‹‹ተባባሪ›› ሕዝብ ግንኙነቶች

ዝርዝር ነገሩን እንተወውና ‹‹የሕዝብ ግንኙነት›› ማለት በጥቅሉ፤ አንድን ተቋም ከሕዝብ ጋር የሚያገናኝ ማለት ነው:: ተቋሙ ከሕዝብ ጋር የሚገናኝበት እና ሕዝብ ከተቋሙ ጋር የሚገናኝበት ማለት ነው:: ሚዲያዎች ደግሞ የሕዝብ ናቸውና የአንድ ተቋም ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ከሚዲያዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው:: ተቋሙን የተመለከቱ መረጃዎች ወደ ሚዲያ(ሕዝብ) የሚደርሱት በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው በኩል ነው::

በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋማዊ አሠራር ይልቅ፣ ከሕግና መርህ ይልቅ… ግለሰባዊ ባህሪ ጎልቶ ይታያል:: ለእዚህም ነው ለአንድ ተቋም አንድ የሥራ ኃላፊ ሲሾም ወይም ሲመረጥ ‹‹ምን አይነት ሰው ነው?›› የሚባለው:: የተቋሙን መተዳደሪያ ሕግና ደንብ ከማጥናት ይልቅ የኃላፊው ግለሰባዊ ባህሪ ይጠናል:: ‹‹ደህና ሰው ነው አሉ!›› ‹‹ኧረ ክፉ ሰው ነው አሉ!›› የሚሉ ገለጻዎች ይደረጋሉ:: ይሄ ማለት ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ወይም ባለጉዳዮችን የሚያስተናግደው በተቋሙ መርህ ሳይሆን በሰውዬው መልካም ፈቃድ ይሆናል ማለት ነው::

ወደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እንመለስ::

ጋዜጠኞች እርስ በእርስ መረጃ ሲለዋወጡ፣ የእዚህን ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስልክ ስጠኝ ሲባባሉ፤ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያውን ሰውዬ ግለሰባዊ ባህሪ ጨምረው በመናገር ነው:: ‹‹ስልክ አያነሳም፣ እንዲህ ሲሉት አይወድም፣ በእንዲህ አይነት ሰዓት ደውልለት፣ ባህሪው እንደዚህ ነውና እንዲህ አድርግለት….›› የሚሉ ነገሮች ይነገራሉ:: እንግዲህ ልብ በሉ! የሕዝብ ግንኙነትን የሚያክል ኃላፊነት ይዞ ባለጉዳይን የሚያስተናግደው ግን በግል ስሜቱ ሁኔታ ነው:: በወጣቶች ቋንቋ ‹‹ሙድ›› ሲመጣለት ነው ማለት ነው:: እንዲህ አይነት ግለሰባዊ ባህሪዎች በተደጋጋሚ ያየናቸው ናቸው::

ባለፈው ሳምንት መረጃ ለማግኘት ወደ አንድ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ስልክ ደወልኩ:: ‹‹ይሄን የሚመለከተው እገሌ ነው›› እያሉ አንዱ የሌላ ሰው፣ አሁንም አንዱ የሌላ ሰው ስልክ እየሰጡኝ ይመለከተዋል የተባለው ላይ ደረስኩ:: ስደውል አያነሳም:: በሥራ መደራረብ ምክንያት፣ በስብሰባ ምክንያት…. ስልክ ማንሳት የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ስለሚኖሩ ማንነቴን እና ጉዳዬን በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ላኩለት:: መልስ አልሰጠኝም:: ምናልባት የጽሑፍ መልዕክትም ለማየት የማይቻልበት ሁኔታ ስለሚኖር ይህንንም ከግምት አስገባሁ::

በተለመደው የሥራ ሰዓት ከምሽት 11፡00 በኋላ መደበኛ ሥራ የሌለበት ነውና ከ11፡30 በኋላ ደወልኩ:: አሁንም አይነሳም:: በነገው ጠዋት መደበኛ ሥራ ሳይጀምር በሚል 2፡30 አካባቢ ደወልኩ:: አሁንም አያነሳም:: ስህተት የሠራሁት ለካ ማንነቴን እና ጉዳዬን በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ማሳወቄ ነው:: ለምን እንደፈለኩት ስላወቀ ማንሳት አልፈለገም:: ከብዙ መደጋገም በኋላ አንስቶ ‹‹ምንድነው በላይ በላይ እየደወልክ የምትጨቀጭቀኝ?›› አለና በቁጣ ተናገረኝ:: ሌላ የተደወለ ቁጥር ጠቅሶ ‹‹አንተ ነህ በ….. የደወልክ?›› አለኝ:: በሌላ ስልክ ይደውላል ብሎ የሌሎችን ሰዎችም እያነሳ አልነበረም ማለት ነው:: ይህ ሰው ስልክ የማያነሳው ሆን ብሎ ነበር ማለት ነው::

ይሄ እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ ተቋማዊ አሠራር ኢ-ሥነ ምግባራዊነት ነው:: ደግሞ እኮ የምፈልገው መረጃ የተቋሙን ችግሮች የሚገልጽ ሳይሆን እንዲያውም ለገጽታ ግንባታ የሚሆን ነው:: ግን ‹‹ሙዱ›› አይደለምና መስጠት አልፈለገም ማለት ነው::

ብዙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና የዘርፍ ኃላፊዎች መረጃ ላለመስጠት ሰበብ ይፈጥራሉ፤ ይሄ የለመድነው ነው:: ዳሩ ግን ሥነ ሥርዓትና በጨዋነት ሰበብ ይፈጥራሉ እንጂ ቢያንስ አይሳደቡም:: እንዲህ አይነት ኢ-ሥነ ምግባራዊነት የሚያሳዩት እጅግ ጥቂቶች ናቸው:: እንዲያውም የእነዚህ ፍፁም ተቃራኒ የሰለጠነ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ገጠመኝ ልናገር::

ከወር በፊት ይመስለኛል የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከት አንድ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጋር ደወልኩ:: ጉዳዬን ካስረዳሁ በኋላ የሚመለከተውን መረጃ አጣርቶ እንደሚደውልልኝ ነገረኝ:: ብዙ ጊዜ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ‹‹እኔ እደውልልሃለሁ!›› ካሉ ሰበብ እየፈለጉ እንደሆነ ለምደነዋል፤ ምክንያቱም እንኳን ራሱ አስቦ መደወል ይቅርና እኛ ደውለንም ቶሎ ስለማይሳካ ማለት ነው::

ይህ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ግን በነጋታው ጠዋት ራሱ ደወለልኝ:: ሥራውን ጠንቅቆ ያውቃል ማለት ነው:: እያንዳንዷን የሥራውን ዝርዝር ጊዜ ያስይዛል(Scheduled ያደርጋል) ማለት ነው:: እኔ ደውዬ ጉዳዬን ስነግረው፤ ‹‹ከዚህ ተቋም፣ እንዲህ አይነት መረጃ፣ በእዚህ ሰዓት…›› ብሎ ማስታወሻ ይዟል ማለት ነው:: በያዘው የሥራ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ራሱ ደወለ:: ተቋማዊ ኃላፊነት እና ግለሰባዊ ብቃት ማለት እንደዚህ ነው::

አስቸጋሪ የሆኑትን ልናገር ብዬ እንጂ ብዙ ቅን እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ባለሙያዎች መኖራቸውን የማላውቅ ሆኜ አይደለም:: ቅን እና ኃላፊነቱን የሚወጣ ማለት የግድ መረጃውን የሚሰጥ ማለት አይደለም:: ቢያንስ መረጃውን መስጠት እንደማይችል በቅንነት መናገር ማለት ነው:: ቁርጥ ያለውን ቶሎ ማሳወቅ ማለት ነው::

አንዳንድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃ መስጠት ግዴታቸው አይመስላቸውም፤ የተቀመጡበት ኃላፊነት አይመስላቸውም:: ለጠየቃቸው ሰው መረጃ የሚሰጡት ‹‹ልተባበርህ!›› በሚል ነው:: ይህ ልማድ በመሆኑ ጋዜጠኛም ሆነ ሌላ አካል መረጃ ሲፈልግ ‹‹እባክህ ተባበረኝ!›› በሚል እየሆነ ነው:: ተቋማዊ ግዴታ መሆኑ ቀርቶ ግለሰባዊ ክፋትና ቸርነት ይሆናል ማለት ነው:: ‹‹ውለታ ልዋልልህ!›› እንደማለት ይሆናል ማለት ነው:: የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የደዋዩ ቆሌ ካላማረው ገላምጦና ተቆጥቶ ሊዘጋበት ይችላል::

ይሄ ማለት ግን ከጋዜጠኞችም ችግር የለም ማለት አይደለም:: ማንነትን እና የሚፈልጉትን ጉዳይ በግልጽ ቶሎ ማሳወቅ የግድ ነው፤ ይህንን ማንም ያደርገዋል:: ብዙዎች ላይ የምታዘበው ነገር ግን አጉል አፋጣጭ እና መርማሪ ጋዜጠኛ ለመምሰል ‹‹ግዴታህ እኮ ነው!›› በማለት ከቁጣ የሚጀምሩ ጋዜጠኞች አሉ:: ሲጀመር በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንድ ኃላፊ መረጃ መስጠት ግዴታው አይደለም፤ ሲቀጥል ግዴታው ቢሆን እንኳን መጠየቅ ያለበት በትህትና እና በሥነ ሥርዓት ነው:: ግዴታህ ነው የሚለውን መንገር ካስፈለገም ቢያንስ ‹‹መረጃ የመስጠት ግዴታ የለብኝም›› ካለ በኋላ ይሻላል::

አንድ ተቋም የትኛውንም የተጠየቀውን መረጃ ሁሉ ይሰጣል ማለትም አይደለም:: ይህ እንደ ተቋሙ ባህሪ ይወሰናል:: ይህ የሚሆነው ግን በሕግና ደንብ እንጂ በግለሰቡ የግል ‹‹ሙድ›› አይደለም:: መሰጠት ያለበትን እና የሌለበትን መረጃ ጠንቅቆ ያውቃል:: የተጠየቀው መረጃ መሰጠት ያለበት መሆኑን ከተጠራጠረ የበላይ ኃላፊውን መጠየቅ አለበት:: መሰጠት የለበትም የሚል መልስ ከተሰጠው ለጠየቀው አካል ‹‹በእዚህ ላይ መረጃ አንሰጥም!›› ብሎ መናገር ነው:: በእዚያ ጉዳይ ላይ ለምን መረጃ አልሰጣችሁኝም ብሎ የሚከስም ሆነ የሚወቅስ ጠያቂ አይኖርም፤ የተቋሙ አሠራር አይፈቅድም ከተባለ አይፈቅድም ነው፤ መረጃ ሁሉ እንደማይሰጥ ግልጽ ነው:: ዳሩ ግን ለሕዝብ መታወቅ ያለበትን ነገር ሁሉ ‹‹አንሰጥም›› ይላሉ::

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች መረጃ መስጠት የተቀመጣችሁበት ኃላፊነት እና ተቋማዊ ግዴታ እንጂ ትብብር አይደለም:: በተቋማዊ መርህ እንጂ በግለሰባዊ ስሜት አትመሩ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You