
ለዓመታት ተቋርጦ የቆየው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችን ዳግም ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ባለፉት 9 ወራት በስፖርቱ ሴክተር ያለውን ክፍተት በጥናት በመለየት ወደ ትግበራ የገባ መሆኑንም ጠቁሟል።
በበርካታ የስፖርት አይነቶች ሁሉንም ክልልና ከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ የሚካሄደው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ከ2008 ዓም በኋላ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በኦሊምፒክ ጽንሰ ሃሳብ መሠረት የሚካሄደውና በርካታ ስፖርተኞችን የሚያሳትፈው ትልቁ ሀገር አቀፍ ውድድር፣ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት አንዱ አማራጭ ይሆናል ተብሎ ቢታመንበትም ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡
ለዓመታት ተቋርጠው የቆዩ መሰል ውድድሮችን ዳግም በማስጀመር ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎችንም ለማስጀመር የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
የሦስተኛውን ሩብ ዓመት የሥራ ክንውን የገመገመው ሚኒስቴሩ በሴክተሩ ያለውን ክፍተት በጥናት በመለየት ወደ ትግበራ መግባቱንም ገልጿል። ‹‹ሀገራዊ የስፖርት ልማት ስብራቶችን በሳይንሳዊ ጥናት እንፍታ›› በሚል ርዕስ የተከናወነውን ጥናት ተከትሎም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቶ በተገኘው ግብዓት መሠረት ወደ ተግባር እንደተገባ ታውቋል። በዘርፉ በተለይም ላለፉት ስድስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ምዘና ውድድር የተጀመረበት ሲሆን፤ በዚህም ከቀበሌ አንስቶ እስከ ወረዳ ባሉት እርከኖች የታዳጊ ወጣቶች ምዘና ውድድር እንደተካሄደበት ተገልጿል። ለረጅም ጊዜ የተቋረጠው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ውድድር እንዲሁም ሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተካፈሉበት የባህል ስፖርት ፌስቲቫልም ባለፉት ወራት የተከናወኑ ውድድሮች መሆናቸውን አስታውሷል።
ሚኒስቴሩ ‹‹ትጋት ለስኬት መሠረት ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ ከተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር በ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት ያደረገም ሲሆን፣ በመድረኩ በቀረበው የዕቅድ አፈጻጸም መሠረትም መንግሥት ባለፉት ስድስት ዓመታት መካከለኛና አነስተኛ ደረጃ ያላቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ደረጃ የተሻሻሉበት፣ አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተገነቡበት፣ የኮሪዶር ልማት ሥራዎችን መነሻ በማድረግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተሠሩበት እንዲሁም የባህል እና የኪነጥበብ መሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች የተከናወኑበት እንደነበረ ተብራርቷል።
በባህልና ስፖርት ዘርፍ አሁን የተገኙ ስኬታማ ተግባራትን ስንቅ አድርጎ በቀጣይ የበለጠ በመትጋት የሚሠራበት እንደሆነም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ተናግረዋል፡፡
የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ውይይት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ተቋም የተከናውኑ ሥራዎችን ለማስገንዘብና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ግብዓት ለመውሰድ ያግዛልም ብለዋል። እንደ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም ባለፉት 9 ወራት ሴክተሩ ላይ ያለው ክፍተትን ለመለየት ጥናትና ምርምር በማድረግ የዘርፉን ችግር ለይቶ ወደ ትግበራ መሸጋገር መቻሉን አስረድተዋል።
በሴክተሩ ተጨባጭና የሚቆጠር ሥራ እየተከናወነ እንዳለ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ በቀሪ ሥራዎች ላይ ሁሉም ኃላፊነት በመውሰድና ተግቶ በመሥራት አሁን ከተገኘው ስኬትና ውጤት በላይ እንዲፈፅም ሚኒስትሯ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
አክለውም የባህልና ስፖርት ዘርፍ ኢትዮጵያን በመገንባት፣ በወልና አሰባሳቢ ትርክት ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ በሕዝቦች አብሮነትና ግንባታ እንዲሁም ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የሴክተሩ ትልቅ አቅም መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፤ የባህልና ስፖርት ዘርፍ ማኅበረሰብን ለመገንባት፣ የወል ትርክትን ለመገንባትና የኢትዮጵያውያንን አብሮነት ለማጽናት ሚናው የላቀና መንግሥትም ትኩረት የሰጠው ሴክተር እንደሆነ ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ያካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የኪነጥበብና ባህል ፌስቲቫል ለኢትዮጵያ የባህል ዲፕሎማሲና ቱሪዝም ዘርፍ ያስገኘው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በስፖርት ዘርፍም የስፖርት ቱሪዝምን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም