የኮሮና ቫይረስ በሽታ በቻይና ሃገር ከታየ ጀምሮ አፍሪካን ጨምሮ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ በርካታ የዓለም ሃገራት እየተስፋፋ ይገኛል። የዓለም የጤና ድርጅት መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን በይፋ አውጇል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንዳሳወቀውም በዓለም ደረጃ እስከ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ወደ 2 ሚሊዮን ሰዎች አካባቢ በቫይረሱ ሲያዙ የበርካቶች ህይወት ሊያልፍ ችሏል። በመሆኑም በዓለም ሃገራት ላይ ከፍተኛ የማሕበራዊ፣ ቁጠባዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል። የሟቾችም ቁጥር በተለይም እንደ አሜሪካ ጣልያንና ስፔን ባሉ አገሮች ላይ ከእለት እለት አስከፊና ከፍተኛ እየሆነ መጥቷል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም የተገኘ ሲሆን እስከ ሚያዝያ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሃገር አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተጠቁ 82 ሰዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል። በአገራችን ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስከ አሁን የሞተው ሰው ቁጥር ሶስት መሆኑንም የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በሽታው የመተንፈሻ አካሎችን በሚያጠቃ ቫይረስ የሚከሰት ሲሆን ቫይረሱ በዓይን የማይታይ ተህዋስ ነው። ኮሮና ቫይረስ ወደ ሰውነት ከገባ ከ 2 እስከ 14 ቀናት ባሉት ጊዜያት ምልክት ሊያሳይ ይችላል። ስለዚህ አንድ ሰው በሽታው ካለባቸው ሃገሮች መምጣቱ ከተረጋገጠ ወይም ህመሙ ካለበት ሰው ጋር ከተነካካ ባሉት 14 ቀናት ውስጥ ከትኩሳት በተጨማሪ ከላይ ከተገለፁት ምልክቶች አንዱ ከታየበት በፍጥነት ለችግሩ ተብሎ ወደተለየ ማዕከል መሄድ ግድ የሚል ነገር ነው።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ በሕዝባችን ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ካህናትና ምዕመናን በጸሎት እንዲተጉ፣ ከመንግሥት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ትምህርት በተግባር ላይ እንድናውል የኢትዮጵያ የሀይማኖት ህብረት ጽህፈት ቤት ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
ጽህፈት ቤቱ የሰጠውን አቅጣጫ በመከተል የበሽታውን ስርጭት ለመግታት አስፈላጊውን ግንዛቤ መፈጠር እንዲቻልና ዘርፍ ብዙ ሥራ መስራት አስፈላጊ ስለሆነ በጽህፈት ቤት በኩል ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩም ይታወሳል።
ሁሉም አማኞች ወደ ፈጣሪያቸው መፀለይ አለባቸው በማለትም ከመጋቢት 28 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ አገር አቀፍ የጸሎት ፕሮግራም በማወጅና የመንግስት የመገናኛ ብዙሀንም ወደ ህዝቡ እንዲያደርሱ በማድረግ ላይ ነው።
“በጦር የማናሸንፈውን ጠላት ከፊታችን ተደቅኗል በኃላፊነት መንፈስ ከተንቀሳቀስን፣ የሚሰጡትን መመሪያዎች ካከበርን በሽታውን እናሸንፈዋለን፤ በየአድባራት ያለው ሁኔታ ትንሽ አሳሳቢ ነው፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከታች ያሉትን የሥራ ኃላፊዎችን ጠንከር ያለ መመሪያ መስጠት ይገባል፣ ፖሊስ የሕዝቡን ሰላም የመጠበቅ ሁለንተናዊ ደህንነት የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት የሚሰጡትን ቅድመ ጥንቃቄ ችላ በሚሉ አካላት ላይ አስፈላጊውን ነገር ይደርጋል” በማለትም የሀይማኖት መሪዎቹ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ሊያስወግዱ እንደሚገባ የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽን አቶ መላኩ ፈንታ ተናግረዋል ።
ሁሉም ቤተ እምነቶች ባሉባቸው ሕዝባዊ ኃላፊነቶች የተነሳ ለቫይረሱ የመከላከል ሥራ ራሱን የቻለ ግብረ ኃይል በማቋቋም ህብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ጥረቶቻቸው መካከልም አማኞች የታወጀወን ምህላና ጸሎት እንዲሁም የሰንበትና የእለተ አርብ የእምነት ተቋማት ስነ ስርዓት በቀጥታ በቴሌቭዥን ስርጭት እንዲከታተሉ ማድረግ ይገኝበታል።
እኛም ስለ ምህላና ጸሎቱ እንዲሁም ምዕመኑ ሊያከብራቸው በሚገቡ ህግና ደንቦች ዙሪያ ከመጋቢ ዘሪሁን ደጉ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ በሁሉም የእምነት ተቋማት ምዕመኑ በቤቱ ሆኖ ጸሎትና ምህላን እንዲያደርግ ሁኔታዎች ተመቻችተዋልና ከዚህ ተነስተው የእናንተ ቤተክርስቲያን በምን መልኩ ነው ሀላፊነቷን እየተወጣች ያለችው?
መጋቢ ዘሪሁን፦ ምህላና ጸሎቱ ከመታወጁ በፊትም ቢሆን በዚህ መልኩ ምዕመኑ ጋር መድረስ እንዲሁም ወደ ፈጣሪ የሚያደርሰንን ጸሎት ሊታወጅ እንደሚገባ የተለያዩ ጥረቶች እያደረግን ነበር። ከታወጀ ጀምሮም ምዕመናን በያሉበት ሆነው ከቤታቸው ሳይወጡ ወደ እምነት ተቋማትም ሳይመጡ እንዲጸልዩ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አማካይነት ምክር እየተለገሰ ይገኛል። በዚህም መሰረት ምዕመኑ መደበኛ ስራ ወይም ደግሞ በየቀኑ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች ሳይገደቡ ጸሎታቸውን እንዲያደርሱ ተደርጓል። የእኛም አገልጋዮች በየተራ በተመደበላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያና የአየር ሰዓት እየወጡ ምዕመኑን እያበረቱ የተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶችንና ጸሎትንም እያካሄድን ነው።
በጸሎት ጊዜም ሶስት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለባቸው ብለን እናምናለን፤ አንደኛው እውነተኛ ንሰሀ ሲሆን ይህም እኔ እግዚአብሔርን ምን በድየው ነው? በማለት ወደራስ ማየት ነው። ሁለተኛው በተሰበረ ልብ ሆኖ እግዚአብሔርን መፈለግና በዚህም ውስጥ የመጸጸት መንፈስን ማሳየት ሲሆን፤ ሶስተኛው ስለሌሎች በማሰብ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንዲፈውስ መለመን ነው ።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ምዕመኑ ይህንን ተረድቶ በየቤቱ ሆኖ እየፀለየ ነው ማለት እንችላለን?
መጋቢ ዘሪሁን ፦ የእኛ ምዕመናን ያሉት በመላው አገሪቱ ነው። በከተማም በገጠርም ይገኛሉ፤ እንዲህ ዓይነት ነገር በአገርና በህዝብ ላይ ሲመጣ ጾም ጸሎት ማድረግ ደግሞ የተለመደ ነው፤ ይህንኛውን ለየት የሚያደርገው በሁሉም ሀይማኖቶች ተመሳሳይ አቋም የተወሰደበት መሆኑ ነው። ወረርሽኙ እየከፋ እየመጣ ከመሆኑም በላይ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል ። የወረርሽኙ የመተላለፊያ መንገድ ደግሞ ከጥንቃቄ ጋር የተዛመደ ቢሆንም ማን ነጻ ማን ደግሞ ቫይረሱ እንዳለበት የሚታወቅ ነገር የለም። ከዚህ አንጻር ደግሞ ነገ ምን ሊመጣ እንደሚችል መገመት ከባድ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ መጸለይ ብቻ ሳይሆን አታድርጉ የተባሉትን ነገሮች አለማድረግ ዋናው መከላከያው በመሆኑ ከጸሎቱ ጎን ለጎን ይህንንም የማስተማር ስራ በመስራት ላይ ነን።
እዚህ ጋር መጸለይ ብቻውን ከወረርሽኝ አያድንም ግን ጎን ለጎን የእግዚአብሔር ቃልም እንደሚያዘው ‘ጥንቃቄ ያድንሃል ማስተዋልም ይጋርድሃል’ ይላልና ሰዎች ይጸልያሉ የእግዚአብሔርን ፊት ይፈልጋሉ ደግሞ መጠንቀቅም አለባቸው፤ ሆኖም ጥንቃቄ ሳያደርጉ ጾም ጸሎት ብቻ ማድረግ ምንም ውጤት የለውም። ጥንቃቄ አድርገን ደግሞ ባንጸልይ የእግዚአብሔርን ፊት ማየት አንችልም። ስለዚህ ሁለቱ ነገሮች አብረው መሄድ አለባቸው።
አንዳንዶች እምነትንና ጥንቃቄን እያጋጩ ነው፤ በዚህም እምነት ስላለኝ ምንም አልሆንም ይላሉ። ይህ ቀላል ነው ቫይረስ ነው በማለትም ያቃልላሉ ግን ደግሞ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አደጋ ውስጥ እየጣለ ያለው፤ በመሆኑም የሚሞቱት እምነት ስለሌላቸው አይደለም ስላልጸለዩም አይደለም። ነገር ግን መጸለይ ብሎም መጠንቀቅ አብረው የሚሄዱ ነገሮች መሆናቸውን ባለማወቃቸው እንጂ፤ እኛም እነዚህ ሁለት ነገሮች ተነጣጥለው መሄድ እንደማይችሉ በእጅጉ ሊገባን ይገባል።
አሁን ብዙ ድካም እየተደረገ እየመጡ ያሉ አንዳንድ ለውጦች አሉ፤ ግን በጣም ብዙ የሚቀረን ነገር ደግሞ አለ፤ በመሆኑም ሁሉም ለሁሉም ይጠነቀቅ ዘንድ ሌት ተቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ እርስዎም እንዳሉት ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ፤ ወደ ቤተ እምነት አትምጡ እየተባለ እንኳን አሁንም ምዕመኑ እየሄደ ነውና ይህንን ህግ ተላላፊ የህብረተሰብ ክፍል ተቋማቱ እንዴት ነው ሊቆጣጠሯቸው የሚገባው?
መጋቢ ዘሪሁን፦ እኔ እንደውም በእኛ እምነት በጣም የታዘብኩት ነገር ከዚህ ቀደም ለሀይማኖቱ ግዴለሽ ወደ እምነት ተቋምም የማይመጣ ሰው አሁን ላይ ግንባር ቀደም ህግ ተላላፊና ቤተክርስቲያን ተመላላሽ ሲሆን እየተመለከትኩ ነው ፤ እንዲህ ዓይነት ጊዜ ላይ መጠንቀቅ ነው የሚያስፈልገው ፤ ለምሳሌ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን በውሃ ላይ ወደ እኔ ና ሲለውና ሲሄድ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ነው ሊሰምጥ ሲል እጁን ይዞ ያሻገረው፤ እና ሁልጊዜ ጌታ አዞኛል ይቻላል ጴጥሮስም በውሃ ላይ ሄዷል ተብሎ በውሃ ላይ አይኬድም በጀልባ የምንሄደው ድልድይ የምንሰራው እምነት ስለሌለን አይደለም ፤ ቤት እየተቃጠለ እኔ ጋር አይደርስም ማለት አይገባም በእንደዚህ አይነት አደገኛ ወቅት ላይም እምነት ስላለኝ ምንም አልሆንም ማለት ከንቱ ድካም ነው። እምነት ማለት እኮ መታዘዝ ነው ።
መታዘዝን ከሶስት ወገን ማየት ይቻላል፤ አንደኛው የእግዚአብሔርን ፍቃድ እንዲሁም ሀሳብ በመስማትና በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመንግስት በኩል የሚሰጠውን ትእዛዝ መስማትና መቀበል ከእምነት የማይተናነስ ባለመሆኑ አስፈላጊ ነው፤ ሶስተኛው የሀይማኖት መሪዎቻችንን መስማት ነው። ይህ ደግሞ በሁሉም ሀይማኖቶች ያሉ አባቶች ምክርና ተግሳጽ ያጠቃልላል። በዚህም ሀይማኖት አባቶች ይህ ነገር የተከለከለ ነው ካሉ መቀበልና ወደ ተግብር መቀየር የእምነቱ አካል ነው። እነዚህን ሳናደርግ የምናካሄዳቸው ነገሮች አመጽ ናቸው እንጂ ሀይማኖተኝነት አይደሉም።
አዲስ ዘመን፦ ከቀናት በኋላ ደግሞ የትንሳኤ (ፋሲካ) በዓልን የምናከብርበት ጊዜ ነውና ምዕመኑ ከለመደው ነገር ወጥቶ እንዴት ነው ማክበር የሚገባው?
መጋቢ ዘሪሁን፦ የትንሳኤ በዓል ከፊታችን እየመጣ ነው። ሆኖም ሁሌም በለመድነውና በተመሳሳይ መንገድ ላናከብር እንችላለን። የትንሳኤ በዓል የእየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሳት የምናስብበት ነው፤ እስከ ዛሬ ድረስ በጋራ ብዙ ሆነን ተሰብስበን በአደባባይ ወጥተን ስናከብር ቆይተናል፤ የዚህኛውን ዓመት በዓል ግን እንደቀደመው ጊዜ ልናከብር የማንችልበት ሁኔታ ስለተፈጠረ እንደ የሀይማኖታችን በግላችን ሆነን የተቸገሩትን በማሰብ ማሳለፍ ያስፈልጋል።
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ከሁሉም በላይ የሚያስጨንቀኝና የሚያሳስበኝ ጉዳይ አብዛኛው ዜጋ ገቢው ከወር እስከ ወር የሚያደርስ አይደለም። የዕለት ገቢ ላይ የተመሰረተ ኑሮን ነው የሚገፋው፤ ለእኔ ደግሞ በትንሳኤው አምናለሁ የሚል ሰው እነዚህን ዜጎች ማሰብ የሚችል ነው።
ሁለት ምግብ፣ ልብስ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ካሉ አንዱን በመስጠት ነው የክርስቶስን ትንሳኤ አከበርኩኝ ማለት የሚቻለው። ስለዚህ ከእኛ መካካል ያሉ ችግረኞችን እንዴት እንደግፋቸውና በየቤታቸው ያክብሩት ብሎ ማሰብ ዋናው ነገር ሊሆን ይገባል።
ከዚህ በፊት በአደባባይ ወጥቶ ሲያመልክ የትንሳኤውን በዓል ሲያከብር በልዩ ልዩ የበዓል ዝግጅቶችም ቤተሰብ ከቤተሰብ ጓደኛ ከጓደኛ እየተጠራራን ያሳለፍነው ብዙ ዘመን አለ፤ አሁን ደግሞ ይህ ቫይረስ መጥቶብናል በመሆኑም እንደ አመጣጡ ተቀብለን የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ በማድረግ ማክበር ያስፈልጋል።
እኔ እንደሚመስለኝ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔርን ማስደሰት የሚቻለው በቤታችን ሆነን በዓሉን በግላችን ስናከብር ነው እንጂ አደባባይ ወጥተን የበሽታው መተላለፊያ በመሆን አደጋ እንዲደርስ ችግራችን እንዲበዛ ማድረግ ትንሳኤን የማክበሪያ ምልክት ሊሆን አይችልም።
አዲስ ዘመን፦ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከህዝቡ እንዲሁም ከእምነት አባቶችና ከሌላውም ምን ይጠበቃል?
መጋቢ ዘሪሁን፦ እኔ እንግዲህ ማለት የምችለው እንዲህ ዓይነት መቅሰፍት የሆነ ወረርሽኝ ባልሰራነው ጥፋት ወይም በደል ሲመጣ ህዝቦች የሚያልቁበት ነው የሚሆነው፤ ይህ ደግሞ በመላው ዓለም የሚሆን ነው። እንዲህ አይነት ነገር ሲመጣ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ መቅሰፍቱን እንዲያስቆም ሁሉም በየእምነቱ መጸለይ አለበት የሚል እምነት አለኝ።
አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የምለው ነገር እግዚአብሔር አውቆ ነው ወረርሽኙን ከእኛ ያልጀመረው፤ ወረርሽኙ እኛ አገር የገባው በሌሎች አገሮች ላይ ከገባ ከ70 ቀናት በኋላ ነው። ይህ በራሱ የሚያመለክተው ነገር አለ፤ እግዚአብሔር ለጥንቃቄ የሰጠንን ጊዜ እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ትምህርት እንድንወስድ ስለመተላለፊያ መንገዱም ጠንቅቀን እንድናውቅ ፈልጓል ማለት ነው። ይህ የተገላቢጦሽ ሆኖ ቫይረሱ ከእኛ ጀምሮ ቢሆን ኖሮ እልቂቱ የከፋ ይሆን ነበር። እግዚአብሔር አዋቂ ነውና ሊቋቋሙት ከሚችሉት አገራት ጀምሮ በሂደት ነው እኛም ጋር የደረሰው። በመሆኑም እግዚአብሔር ይህንን መሳይ እድል ሲሰጠን እኛ ደግሞ ራሳችንን ከፖለቲካም ይሁን ከሌሎች አመለካከቶች ለጊዜው ወጣ በማድረግና ጥንቃቄው ላይ በማተኮር መስራት ተገቢም አስፈላጊም ነው።
ሌላው እንደ አገርም እንደ ሀይማኖትም ማሰብ ያለብን በዚህ ጊዜ የእለት ጉርሳቸውን የሚያጡ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ነው፤ እነርሱን ማሰብና እንዳይራቡ ማድረግ አስፈላጊና ሊተኮርበት የሚገባ ሀሳብ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከላይም እንዳልኩት በሽታው እኔን አይነካኝም በማለት ከጥንቃቄ መራቅ ወይም ቸል ማለት ደግሞ አላስፈላጊና ፈጣሪንም መፈታተን በመሆኑ ሀይማኖት አለኝ አማኝ ነኝ የሚል ሁሉ ትኩረት ሊያደርግበት ይገባል።
እንደ አገርም ይህንን ወረርሽኝ ተገቢውን ትኩረት መንፈግና ቸል ማለት የደህንነት ስጋትም ሊሆን ስለሚችል ቀላል ጉዳይ አድርጎ መውሰድ አይገባም። ለዚህ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ በጣም ብዙ ስራ አጥ ያለበት አገር እንደመሆኑ ሁሉም ነገር ሳይታሰብ ዝግትግት ማለቱ ችግሩን ስለሚያባብሰው መንግስት ልዩ ትኩረት መስጠት ምዕመኑም እርሱ በልቶ ጎረቤቱ ጾሙን እንዳያድር ያለውን ማካፈልና ይህንን መጥፎ ጊዜ ማለፍ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
መጋቢ ዘሪሁን፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ!
አበቃሁ! አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
እፀገነት አክሊሉ