መልካምነት፣ እንግዳ ተቀባይነትና እርስ በእርስ ተደጋግፎ ችግርን አብሮ መሻገር የኢትዮጵያውያን የኖረ፤ ተፈትኖም በአሸናፊነት ዘመናትን ያሻገረ ተግባር ነው።ዛሬም ይሄው የኢትዮጵያዊነት እሴት በጽኑ እየተፈተነ፤ በተባበረ ክንድም ህዝቦችን ለማሻገር በሙሉ ተነሳሽነት እየተጓዘ ይገኛል።የዛሬው አገርኛ አምዳችንም ከቅርብ የመገናኛ ብዙሀን አፍንጫ ስር ሆነው ትንሽም ትልቅም ሲያደርጉ የዜናና ፕሮግራም ማሞቂያ ከሆኑት ወጣ በማለት ከዜናና ዝና ርቀው ግን ዘወትር ለሰብዓዊነት ወደሚሰሩት ወጣቶች ተጉዟል፡፡
እናም ከአዲስ አበባና አካባቢዋ ራቅ ብለን ሰው ከላወራላቸው፤ ሚዲያውም ካልዘመረላቸው፤ ለወሬና ዝና ሳይሆን ለሰብዓዊነት እየሰሩ ካሉት የመልካም ተግባር አምባሳደሮች የሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ ባለ ቅን ልብ ወጣቶች ዘንድ ዘልቀናል።በዚህ ጽሑፍ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት ግን ብዙ ስለተባለለት የወሎዬዎች መልካምነት፤ አብሮነትና የመረዳዳት እሴት ለመናገር አይደለም።ይልቁንም የእነዚህ ህዝቦች አብራክ ክፋይ ስለሆኑ መልካም ወጣቶች ያውም በወልድያ ከተማ ተወስኜ፤ ከዚህም ለማሳያነት ያክል የአንድ እጅ ጣት የማይሞሉትን ተሞክሮ በወፍ በረር ለመዳሰስ እንጂ፡፡
በወልድያ ከተማ ተወልዶ ያደገውና ዛሬም በከተማዋ በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ያለው ወጣት አማኑኤል ይማም፣ ከአስር ዓመታት በፊት በቅርብ ከሚተዋወቁ ስምንት ያክል ወጣት ጓደኞቹ ጋር በመልካም ሀሳብ ለመልካም ተግባር ተሰባሰቡ።በመካከላቸው መግባባት ሲፈጠርም ከራሳቸውም ከሩቅም ከቅርብም በዙሪያቸው ያሉ ነዋሪዎችና አብሮ አደጎችን በማስተባበር እንደ መስቀል ያሉ ዓመታዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ አቅመ ደካሞችን፣ ያለ ደጋፊና ጠያቂ በቤታቸው ያሉትን፣ አረጋውያንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች በገንዘብ መደገፍ ጀመሩ፡፡
በዚህ መልኩ አስር ዓመታትን የዘለለው የወጣት አማኑኤል እና ጓደኞቹ ተግባር፤ ዛሬም የዓለምም የአገርም ስጋት ሆኖ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የበለጠ ተጠናክሮና አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል።በእነዚህ ወጣቶች ተግባር ዙሪያ ያነጋገርነው ወጣት አማኑኤል እንደሚገልጸውም፤ ወረርሽኙ እንደተከሰተ በአመዛኙ ሲነገር የነበረው ስለ እጅ መታጠብና ንጽህና መጠበቅ ነበር።ይሄን መነሻ በማድረግም እነዚህ ወጣቶች አንድ ነገር አሰቡ፤ ይሄም ‹‹እኛ በግላችን ሳሙና ገዝተን ንጽህናችንን መጠበቅ ስንችል ይሄን ማድረግ ላልቻሉት ማን ይድረስላቸው›› የሚል ነበር።አስበውም አልቀሩም፤ በራሳቸውም በውጭ ያሉ አብሮ አደጎቻቸውን አስተባብረው የእጅ መታጠቢያ ሳሙና በመግዛት ቤት ለቤት እየዞሩ በሁሉም ቀበሌዎች ማደል ጀመሩ፡፡
ይሄን በምናደርግበት ጊዜ ለአስር ዓመታት ያላስተዋልነውን ትልቅ ችግር ተመለከትን የሚለው ወጣት አማኑኤል፤ በሂደቱ ችግሩ ከፍቶ ለአንድ ቀን እንኳን በቤት ዋሉ ቢባል ምግብ በልተው ማደር የማይችሉ ወገኖች መኖራቸውን እንዳስተዋሉ ይገልጻል።ይሄን ያክል ከተማ ውስጥ እየኖሩ እንዲህ አይነት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች መኖራቸውን ያለማወቅ በራሱ አሳዛኝም አሳፋሪም መሆኑን በመጠቆምም፤ ሳሙና ለማደል ባደረጉት እንቅስቃሴም ረሃባቸውን ለማስታገዝ እንኳን መውጣት አቅቷቸው ቤት ዘግተው በጉስቁልና ያሉ እናትና አባቶችን ስለማግኘታቸው ይናገራል፡፡
እነዚህ አቅመ ደካማ ወገኖችም በወቅቱ ራበን የት እንሂድ የሚል ሀሳብን አቅርበውላቸው ነበርና፤ እነዚህ ወጣቶችም የተለመደ የመልካምነት እጃቸውን ለመዘርጋት ይመክራሉ።ወዲያውም እንቅስቃሴ ጀምረው በውስጥም በውጭም ካሉ አብሮ አደጎቻቸው ጋር በመሆን ወደ 109 ሺህ ብር በመሰብሰብ 50 ኩንታል ዱቄት በመግዛት ለ500 ሰው ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም ዱቄት ይሰጣሉ።ይህ ግን የእነዚህን ወገኖች ችግር ከመሰረቱ የሚፈታ ሳይሆን ከእለት ችግራቸው የሚታደግ እንደመሆኑ፤ ድጋፉን በዱቄትም ሆነ በሌላ መልኩ ዘላቂ ለማድረግና ሌሎችንም ለማካተት የሚያስችል እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም እነዚህ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችም አብዛኞቹ ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉ፤ ይልቁንም በቤት ውስጥ ሆነው የሚጠባበቁ እንደመሆናቸው የሚደረገው ድጋፍም በአግባቡ ተደራሽ ሊሆንና ቤት ለቤት ሊከናወን ያስፈልጋል።ለዚህ ደግሞ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያለን ችግር ላይ የወደቀ ሰው አንድም ሊያግዝ፤ ካልሆነም እዚህም አለ ብሎ በመጠቆም ችግረኞች ሳይረዱ እንዳይታለፉ ሊተባበርና ለድጋፉ ተደራሽነት የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል፡፡
እንዲህ አይነት የመልካምነት ስጦታዎችና ተግባራት ለነፍስም ለህሊና እረፍትም ዋጋ እንዳላቸው የሚናገረው ወጣት አማኑኤል፤ ሰው ያለውን ማካፈል እንዳለበት ከፈጣሪ የተሰጠ ትዕዛዝ ከመሆኑም ባለፈ በዚህ በችግር ወቅት ያለውን ይዞ ከፊት ቀድሞ ለሰው መድረስ ለተደጋፊዎች ከሚኖረው ፋይዳ በላይ ለሰጪው ደስታን የሚሰጥ ስለመሆኑ ይናገራል።እነርሱም የጀመሩትን ድጋፍ የሚያጠናክሩ መሆኑን በመግለጽ፤ የሌሎችንም መተባበር የሚጠይቅ ስለመሆኑ ያስረዳል።ዛሬም እነርሱ በጀመሩት በርካቶች መንቀሳቀስና መደገፍ መጀመራቸውን በመግለጽም፤ ይህ ተግባር በወልድያ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ሊለመድና ሊጠናከር፤ የመንግስት የቅርብ ድጋፍና ክትትል ሊኖረው የሚገባ ተግባር ስለመሆኑ ይናገራል፡፡
ሌላው በወልዲያ ከተማ ተወልዶ ያደገና እዛው በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ያለው ወጣት አንዳርጌ ሞላ እንደሚለው ደግሞ፤ ቀደም ሲል ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በተለይም በሆስፒታል አካባቢ ለህክምና የሚመላለሱ ነገር ግን አቅም የሌላቸው ወገኖችን እንዲሁም ወላዶች ወደቤታቸው ሲመለሱ የሚገጥማቸውን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ያግዙ ነበር።አሁንም የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ በቀረበው ጥሪ መሰረት ያሉትን ሁለት ዶልፊን ሚዲባስ መኪኖች ለበጎ ተግባር እንዲውሉ ያበረከተ ሲሆን፤ ይሄን ማድረጉም ስራውን ሊሰራም ሆነ ገንዘቡም ሊገኝና ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው አገርና ወገን ሰላምና ጤና ሲሆኑ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ፤ ችግሩን በመከላከል ሂደት ውስጥም የድርሻውን ለማበርከት ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡
ወጣት አንዳርጌ እንደሚለው፤ ጥሪውን ተከትሎ ሁለቱንም ሚዲባስ መኪኖች የፈቀደ ቢሆንም፤ እስካሁን ችግሩ ያን ያክል ጎልቶ ባለመውጣቱ አንዱን ብቻ እየተጠቀሙበት ይገኛል።በቀጣይም ቢሆን ችግሩ እስኪወገድ መኪኖቹን ለአረጋውያን ማንቀሳቀሻም ሆነ ለሌሎች ከወረርሽኙ ጋር ለተገናኙ አገልግሎቶች መጠቀም የሚችሉ ሲሆን፤ የሰው ህይወት እየጠፋ ንብረት አለኝና ለግሌ ማለቱ ትርጉም አልባ ንብረትም ያለሰው ጥቅም የሌለው በመሆኑ መኪኖቹ ለሰው ህይወት ማትረፍ ላይ መሰማራታቸው ደስታና እርካታ እንጂ ጉዳት እንደሌለው መሆኑን ተገንዝቦ ያደረገውም ነው።ይህን መሰል ተግባር ደግሞ በከተማዋ እየተበራከተ ሲሆን፤ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም ተጠናክሮ ሊቀጥል፤ ህብረተሰቡ፣ መንግስትና ባለሃብቱ ተቀናጅተው ሊሰሩም ይገባል፡፡
አቶ ዘለቀ ደምሴ፣ የወልድያ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ጡረተኛና የውትድርና ህይወታቸውም ለአካል ጉዳት የዳረጋቸው የልጆች አባት ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት፤ ወረርሽኙ በጣሙን አስከፊና ዘር ቀለም የማይለይ ነው።በከተማዋ ያሉ የጎዳና ልጆች በተለይም መናኸሪያ አካባቢ ያሉ ልጆች ደግሞ የአኗኗር ሁኔታቸው ለዚህ ወረርሽኝ በእጅጉ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።እንደ ሰው ደግሞ እነዚህን ማረፊያ ብቻ ሳይሆን የእለት ጉርስ እንኳን አጥተው ውለው የሚያድሩ ወገኖችን ማሰብና በዚህ ችግር ወቅት ከጎናቸው መሆን ተገቢ ነው።ይሄን በማሰብም እነዚህ ወገኖች መጠለያና ልብስ ማግኘት ባይችሉ እንኳን ቢያንስ መብላት የሚችሉበትን እድል ለመፍጠር በበጎ ፈቃድ በጎ ፈቃደኞችን ማሰባሰብና ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡
ስራውን ከሞላ ጎደል እየፈጸምን ነው የሚሉት አቶ ዘለቀ፤ ስራውን ሲጀምሩ ከኪሳቸው አዋጥተው ስለመሆኑ ይናገራሉ።ከዚህ በኋላ የከተማው ባለሃብት፣ የ03 (አድማስ ባሻገር) ቀበሌም ትልቅ እገዛ እያደረገ፣ እድሮችም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ይናገራሉ።በዚህም ለእነዚህ ወገኖች ብዙ ነገር የሚጎድላቸውና ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ባይሆንም ለእለት ጎርሰው እንዲያድሩ የማስተንፈስ ስራ እያከናወኑ መሆኑን በመጠቆም፤ በእስካሁን (ከ10 ቀን በዘለለው የበጎ ስራቸውም) ሂደት ቁርስ፣ ምሳና እራት እያበሉ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
እነዚህ ወገኖች የሰው ልጅ እንደመሆናቸው መጠለያ ያስፈልጋቸዋል፤ የሚተኙበት ፍራሽና የሚለብሱት አልባሳትም የላቸውም።እኛም እነዚህ ሁሉ ባልተሟሉላቸው ሁኔታ የግል ንጽህናቸውን ብቻ እያስጠበቅን ወስፋታቸውን ገድለው እንዲያድሩና ረሃባቸውን እንዲያስታግሱ ለሆዳቸው ብቻ ነው እየሰራን ያለነው ሲሉም ያስረዳሉ።
ይህ የበጎ አድራጎት ስራችን አቅማችን በፈቀደ መልኩ ወረርሽኙም እስኪቆም እንኳን ቢሆን የሚቀጥል ይሆናል።ነገር ግን ዘለቄታዊ መፍትሄ የሚያገኙት መንግስት ሲያግዝ እንደመሆኑ፤ መንግስት የራሱን አስተዋጽዖ ሊያበረክትና ሊደግፍ ይገባል። እኛም መንግስት እስከሚረከበን ድረስ ይሄን ጊዜያዊ መፍትሄ መስጠት አናቋርጥም።ለዚህ ተግባር እንዲያግዘንም እስካሁን ዝም ብለን ስናስተናግዳቸው የነበረውን አካሄድ ቀይረን በኩፖን ልናደርግ ሲሆን፤ በቀጣይም 150 የጎዳና ላይ ልጆችን በኩፖን እያስተናገድን የምንመግብ ይሆናል፤ ሲሉም የቀጣይ እቅዳቸውን ይገልጻሉ፡፡
እኔ እንደ አንድ አባ ወራና የልጆች አባት እነዚህ ልጆች ጎዳና ላይ ሆነው ሲራቡ፣ ሲጠሙ፣ ሲታረዙና ብርድ ሲመታቸው ሳይ ከማዘንም በላይ ማታ ማታ ቤቴ ገብቼ ሳርፍም ሆነ ስተኛ የሚታዩኝ እነርሱ ናቸው የሚሉት አቶ ዘለቀ፤ ሁነቱ አሁን ላይ ለወረርሽኙ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን እንድትረዳና የአቅምህን ለማድረግ እንድትነሳሳ ያደርግሀል ይላሉ።እርሳቸውም በዚህ መልኩ ለጀመሩት ተግባር መነሳሳትን የፈጠረባቸው ይሄው ስሜትና ሰብዓዊነት መሆኑን በመጠቆምም፤ በከተማዋም ሆነ በመላው አገሪቱ ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሌሎች አካላትም በዚህ መልኩ መሰል ወገኖችን ሊያስታውሱና ሊደግፉ እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን ባለው ሁኔታ የከተማዋ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚነገረውና ከሚያየው ነገር የሚማር አይመስልም፤ የሚሉት አቶ ዘለቀ፤ ቫይረሱ ጨክኖ እየገደለን የሚመጣ ከሆነ ባለው የጥንቃቄ ደረጃ ከጣሊያን፣ ከስፔንና አሜሪካም የከፋ ሞት ነው እኛን የሚጠብቀን ይላሉ።ምክንያቱም የእኛ ህዝብ ርቀትህን ጠብቅ ሲባል አይሰማም፤ እጅህን ታጠብ ሲባል እንኳን እየተበሳጨ ነው የሚታጠበው፤ ይህ ደግሞ ለበሽታው ቦታ እንዳልሰጠው አመላካች እንደመሆኑ ከዚህ አይነቱ አካሄድና አስተሳሰብ በመውጣት ለወረርሽኙ ትኩረት መስጠትና ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራስንም፣ ወገንንም አገርንም መታደግ ይገባል።
ከድጋፍ ባለፈ ወረርሽኙን ከመከላከል አኳያ በሚስተዋለው ሂደት ላይ ወጣት አማኑኤል እና ወጣት አንዳርጌም የአቶ ዘለቀን ሀሳብ ያጋራሉ።ወጣቶቹ እንደሚሉት፤ ከድጋፍ ባለፈ ትልቁ ስራ ግንዛቤን ማሳደግና ወረርሽኙን መከላከል ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው።ለዚህ ደግሞ በመኪና እየተዞረ ጭምር የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ ነው።ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ህብረተሰቡ በአግባቡ አድምጦ የመተግበር ችግር አለ።ለምሳሌ፣ በታክሲና ባጃጆች ላይ ርቀት እንዲጠበቅ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ ቢሆንም፤ ሰዎች በመንገድም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች ተጠጋግተውና ተቃቅፈው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል።ለተወሰነ ጊዜ የመኪና እንቅስቃሴ ተከልክሎ አሁን መፈቀዱ ደግሞ ህዝቡ ላይ በተወሰነ መልኩ አሳድሮ የነበረውን ስጋት ያስቀረ በሚመስል መልኩ እንቅስቃሴዎች ወደመደበኝነታቸው የተመለሱ መምሰላቸውም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ይሆናል።በመሆኑም ጉዳዩ በመንግስትም በህብረተሰቡም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9/2012
ወንድወሰን ሽመልስ