ዘመናዊ መሳሪያ በመታጠቁ ሰራዊቱን አልፈራም፤ 500 የግብፅ ወታደሮችን ከአልጋ ላይ አስተኝቷል። የአገር መሪዎችን አልራራላቸውም የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችን ከባድ የጤና ቀውስ ውስጥ ከቷል። የቤተ መንግስት በር ሲያንኳኳ ከቶውንም ማንንንም አልፈራም። ድኸዎችን ሲያመሰቃቅል አንዳችም ተው ያለው የለም።
ኮረና ቫይረስ ዓለምን በአንድ የጭንቀት ቋት ውስጥ ያስገባ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክፉ ደዌ ሆኗል። በዚህ በሽታ አስካሁን ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተጠቅተዋል። ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ከበሽታው ሲያገግሙ 100ሺ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከኮረና ቫይረስ አገግመው መደ መደበኛ ሕይወታቸው አሊያም ደግሞ አኗኗራቸው የተመለሱት ሲሆን ይህን ክስተት ስሜት በሚነኩ ቃላት እየገለፁት ነው። በአማካይ ከ10 እስከ 24 ቀናት በለይቶ ማቆያ የሰነበቱበትን ቀን ደግሞ ከመቼውም በላይ እንደማይረሱት ይነገራሉ። አጠገባቸው የነበሩ ወዳጆቻቸው፣ ጓደኛቸው አሊያም ደግሞ የአገራቸው ሰው ከአጠገባቸው እስከ ወዲያኛው ሲያሸልብ እየተመለከቱ የሥነ ልቦና ቀውስ አጋጥሟቸዋል። ለራሳቸው በመዳናቸው ሲደሰቱ አጠገባቸው ያለው ሰው እስከ ፍፃሜው ሲያሸልብ ልባቸው አብሮ አሸልቧል። ነገሮች በቅጽበት በሚለዋወጡባት በዚህች ዓለም ብዙ ያልተጠበቁ ውሳኔዎችና ክንውኖችም እየተስተዋሉ ነው። ምንም እንኳን ኮረና ቫይረስ መድሃኒት ባይገኝለትም በርካቶች ከበሽታው እያገገሙ ሲሆን፤ ‹‹ትረፊ ያላት ነብስ›› እንደሚባለው ወጋቸውን ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እያጋሩ ነው።
አንጀላ እድሜዋ 27 ሲሆን አሜሪካ ሀገር ዋሽንግተን ዲሲ የምትኖርና ስራዋም ሆስፒታል ውስጥ ነበር። አንጀላ የ34 ሳምንት እርጉዝ ነች ልትወልድ ትንሽ ቀናቶች ቀርተዋት ነበር፤ ነገር ግን ሆስፒታል ውስጥ ስትሰራ ኮሮና ቫይረስ ይይዛታል፤ ወዲያው እዛው ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ማድረግ ትጀምራለች። ህመሟም እየባሳ ይሄዳል። መተንፈስም ያቅታታል፣ ሳንባዎቿ እየደከሙ ይመጣሉ፤ ዶክተሮች ቶሎ ብለው በመተንፈሻ መሳሪያ ሰጥተዋት በእርሱ እየታጋዘች መተንፈስ ትጀምራለች። እራሷን ሳታውቅ ለ10 ቀን ከፍተኛ ህክምና ክፍል ውስጥ ትቀመጣለች። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ አንጀላ እራሷን ምንም ሳታውቅ ልጇን ትወልዳለች።
ከ10 ቀን በኋላ ትነቃለች። ወዲያው ሆዷን ስታየው ሆዷ ወደ ውስጥ ገብቶ ታየዋለች። እርጉዝ ነበርኩኝ ልጄስ ስትል፤ አይዞሽ ልጅሽን በሠላም ተገላግለሻል ይሏታል። አንጀላ ልጇን ስትወልድ ባታያትም ልጇ ጤነኛ ሆና፤ በሆስፒታል ውስጥ ህክምናዋ እየተከታተለች ትገኛለች። ሙሉ በሙሉ ተሽሏት ከሆስፒታል ወጥታ ቤቷ ቁጭ ብላ ከልጇ ጋርም ለመገናኘት እየጠበቀች ትገኛለች ሲል ሲኤን ኤን የወሬ ምንጭ የችግሩን ውስብስነት ብሎም ደግሞ የሰዎችን ተስፋ በአጭር ዘገባው ያስዳስሰናል።
ኮረና በኢትዮጵያም ውስጥም ዳዴ እያለ ነው። በርካቶዎችም በቫይረሱ እየተጠቁ ሲሆን ሕይወታቸውን የተነጠቁም አሉ። ወዲህ ደግሞ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን አውቀው ህክምና ያደረጉና በጤናቸው ላይ መሻሻል ያሳዩ ሰዎችም በርካቶች ናቸው። ከኮቪድ- 19 ያገገሙት የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና የፋርማሲ ባለሙያ አቶ ዳግማይ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የችግሩን አስከፊነትና በእነዚህ ቀናት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው እንደታወቀ የተወሰዱት አዲስ አበባ ወደ የሚገኘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲሆን፤ እዚያ ተኝተው በሚታከሙበት ወቅት ልጃቸውን ማየታቸውን የፈጠረባቸውን ስሜት ነበር ለቢቢሲ ያጋሩትአቶ ዳግማይ በቀለ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀውእኚህ የ61 ዓመት አዛውንት አዲስ አበባ በሚገኘው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው በአሁን ጊዜ ከቫይረሱ በማገገማቸው አዳማ ወደ ሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተመልሰዋል።
የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳግማይ፣ ቫይረሱ እንዴት ሊይዛቸው እንደቻለ እንደማያውቁ ይናገራሉ፤ ነገር ግን አንዳንድ ምልክቶችን በማየታቸው ራሳቸውን ለመለየት ስለፈለጉ ከቤተሰባቸው ርቀው ሆቴል ተከራይተው መቀመጣቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል“ራሴን ስለጠረጠርኩኝ ከዚህ እስከምወጣ ማንም ሰው እኔ ጋር እንዳይመጣ፤ ከመጣም የእጅ ጓንትና ጭምብል አድርጎ ይምጣ በማለት ለሆቴሉ ሠራተኞች ጭምር ተናግሬ ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ አውግተዋል። የኮቪድ-19 ምልክቶች የተባሉትን ራሳቸው ላይ ማየት እንደጀመሩ አዳማ ከተማ ወደሚገኙ የጤና ተቋማት መሄዳቸውን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ዳግማይ ከሆነ ማንም ቫይረሱ አለብህ ሊላቸው አልቻለምከዚያም ይላሉ አቶ ዳግማይ ‹‹ወደ ጤና ሚኒስቴር ደውዬ ያመኛል ነገር ግን የሚመረምረኝ ሰው አላገኘሁም ብዬ ነገርኳቸውከጤና ሚኒስቴር ወደ ኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከዚያም ወደ አዳማ ከተማ ተደወለ›› በማለት በወቅቱ እንዴት መመርመር እንደቻሉ ያስረዳሉአቶ ዳግማይ በቀለ የኮቪድ-19 በማስመልከት አዳማ ላይ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ነበሩመጀመሪያ ደረቅ ሳል ያስለኝ ነበር የሚሉት አቶ ዳግማይ በመቀጠልም ጉሮሮዋቸው ውስጥ የመብላት የማሳከክ ስሜት እንደጀመራቸው ይናገራሉ።
“ኮሮና ይሆን ብዬ በቀልድ ሳወራ ሰዎች አይ አይደለም ሳይነስ ነው የተነሳብህ እንጂ ኮሮና አይደለም ይሉኝ ነበር።” በመቀጠልም ከባድ ራስ ምታት እንደጀመራቸውና ሰውነታቸውም መደከም እንደጀመረ ያስታውሳሉ“ትንሽ ያሳሳተኝ የሰውነቴ ሙቀት ረዘም ላለ ጊዜ ከ36 በልጦ አያውቅም፤ ሁልጊዜም ከሦስት እስከ አራት በሚሆን ሰዓት ልዩነት ውስጥ የሰውነቴን ሙቀት እለካ ነበርከዚያ በኋላ አንድ ቀን ማለዳ ስለካ ሙቀቴ 38 ሆኗል፤ በዚህ ጊዜ እርሱ ኮሮና ነው ብዬ መያዜን ተጠራጠርኩኝ።” ከዚህ በኋላ የድጋፍ አሰባሳቢው ኮሚቴ ስብሰባ መካፈል ማቆማቸውን ይገልፃሉ
የኤካ ኮተቤ ቆይታና ድንጋጤ
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች የሚቆዩበትና ህክምና የሚከታተሉበት ሆስፒታል ነውበዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከ20 ቀናት በላይ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ዳግማይ በሆስፒታሉ ውስጥ ከ10 ቀን በላይ ከባድ ህመም ላይ እንደነበሩ ለቢቢሲ አማርኛው ተናግረዋል“የህክምና ባለሙያዎችም የሜካኒካል ቬንትሌተር ገጥመውልኝ እና የተለያዩ መድኃኒቶች ሲሰጡኝ ነበር” በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ለሰባት ወይንም ለስምንት ቀናት ምግብና ውሃ እንዳልወሰዱ ከወሰዱም ደግሞ ያስመልሳቸው እንደነበር ያስረዳሉአቶ ዳግማይ በከባድ ህመም ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ባለቤታቸውና የ14 ዓመት ወንድ ልጃቸው በበሽታው ተይዘው ወደ ሆስፒታሉ መጡ“ለሦስትና ለአራት ቀን ደብቀውኝ አልተገናኘንም ነበር” የሚሉት አቶ ዳግማይ “እኔም በወቅቱ ከባድ ህመም ላይ ነበርኩ” ብለዋልእርሳቸው ወደ ሆስፒታል ከገቡ ከሶስተኛው ቀን በኋላ ወደ ባለቤታቸው በመደወል መያዛቸውን መስማታቸውን ይገልፃሉበዚህ ወቅት ስለልጆቻቸው ጤንነት የጠየቁት አቶ ዳግማይ ሁሉም ደህና መሆናቸው እንደተነገራቸው ገልፀዋልነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ባለቤታቸው የተኙበት ክፍል ድረስ በመምጣት ሲያናግሯቸውና እርሳቸውም መያዛቸውን ሲግሯቸው አዘኑ።
ወንድ ልጃቸው በበሸታው እንደተያዘ ያልተነገራቸው አቶ ዳግማይ፤ ልጃቸውን ሆስፒታል ውስጥ በማየታቸው ከባድ ስሜት እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ‹‹ከአምስት ቀን በኋላ ወደ ንጽህና መስጫ እየሄድኩኝ ልጄን ኮሪደር ላይ አየሁት በጣም ደንግጬ ጮህኩና ወደኩኝ፤ ከዚያ በኋላ ደብቀንህ ነው እንጂ እዚህ ከገባን አንድ ሳምንት ሆኖናል አሉኝ›› ይላሉ።
አቶ ዳግማዊ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸው በአሁኑ ሰዓት አገግመው አዳማ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመልሰዋልበእርግጥ አቶ ዳግማይ አሁንም በመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ እንደሚተነፍሱ ነግረውናል“እንደኔ ራሱን የሚጠብቅ ሰው የለም” የሚሉት አቶ ዳግማይ ሕዝቡ ስለኮሮና ቫይረስ በደንብ ማወቅ አለበት ሲሉ ይመክራሉየዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የሚሰጡትን ምክር መስማት ያስፈልጋል ሲሉም ያብራራሉእጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ከተቻለ የአፍ መሸፈኛ ማድረግ አለብን በማለትም መጨባበጥን ማስወገድና ርቀትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ‹‹ግዴታ የሌለባቸው ቤት መቆየት አለባቸው፤ ከቤት መውጣት አያስፈልግም፤ ቤት ሲሆኑም ደግሞ አልጋ ላይ ተኝቶ ቴሌቪዥን ማየት ብቻ ሳይሆን መጽሀፍ ማንበብ፤ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋልእኔ ራሴ አሁን ጠዋት ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ያህል ስፖርት ከልጄ ጋር እሰራ ነበር›› ሲሉ ልምዳቸውን ያጋራሉበመጨረሻም ‹‹ለራስ የምናስብ ከሆነ፣ ለሕዝብም እናስባለን፤ ይህንንም መጥፎ ወቅት አብረን እንሻገራለን፤ አገራችንንም እንጠብቃለን” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር