‹‹እኔም እችላለሁ›› – የኩባ ተሞክሮ በኢትዮጵያ ጎልማሶች ትምህርት

በሃይማኖት ቢለያዩም ቀሲስ መዝሙር ማዳ እና ሼህ ሙስጠፌ ነሰርዲን ባልንጀራሞች ናቸው:: ሁለቱም የአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ መደብር አላቸው:: መደብራቸው ደግሞ ጎን ለጎን ነው። በመደብሮቻቸው ውስጥ በሥራ ከ12 ሰዓት በላይ ያጠፋሉ:: በዚህ መካከል በሚያገኟት ክፍተት ባልንጀራሞቹ ከሀሁ ጀምሮ እየተረዳዱ ፊደል በመቁጠር ተማምረዋል:: መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ማጥናት፤ ቁራን እስከ መቅራትና ሃይማኖታዊ ትዕዛዙቱን ለሌላው እስከ ማካፈል የደረሰ እውቀት ጨብጠዋል:: ቆሎ የመሰለ የእጅ ጽሕፈትም ይጽፋሉ:: በተለይ ሼሂው በዚህ መልኩ ባደረጉት ጥረት ከአማርኛ አልፈው ዓረብኛ ጭምር ለመፃፍና ለማንበብ በቅተዋል::

ይሁን እንጂ ‹‹የምንኖርበት ቀበሌ ትምህርት ቤት ገብተን ስላልተማርን ለእውቀታችን እውቅና አልሰጠውም:: የመዘገበንም ማንበብና መፃፍ ከማይችሉት ጋር ነው›› ሲሉ በየፊናቸው ይናገራሉ:: ያላቸውን እውቀት ይዘው መደበኛ ትምህርት ቤት ሊገቡ ሞክረው እንደነበርም ያነሳሉ:: ባለታሪኮቻችን እንደሚሉት ማንበብና መጻፍ ለመቻላችሁ ከተማራችሁበት ትምህርት ቤት ሕጋዊ ሰርተፊኬት አምጡ በመባላቸው አልቻሉም:: አለዚያ ከዜሮ ጀምረው ፊደል መቁጠር እንዳለባቸው የተነገራቸው ቢሆኑም ጊዜያቸውን ማባከን ስላልፈለጉ ትተውታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ መልኩ ራሱን ያስተማረ ሕዝብ ቁጥሩ ቀላል አይደለም:: ሆኖም የትምህርት ሥርዓቱ የግድ ትምህርት ቤት ገብቶ ካልተማረ እውቅና አይሰጠውም::

በትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶች እና መደበኛ ያልሆኑ ትምህርት ፕሮግራሞች መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዮሴፍ አበራ እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትምህርት ሥርዓቱ በዚህ መልክ ራሳቸውን ላበቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች እውቅና ይሰጥ የነበረበት አሠራር አልነበረም:: በመሆኑም በኢትዮጵያ የተማረ የሰው ኃይል ምጣኔ 52 በመቶ ብቻ ለመሆን ተገድዷል:: በዚህ ምክንያት በተማረ ሰው ምጣኔ ብዛት ኢትዮጵያ በቅርቡ ከተወለደችው ደቡብ ሱዳን በስተቀር ከጎረቤቶቿ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሙሉ በታች ነች:: ኬንያ፤ ጅቡቲ፤ ሰሜን ሱዳን፤ ኤርትራ ይበልጧታል:: ኤርትራ የተማረ ሕዝብ ምጣኔዋ ከ76 በመቶ በላይ ነው:: ሀገራቱ የተማረ የሰው ኃይል ምጣኔያቸውን ከፍ ያደረጉት በራሳቸው ለተማሩት እውቅና በመስጠት ነው:: ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ እውቅና ባለመስጠቷ የተማረ የሰው ኃይሏ ዝቅተኛ ለመሆን ተገድዷል::

ይሄ ሀገራችንን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በመልካም እይታ እንዳትታይ አድርጓት ቆይቷል:: ትምህርት አንዱ የሥልጣኔ መገለጫ እንደመሆኑ የሰለጠነ ሕዝብ እንደሌላት፤ ከዚህ የተነሳም ገጽታዋ በደህነትና በሌላ እንዲሳልና እንዲገለጽ ሲያደርጋት ቆይቷልም ይላሉ አቶ ዩሴፍ::

በደርግ ዘመን ችግሩን ለመቅረፍ በእድገት በሕብረት ዘመቻ በየገጠሩ ያለው ሕዝብ እንዲማር ተደርጓል:: ውጤታማ በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥርዓቱ ሽልማት አግኝቶበታል:: ይሄ በኢህአዴግ ሥርዓት የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ነበር::

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ይሄን ችግር ለመቅረፍ ከለውጡ ወዲህ ከጎልማሶች ትምህርት ጋር ተያይዞ ልዩ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ አሠራሮች ተዘርግተዋል:: አንዱ እንደ ባልንጀራሞቹ ላሉትና በራሳቸው ተምረው ለሚመጡት ዜጎች እውቅና የሚሰጥበት የትምህርት ብርሃን ምዘና ነው:: በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ራሳቸው ተምረው የሚመጡ ሲሆን እነዚህም ተመዝነው የሁለተኛ ክፍል ሰርተፊኬት ያገኛሉ:: ይሄ ከፈለጉ በመደበኛው ትምህርት እና በማታው ክፍለ ጊዜ ሦስተኛ ክፍል ገብተው የሚማሩበት፤ ካልፈለጉ ደግሞ ኑሯቸውን የሚያሻሽሉበት፤ ሕይወታቸውን የሚለውጡበት የተግባር ትምህርት ለመቅሰም እድል ይፈጥርላቸዋል::

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንዳከሉት ሌሎች ሀገራት ማደግ የቻሉት በራሳቸው ተምረው ለሚመጡት እውቅና በመስጠትና የተማረውን ኃይል ምጣኔ በማብዛት ነው:: ጎልማሶች ከማንበብ፤ መጻፍና ማስላት ውጭ በዘላቂነት ሕይወታቸውን እንዲለውጡ እንደ ሀገር ላለው እድገትም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በትኩረት እንደሚሠሩም ያነሳሉ:: አፍሪካ ውስጥ ናይጀሪያ፤ ደቡብ አፍሪካና ግብጽ የተሻለ ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስ የቻሉት በዚህ መልኩ የተማረ የሰው ኃይል ምጣኔያቸውን ከፍ በማድረግ ስለመሆኑም ይናገራሉ:: የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) በቅርቡ ያወጣውን መረጃ ዋቢ በማድረግም አንድ መፃፍ፤ ማንበብ፤ ማስላት የሚችል ሰው መፃፍ፤ ማንበብ፤ ማስላት ከማይችለው 85 በመቶ ገቢውን ማሳደግ እንደሚችል ያስረዳሉ::

ኢትዮጵያም ከለውጡ ወዲህ በተለይም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአጭር ጊዜ የተማረ ኅብረተሰብ መፍጠር በሚቻልበት መንገድ እየተጓዘች መገኘቷንም ያነሳሉ:: ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ከ2015 ዓ.ም በፊት የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተብሎ ይሰጥ የነበረውን መርሐ ግብር የአንድ ዓመት የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት ተብሎ በመከለስ እንደ ሀገር ትምህርት እየተሰጠ ስለመገኘቱም ያክላሉ:: የኢትዮጵያን የተማሩ ሰዎች ምጣኔ (ሊትረሲ ሬት) በፍጥነት ያሳድጋል ተብሎ ስለመታመኑም ያነሳሉ:: እንደ ሀገር የተሻለ ኑሮ መኖር የሚችል የበለፀገ ዜጋ መፈጠርና በዚህ ዜጋ ሀገርም መበልፀግ አለባት ተብሎና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራበት ስለመገኘቱ ያወሳሉ:: የደርግ ተሞክሮ በጎ ፈቃደኞችን ከማሳተፍ ረገድ ተቀስሞ እየተሠራበት ስለመገኘቱም ይናገራሉ::

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት ዘንድሮ የትምህርት ብርሃን ምዘና ከወሰዱት በተለይ እድሜያቸው ከ15 እስከ 20 የሚደርስ ጎልማሶች ፍላጎታቸውን ተጠይቀው ትምህርት መቀጠል መሆኑን በመግለፃቸው በመደበኛው እና በማታው ክፍለ ጊዜ ሦስተኛ ክፍል ገብተው እንዲማሩ ተደርጓል::

አንድ ጎልማሳ ‹‹እኔ እድሜዬም ከፍ ስላለ የመደበኛ ትምህርት አልፈልግም፤ ግን ኑሮዬን ማሻሻል ማዘመን እፈልጋለሁ፤ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እፈልጋለሁ ካለ›› የሰልጣኝ ሞጁል 70 እንዲሁም 70 የአሰልጣኞች ሙጁል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሁሉም ክልሎች እንዲደርስ ስለተደረገ በዚህ መሠረት የሙያ ክህሎት ሥልጠና ይሰጠዋል:: ሥልጠና የሚወስደው በእንጨት ሥራ፤ ብረታ ብረት፤ ንብ በማነብ እና በሌሎች ሙያዎች ሲሆን መንግሥት የሌማት ቱሩፋት በሚል የጀመረውም በቀጥታ ከሙያ ክህሎት ሥልጠናው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑም ያነሳሉ መሪ ሥራ አስፈፃሚው:: ዜጎች ሥልጠናውን በአራቱም የሀገሪቱ ጫፍ አካባቢ መውሰድ እንደሚችሉም ይጠቅሳሉ::

ኑሮውን የበለጠ በማሻሻል ገቢውን የማሳደግ ዓላማ የሰነቀው እያንዳንዱ ጎልማሳም በየአካባቢው በሚገኝ የጎልማሶች ማሰልጠኛ ጣቢያ (ጎማጣ) በመገኘት የሙያ ክህሎት ሥልጠናዎችን ማመቻቸቱንም ያነሳሉ:: በሰባት ክልሎች ይሄን ሥልጠና የሚሰጡ ሞዴል የጎልማሶች ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ከነአመቻቾቻቸው መዘጋጀታቸውንም አቶ ዮሴፍ ይናገራሉ። ትምህርት ሚኒስቴር ከየክልሉ የትምህርት ተቋማት ጋር ሆኖም ሁሉም ክልሎች እንደ ሀገር እነዚህን ሰባት ሞዴል ጣቢያዎች በማስፋት እንዲጠቀሙ እየሠራ ስለመገኘቱም ያብራራሉ::

ከነዚህ ክልሎች መካከል በሲዳማ ክልል የሚገኘው ይሄም እንደ ሀገር የመፃፍ፤ ማንበብ ማስላት ምጣኔ እንዲያድግ እንዲሁም ዜጎች የፈለጉትን የሙያ ክህሎት መርጠው በመሰልጠን ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እያስቻለ መሆኑን ያስረዳሉ:: ፊደል በመቁጠር ቃልና ዓረፍተ ነገር የሚመሰርቱት በአጠቃላይ ማንበብ፤ መጻፍና ማስላት የሚማሩትም ከእለት እለት ሥራቸው ጋር በተገናኘ ነው:: ለምሳሌ በመስመር መዝራት የሚያስገኘው ጥቅም በሚለው ዓረፍተ ነገር እንዲመሰርቱ ይደረጋል” ይላሉ:: በዚህ መልኩ በሦስት ወር ማንበብ መጻፍ ችለው ውጤታማ ከሆኑት ሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ የሚገኘው አላዋርፌ፣ በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ የሚገኘው የላላ ዋንደራ የማኅበረሰብ የመማማሪያ ማዕከላትንም በማሳያነት ይጠቅሳሉ:: አሁን ላይ ባለው የትምህርት ፖሊሲ መሠረት አንድ ሕፃን ልጅ ሰባት ዓመት ሲሞላው በመደበኛው ትምህርት አንደኛ ክፍል ገብቶ ይማራል። ሆኖም ብዙዎቹ ሕፃናት በዚህ ዕድሜያቸው አንደኛ ክፍል የማይገቡበትና እስከ 14 ዓመት የሚዘገይበት ሁኔታ ነው ያለው::

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ 15 ዓመት ስላልሞላቸው በጎልማሶች ትምህርት መማር የማይችሉ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ታዳጊዎች አሉ:: አሁን ላይ ታዳጊዎቹ አማራጭ የመማሪያ ዘዴ ተፈጥሮላቸው በ‹‹አክስለሬትድ›› የትምህርት መርሐ ግብር እንዲማሩ እየተደረገ ነው።

በዚህም በፍጥነት ተምረው ተመልሰው ወደ መደበኛ ትምህርት ይላካሉ:: ተሞክሮው በተማረ ሰው ምጣኔ ከ98 በመቶ በላይ በመድረስ በዓለማችን ስኬት ማስመዝገብ ከቻለችው ኩባ ስለመቀሰሙም መሪ ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ:: ይሄን “እኔ እችላለሁ” በሚል በቁርጠኝነት የጀመሩት ሞዴል አውስትራሊያዎች፤ የካረቢያን ሀገራትም እንዲሁ ወስደው በመጠቀም ውጤታማ እንደሆኑም ያነሳሉ:: ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ትተገብረው ከነበረ የሁለት ዓመት መርሐ ግብር ይልቅ ይሄ የኩባዎቹ በአጭር ጊዜና በሚፈልጉት አቀራረብ መጻፍ ማንበብ፤ ማስላት እንዲችሉ ስለማድረጉም ይጠቅሳሉ:: መርሐ ግብሩ በአጠቃላይ ለጤናውም ለግብርናውም ሙያ ላይ ላለው ሥራ መሠረት እየጣለ ስለመሆኑም ያወሳሉ::

እንደሳቸው ወደዚህ ወደ አዲሱ የኩባ መርሐ ግብር ወደ ትግበራ ከተገባ ጀምሮ ከ2015 ጀምሮ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በመድረስ ወደ ተማሩ ዜጎች ምጣኔ መቀላቀል ተችሏል:: ይሄ በኢትዮጵያ የተማረውን የሰው ኃይል ምጣኔ በብርቱ ከፍ እያደረገው መጥቷል:: በዓለም አቀፉ ደረጃም ኢትዮጵያ በመልካም እይታ የምትታይበትን መደላድል መፍጠር እየቻለች ነው:: በዚህ ዓመት ብቻ አንድ1 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ጎልማሳ ዜጎችን ለመድረስና ለመቀላቀል ታስቦ እየተሠራ ይገኛል:: እስከ አሁን አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን አካባቢ ደርሷል:: አምና እና ካቻምና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ማድረስ ተችሎ የነበረ መሆኑንም አቶ ዮሴፍ ነግረውናል::

‹‹ዜጎችን በአጭር ጊዜ የተማሩ ማድረግ እንደሌላው ኢንቨስትመንት ብዙ ወጪ የሚጠይቅ አይደለም›› የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው በጎ ፈቃደኞችን በመጠቀም የሚከወን ስለመሆኑም ያነሳሉ:: ደርግ በእድገት በሕብረት በዓለም ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን የበቃው በጎ ፈቃደኞችን ተጠቅሞ ዜጎችን በየክልሉ በማዝመት በማስተማሩ ስለመሆኑም ያስረዳሉ::

“በሌሎች ሀገሮችም ከትምህርት ቤት እንደተመረቁ ሥራ መቀጠር የለም:: ለሁለት ዓመት የብሔራዊ አገልግሎት ይሰጣል” ይላሉ:: እርሳቸው እንዳሉት ከ500ሺ በላይ ጎልማሶችን መፃፍ ማንበብ ማስላት እንዲችሉ ማድረግ የተቻለው ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤታቸው ለዓረፍት የሚሄዱትን፤ በጡረታ የተገለሉ፤ ሌሎች 16 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ነው:: በዚህ ክረምትም አጠናክሮ የመቀጠል እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው::

እንደ አቶ ዮሴፍ ገለፃ በተለይ ክልሎች አካባቢ አርሶ አደሩ በዚህ መንገድ በመሄድ የራሱን ብሎም የቤተሰቡን ሕይወት እየቀየረ ነው:: የዚህ ድምር ውጤት እንደ ሀገር ባለው ኢኮኖሚ ላይ በጎ ተጽዕኖ እያሳደረና ብልፅግናም እያመጣ ይገኛል::

አሁን ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከሚያንቀሳቅሱት ሀገራት ተርታም እንድትሰለፍ እያደረጋት ነው:: ደቡብ አፍሪካ አንደኛ፤ ናይጀሪያ ሁለተኛ፤ ግብጽ ሦስተኛ አልጀሪያ አራተኛ፤ ኢትዮጵያ አምስተኛ ላይ እንድትሰለፍ አግዟል:: ግዙፍ ኢኮኖሚ በማንቀሳቀስ ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ኬንያንም የምትበልጥ አንደኛ ሆናለች:: የነፍስ ወከፍ ገቢዋም ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል:: የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ከመጡ በኋላ ማስላት፤ ማንበብ፤ መፃፍ ላይ ብቻ ትኩረት ይደረግ ተብሎ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የአንድ ዓመት የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት እየተተገበረ የሚገኘውም ይሄንኑ ለማምጣት ነው ይላሉ:: በዚህ መካከል የሚገጥሙ ተግዳሮቶች ስለመኖራቸውም ይናገራሉ:: የፖለቲካ ቁርጠኝነት ባለመኖር እንዲሁም በሌላ ሥራ በመጠመድ መተው፤ በተለይ ከሙያ ክህሎት አንፃር በጀት እጥረት ከተግዳሮቶቹ ስለመጠቀሳቸውም ያነሳሉ::

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You