ጸሎትና ስግደት ከልብ ይሁን!

ዛሬ በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ የሰሞነ ሕማማት ሳምንት የሚጀምርበት ቀን ነው:: የፊታችን ዓርብ ደግሞ ስቅለት ነው:: በዚህ በሰሞነ ሕማማት እንደ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ፆምና ፀሎት፣ ስግደት ይደረጋል:: ይህ ሳምንት የይቅርታ ሳምንት ነው:: የተጣላ፣ የተኳረፈ ይቅር የሚባባልበት ነው:: የሃይማኖት አባቶች ለስግደት የመጡትን ሰዎች ‹‹በሆዳችሁ ያለውን ቅሬታ ሁሉ የምታስወጡበት ነው! ቅር ያሰኛችሁት ሰው ካለ ይቅርታ ጠይቁ!›› እያሉ ይናገራሉ:: ይህን ሰው አስቀይሜያለሁ ብሎ የሚያምን ሁሉ ያንን ያስቀየመውን ሰው ይቅርታ ይጠይቃል:: እዚህ ላይ በልጅነቴ የማስታውሰው አንድ አስቂኝ መሳይ ገጠመኝ ልናገርና ወደ ዋናው ትዝብቴ እገባለሁ::

በሰሞነ ሕማማት ነው:: ምዕመናን ሲሰግዱ ቆይታው የሃይማኖት አባቶች ማስተማር ይጀምራሉ:: በሆዱ ቅሬታ ያለው ሁሉ ቅሬታውን ትቶ ይቅርታ እንዲያደርግ ያዝዛሉ:: ይሄኔ አንዱ ሰውዬ ወደ አንደኛው ሄደና(በአንድ አጋጣሚ ተጋጭተው ነበር) ስሙን ጠርቶ ‹‹አንድ ቀን ልገድልህ ቦታ ይዤ ስጠብቅህ በሌላ ቦታ ሄድክና አመለጥከኝ:: እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ!›› ይለዋል:: ይሄኔ ይቅርታ የተጠየቀው ሰው ‹‹ቱግ!›› ብሎ አካኪ ዘራፍ አለ፤ ምክንያቱም በአጋጣሚ ባያመልጥ ኖሮ ሊገደል ነበር:: የፆም ጸሎትና የይቅርታ የሆነው መድረክ ‹‹የገላጋይ ያለህ!›› የሚያሰኝ የሁለት ግለሰቦች ፀብ ተፈጠረበት:: በሃይማኖት አባቶችና በሽማግሌዎች ርብርብና ቁጣ ወዲያውኑ አስታረቋቸው:: ከዚያ በኋላ እኔ እስከማውቀው ድረስ ተጣልተው አያውቁም::

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት የይቅርታ ጠያቂው የዋህነት ነው:: ይቅርታው ከልብ ነበር ማለት ነው:: ከልቡ ተጸጽቶ ነበር ማለት ነው:: ከአንገት በላይ የሆነ ይቅርታ አልፈለገም ማለት ነው:: የሆዱን በሆዱ ይዞ ለሰው ይምሰል ብቻ ይቅርታ ማለት አልፈለገም ማለት ነው:: የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት ነበር ማለት ነው::

ይቅርታ ተጠያቂው ደግሞ ግጭታቸው እስከ ግድያ ያደርሳል ብሎ አልገመተም ነበር:: ይገለኛል ብሎ አልገመተም ነበር ማለት ነው:: ድንገት ሲነገረው ‹‹ለካ እንዲህም ታስቦልኝ ነበር እንዴ!›› ብሎ የእምነት ቦታ መሆኑን የሚያስረሳ ንዴት ተናደደ::

የዚያን ሰሞን በተለይም ወጣቶች ይቅርታ ጠያቂውን ሰውዬ ‹‹ምን ዓይነቱ ጅል ነው!›› እያሉ ሲስቁበት ነበር:: አዋቂዎች ግን የዋህነቱንና ከልቡ መሆኑን ሲያደንቁ ነበር:: ያም ሆነ ይህ ይቅርታቸው ሰምሮ ሰላም ሆነው ኖረዋል::

በዓመታዊ የንግስ በዓላት ቀን የሚነግስ ቤተክርስቲያን ባለበት አካባቢ በትራንስፖርት ሳልፍ መንገድ ይዘጋጋል:: ይሄኔ አንድ ትዝብት በተደጋጋሚ ይመጣብኛል:: ‹‹ይሄ ሁሉ አማኝ ባለበት ነው ይሄ ሁሉ ጥፋት እየተፈጸመ ያለው!›› እላለሁ:: ወዲያው ደግሞ ጥያቄውን ራሴው እመልሳለሁ:: አጥፊዎች ጥቂት ሆነው ሳለ ለምን ይህን ሁሉ አማኝ አብሬ እወቅሳለሁ የሚል የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል:: ያም ሆኖ ግን አጥፊዎችም ቢሆን እየበዙ ነው::

በግብይት ቦታ ላይ የማናየው የወንጀል ዓይነት የለም:: በሚበላ ነገር ላይ ባዕድ ነገር እንደ መጨመር አደገኛ ወንጀል የለም፤ በሰለጠነው ዓለም ቢሆን በሰው ሕይወት ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው:: ሰውን በሕመም እንዲሰቃይ አድርጎ መግደል ወይም ሆን ብሎ እንዲታመም ማድረግ ወንጀል ነው:: የኅሊና ወንጀል ብቻ ሳይሆን የሕግ ወንጀል ነው:: በየሱቁ የሚሸጠውን ደረቅ እንጀራ ግን ልብ በሉ! እሁድ ጠዋት ወይም በንግሥ ቀን ጠዋት ነጠላ ለብሳ የጄሶ እንጀራ የምትሸጥ ሴትዮ ያለችበት ነው:: ምናልባት እሷ አልጋገረችውም ሊባል ይችላል:: ዳሩ ግን ጋጋሪዋም ቢሆን ያው ናት:: ሲቀጥል ሻጯም ቢሆን ያ የምትሸጠው እንጀራ ሽታው ብቻ እንደሚሰነፍጥ ታውቀዋለች:: ምናልባትም ራሷ የማትበላው ሊሆን ይችላል:: ይህን እንጀራ ሌላ ሰው እንዲበላው ስትሸጥ ኅሊናዋን አልከበዳትም ማለት ነው::

‹‹ሐበሻ ምቀኛ ነው!›› የሚባለው አባባል እንደዋዛ መደበኛ የአበው አባባል እየሆነ ነው:: ችግሩ አባባሉንም የሚጠቀመው ራሱ ሐበሻ መሆኑ ነው:: ከብዙዎች የምንታዘበው ምቀኝነት እና ክፋት ነው:: እልህ እና ብሶተኛነት ነው:: አማኝ ነኝ ከሚል ማኅበረሰብ ደግሞ ይህ አይጠበቅም ነበር!

ወደ ሰሞነ ሕማማት እንመለስ

ይህ የሰሞነ ሕማማት ሳምንት አማኞች በባዶ እግር(በገጠር አካባቢ) የሚሄዱበት፣ ንሰሃ የሚገቡበት ነው:: በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ዓርብ ደግሞ የዓመቱ ንሰሃዎች ሁሉ ለንስሃ አባት ተነግረው(ልጅ እያለሁ በገጠር አካባቢ በማውቀው ልማድ) ከፍተኛ ስግደት የሚሰገድበት ነው:: ይህ ሳምንት ትልልቅ ሰዎች የተጣላን የሚያስታርቁበት ሳምንት ነው:: ምንም ዓይነት በደል ቢሆን ሰዎች ያስቀየሙትን ሰው ይቅርታ የሚያደርጉበት ነው:: የእኔ ትዝብትም እዚህ ላይ ነው:: ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ይሄ ቢሆንም፣ የምር ግን በዚህ ልክ የይቅርታ ልብ አለን ወይ? ከራሳችን በላይ ለሌሎች የምናስብ ነን ወይ?

በአማኝ እና በወታደራዊ መርህ አንድ ደስ የሚል ነገር አለ:: ይሄውም የሚኖሩት ከራሳቸው በላይ ለሌላው ነው:: የወታደር መሞት ‹‹መስዋዕትነት›› የሚባለው ለዚህ ነው:: መሰዋት ማለት ለሌሎች ዋጋ መክፈል ማለት ነው:: ሌሎችን ለማዳን መሞት ማለት ነው:: ወታደር የሚሞተው ሌሎችን ለማዳን ነው:: ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለማዳን እንደተሰቀለው ማለት ነው::

ታዲያ እኛ አማኞች ሌሎችን ለማዳን መሞት ቢቀር ምነው ሌሎችን ለመግደል የምንሠራ መሆናችን? ሌሎችን ለማዳን መሞት ግዴታ አይደለም፤ ለመግደል መነሳሳት ግን በኅሊናም በሕግም ወንጀል ነው:: ሌሎችን ለመግደል ማለት የግድ በጦር መሳሪያ ማለቴ አይደለም፤ እንዲያውም ከጦር መሳሪያ ግድያ በላይ የሆነ ወንጀል ነው እየፈፀምን ያለነው:: በጥይት መግደል ብዙም ስቃይ የለውም፤ አንድ ጊዜ መገላገል ነው:: ሰውን በበሽታ ተሰቃይቶ እንዲሞት ማድረግ ግን ከባድ ወንጀል ነው:: የሚበላ ነገር ውስጥ ባዕድ ነገር መጨመር ሰዎች እንዲታመሙ ማድረግ ነው:: ይህን የሚያደርገው ጥቂት ሰው ቢሆንም ችግሩን ለመቅረፍ አለመሥራትና አለማጋለጥም የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ነው::

የይቅርታ ልማዳችን ደካማ ነው:: ብዙዎቻችን ቂመኞች ነን:: ቂመኛነት ደግሞ በራስ ያለመተማመን ችግር ነው:: ከእኔ ይቅር ማለት አለመቻል ነው:: ከእኔ ይቅር ማለት አለመቻል ምቀኝነትና ክፋት ነው:: ከእኔ ይቅር የሚሉ ሰዎች እጅግ የታደሉ፣ በራስ መተማመን ያላቸው፣ ኅሊናቸው ንጹህ የሆነ እና ራስ ወዳድ ያልሆኑ ናቸው:: ይቅርታ የማያደርጉ፣ ይቅርታ ሲጠየቁም የማይቀበሉ ግን የበታችነት ስሜት ያለባቸው፣ እልህ እና ጥላቻ ያለባቸው ናቸው:: ይህ በሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦና ራሱ ምክንያት ያለው ነው:: የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት እልኸኛ እና ብሶተኛ የሚሆኑት የበታችነት ስሜት ያለባቸው ሰዎች ናቸው:: ሕይወታቸው የተመሳቀለ መስሎ የሚሰማቸው ሰዎች ናቸው፤ በሆነ ነገር ጎደሎነት የሚሰማቸው ሰዎች ናቸው::

አማኝ ሰው ኅሊናው ነፃ ነው መሆን ያለበት፤ ምቀኛ እና ስግብግብ ከሆነ ወደ እምነት ቦታ የሚሄደው ለይስሙላ ብቻ ነው ማለት ነው፤ ወይም በጭንቀት ብቻ ነው ማለት ነው:: የፆም፣ ጸሎትና ስግደት ሳምንቱ ከልብ ይቅር የምንባባልበት፣ ከራሳችን በላይ ለሌሎች የምናስብበት ይሁን!

መልካም ሰሞነ ሕማማት!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You