህን እውን ለማድረግ ራሱን ያዘጋጀ፤ ባጭሩ ከእንዲህ ዓይነት ሥርዓት ጋር እየተጃጃለና እየተሞዳሞደ መቀጠል የሚፈልግ ትውልድ አይደለም።
ለራሳችን ሳንዋሽ መንገር ካለብን ኢትዮጵያን አደገኛ ቁልቁለት ላይ አድርሰናታል። አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ ዛሬ መንታ መንገድ ላይ ነች ይላሉ። አንደኛው መንገድ ወደ ጨለማ የሚወስድ፤ ሌላኛው ወደ ብርሃን የሚያወጣ ነው። ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነን። እስካሁን የነበርንበት መንገድ መዘጋት አለበት – የማያለማ ወይም የማያጠፋ መንገድ ነው። በሀገራችን በጠመንጃ ያልታገዘ የሥልጣን ሽግግር፤ በፖለቲካ ዙሪያ ጥልቅና ምክንያታዊ የሆነ ውይይትና ምክክር ተደርጎ አያውቅም። አንዱ ለሰላም ሲዘምር ሌላው ለጦርነት ያቅራራል፤ አንዱ ስለፍቅር ሲሰብክ ሌላው ጥላቻን ያስተምራል። በአጋጣሚ በሐሳብ ደረጃ መልካም ነገሮች ቢያሸንፉ እንኳ በተግባር መጥፎ ድርጊቶች ድሉን ይነጥቃሉ። መልካም በሆኑ ቋንቋዎች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። የበግ ለምድ የለበሱ ቀበሮዎች ያለማቋረጥ የክፋትና የጥፋት መረቦች ይተበትባሉ። አሁን የኢትዮጵያ መሬትና ሕዝብ ክፋትና ጥፋትን መሸከም ከማይችሉበት ጊዜ ላይ ደርሰዋል። እውነተኛ ዜጎች የሚመኟት ኢትዮጵያ የበለፀገችና የደመቀች፤ የተከበረችና የታፈረች፤ ለልጆችዋ የምትቆረቆርና የምትመችዋን ነው።
እስካሁን ለነበሩት የጉግማንጉግ ፖለቲካ ሥርዓቶች መሠረትና ጉልበት ሆነው ከቆዩት ነገሮች መካከል አንዱ የሕዝቡ አለማወቅና የንቃተ-ሕሊና ደረጃው ዝቅተኛ መሆን ነው። አሁን ግን የሕዝብ የፖለቲካ ንቃተ-ሕሊና ከፍ ብሏል። ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ሌሎችን እያዳከመና እያጠፋ ራሱን ማልማት የሚችል ሥርዓትም ሆነ ኃይል አይኖርም። ቢሞከርም መጠፋፋት እንጂ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ አይፈጠርም። አሁን የተፈጠረው ትውልድ የሌሎችን መብትና ጥቅም በመሸራረፍ ለግል ወይም ለቡድን ትርፍ ለሚያስገኝ ሥርዓት ፍቃድ አይሰጥም። የኢትዮጵያንና የሕዝብዋን ፍላጎት ማዕከል ያላደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ይህችን ሀገር መምራት የሚያስችል አቅምና ቁመና አይኖረውም። በጥቅሉ በግለሰብ ወይም በቡድን አቅምና ፍላጎት ሀገርን መግዛት ታሪክ እየሆነ ነው፤ በተራው በሀገራዊ፤ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ አቅምና መንፈስ ኢትዮጵያን መምራት አማራጭ የማይገኝለት መንገድ ሆኗል። ስለዚህ ካሁን ወዲያ የሚያዋጣው ሁሉም ባንድ ገዢ ሐሳብ ስር ተሰባስቦ፤ በቁመቱ ልክ ተሰልፎና በአስተዋጽኦ መጠን እውቅና ተሰጥቶት መኖርና ማደግ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር ብቻ ነው።
የዛሬው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ይህን የሚመስል ከሆነ አሁን ካለንበት ሥርዓት ተላቀን ወደምንፈልገው የፖለቲካ ሥርዓት እንዴት እንሻገር? ማን ያሻግረን? በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በወጣቶች ትግል አበረታችነትና ግፊት አሁን በዘልማድ “የለውጥ ኃይል” ተብሎ የሚታወቀው የአመራር ቡድን ተፈጠረ። የኢትዮጵያና የሕዝብዋ ዕጣ-ፋንታ አሁን ያለው በዚህ የለውጥ ኃይል በሚያንቀሳቅሰው መንግሥት መዳፍ ውስጥ ነው። ይህ መንግሥት ሁለት መንታ መንገዶች ከፊቱ ይታያሉ – አንደኛው ወደ ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሽግግር የሚያሳልጥ መንገድ ነው፤ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ታሪክ እንደተለመደው በሕዝብና በዲሞክራሲ እየተገዘቱ ወደ አምባገነን ሥርዓት የሚያንሸራትት ነው። የሀገራችንና የሕዝባችን ምርጫ የመጀመሪያው ቢሆንም የለውጥ ኃይሉ መንግሥት ምርጫ ምን ሊሆን እንደሚችል በታሪክ የሚረጋገጥ ይሆናል።
የፖለቲካ ሥርዓቶቻችን መሪዎች ከነበሩአቸው ኃጢአቶች መካከል አንዱና ትልቁ በነባር እሴቶቻችን መገልገልና ማገልገል የማይፈልጉ መሆናቸው ነው። መሪዎች ለርዕዮተ-ዓለም ብድር አንዴ ወደ ምዕራብ፤ አንዴ ወደ ምሥራቅ መንከራተት አንጂ ቁጭ ብለው በራሳችን የእሴት ሥርዓት ውስጥ ያለውን ጠቃሚና ጎጂ ነገር መለየት አልፈለጉም። ጎጂውን አስወግደው ጠቃሚውን ማጎልበት አይታያቸውም። ይኸ ካለማወቅ የሚመጣ ብቻ ሳይሆን ካለመፈለግም የሚፈጠር ነው። ባንድ በኩል ከአውሮፓ፤ ከአሜሪካና ከእስያ ተውሰን ያመጣናቸውን አስተሳሰቦች ወደ ተግባር ለመተርጎም ስንደክም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ነባር እሴቶቻችን መጤዎቹን ለመቀበል አቅም አንሶኣቸው ሀገርና ሕዝብ ለትርምስ ተዳርገዋል። በእርግጥ ይህን ማድረግ ለመሪዎች ጊዜ ሊገዛላቸው ይችል ይሆናል፤ ለሀገርና ለሕዝብ ግን የሚያመጣው ጥቅም የለም። ነባር እሴቶችን ሕዝቡ ያውቃቸዋል፤ በተጨባጭም ይኖራቸዋል። ከውጭ በውሰት የሚመጡትን ግን በደንብ አይረዳቸውም። በሚያውቃቸው ነባር እሴቶች ከመስራት ይልቅ በማያውቃቸው እሴቶች ማደናበር የመሪዎች ምርጫ ነው። ለምሳሌ ግጭት ሲፈጠር ሰላምን እንዴት ማምጣት እንደሚቻል፤ ይቅርታ እንዴት እንደሚጠየቅና እንዴት እንደሚሰጥ፤ እርቅ እንዴት እንደሚፈጠርና እንዴት እንደሚቀጥል ባብዛኛው በነባር እሴቶቻችን ውስጥ አሉ። መሪዎች ግን የሀገር በቀል እሴቶችን፤ አስተሳሰቦችን፤ ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን አሳንሰው ማየታቸውና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረጋቸው ጎድቶናል።
ታሪክ የሆኑትን ትተን ዛሬ የሀገራችን የፖለቲካ ሊህቃን የሚጠቀሙትን ጽንሰ-ሐሳቦች በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ሥልጣን ለመያዝ እንወዳደራለን የሚሉ በርካታ የሀገራችን ፓርቲዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ከአውሮፓና ከኤስያ የተዋሱአቸው እንደ ሶሻል ዲሞክራሲ፤ ሊብራል ዲሞክራሲ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ ልማታዊ ዲሞክራሲና የመሳሰሉ ጽንሰ-ሐሳቦች እንደሚጠቀሙ/እንደሚከተሉ ይነግሩናል። እነዚህ ጽንሰ-ሐሳበች የተፈጠሩት በፈጣሪዎቻቸው ልክ ነው። ለኛ የሚጠቡ ወይም የሚሰፉ ናቸው። ዋናው ጉዳይ እነዚህን ጽንሰ-ሐሳቦች የተረዳናቸውና የምንረዳቸው ምን ያህል ነው የሚለው ነው። እኛ ከአውሮፓውያኑም ሆነ ከኤስያውያን በብዙ ነገሮች እንለያለን። የምንመሳሰልባቸው ነገሮች ቢኖሩም በእሴት ሥርዓታችን፤ በአኗኗራችን፤ በአሠራራችን፤ በዕድገታችን፤ በአመለካከታችን ውስጥ ባሉ አንዳንድ ነገሮች እንለያለን።
ከፖለቲካ አመለካከታችን አንጻር ራሱ ውስጣችን ወደ ውጭ ተገልብጦ ቢታይ የካፒታሊዝም ወይም የሶሻሊዝም ሳይሆን የፊውዳሊዝም ማሕተም ያረፈበት ነው። ያለፉት የአራትና አምስት አሥርተ-ዓመታት ታሪካችን የሚያረጋግጠው ከውጭ የተዋስናቸው ጽንሰ-ሐሳቦች ከጠቀሙን በላይ ጎድተውናል። ታሪካችንና አፈራችንን፤ ሀገር በቀል እሴቶችንና ትውፊቶችን፤ ባለብዙ ቀለም ብዝሃነታችንና ፀጋዎቻችንን፤ ፍልስፍናዎቻችንና እምነቶቻችንን መሠረት አድርጎ በኛ ልክ ተሰፍሮ የተሰፋ የፖለቲካ ሥርዓትና ርዕዮተ-ዓለም ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የመደመር ፍልስፍና ይረዳን ይሆን? ከርዕሳችን ጋር ባለው ተዛማጅነት ምክንያት የመደመር ፍልስፍናን ባጭሩ መቃኘት አስፈላጊ ነው (በጥልቀት ሌላ ጊዜ እመለስበት ይሆናል)።
መደመር ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ቃል ከሂሳብ ዓለም ወደ ፖለቲካ ዓለም ያመጡት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከታየው ተሞክሮ በመነሳት ከተውሶ ፍልስፍና ይልቅ ሀገርኛ ፍልስፍና መቀመር የሚያስፈልግ መሆኑ ታይቶአቸው ይሆናል ብዬ ኣስባለሁ። ቃሉን እንዳለ ወይም በነበረው ትርጉሙ ከወሰድን አንድ መሆን፤ ወደ አንድ መምጣት፤ መቀላቀል፤ አብሮ መሆንና መኖር ማለት ይሆናል። ወይም አንድ ከመሆን ሁለት፤ ሶስት፤ … ከዚያ መቶዎች፤ ሺዎችና ሚሊዮኖች መሆን ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንደመር” ሲሉ በዚሁ ትርጉሙ ብቻ አይመስለኝም። ቃሉን የተጠቀሙት በዚህ ትርጉሙ ብቻ ከሆነ በጣም ውስን ይሆናል። ምክንያቱም በዚህ ትርጉሙ ብቻ ከተረዳነው እስካሁን ከነበረው የአንድነት አስተሳሰባችን እምብዛም የሚለይ አይደለም። በጥሬ ትርጉሙ መደመር በመጠን የሚመጣ ግዝፈትን የሚገልጽ እንጂ የዓይነት ለውጥን/ዕድገትን አያመለክትም። የሚቆጠሩ ተጨባጭ ነገሮችን የሚያመለክት እንጂ መቆጠር የማይችሉ እሴቶችን አይገልጽም።
የሰው ልጅ ሕይወትና ግንኙነት፤ ዕድገትና ኑሮ ደግሞ በመጠን ብቻ ሳይሆን በዓይነትም፤ በሚቆጠሩ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በማይቆጠሩ እሴቶችም ይገለጻል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጊዜው ከሚያደርጉት ንግግርና ከሚጽፉአቸው ጽሑፎች መረዳት የሚቻለው ግን መደመር የመጠን ብቻ ሳይሆን የዓይነት ዕድገትንም የሚገልጽ ነው፤ በተጨባጭ የሚቆጠሩ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን አንድ፤ ሁለት ተብለው የማይቆጠሩ እሴቶችንም ይይዛል። ስለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና እስካሁን ከነበረው የኢትዮጵያ አንድነት ፍልስፍና ይለያል ብዬ አስባለሁ።
ይቀጥላል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ)