ነገረ ፋሲካ

ትንሳኤ ከሃምሳ አምስት ቀን ጾም በኋላ በብዛት በሚያዝያ ወራት የሚከበር በዓል ነው:: የትንሳኤ ጾም፣ የፋሲካ ጾም በመባል ይጠራል :: በተጨማሪም ጾሙ ሁዳዴ፣ ዐቢይ ጾም እንዲሁም ጾመ ኢየሱስ በሚል ስያሜ ይታወቃል:: ሁዳዴ ማለት ሠፋፊ መሬት ነው:: የጾሙ ጊዜ ከሁሉም አጽዋማት በቀናት ብዛት ስለሚልቅ ወይም ስለሚሠፋ ሁዳዴ ተባለ:: ዐቢይ ጾም ማለትም ትልቅ ጾም ማለት ነው:: ከአጽዋማቱ ሁሉ ትልቅ ስለሆነ እና ጌታ ኢየሱስ ለሰው ልጆች በመጾም አብነት ስለሆነበት ነው::

ጾመ ኢየሱስ የተባለውም ኢየሱስ 40 መዓልት እና ሌሊት የጾመበትን፣ እና በአይሁድ እጅ ተይዞ፣ ተገርፎ፣ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ፣ተቀብሮ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበትን ምክንያት በማድረግ የሚጾምና የሚከበር በዓል በመሆኑ ነው ሲሉ አባቶች ይናገራሉ:: ሐዋ13፥3 የሦስት መቶ የኒቂያ ጉባኤ አባቶችም አጽዋማት እንዲጾሙ ወስነዋል:: የጌታ ጥንተ ትንሳኤ መጋቢት 29 ቀን 34 ዓ.ም በዕለተ እሁድ እንደነበር ሊቃውንት ያስረዳሉ:: በዓሉ እሁድ ቀን እንዳይለቅ በተለያየ ቀን እንዲከበር ሊቃውንት ስለደነገጉ ትንሳኤ እንደ ልደት ጥምቀት በዓላት ቋሚ ቀን ሊኖረው አልቻለም::

ዐቢይ ጾምን ከክርስቶስ ቀጥሎ ሐዋርያትም ጾመውታል:: ጌታ ኢየሱስ ‹‹ሙሽራው ከእነሱ ለይተው የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል:: ያን ጊዜ ይጾማሉ ›› ባለው መሠረት፤ ሐዋርያት እና አርድእት ጾመዋል:: የጾምን ሕግ ሠርተዋል:: በኣለ ትንሳኤ፣ ፋሲካ በሚሉ ስያሜዎች ይጠራል :: ትንሳኤ ቃሉ የግእዝ ሲሆን መገኛ ቃሉ ‹‹ተንሥአ ›› ተነሣ የሚለው ግስ ነው:: የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ትንሳዔ ከሞት በኋላ በስጋና በነፍስ ሕይወት ማግኘት ማለት ነው ሲል ያስረዳል:: ቀሲስ በላይ መኮንን በ2010 ያሳተሙት ሕያው ልሳን ግዕዝና አማርኛ መዝገበ ቃላት ቃሉን መነሳት (ከሞት በኋላ)፤ የፋሲካ በዓል በሚል ይፈታዋል:: ፋሲካ የሚለውን ቃልም የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የእስራኤል ልጆች በግብጽ ሀገር በግ አርደው የበራቸውን መቃንና ጉባን ደም በመርጨት ከእግዚአብሔር ቁጣ የዳኑበት በዓል ነው በሚል ያብራራዋል:: በተጨማሪም የክርስቶስ ትንሳኤ በዓል ፋሲካ ተብሎ ይጠራል ሲል የመጽሕፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቱ ይገልጸዋል::

የእግዚአብሔር መልአክ ግብጻውያንን ሲቀስፍ በግ አርደው በደጃቸው ደም የተረጨበትን የእስራኤላውያንን ቤት ስላለፈ ፋሲካ አሉት:: ፋሲካ በዕብራያስጥ ፓሳህ ማለት ሲሆን ፍቺው አለፈ ማለት ነው:: በአብያተ ክርስቲያናት ትንሳኤን ሲያከብሩ ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሃጺባ በደመ ክርስቶስ›› እያሉ ይዘምራሉ:: ምድር በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች ማለት ነው:: በኦሪት ዘመን እስራኤል የሚያከብሩት በዓሉ ፋሲካ ሲባል፤ የእርዱም በግ ፋሲካ በሚል ይጠራል:: ዘጸ 12 ፥1-13 እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል የሚያከብሩት በየዓመቱ በመጀመሪያ ወራቸው በ14ኛው ቀን ነው ::

ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንትም የአይሁድ ፋሲካ ነበረ:: ሉቃ 12፥14 መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤም ሲያስረዳ ‹‹እርሱምን ንጹህ በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፋሲካችን ክርስቶስ ተባለ:: ›› ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ5፥7 ገልጾታል :: ስለዚህ በአብያተ ክርስቲያናት ትንሳኤን ሲያከብሩ ‹‹ትንሳኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ›› እየተባለም ይዘመራል:: ትንሳኤህን ለምናምን ብርሃንክን ላክልን ማለት ነው:: በተለይ በትንሳኤው እለት ምእመናን አስቀድሰው ሌሊት 9 ሰዓት ከቤተክርስቲያን ሲወጡ፤ ጧፍ አብርተው ከላይ የጠቀስነውን መዝሙር እየዘመሩ ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ:: ብዙ ሆነው ጧፍ አብርተው ሲሄዱ ምዕመናን በመንገዱ ሁሉ የብርሃን ጎርፍ ይመስላሉ:: ዘንድሮ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 የሚከበረው የትንሳኤ በዓል ከምዕራባውያን የፋሲካ በዓል ጋር አንድ ላይ ይከበራል:: ባለፈው ሳምንት የተከበረው የሆሳዕና በዓልም በተመሳሳይ ቀን በምዕራባውያንም ተከብሮ ነበር::

የጌታ ትንሳኤ በነቢያት ትንቢት ተነግሮለትም ነበር:: ‹‹እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ›› ‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላው መታ›› መዝ.77፥6 ‹‹እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር አሥነስቶኛልና ተነሣሁ›› መዝ.3፥5 ‹‹እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ ይላል መድኀኒት አደርጋለሁ:: ›› በመዝሙረኛው ነቢዩ ዳዊት በብሉይ ኪዳን ከተነበዩት መካከል ናቸው::

በሐዲስ ኪዳንም ምዕራፍ 28፥1-16 ‹‹ በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዷልና ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ ››ይላል በዕለተ ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማየት መላእክት እንዲሁም ቅዱሳት አንስት መገኘታቸውን በሐዲስ ኪዳን ተገልጿል:: ኢየሱስ በቤተልሄም ሲወለድ የመወለዱን ዜና ለእረኞች የተናገሩ መላእክት በትንሣኤው ዕለትም ዜና ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት ለመንገር በመቃብሩ አካባቢ ተገኝተው የትንሣኤው ምስክሮች ሆነዋል::

ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ወደመቃብሩ ገስግሰው በመሄድ ትንሣኤውን ለማየት እንደበቁ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራቹን እንደተናገሩ ወንጌላዊ ዮሐንስ ከትቦታል:: ዮሐ.20፥1 ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በዝግ ደጅ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሉበት መግባቱን ትንሣኤው እንደገለጠላቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ የሰላም አምላክ ከሀዘናቸው እንዲጽናኑ ፍርሀታቸውን አርቆ አይዞአችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ እጄን እግሬን እዩ በማለት በሚስማር የተወጋውን እጅና እግሩን እና በጦር የተወጋው ጎኑን አሳይቷቸዋል::

በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ከትንሳኤ በኋላ ያሉት 50 ቀናት ወይም እስከ በዓለ ሃምሳ (ለሐዋርያት በአንድ ቤት በር ዘግተው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ዕለት) በሙሉ እንደ አንድ ትንሳኤ ቀን ተደርገው ይታሰባሉ:: የትንሳኤ መዝሙሮችም ይዘመርባቸዋል:: ኢየሱስ በአይሁድ እጅ ተይዞ ተገርፎ ተሰቅሎ ተቀብሮ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ በአርባኛው ቀን በደብረ ታቦር ወደ ሰማይ ስላረገ የዕርገት በዓል ተብሎ በአብያተ ክርስያናት ይከበራል:: ዳዊትም በመዝሙሩ ትንቢት ተናግሮለታል:: ‹‹ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርነ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ:: ›› የሚል የዳዊት መዝሙርም በዜማ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይባላል:: ትርጓሜውም እግዚአብሔር በምስጋና አረገ፤ ጌታችን በመለከት ድምጽ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ ማለት ነው::

ትንሳኤ የሰላም፣ የብርሃን፣ የፍቅር፣ የእርቅ ትእምርት ወይም ተምሳሌት ነው:: ትንሳኤ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ አዳምንና ልጆች ከዲያብሎስ እስር ነፃ ያዋጣበት በመስቀሉ ሰላም የሰጠበት ነው ተብሎ ይታመናል:: ብርሃን የተባለውም የዲያብሎስ የጽልመት አገዛዝ ሰብሮ ሞትን ድል አድርጎ ብርሃንን ለሰው ልጆች ስለሰጠ ነው:: ፍቅር የተባለው ለአዳምና ልጆች በመስቀል መስዋዕት ሆኖ ፍቅሩን ስለገለጸበት ነው:: እርቅ የተባለው አዳም እጸ በሉስን እንዳትበለ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታህ ሲባል የዲያብሎስን ምክር ሰምቶ አምላክ መሆን ሽቶ ዕጸ በለስ በልቶ ከፈሪጣው የተጣላበት የወደቀበት ስለነበር ጌታ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎን አዳምን ከዲያብሎስ አገዛዝ ነፃ አውጥቶ በይቅርታ እርቅ ስለፈጸመ ነው ተብሎ ይታመናል::

ፋሲካ ከጾም በኋላ የሚከበር በመሆኑ ሰዎች ዶሮ፣ በግ፣ በሬ ፣ፍየል በማረድ ከፊሎችም በሬ ገዝተው በቅርጫ ገዝተው ይከፋፈላሉ:: ዳቦው ጠላው ይዘጋጃል፤ ጎረቤት ይገባበዛል:: ፋሲካ ብዙውን ጊዜ በከተሞች በዶሮ እርድ ይከበራል:: ይህ ሃይማኖታዊ ግዴታ ሳይሆን ባሕላዊ ገጽታ ነው:: ለፋሲካ ዶሮ እረድ በሚል የሚገደድ አማኒ የለም :: በአንዳድ ገጠራማ ሥፍራዎች ጾሙ ሲፈታ ሌሊቱን በቅቤ ክሽን ያለ ሽሮ ወጥ ሠርተው በአይብ ቀላቅለው በመብላት ያከብራሉ:: ሲነጋ ደግሞ በግ አርደው በዓሉን ቦግ ቦግ ያደርጉታል:: ‹‹ ስጋ በቅርጫ ጠጅ በዋንጫ›› እንደሚባለው ተረት በእርድ አክብረው ከወዳጅ ዘመድ ጋር እየበሉ እየጠጡ ፈጣሪ ሰላሙን ሰጥቶ እንኳን ለብረሃነ ትንሳዔው አደረሰን ይባባሉበታል:: ለከርሞ ጠብቆ ያድርሰን በሚልም ይመራረቁበታል::

ከፋሲካ ዋዜማ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሳ ወይም እስከ ሃምሳኛው ቀን መጨረሻ በአብያተ ክርስቲያናት የጸሎት የስብከት መጀመሪያው ካሕኑና ሕዝቡ እርስ በርስ እንህ እያሉ እንደ ሰላምታ ይለዋወጣሉ::

‹‹ ክርስቶስ ተንስአ እሙታን፣

በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፣

አሰሮ ለሰይጣን፣

አጋእዞ ለአዳም፣

ሰላም፣

እምይዜሰ፣

ኮነ

ፍስሃ ወሰላም:: ››

ትርጓሜውም ‹‹ክርስቶስ ከሙታን ተነሳ፣ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን፣ ሰይጣንን አሰረው፣ አዳምን ነፃ አወጣው፣ ሰላም ከዛሬ ጀምሮ፣ ፍስሃና ሰላም ሆነ›› ማለት ነው:: በዚህ ሰላምታ ውስጥም የክርስቶስን መነሳት ይመሰክሩታል:: በመዝሙርም ካህናቱ፣ ወራዙቱ፣ ወይዛዝርቱ፣ አእሩግ ሕፃናቱ ምዕመኑ ሁሉ ይዘምሩታል::

ቃሉ የትንሣኤው የምሥራች ለምእመናን የሚታወቅበት ነው:: የሚቀድስ ካህን፣ ሰባኪ በዘመነ ትንሣኤ ከስብከቱ አስቀድሞ ከታች በተጠቀሰው ቃል የክርስቶስን መነሣት ያውጃል:: የሚቀድሰው ካህንም በኪዳን ጊዜ ሕዝቡን ከመባረኩ አስቀድሞ ይህንኑ ቃል ይናገራል፣ ሰላምታ የሚቀባበሉ ምእመናንም ሰላምታ ከመስጠት አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር ትንሣኤውን በማወጅ ይመሰክሩበታል:: በርግጥም በዓሉ የሰላም ይሁንልን:: እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው አደረሳችሁ እንላለን::

ይቤ ከደጃች.ውቤ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You