‹‹ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አያድርም›› የሚል አባባል አለን። በበዓል ሰሞን ይህ አባባል ይደጋገማል። መልዕክቱም፤ ጎረቤት ይህን አደረገ ብለን ያለአቅማችን አናድርግ ለማለት ነው። ጎረቤት በግ የመግዛት አቅም ቢኖረው፤ የእኛ አቅም ደግሞ ዶሮ የመግዛት ከሆነ ዶሮ ይበቃል ለማለት ነው።
ይህ አባባል ለዘንድሮው የፋሲካ በዓል ተገቢ መልዕክት አለው። የዘንድሮው የፋሲካ በዓል በለመድነው ወግና ባህላችን የሚከበር አይደለም። ጎረቤት ተጠራርቶ በመሰባሰብ የሚከበር አይደለም። እገሌ ሳይጠራኝ፤ እነ እገሌን ሳንጠራቸው የሚያባብል አይደለም። በበዓል ሁኔታ ደግሞ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ ነው። የሚነካኩ ዕቃዎች ይበዛሉ፤ እነዚያን ዕቃዎች መቀባበል ይበዛል። ስለዚህ ለዚህ ዓመት ይቅርብን! በዓሉን በቤታችን ሆነን እናክብር።
በቤታችን ጥሩ በዓል ማሳለፍ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን የሚቀጥሉትን ዓመታት በዓል በሰላምና በጤና ለማክበር እንበቃለን። ለዚያ ያብቃን። ለዘንድሮው ግን ስለበዓል አጠቃላይ ድባብ በመገናኛ ብዙኃን እናያለን፣ እንሰማለን፣ እናነባለን።
በዓል በጣም ደስ የሚለው ሰሞነኛው ነበር። ለበዓሉ ዝግጅት የሚደረገው ሽር ጉድ፣ ከወትሮው በተለየ ቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ነገሮች፤ በተለይ የዋዜማ ዕለት ያለው ድምቀት በጣም ይናፍቃል። በዋዜማ ወዳጅ ዘመድ ይመጣል፤ ከእነርሱ ጋር የሚኖረው ጨዋታ ይደራል።
የበዓሉ ዕለት ግርግር ስለሚበዛ እንደዋዜማው አይሆንም፤ በዚያ ላይ ደግሞ አንድ ነገር ገና ወደፊት ሆኖ በተስፋ ሲጠበቅ ነው ደስ የሚለው። ለበዓል ከሚመጣው ዘመድ ጀምሮ ለልጆች አዳዲስ ልብስ ይገዛል፤ ልጆችን በጣም የሚያጓጓው ይሄ ይመስለኛል።
ሌላው የበዓል ማግስት ነው። የበዓል ማግስት እንዲውም ቅር ቅር እያለን የምንሄድበት ነው፤ ምክንያቱም የመጣው ወዳጅ ዘመድ ለመሄድ ይነሳሳል። በተለይ አብዝተው ለሚጠጡና ለሚበሉማ እንዲያውም ህመምም አለው። ለዚህ እኮ ነው የጤና ባለሙያዎች ሁል ጊዜ ምክራቸውን የሚለግሱን። በዓል ማግስት ከተነሳ አይቀር የመስሪያ ቤቶች እና የትምህርት ቤቶች መዘጋት ሁልጊዜ የተለመደ ነው። ካላንደር የማይዘጋው በስምምነት የተደረገ ውል ይመስል ወደ መስሪያ ቤት ወይም ትምህርት ቤት ዝር የሚሉ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ዘንድሮ ደግሞ ሁሉም ነገር በህጋዊ መንገድ (በችግር ምክንያት) ተዘጋ።
ተማሪዎች ‹‹ለምን አትሄዱም›› ተብለው ሲጠየቁ ‹‹አስተማሪዎች አይገቡም!›› ይላሉ፤ አስተማሪዎችም በአለቆቻቸው ለምን እንደማይገቡ ሲጠየቁ ‹‹ተማሪ የለም›› ይላሉ። የበዓል ሰሞን ከዋዜማ ጀምሮ በዕለቱም በማግስቱም ይዘጋል ማለት ነው። ቢኖር እንኳን አንድ ወይም ሁለት ክፍለ ጊዜ ብቻ ነው። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ወደ መደበኛው ትምህርት የሚገባው። በመስሪያ ቤቶችም ተመሳሳይ ነው፤ ሰራተኞች አይገቡ፣ ባለጉዳዮች አይሄዱም። እስኪ ዘንድሮ ከቤት አለመውጣት ተመክሯልና አለመሄድን እንተግብረው!
በነገራችን ላይ ፋሲካ የሚለው ቃል ትርጉሙ ይሄ ዛሬ የምናከብረው የትንሳኤ በዓል ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ተደራቢ ትርጉሞችም ተሰጥቶታል። አንድ ነገር የተትረፈረፈ ከሆነ ፋሲካ ሆነ እኮ ይባላል፤ አስደሳች የሆነ ነገርም ፋሲካ እየተባለ ይገለጻል።
ወደበዓሉ አከባበር ስንመጣ እንግዲህ አከባበሩ የተለያየ ነው። አከባበሩ የተለያየ ነው ሲባል እንደ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል ተንታኞች ከሌሎች አገራት ጋር እያነጻጸርን ማለት አይደለም። የበዓሉ አከባበር የሚለያየው እንደየሰዉ አቅም ነው።
በዓል በመጣ ቁጥር ‹‹ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አያድርም›› የሚለው አባባል ይደጋገማል፤ የሚደጋገመው ግን በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ነው። በተግባር ያለውን አባባል ካየነው ‹‹ሰው እንደ ጎረቤቱ እንጂ እንደቤቱ አያድርም›› የሚለው ነው።
ለማንኛውም ‹‹ሰው እንደጎረቤቱ እንጂ እንደቤቱ አያድርም›› የሚለው ያመዝናል። ብዙ ሰዎችን ልብ ብላችሁ ሰምታችኋል? ‹‹እንዲያው ይህን ባናደርግ፣ ይህ ባይገዛ…ጎረቤትስ ምን ይላል!›› የሚሉ እኮ አሉ። ያ ማለት ከእነርሱ ፍላጎት ይልቅ ጎረቤት አድርገዋል እንዲላቸው ታስቦ ነው ማለት ነው። ለነገሩ አልፈርድባቸውም፤ ችግር እኮ ነው ጎበዝ!
እኔ ካልቻልኩ ወይም ካልፈለኩ ብለህ ብትተወው የት ትውላለህ? በዚያ ላይ የአዲስ አበባ ቤት ደግሞ ተደጋግፎ ያለ ነው፤ ስትወጣ ስትገባ ከመታየቱም በላይ የጎረቤት ድስት ሲንተከተክ ሁሉ የሚሰማበት ነው። ቤትህ ዝም ብለህ ቁጭ ብትል ከጎረቤት ያለው ነገር ይሰማሃል፣ ይታይሃል። አይ ከዚህማ ወጣ ማለት አለብኝ ብለህ ብትሄድ መንገዱ ሁሉ ጸጥ ብሎ አንተ ብቻ ልትሆን ትችላለህ። ስለዚህ ጎረቤት ለመምሰል ተብሎ ይደረጋል።
የበዓል ሰሞን ሌላው ትዝታ (ዘንድሮ እንግዲህ በትዝታ ነው የምናሳልፈው) የሥጋ ሰልፍ ነው። ቆይ ግን ያ ሁሉ ሥጋ ሊገዛ ነው ወይስ ለጎረቤት ይምሰል ተሰልፎ ነበር ለመባል ነው? አንዳንዱ እኮ ሰልፉ ላይ ቆሞ ‹‹ኧረ እረፈደብኝ፤ ገና በግ አርዳለሁ፣ ብዙ እንግዳ ስለሚመጣብኝ ለመጨመሪያ ብየ እንጂ›› የሚልም አለ፤ ለነገሩ ለጎረቤት ይምሰል ከተሰለፍኩ የፈለገኝን መዋሸት ነው። ግን እንዲህ አድርጎ ሰልፉ ሲደርሰውስ? ቀላል ነው፤ ሥጋውን አየት አድርጎ ‹‹እኔ እገሌ ነኝ እንዲህ አይነት ሥጋ የምወስደው!›› ብሎ መተው ነው (አህያ የሌለው በቅሎ ይንቃል እንደሚባለው)።
በነገራችን ላይ ሰልፉ የጾመው ብቻ አይደለም፤ በተለይ የጾም መያዣ ወቅት ላይ የሚጾመውም የማይጾመውም አብሮ የሚጋፋ ለምንድ ነው? የማይጾመው እኮ በነጋታው መውሰድ ይችላል። እያልኩ ያለሁት ጾሙ ከሚገባበት እምነት ውጭ ያሉትን እንዳይመስላችሁ። የእምነቱ ተከታዮችን ነው። ለምሳሌ የሁዳዴ ጾም መያዣ የኦርቶዶክስ አማኞች ነው፤ ኦርቶዶክስ ሆኖ የማይጾም የዚያን ቀን አብሮ ይሰለፋል። የበዓሉ ድባብ ይናፍቀዋል ማለት ነው እንግዲህ። ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ሥጋ ሲበላ ቆይቷል፤ ግን ዛሬ እንደ አዲስ አብሮ መሰለፉ የሆነ የሚሰጠው ደስታ ይኖራል ማለት ነው፤ በቃ በዓል ነዋ!
ደግነቱ የፋሲካ በዓል ያለፈውን የጾም ጊዜ ያካክሳል። 40 ቀን ሙሉ አርብም ረቡዕም ሥጋ ይበላል። ለዚህ ይሆን እንዴ ‹‹ፋሲካ›› የሚለው ቃል የደስታና ፈንጠዝያ ምሳሌ የተደረገውና ቃሉ ለሌላም ደስታ ለበዛበት ነገር ምሳሌ የሆነው?
እና በዓሉን እንዴት እያከበራችሁት ነው? በግ ያለው በበጉ፣ ዶሮም ያለው በዶሮው፣ ዶሮም የሌለው በጆሮው ሙዚቃ እየሰማ ሊሆን ይችላል።
የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው ነገር እንግዲህ ከላይ የተገለጹት የበዓል ድባቦች የማይከወኑ መሆኑ ነው። በየዓመቱ ‹‹የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው›› የሚባል አገላለጽ አለ አይደል? ምንም እንኳን በየዓመቱ አዳዲስ ነገር ባይጠፋም የዘንድሮው ግን የምርም ይለያል።
የተባልነውን እናድርግ፤ የአብሮነት ወግና ባህላችን እንዲቀጥል ዛሬ እንራራቅ (አካላዊ ርቀት)። ዛሬ ከተራራቅን ነገ አብረን እናከብራለን።
መልካም በዓል !
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2012
ዋለልኝ አየለ