
አራት ኪሎ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት (የስድስት ኪሎ መስመር) ለመሻገር አዲሱ ዘመናዊ የውስጥ ለውስጥ መሻገሪያ ከተመረቀ ቆይቷል:: በዜናም ተነግሯል:: ምናልባት ዜናውን መስማት ላልቻለ ሰው ደግሞ ሰዎች በዚያ መሻገሪያ ሲሻገሩ ይታያል::
ይሄ ሁሉ ይቅር! እዚሁ ቦታ ላይ ዜብራ በሌለበት (ለእግረኛ መሻገሪያ ያልተፈቀደ ማለት ነው) አንድ ማስታወቂያ ተጽፎ ተለጥፏል:: ማስታወቂያውም ‹‹በዚህ መሻገር ክልክል ነው!›› የሚል ነው:: መቼም በዚህ ዘመን (ለዚያውም አዲስ አበባ ውስጥ) ቢያንስ ማንበብ የማይችል ይኖራል ተብሎ አይታሰብም:: ማንበብ ባለመቻል ሳይሆን ማየት ባለመቻል ነው:: ማንበብና ማየት አለመቻል ብቻ አይደለም፤ መስማትም አለመቻል ጭምር ነው:: መስማት አለመቻል ሲባል ጆሯቸው ድምጽ መስማት የተሳነው ሆኖ ሳይሆን ልብ ማለት አለመቻል ማለት ነው::
ከመሻገሪያውም፣ ከማስጠንቀቂያው ጽሑፍም በተጨማሪ ከማስጠንቀቂያ ጽሑፉ አጠገብ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ቆመው ይጠብቃሉ:: እነዚህ ተቆጣጣሪዎች ልክ እግረኛ ሊሻገር ሲል ገና ወደ አስፋልቱ ሳይገባ እንዲመለስ ያስጠነቅቁታል::
መጀመሪያ ቀን የማስጠንቂያ ጽሑፉን እንዳየሁ፤ ይህን የመሰለ ዘመናዊ የእግረኛ መሻገሪያ ተሰርቶ ‹‹በዚህ አትሻገሩ›› የሚል የታፔላ ኮተት ለማን አስፈለገ! ብዬ ነበር:: የእግረኛ መሻገሪያው ዘመናዊ ስለሆነና እንዲህ አይነት የእግረኛ መሻገሪያ ስላልተለመደ፤ ምናልባትም ሰዎች ሌላ የመዝናኛ ሥፍራ፣ ምናልባትም ወደ ዳር የማያስወጣ ሊመስላቸው ይችላል ብዬ አሰብኩ:: ስለዚህ ማስጠንቀቂያ መደረጉ ትክክል ነው ብዬ አመንኩ::
ቀጥሎ ደግሞ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ቆሞ ሳይ ‹‹እንዴ! ይህን የሚያህል ጽሑፍ ተለጥፎ ተጨማሪ የሰው ሃይል ማባከን፣ ለዚያውም እዚህ ፀሐይ ላይ ቆሞ መዋል ለምን አስፈለገ? ብዬ አሰብኩ:: ዳሩ ግን ችግሩ አሁንም ወዲህ ነው! የእግረኛ መሻገሪያውንም የማያውቁ፣ ጽሑፉንም የማያዩት ብዙዎች ሆኑ! የማያዩት ማለት ዓይነ ሥውራንን ማለቴ ሳይሆን ልባቸው የማያይ ማለቴ ነው:: ስለዚህ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አስፈለጉ! ያስፈለጉበት ምክንያት አንድም ለማስጠንቀቅ፤ ሁለትም ሕግ የተላለፉትን ለመቅጣት ማለት ነው፤ ተቆጣጣሪዎች ባይኖሩ የማስጠንቀቂያ ጽሑፉን እያዩትም ቢሆን የሚሻገሩ ይኖራሉ ማለት ነው::
እዚህ ላይ አንዳንድ አስቂኝ ነገሮችም አሉ:: የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አንድ ሰው ገና ሊሻገር ሲል ምልክት እያሳዩ ተመለስ ይሉታል፤ ይህኔ ምን እያሉ እንደሆነ ልብ ባለማለት ተንደርድሮ ይገባበታል:: ይህኔ በትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በኩል ሆኖ የሚያየው ተላላፊ መንገደኛ በድርጊቱ ይስቃል:: እንደ ሞኝ ቆሞ ሁነቱን የሚከታተሉ ሁሉ አሉ:: አንዳንዶች ደግሞ እግረኛው ከወዲያ ማዶ ገና ሊገባበት ሲል ከወዲህ ማዶ ሆነው ትራፊኮችን እየጠቆሙ ተመለስ የሚል ምልክት ያሳዩታል:: ልክ የታክሲ ሾፌሮች ትርፍ የጫኑ የሙያ ባልደረቦቻቸውን ‹‹ትራፊክ አለ!›› ብለው እንደሚያስጠነቅቁት ማለት ነው:: እግረኛ ለእግረኛም መተዛዘናቸው መሆኑ ነው!
እግረኛው በትራፊክ ተቆጣጣሪዎችም ሆነ በመንገደኞች ‹‹ተመለስ!›› እየተባለ ተንደርድሮ ሲገባበት ብዙዎች ይስቃሉ:: ሁለተኛው ሳቅ ልክ እንደተሻገረ ሲያስቆሙት ነው:: የእግረኛ ቅጣት የተለመደ ስላልሆነ ፈገግ ማሰኘቱ የግድ ነው:: ለእግረኛውም አሳፋሪ የሚሆነው እግረኛ ሆኖ መቀጣት ነው:: እግረኛ መሆን የሚያሳፍር ሆኖ ሳይሆን፣ ዳሩ ግን በጣም ቀላል የሆነውን የእግረኛ ሕግና ደንብ አለማክበር ያሳፍራል፤ ምክንያቱም ትልቅ አላዋቂነት ነው:: ተሽከርካሪ ማሽን ነውና ከአቅም በላይ በሆነ ችግርም ለቅጣት ሊዳርግ ይችላል:: እርግጥ ነው ባለተሽከርካሪዎችም የሚቀጡት ሆን ብለው በሚሠሩት ስህተትና ጥፋት እንጂ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር አይደለም:: ከአቅም በላይ በሆነ ችግር አደጋ ሊያጋጥም ይችላል እንጂ ደንብ መተላለፍ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር አይሆንም::
ያም ሆነ ይህ እግረኛ ሆኖ መቀጣት ያሳፍራል:: ምክንያቱም አለመሠልጠንን፣ ልብ አለማለትን፣ አለማስተዋልን፣ አለማሰብን ያሳያል:: ይህ ደግሞ ለትራፊክ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለብዙ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን መሰናክል የሚሆን ነው::
የሚቀጡት ሰዎች በአለባበስም ሆነ በተክለ ሰውነት ሲታዩ ከገጠር የመጡ አይነት ሰዎች አይደሉም፤ እንደማንኛውም የልብስ አራዳ ዘመናዊ ሰዎች የሚመስሉ ናቸው:: የያዙት ስልክ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እንኳን ያልያዙት ውድ ስልክ ነው፤ አሉ የሚባሉ መተግበሪያዎችን ሁሉ መጠቀም የሚያስችል ነው፤ ዳሩ ግን ቁም ነገር አያዩበትም:: ያ ሁሉ ሰው የእግረኛ መሻገሪያ እንኳን የማያውቅ ቲክቶክ እና ፌስቡክ ላይ ተጥዶ የሚውል ነው ማለት ነው:: እንዲያውም ይባስ ብሎ ሀሰተኛ መረጃ ሲቀባበል የሚውል ሊሆን ይችላል:: ይህን ሁሉ ሲያይበት ሀገራዊና መንግሥታዊ የሆኑ ጉዳዮችን ግን አያይበትም:: የተከለከሉና የተፈቀዱ ነገሮችን ግን ልብ አይልም::
አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በኑሮ ውጣ ውረድም ሆነ በሥራ ጫና ምክንያት ቀልብ የሚባል ነገር አይኖርም:: ለዚህም ነው የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንኳን እየጠሯቸው የማይሰሙት:: ቀልቡ ያለው የዕለት ሩጫው ላይ ነው:: የዚህ አይነቶቹ ምናልባትም ‹‹አይፈረድባቸውም!›› ሊባል ይችላል::
ዳሩ ግን ሙሉ በሙሉ ልንፈርድባቸውና ልንወቅሳቸው የሚገባ ግልጽ ጉዳይ ደግሞ አለ:: ዜብራ የእግረኛ መሻገሪያ መሆኑ ስንት ዘመን የቆየ አሠራር ነው? ዜብራ የታወቀው አሁን ነው ወይ?
አዲስ አበባ ውስጥ ከኮሪደር ልማቱ በፊትም ሆነ በኋላ ብዙ ሰው ዜብራው አጠገቡ በቅርብ ርቀት ላይ እያለ ያለ ዜብራ ይሻገራል:: በተለይም ከኮሪደር ልማቱ ወዲህ ደግሞ በተደጋጋሚ በዜና ተነግሯል:: መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል:: ቅጣት እየቀጡ በማሳየትም ለማስተማር ብዙ ርቀት ተሄዷል:: ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ልክ እርሻ ማሳ ውስጥ ያለ ይመስል እግሩ በመራው አስፋልት የሚሻገር ብዙ የልብስ ዘመናዊ ሰው አለ:: ይህን ሲያደርግ ዜብራው የሁለት እርምጃ ርቀት የለውም::
አንዳንድ ቦታ ላይ ዜብራው ብዙ ርቀት ሊኖረው ይችላል፤ ዳሩ ግን ሕግ ህግ ነውና ለምን አራቁት በሚል በእልህ እንደፈለጉ አይደረግም፤ ሲቀጥልም ያን ያህል የተጋነነ ሩቅ የሚባል አይደለም::
በበኩሌ የእግረኛ ቅጣት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እላለሁ:: እርግጥ ነው አንድ ችግር አለ:: የእግረኛ ሕግና ደንብ ከሚተላለፉ ሰዎች ውስጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ ምናልባትም የቅጣቱን መጠን በዕለቱ ያልያዙ ሊሆኑ ይችላሉ:: የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን የማይጠቀሙ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ባንክ ውስጥ ራሱ ገንዘብ የሌላቸውም ሊሆኑ ይችላሉ:: እንዲህ አይነቶችን ‹‹ርቱዕነት›› በሚባለው አስጠንቅቆ ብቻ ማለፍ የሚሻል ይመስለኛል:: ርቱዕነት ማለት ሕግና ደንብ ተላልፈን በጎ ነገር ማድረግ ማለት ነው:: ያ ያደረግነው ነገር ሕግና ደንብን የጣሰ ቢሆንም ዳሩ ግን በሀገርና ሕዝብ ላይ ጉዳት የማያመጣ ማለት ነው:: አንዳንዴ ሕግ እና ህሊና ሊለያዩ ይችላሉ:: እንዲህ አይነት ሲያጋጥም ቅጣቱን በአቅማቸው ልክ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ምናልባት የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል::
በተለይ ፊደል የቆጠረው ‹‹የተማረ መሃይም›› ግን ቅጣት ይገባዋል:: ሌሎችን ሊያስተምርና ሊያሰለጥን ሲገባው ጭራሹ ራሱ መሰልጠን ሲቸግረው ማየት ያሳዝናል::
በአጠቃላይ እግረኛ ሆኖ መቀጣት ያሳፍራልና ሕግና ደንብ እንልመድ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም