ከኮንስትራክሽን ግብዓት የውጭ ጥገኝነት ለመውጣት – የባለድርሻ አካላቱ ሚና

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉን በማላቅ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ድርሻውን እንዲወጣ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ዘርፉን የሚያሠሩ የሕግ ማሕቀፎችን በማውጣት፣ በዘርፉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ላይ ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር በመምከር ይሠራል፡፡ ዘርፉ በጥራት በኩል ያሉበትን ችግሮች ፈትቶ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ የመንግሥት ፍላጎት ነው፡፡

ይሁንና ዘርፉ ከተለያዩ ፈተናዎች ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ማከናወን ሳይችል ቆይቷል፡፡ ለዘርፉ ፈተና ሆነው ከቆዩት ችግሮች አንዱ የግብዓት አቅርቦት አለመኖር መሆኑ ይታወቃል፡፡ አብዛኛዎቹ የማጠናቀቂያ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ ናቸው፤ ለእዚህ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የግድ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሁሉ የሚደርስ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሊያደርግ አይችልም፡፡

እንዲያም ሆኖ መንግሥት ይህን የዘርፉን ችግር ለመፍታት ጥረት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ ከእነዚህ ጥረቶቹ መካከል ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚያስፈልጉ ከውጭ የሚመጡ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ግብዓቶች ለመተካት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይጠቀሳሉ።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ግብዓት ከውጭ ማስገባቱ የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሪ እየፈተነው ስለመሆኑም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በዚያው ልክ ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ግብዓት በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ጥሬ እቃን ጨምሮ ሰፊ አቅም እንዳላት ጥናቶች ያመላክታሉ።

ይህንን አቅም በመጠቀም የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የመተካቱ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ በዚህ በኩል የሁሉም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ነው።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም በሆነው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በኩል የዘርፉን ባለሙያዎች ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ ሥልጠናዎች ይሰጣሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰርቲፋይድ የሆኑ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ኮንትራክተሮች፣ አርክቴክተሮች እና ዲዛይነሮች እንዲፈጠሩ ሥልጠናዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።

ከሰሞኑም ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ አርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ ማኅበር ጋር በመተባበር የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የጋራ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የኮንስትራክሽን ዘርፉን ተኪ ምርቶች ከ20 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማድረስ መቻሉም በእዚሁ መድረክ ላይ ተጠቁሟል። የኮንስትራክሸን ዘርፉን በሀገር ውስጥ ግብዓት የመተካት ሂደቱን በ10 ዓመቱ ውስጥ 80 በመቶ ለማድረስ 38 ባለድርሻ አካላት መለየታቸውም ተመላክቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለፁት፤ መድረኩ ለግንባታ ዘርፉ በቀረበው ጥናት መሠረት ከውጭ የሚገቡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሀገሪቷ ምን ሀብት አለ በሚለው ላይ ትኩረት በማድረግ የጥናት ውጤት የቀረበበት ነው። ጥናቱ ለባለድርሻ አካላት በተለይ ለአቅራቢዎች፣ ለኮንትራክተሮች፣ ለአማካሪዎች የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

እንደ ቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ማብራሪያ፤ ጥናቱ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ከውጭ የሚገባውን ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ምን መሠራት እንደሚገባ፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚለው መሪ ቃል ምን መሠራት እንዳለበት ያመላከተ ነው፡፡

ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በኮንስትራክሸን ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩት ያስጠናቸው በርካታ ጥናቶች ተግባራዊነት የማረጋገጫ መድረክ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተለይተውና ተቆጥረው ገቢ ምርት መተካት የሚያስችሉ ግብዓቶች የታዩበት ነው ሲሉ አመልክተዋል።

ይህም ጥናት እንደከዚህ በፊቱ መደርደሪያ ላይ ብቻ እንዳይቀር እና ወደ ተግባር እንዲገባ ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴውም እንደ ሕግ አውጪ ተቋምነቱ፣ እንደአስፈፃሚ በመሆን እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡ ይህም መድረኩን ከሌላው ጊዜ መድረኮች ልዩ ያደርገዋል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሆኑት የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎች እና አስመጪዎች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ አርክቴክቶች፣ ፕላነሮች፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዚህ መተባበር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

መንግሥት ወይም ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ብቻ በሚያደርጉት ጥረት ወይም በከተማና መሠረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ እገዛ ብቻ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ችግሮች መፍትሔ አያገኙም ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ ሁሉም ብሎ በሀገር ደረጃ የዘርፉ ማነቆና ተግዳሮት የሆኑትን ችግሮች የእኔም ችግሮች ናቸው ብሎ በቀረበው ጥናት እና ሌሎችንም መንገዶች በመጠቀም በቅርቡ እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት አመላከተዋል።

እሳቸው እንደጠቆሙት፤ የኮንስትራክሽን ዘርፉን የማሳደግ ሥራን በሁለት ከፍሎ ማየት ይገባል። የመጀመሪያው ተግዳሮቶቹ ምን እንደሆኑ በጥልቀት መፈተሽ፣ ሁለተኛው ተግዳሮቶቹን የሚፈቱ ተቋማት፣ ባለሙያዎች እንዴት ይታያሉ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

አስፈፃሚ አካላት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና በስሩ የሚገኙ እንደ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ያሉት ተቋማት በጋራ ሆነው በእነዚህ ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ ምርጥ ተሞክሮን ከውጭ በማስገባት የካበተ እውቀትን በማውጣት እና በማዋሓድ ዘርፉን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

‹‹በ24 ሰዓት ውስጥ ወይም በአንድ ዓመት የዘርፉን እድገት ማምጣት አይቻልም፤ ውጤቱ በሁለት ዓመት ሊታይ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን አይመጣም›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ስለዚህ የሕግ አውጪው የሕግ አስፈፃሚውና ባለድርሻ አካላት በጋራ ሆነው መሥራት ከቻሉ ዘርፉ ሊዘምን ሊያድግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ እውቀታችንን ሳንሰስት ተጠቅመን እንደዜጋ ከሠራን እድገትና ውጤቱን የማያው ጊዜ ቅርብ እና አጭር ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።

የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ታምራት ሙሉ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ሴራሚክ፣ መስታወትና መሰል የኮንስትራክሽን ምርቶችን በተወሰነ ደረጃ ሀገር ውስጥ ብታመርትም በአጠቃላይም ሀገሪቷ በሁሉም መስኮች በውጭ የግንባታ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ መሆኗ አሁንም በስፋት ይስተዋላል።

ይህን ሁኔታ ለመቀየር ከውጭ የሚመጡ የዘርፉን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች የሀገር ውስጥ ምርቶች አጠቃቀምን ከ20 በመቶ ወደ 50 በመቶ በማድረስ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ ይህን ለውጥ በ10 ዓመቱ የልማት ግብ 80 በመቶ ለማድረስ ከታቀደው አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ በውጭ የግንባታ ግብዓቶች ላይ ጥገኛ ነው፡፡ ይህም ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ሁኔታ በዋጋ፣ በጊዜና በጥራት ተወዳዳሪ እንዳይሆን አድርጎት ቆይቷል። ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታዎች እንደ ኮቪድ 19 ዓይነት ወረርሽኝ ዓይነት ተግዳሮቶች የግንባታ ግብዓቶች ምርት መጠን እንዲቀንስ ወደ ሀገር ውስጥ ለማጓጓዝም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ ያደረገበት ሁኔታ ዘርፉን ጎድቶታል። ሀገሪቷ መሰል ተግዳሮቶችን መቋቋም እንዲቻላት ጤናማ የሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያስፈልጋታል።

ይሄንንም ከማረጋገጥ አኳያ መሥራት ከሚገባቸው ከኮንስትራክሽን ግብዓት የውጭ ጥገኝነት መውጣት ላይ በትኩረት መሥራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለእዚህም ከግንባታ ግብዓት ጋር ተያያዥ የሆኑ ሦስት ጥናቶች ቀርበዋል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ ከዚህ አኳያ በ10 ዓመቱ እቅድ የተቀመጠውን ለማሳካት መጀመሪያ እስካሁን የኢትዮጵያ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት እና አጠቃቀም ምን ይመስላል በሚለው ላይ ጥናት ተደርጓል። አቅዱን ለማሳካት ማን ምን ይሥራ? የሚሉ የሥራ ክፍፍል የተመላከተበት መሆኑንም አስረድተዋል።

አንድ ተቋም ብቻውን ሠርቶ ለውጥ አያመጣም፤ ተቋማት መደመር አለባቸው፡፡ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ እና ሌሎችም ተቋማት በየደረጃው የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው ሲሉም አመላክተዋል። ይህም ሲሆን ለየተቋማቱ በየድርሻቸው የተቀመጠውን የተበታተነውን ሀብት አሰባስቦ መሥራት ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ሁለተኛውን ጥናት አስመልክተው ሲያብራሩ፤ ስለግንባታ በሚታሰብበት ሁልጊዜ ድንጋይ፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶ ወይም ብረትን ብቻ ማሰብ እንደማይገባ አስታውቀው፣ ሀገሪቱ ሌሎች ፀጋዎች እንዳሏትም አመላክተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ አማራጭ ተኪ የግንባታ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ቀርከሐ የሚባለው ነው። ከፍተኛ የቀርከሐ ምርት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢ እንዲሁም በሌሎችም የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ይገኛል።

እነዚህን የቀርከሐ ሀብቶች የምሕንድስና ባሕሪያቸውን በማጥናት አማራጭ ተኪ የግንባታ ግብዓት እንዲሆኑ ማድረግ ላይ መሥራት አለብን በሚል ይህ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው ጥናት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሶስዬሸን ጋር በመተባበር፣ ሁለተኛው በቀርከሐ ላይ የተደረገው ጥናት ደግሞ ከሕንፃ ኮሌጅ ጋር በመሆን መካሄዳቸውን አመልክተዋል፡፡

ሦስተኛው ጥናት ደግሞ የኢንዱስትሪያል ቢዩልዲንግ ሲስተም (IBS) ጥናት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡፣ ግንባታ ሲታሰብ ጥራት ለድርድር አይቀርብም፤ በተያዘለት በጀት መጨረስም ለድርድር አይቀርብም፤ ሦስተኛ በአጠረ ጊዜ ውስጥ አንዲያልቅ ይጠበቃል ሲሉ አስገንዝበዋል። እነዚህንም ከማረጋገጥ አንፃር ጥናቱ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በ14 ቀናት፣ በአንድ ቀን ትላልቅ ሆስፒታሎችን መገንባት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል። ይህም በአይቢኤስ ወይም የሕንፃ የተናበቡ የተለያዩ ክፍሎች በተለያየ ቦታ ላይ ተመርተው በሚፈለገው ቦታ ላይ የመግጠም ሥራ ነው። ይህን ዓይነቱን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ማምጣት ተገቢ ነው ሲሉም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ዕድገት የዚህ ዓይነት ግንባታዎችን የሚጠይቅ መሆኑን ያመላክታሉ።

በአዲስ አበባ አንድ ሕንፃ ተጀምሮ 14 ዓመት እና 10 ዓመት መጠበቅ የተለመደ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በቆርቆሮ ታጥሮ በቆየ ስፍራ ውስጥ በጥቂት ወራት ያለቀ ሕንፃ ማየት እየተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የግንባታ ባህል እየተቀየረ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚያ የሚመጥን ቴክኖሎጂ ማሰብ አለብን በሚል የኢንዱስትሪያል ቢዩልዲንግ ሲስተም (IBS) በጥናት እንዲዳብር ታሳቢ መደረጉን አስታውቀዋል። ለዚህም አንዱ አማራጭ የግንባታ ግብዓት እንዲሆን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲዘምን ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል። መድረኩም ይሄንንም የጋራ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የቢም ቴክኖሎጂ በግንባታ እና በዲዛይን ላይ ያሉ አለመጣጣሞችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማረም የሚረዳ ምንም ኢንቨስትመንት ማድረግ ሳያስፈልግ በግንባታ ደረጃ ላይ እያለ ችግሮችን በመለየት እርምጃ መውሰድ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል። ኢንስቲትዩቱም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ለሥራ ተቋራጮች፣ ለአማካሪዎች፣ ለኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ ለፕሮጀክት ባለቤቶች በከፍተኛ ሁኔታ ሥልጠና መስጠቱን አስታውሰዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሀገሪቷ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በምታስገባበት ጊዜ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። በብዙ ድካም የተገኙ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መልሶ ብረትና መሰል የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ከውጭ ለመግዣ ይውላል፡፡ ከዚህ ለመውጣት ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት ሰጥቶ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል።

የሀገር ውስጥ አምራቾችም ገበያው ሲመቻችላቸው ምርታማነታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፤ ምርቶቻቸው ጥራታቸውን የጠበቁና በሚፈለጉ አማራጮች የሚያቀርቡ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው። በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን የማምረት አቅማቸውን መጨመር ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነም ሰዎች ከውጭ ወደ ማምጣት ሊያዘነብሉ ይችላሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ጥናት ያቀረቡት ሰለሞን እንድሪያስ (ዶክተር) በበኩላቸው በሀገር ውስጥ ያሉ የግንባታ ግብዓቶችን በመለየት ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ጥናት መደረጉን አስታውቀዋል።

በጥናቱ የአቅርቦት ሠንሠለት ዋነኛ ችግር መሆኑ ታይቷል ሲሉም ጠቅሰው፣ በፋብሪካ ገብተው ፕሮሰስ የሚደረጉ ምርቶች የሚጠቀሙ ጥሬ እቃዎች የእሴት ሠንሠለቱ አካል መሆናቸውን ጠቁመዋል። ለእነዚህ የእሴት ሠንሠለቶችም 38 ባለድርሻ አካላት በጥናቱ መለየታቸውን ገልፀዋል። የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋነኛ ባለድርሻ አካላት መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በ10 ዓመት እቅዱ 80 በመቶ የኮንስትራከሽን ግብዓትን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት አቅዷል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም የኮንስትራከሸን ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እንደ አንድ ግብዓት ለይቷል። የማዕድን ሚኒስቴርም ለኮንስትራከሽን ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናትን የመለየት እና በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የፖሊሲ ትኩረት የሚሰጣቸው የኮንስትራክሸን ግብዓቶች ከተለዩ በኋላ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ታምርት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ቢሆንም የማስተባበር ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል። የሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓቶችን የሚጠቀሙትን ማበረታታት ላይ መሠራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You