ይህን አጀንዳ በመቅረፅ እያለሁ ዩናይትድ ስቴትስ በኖቭል ኮሮና ቫይረስ እየደረሰባት ባለ ጉዳት ቻይናን በመብለጥ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ይህ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቸልታ ያመጣው ዳፋ ነው። ወረርሽኙን ለመከላከል እያንዳንዷ ሰዓት ትርጉም አላት። ይቺን ሰዓት በአግባቡ ያልተጠቀመ ምንም ያህል በኢኮኖሚ የበለጸገ ቢሆን ዋጋ ይከፍላል። በማህበረሰብ በቤተሰብ ደረጃም እንደዚሁ ነው። በአሜሪካ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሻይረሱ የተያዙ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር ደግሞ ከ22ሺህ በልጧል። በዓለማችን ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በኖቭል ኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ፤ ወደ 110 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸው አልፏል። ከሁሉም የአሜሪካ ከተሞች እንደ ኒውዮርክ የተጎዳ ግን የለም። ከ181ሺህ በላይ ኒውዮርካውያን በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ወደ 9ሺህ የሚጠጉት ደግሞ በሞት ተለይተዋል። የኒዎርክ ገዥ አንድሪው ኮሞ ( በቫይረሱ በመያዙ አስገዳጅ ወሸባ / ኳራንቲን / የገባው የCNNኑ ክሪስ ኮሞ ወንድም ) ከበርካታ ቀናት መርዶና አሳዛኝ ዜና በኋላ የምስራች ማብሰር ጀምረዋል።
ማህበራዊ ፈቀቅታን በመተግበራችን በቫይረሱ የሚሞቱም ሆነ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየቀነሰ ነው ብለዋል። የበለጸግን ፣ የዓለም የንግድ መናኸሪያ ፣ የሽርክና ገበያ እምብርት ስለሆን ፣ የደረጀ የጤና ተቋም ፣ የበቃ የነቃ የህክምና ባለሙያ ስላለን ፣ የተመድ መቀመጫ በመሆናችን ፣ ወዘተረፈ የወረርሽኙን ስርጭት ሆነ ሞት ቀነስን አላሉም። ሕዝብ በብዛት የሚሰባሰብባቸው እንደ አብያተ ክርስቲያናት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ ቴአትር ቤቶች ፣ ወዘተረፈ በአስቸኳይ አዋጅ በመዘጋታቸው ማህበራዊ ፈቀቅታውን በትክክል ስራ ላይ ለማዋል አግዟቸዋል። ይህ ደግሞ የከተማዋ ገዥ ከፍ ብለው እንደገለጹት ተስፋ የሚጣልበት ውጤት ማስመዝገብ አስችሏል። ቻይናም መጀመሪያ በውሃን ግዛት በኋላም በሌሎች ግዛቶች የአስቸኳይ ጊዜ በማወጅና የከተሞችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ቀጥ በማድረግ ሌት ተቀን በመስራቷ ዛሬ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በመቆጣጠር ለዓለም ምሳሌ ለመሆን በቅታለች። ደቡብ ኮሪያም ሆነ ሲንጋፖር በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋል የቻሉት በጥብቅ ዲሲፕሊን ማህበራዊ ፈቀቅታን፣ ምርመራንና ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች የግንኙነት ታሪክ ተከታትሎ በመለየት ( ኮንታክት ትሬሲንግ ) በመተግበር እና አስገዳጅ ወሸባ ማስገባት ላይ ትኩረት ሰጥተው በመተግበራቸው ነው።
ማህበራዊ ፈቀቅታን በጥብቅ ዲሲፕሊን የተገበሩ ሀገራት ባጠረ ጊዜ እና በውስን ኢኮኖሚያዊ ጫና ዜጎቻቸውን ከከፋ እልቂት፣ የአልጋ ቁራኛነት፣ ፍርሀትን ሽብርን ተከትሎ ከሚመጣ ስነ ልቦናዊ ቀውስ መታደግ ችለዋል። ማህበራዊ ፈቀቅታን በትክክለኛው ጊዜ ( ታይሚንግ) ያልፈፀሙት ሀገራት፣ መንግስታት ደግሞ በተቃራኒው በ21ኛው ክ/ዘ የሰው ልጅ ይገጥመዋል ተብሎ ጭራሽ በማይታሰብ ደረጃ በወረርሽኙ ክፉኛ ሲጠቁ፣ ሲረበሹ፣ ይይዙት ይጨብጡት ሲያጡ ተመልክተናል። ለማመን በሚቸግር ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው አልቀዋል፣ ታመዋል የተረፉት ደግሞ በፍርሀትና በጭንቀት እየተሰቃዩ ይገኛል። ኢኮኖሚያቸው ደቋል። ዜጎች በመንግስታቸው የነበራቸው እምነት ተሸርሽሯል። አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ ዜጎቻቸውን፣ ኢኮኖሚያቸውን ውድ ዋጋ እያስከፈሉ ካሉ ሀገራት ቀዳሚዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
በእንቅርት ላይ እንዲሉ የመሪዎቻቸው ዳተኝነት እያስከፈላቸው ባለው ዋጋ ላይ ወረርሽኙ ያስከተለው ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝና ጫና ሲታከልበት ከድጡ ወደ ማጡ ሊከታቸው ችሏል። ከረፈደ ቢሆንም ብዙዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የወረርሽኙን ፈጣን ስርጭትና ጉዳት ለመግታት ሌት ተቀን በመረባረብ ላይ ይገኛሉ። በዚህም ተስፋ የሚጣልበት ውጤት እያስመዘገቡ ነው። በተለይ ማህበራዊ ፈቀቅታን መተግበር ወረርሽኙን ለመከላከል ምን ያህል የማይተካ ሚና እንዳለው እየተመለከትን ነው። የአፍንጫ ተአፍ መሸፈኛ፣ ምርመራን፣ ወሸባን፣ የከተሞችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ከመዝጋት በላይ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ ነው። መንግስት ይሄን በመገንዘብ ማህበራዊ ፈቀቅታን እንድንተገብር ሌት ተቀን ቢለፍፍም በጀ አላልንም። ማህበራዊ ፈቀቅታን በመተግበር ወረርሽኙን ለመከላከል ሰራተኞች ከቤታቸው ሁነው እንዲሰሩ፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዘጉ፣ ምዕመናን በቤታቸው እንዲያመልኩ፣ የሕዝብ መጓጓዣዎች በግማሽ ቀንሰው እንዲጭኑ፣ የመገበያያ ቦታዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ ወዘተርፈ ሲሉ የህክምና ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ብዙኃን መገናኛዎች ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፣ የካቢኔ አባላትና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ቢወተውቱም ሰሚ ጆሮ ባለመገኘቱ የባህሪ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም። በዚህ የተነሳ መንግስት በተለመደው አሰራር ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ሲገነዘብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዷል። የዜጎች መብት ሳይገደብ ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረገው ጥረት ተገቢውን አጸፌታዊ ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ አስገዳጅ ገደብና ክልከላ ለመጣል ተገዷል።
ኖቭል ኮሮና ቫይረስን ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ወረርሽን በመሆኑ እንደ አገር የተቀናጀና የተሳለጠ የመከላከል፣ የመቆጣጠር እርምጃዎችን ለመውሰድ በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 93 (1) (ሀ) መሠረት አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማውጣት እንዳስፈለገ ያስታውቃል። በመሆኑም ማንኛውም ሰው በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሰጥ ሕጋዊ ትዕዛዝና መመሪያ የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት እና ከዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር የሚቃረኑ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ሕጎች ፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ይደነግጋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካፀደቀ በኋላ፣ የአዋጁን አፈጻጸም የሚከታተል ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሰይሟል።
ማህበራዊ ፈቀቅታን የትም ይሁን የት በጥብቅ ዲሲፕሊን ማክበር፣ ማስከበር እና ይህን ለማስፈፅም ለወጣ አዋጅና ደንብ ተፈጻሚነት ተባባሪ ተገዥ መሆን ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ መግቢያዬ ላይ በአርዓያነት የሚገለጹ ሀገራትን በመዘርዘር ያሳየሁ ሲሆን በተቃራኒው ማህበራዊ ፈቀቅታን ፈጥኖ መተግበር ላይ እግራቸውን የጎተቱ ዳተኛና ቀሰስተኛ መሪዎችና መንግስታት ደግሞ እየከፈሉት ያለ ዋጋን በየሰዓቱ በቴሌቪዥን እየተመለከትን ነው። ብልጥ ከራሱ ሳይሆን ከሌሎች ስህተት ይማራል ነውና ይትበሀሉ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለምንም መሸራረፍና መደነቃቀፍ ስራ ላይ እንዲውል የዜግነት ድርሻችንን በመወጣት ሕዝባችን ከእልቂት፣ ሀገራችን ከለየለት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በመከላከል በሀገራችን ሰማይ የረበበውን የደህንነት የስጋት ዳመና በአንድነት በመግፈፍ ከታሪክና ከትውልድ ተወቃሽነት እንዳን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳይን )
fenote1971@gmail.com