ድባበ በዓላት

‹‹ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አያድርም›› የሚል አባባል አለን፡፡ በበዓል ሰሞን ይህ አባባል ይደጋገማል፡፡ መልዕክቱም፤ ጎረቤት ይህን አደረገ ብለን ያለአቅማችን ማድረግ የለብንም ለማለት ነው፡፡ ጎረቤት በግ የመግዛት አቅም ቢኖረው፤ የእኛ አቅም ደግሞ ዶሮ የመግዛት ከሆነ ዶሮ ይበቃል ለማለት ነው፤ ዶሮም የመግዛት አቅም ከሌለን ደግሞ ይቀራል ማለት ነው፡፡

ይህ ችግር የተፈጠረው በዓልን ከመብል ጋር ብቻ ስላያያዝነው ይመስለኛል፡፡ የበዓል ውበቱ ግን መብሉ ብቻ ሳይሆን በበዓሉ ሰሞን የሚፈጠረው ድባብ ነው፡፡ ምንም ነገር እንደማልገዛ እያወቅኩት የሌሎች ሰዎች ሽር ጉድ በራሱ የሚሰጠኝ ደስታ አለው፡፡

በዓል ለብዙዎች ደስ የሚለው ሰሞነኛው ነው። ለበዓሉ ዝግጅት የሚደረገው ሽር ጉድ፣ ከወትሮው በተለየ ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ነገሮች፤ በተለይ የዋዜማ ዕለት ደግሞ በጣም ድምቅ ማለቱ ይናፍቃል፡፡

በዋዜማ ወዳጅ ዘመድ ይመጣል፤ ከእነርሱ ጋር የሚኖረው ጨዋታ ይደራል፡፡ ስለዚህ አጋጣሚው ምግብ ብቻ ሳይሆን ጨዋታውም ጭምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ያለ ድግስ ለጨዋታ ብቻ ተብሎ ዘመድ ሲጠራ አላየሁም!

የበዓሉ ዕለት ግርግር ስለሚበዛ እንደዋዜማው አይሆንም፤ በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ነገር ገና ወደፊት ሆኖ በተስፋ ሲጠበቅ ነው ደስ የሚለው፡፡ ለበዓል ከሚመጣው ዘመድ ጀምሮ ለልጆች አዳዲስ ልብስ ይገዛል፤ ልጆችን በጣም የሚያጓጓው ደግሞ ይሄ ይመስለኛል፡፡ ብቻ ግን ቀኑ በጉጉት ይጠበቃል፡፡

ሌላው ድባብ የበዓል ማግስት ነው፡፡ በእርግጥ የበዓል ማግስት ቅር ቅር እያለን የምንሄድበት ነው፤ ምክንያቱም የመጣው ወዳጅ ዘመድ ለመሄድ ይነሳሳል፡፡ በተለይ አብዝተው ለሚጠጡና ለሚበሉማ እንዲያውም ሕመምም አለው፡፡ ለዚህ እኮ ነው የጤና ባለሙያዎች የሚመክሩት፡፡

በተለይም እንዲህ እንደ ፋሲካ ባለው ከፆም በኋላ በሚደረግ በዓል ሕመም ያጋጥማል፡፡ ጨጓራ ከቅባታማ ነገሮች እና ከሥጋ ነክ ምግባር ርቆ ስለሚቆይ በአንድ ጊዜ ማጨናነቅ ሕመም አለው፡፡ እንኳን ርቆ የቆየውን፣ በአዘቦት እንኳን ብዙ መመገብ አይመከርም በዚያ ላይ የአልኮል መጠጥ ይጨመርበታል፡፡

ሲፆም የቆዬ ጨጓራ አልኮል ሲጠጣበት ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት። ተቀጣጣይ ነገር ላይ ጋዝ እንደመጨመር ማለት ነው። ስለዚህ ፋሲካው ስቃይ እንዳይሆን፣ ትንሣዔው መተኛት እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡

በነገራችን ላይ ፋሲካ የሚለው ቃል ትርጉሙ ይሄ ዛሬ የምናከብረው የትንሣዔ በዓል ብቻ ማለት አይደለም፤ ሌሎች ተደራቢ ትርጉሞችም ተሰጥቶታል። አንድ ነገር የተትረፈረፈ ከሆነ ፋሲካ ሆነ እኮ ይባላል፤ አስደሳች የሆነ ነገርም ፋሲካ እየተባለ ይገለጻል፡፡ ትንሣዔ በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ሲሆን፤ በማኅበራዊና ዓለማዊ አጠራሩ ግን ፋሲካ ይባላል፡፡ ደስታ እንደማለት ነው፡፡

ወደ በዓሉ አከባበር ስንመጣ እንግዲህ አከባበሩ የተለያየ ነው፡፡ አከባበሩ የተለያየ ነው ሲባል እንደ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል ተንታኞች ከሌሎች ሀገራት ጋር እያነጻጸርን ማለት አይደለም፡፡ የበዓሉ አከባበር የሚለያየው እንደየሰዉ አቅም ነው ለማለት ነው፡፡

በዓል በመጣ ቁጥር ‹‹ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አያድርም›› የሚለው አባባል ይደጋገማል፤ የሚደጋገመው ግን በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ነው፡፡ በተግባር ያለውን አባባል ካየነው ጭራሽ በተቃራኒው ተገልብጦ ‹‹ሰው እንደ ጎረቤቱ እንጂ እንደቤቱ አያድርም›› የሚለው ነው፡፡ ይሄ ማለት ጎረቤቱን መስሎ ለማደር ይታገላል ማለት ነው፡፡

ለማንኛውም ‹‹ሰው እንደጎረቤቱ እንጂ እንደቤቱ አያድርም›› የሚለው ያመዝናል፡፡ ብዙ ሰዎችን ልብ ብላችሁ ሰምታችኋል? ‹‹እንዲያው ይህን ባናደርግ፣ ይህ ባይገዛ…ጎረቤትስ ምን ይላል!›› የሚሉ ብዙዎች ናቸው፤ የተለመደ ሆኗል፡፡

ያ ማለት ከእነርሱ ፍላጎት ይልቅ ጎረቤት አድርገዋል እንዲላቸው ታስቦ ነው ማለት ነው፡፡ ካለው አጉል ልማድ አንፃር አይፈረድባቸውም ሊባል ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ለአንድ ቀን ብለው አግባብ ያልሆነ ዕዳ ውስጥ መግባት ችግሮችን ማብዛት ነው፡፡

አንዳንድ ልማዶቻችን አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ አንድ ሰው እኔ ካልቻልኩ ወይም ካልፈለኩ አላደርግም ብሎ ቢተወው የት ይውላል? በዚያ ላይ የአዲስ አበባ ቤት ደግሞ ተደጋግፎ ያለ ነው፤ ሲገባና ሲወጣ ከመታየቱም በላይ የጎረቤት ድስት ሲፈላ ሁሉ የሚሰማበት ነው፡፡

ቤቱ ዝም ብሎ ቁጭ ቢል ከጎረቤት ያለው ነገር ይሰማል፣ ይታያል፡፡ አይ! ከዚህማ ወጣ ማለት አለብኝ ብሎ ቢሄድ መንገዱ ሁሉ ፀጥ ብሎ የመንገዱ ሰው እሱ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለዚህ ጎረቤት ለመምሰል ተብሎ የሚደረጉ ነገሮች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ልጆች ያሉበት ቤት ደግሞ የግድ መሆኑም አልቀረም፡፡ ማኅበራዊ ልማዳችን በግል ፍላጎት ብቻ ነፃ ሆኖ ለመኖር ምቹ አይደለም፡፡

የበዓል ሰሞን ሌላው ትዝታ የሥጋ ሰልፍ ነው። ‹‹ቆይ ግን ያ ሁሉ ሥጋ ሊገዛ ነው ወይስ ለጎረቤት ይምሰል ተሰልፎ ነበር ለመባል ነው?›› ያሰኛል፡፡ አንዳንዱ እኮ ሰልፉ ላይ ቆሞ ‹‹ኧረ እረፈደብኝ፤ ገና በግ አርዳለሁ፣ ብዙ እንግዳ ስለሚመጣብኝ ለመጨመሪያ ብዬ እንጂ›› የሚልም አለ፤ ይሄ ለጎረቤት ይምሰል የተሰለፈ ይመስላል፡፡ ምናልባትም ሰልፉ ሊደርሰው ሲል የሆነ ሰበብ ፈጥሮ ይወጣ ይሆናል፡፡ ወይም ሥጋውን አየት አድርጎ ‹‹እኔ እገሌ ነኝ እንዲህ አይነት ሥጋ የምወስደው!›› ብሎ መተው ነው (አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል እንደሚባለው)፡፡ እንዲያው ለጨዋታው እንጂ በዚህ ዘመን በዚህ ልክ የዋህ ይኖራል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡

በነገራችን ላይ የሥጋ ሰልፍ የሚፆመው ሰው ብቻ አይደለም፤ በተለይ የፆም መያዣ ወቅት ላይ የሚፆመውም የማይፆመውም አብሮ የሚጋፋ ለምንድነው? የማይፆመው እኮ በነጋታው መውሰድ ይችላል፡፡ እያልኩ ያለሁት ፆሙ ከሚገባበት እምነት ውጭ ያሉትን እንዳይመስላችሁ፡፡ የእምነቱ ተከታዮችን ነው፡፡

ለምሳሌ የሁዳዴ ፆም መያዣ የኦርቶዶክስ አማኞች ነው፤ ኦርቶዶክስ ሆኖ የማይፆም የዚያን ቀን አብሮ ይሰለፋል፡፡ የበዓሉ ድባብ ይናፍቀዋል ማለት ነው እንግዲህ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ሥጋ ሲበላ ቆይቷል እንበል፤ ግን ነገ እንደ አዲስ አብሮ መሰለፉ የሆነ የሚሰጠው ደስታ ይኖራል ማለት ነው፤ በቃ በዓል እንደዚህ ነው!

ደግነቱ የፋሲካ በዓል ያለፈውን የፆም ጊዜ ያካክሳል። 40 ቀን ሙሉ ዓርብም ረቡዕም ሥጋ ይበላል፡፡ ለዚህ ይሆን እንዴ ‹‹ፋሲካ›› የሚለው ቃል የደስታና ፈንጠዝያ ምሳሌ የተደረገውና ቃሉ ለሌላም ደስታ ለበዛበት ነገር ምሳሌ የሆነው?

በዓሉ የደስታና የሰላም ይሆን ዘንድ ብዙ ባለመብላትና ባለመጠጣት አካላዊ ጤናችንን እንጠብቅ፤ ‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አያድርም›› የሚለውን አባባል በተግባር በመኖር አዕምሯዊ ጤናችንን እንጠብቅ!  መልካም በዓል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You