ምዕመናን የትንሣዔ በዓልን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ ገለፁ

አዲስ አበባ፡- ምዕመናን የትንሣዔ በዓልን ሲያከብሩ ለተቸገሩ ወገኖች ካላቸው ላይ በማካፈል ሊሆን ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች መልዕክት አስተላለፉ።

የትንሣዔ በዓልን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት፤ ምዕመናን የትንሣዔ በዓልን ሲያከብሩ ለተቸገሩ ወገኖች ካላቸው ላይ በማካፈል ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትሪያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ የትንሣዔ በዓልን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፤ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው፤ በየአካባቢው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን በትንሣዔ በዓል ተፅናንተውና እፎይ ብለው በደስታ እንዲያሳልፉ ካለን ላይ አካፍለን መመገብና ማልበስ ይኖርብናል ብለዋል።

‹‹ዘር ሳይኖር ፍሬ እንደማይገኝ ሁሉ ሕይወታዊ ትንሣዔም ያለ ሃይማኖትና ሥነ- ምግባር ሊገኝ አይችልም›› ያሉት ብጹዕነታቸው፤ ይህንን አስመልክቶም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ‹‹መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣዔ ይነሳሉ፤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣዔ ይነሳሉ›› ማለቱን አስታውሰዋል።

ከትንሣዔ በኋላ የሚጠብቀን ሕይወት በዚህ ዓለም በሕይወተ- ሥጋ ሳለን በሠራነው ሥራ የሚወሰን እንደሆነ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጦልናል ብለዋል። የመጨረሻ እድላችን የተንጠለጠለው እምነትን ተከትለን በምንሠራው ሥራ እንደሆነ አባ ማቲያስ አጽንኦት ሠጥተዋል።

ዛሬ እምነትና ሥነ- ምግባር ከሰው አዕምሮ በእጅጉ እየራቁ መምጣታቸውን ተከትሎ ሕይወት መራራ ለመሆን እየተገደደች ነው ያሉት ብጹዕ አባ ማቲያስ፤ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በእምነትና ሥነ-ምግባር እየተመሩ ፣ በደልን በይቅርታ እየዘጉ፣ እስከ ጋብቻ በሚዘልቅ ባህለ-ዕርቅ ደምን እያደረቁ በወንድማማችነት ፍቅር ተስማምተው በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት መኖራቸውን አስታውሰዋል። አሁን አሁን እያሳዩ ያሉት መለያየት ፣ መጣላት፣ እርስ በእርስ መገዳዳል ታላቅናቸውን የማይመጥን እንደሆነ ገልጸዋል።

በእርቅ፣ በይቅርታና በውይይት ችግሮችን መፍታት እየተቻለ መጨካከንን እንደመፍትሄ መውሰድ ተገቢ አለመሆኑንም አስገንዝበው፤ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ሸምጋይ እና ተሸምጋይ ሆነን ችግሮቻችንን እንፍታ ሲሉ አሳስበዋል።

‹‹ መሣሪያ አንስታችሁ እርስ በእርስ በመገዳደል ላይ የምትገኙ ወገኖች ቆም ብላችሁ በማሰብ ሰላም እና ዳቦ አጥቶ ለተቸገረው ሕዝባችሁ ስትሉ ለሰላማዊ መፍትሄ እድል ስጡ ›› ሲሉ ብጹዕነታቸው ጥሪ አስተላልፈዋል። ‹‹ገዳዩን መሣሪያ አስቀምጣችሁ በሃይማኖት፣ በአንድነት፣ በስምምነትና በጭንቅላት ኃይል ሰላምን እንድታመጡ ስትል ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁእ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ የትንሣዔ በዓልን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ፤ ትንሣዔ ሁሉንም ነገድ፣ ሁሉንም ቋንቋ ፣ ሁሉንም ባህል ወደ አንድ ያመጣዋል፤የጎደለውንም ይሞላል ሲሉ ተናግረዋል።

የትንሣዔው የምስራች ከምንም በላይ የምርምር ውጤት ሳይሆን የእምነት ፍሬ መሆኑን ማስተዋል ያሻል ያሉ ሲሆን፤ ትንሣዔው ደግሞ ሰውን በሙሉ በድጋሚ ወደ አንድ ማምጣቱን ያሳየናል ሲሉ ገልጸዋል።

ብዙ የሚያሳዝኑ ነገሮች በዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ያጋጥሙናል ያሉት ብፁእ ካርዲናሉ፤ የተፈጠርንበትን ዓላማ ስንስት ወደ መሠረታዊው ዓለም የሚመልሰን ፈጣሪ ብቻ ነው፤ መከፋፈል፣ መድሎ፣ ምቀኝነት፣ ጭካኔ የተፈጠርንበት ዓለም አይደሉም ሲሉ ገልፀዋል።

በመስቀሉ እና በትንሣዔው እግዚአብሔር እራሱን ከዓለም ጋር አስታርቋል፤ቅዱስ ጳውሎስም የማስታረቅን ሚስጥር በሰፊው አስተምሯል ያሉት ብፁእ ካርዲናሉ፤ በምድር ላይ ያሉ ውብ ነገሮች እውነተኛውን ውበት የሚላበሱበት በትንሣዔው ብርሃን ነው ብለዋል።

የተስፋ ጭላንጭል ደምቆ የወደፊቱን የሚገልጠው የእምነት ብርሃን ጠቢባንን የሚወልደው በትንሣዔ ብርሃን ነው፤ ቅዱሳት መፃሕፍት ስናነብና ስናሰላስል በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ ብርሃን የምናይበት ወቅት ያስፈልጋል።

የሰውን ልጅ ታሪክም ሆነ የራሳችንን ታሪክ እንዲሁም በክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ ብርሃን ልንቃኘው ያሻል፤ በዚያን ወቅት አዲስ መረዳትን እናገኛለን፤ዘመናችንን በልዩ ብርሃን እንረዳለን፤ ለሕይወትም የምንሰጠው ትርጉም ሙላትና በረከት ይኖረዋል ብለዋል።

በዓሉን ስናከብርም አቅመ ደካሞችን በመደገፍና በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ እንደገለጹት፤ ምዕመናኑ የትንሣዔን በዓል ሲያከብር ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተጓዘበትን የትህትና፤ የመከራና የስቃይ ጎዳና በማሰብ ጭምር ሊሆን ይገባል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ቂም በቀልን፣ ተንኮል እና ሴራን በመስቀሉ እንዳመከነው፤ ምዕመኑም ከዚህ ድርጊት ለሕዝቡ የሚያካፍለው የፍቅር እና የይቅርታ መንፈስ እንዲኖር ጠይቀዋል።

ፓስተር ጻድቁ እንደተናገሩት፤ በክርስትና እምነት በህማማት ሳምንት ከሆሳእና እስከ ትንሣዔው ቀን የተደረጉ ተግባራት ለክርስትና እምነት ተከታዮች ሆነ አጠቃላይ ለሰው ልጅ ብዙ ትምህርት አላቸው። በመሆኑም ምዕመናኑ ከሆሳና እስከ ትንሣዔው በተከናወኑ ሁነቶች ንጹህ አምልኮን፤ ትህትናን እና ከፈተናዎች በኋላ ትንሣዔ መኖሩን ሊማሩ ይገባል በለዋል።

ኢሰሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበለው ለሰው ልጅ ሲል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ይህን እሴት በመከተል በበዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜ ክፉ ነገሮችን እምቢ በማለት፤ ሌሎችን በትህትና ማገልገልን፤ ለሌሎች ምህረት እና ይቅርታ ማድረግን ባህል ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምዕመኑ በትንሣዔው ብርሃን እየተመራ በዓሉን ሲያከብር የተራቡትን በማብላት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታሰሩትን በመጠየቅ፣ ለተሰደዱት እና ለሀገር ሰላም በመጸለይ መንፈሳዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ትንሣዔ ክፉ ነገሮች የተሸነፉበት ጨለማ በብርሃን የተዋጠበት፤ የክፋት ኃይላት ሁሉ አቅማቸው የደከመበት ስለሆነ፤ የጥላቻ፤ የተንኮል እና የበቀል ፍላጎት ተሸንፎ፤ ክርስቶስ በተነሳበት ጊዜ የእግዚአብሔር ብርሃን በሰዎች ሁሉ የታየበት ነው። ከዚህ መነሻነትም ትንሣዔው ሲከበር ፍትህ ላጡ፤ ለተቸገሩ ሁሉ ምህረት እንዲደረግ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚገኙ ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን እንዲሁም፤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለ2017 ዓ.ም ለጌታችን እና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣዔ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም የሃይማኖት አባቶቹ በሀገራችን ኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለሚኖሩ ወገኖች፣ የሀገርን ዳር ደንበር ለማስከበር በየጠረፉ ዘብ ለቆሙ፣ ታመው በአልጋ ላይ ላሉና በሆስፒታል ለሚገኙ፣ በማረሚያ ቤት ላሉ የሕግ ታራሚዎች፤ በትንሣዔ የሕይወት መንገድን ያሳየን ጌታችን አምላካችን እና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ2017 ዓ.ም በዓለ ትንሣዔ በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ኢያሱ መሰለና አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You