“የድል ዜና ተደጋግሞ የሚደመጠው በጦርነት ፍልሚያ መካከል ነው” የሚል የተዘወተረ ወታደራዊ አባባል አለ። እርግጥ ነው በነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ግብግብ መሃል የአሸናፊነት መንፈስ ከዳመነ፣ ወይንም በአትሌትክስ የሩጫ ትራክ ላይ ፉክክሩ እየተጧጧፈ ባለበት ሰዓት አትሌቱ ሜዳሊያ ማጥለቅ እኮ የሚሞከር አይደለም እያለ ሃሞቱ ከፈሰሰ፣ በከፋ የሀዘን ድባብ ውስጥ መጽናናት ጠፍቶ ስሜት በድቅድቅ አረንቋ ውስጥ ከተዋጠ፣ አለያም ጨለማው ቢከብድም የብርሃን ወገግታ መታየቱ አይቀሬ መሆኑ ካልታመነ ሕይወት ትርጉምና ጣዕም አልባ ትሆናለች። ትርጉሙና ጣዕሙ የጠፋበት የሕይወት ዘይቤ ደግሞ የሚያስከተለው ድቀት በቀላሉ የሚገላገሉት ሳይሆን የራስን እጅ የፊጥኝ አስሮ ለጠላት ከማስረከብም የከፋ ነው።
የተከፈተብንን የኮሮና ቫይረስ ጦርነት ለመፋለም የዓለማችን ማኅበረሰብም ሆነ ሀገራችን “በዐውደ ውጊያው” ላይ የሞት የሽረት ትንቅንቅ እያደረጉ እንዳሉ ይታወቃል። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከተከሰቱት በርካታ መሰል ቸነፈሮች መካከል ኮቬድ 19 በክብደቱም ሆነ በተስፋፊነት ግልቢያው አስደንጋጭና የከፋ ሆኗል። የወረርሽኙ አደጋና የተፋፋመው ጦርነት እንደ ሌሎች ሀገራት የከፋ ደረጃ ላይ ባያደርሰንም በጣት የሚቆጠሩ የውድ ዜጎቻችንን ሕይወት ነጥቆናል። የተጠቂዎቹ ቁጥርም እያሻቀበ እንጂ ሲቀንስ አላስተዋልንም። ከበሽታው ስላገገሙት ህሙማንም የምሥራች ዜና አድምጠን ለፈጣሪ ምሥጋናና ክብር፣ ለጤና ባለሙያዎቻችን ደግሞ የአድናቆት ጭብጨባ ለግሰናቸዋል። ጥረቱ ይበል የሚያሰኝ ነው።
ጀግንነት ከጠላት ጋር ሙሉ ኃይልን አሰባስቦ መታኮስ ብቻ ሳይሆን፤ ተገዳዳሪው እንደሚንበረከክም አምኖ መዋጋትን ግድ ይሏል። ከመደበኛ ጦርነት ፍልሚያ ጎን ለጎን በጠላት የተያዙ ገዥ መሬቶች ነፃ ሲወጡ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ እንዴት እንደሚረጋጋና እንደሚተዳደር አብሮ ማሰቡ ከጦርነት ስትራቴጂዎች መካከል የማይዘነጋ ዋና ሃሳብ ነው። የዓለም ማኅበረሰብም ሆነ እኛ “በዐውደ ውጊያው” አቅማችን በሚፈቅድልን መሠረት እየፈጸምን ያለነው እንዲህ ዓይነቱን መሰል የምክቶሽ ፍልሚያ ነው።
ወረርሽኙ ከ እስከ የማይባል ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ፣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እያደረሰብን እንዳለ የምንክደው ሐቅ አይደለም። በበርካታ ተግዳሮቶች መከበባችንና በከፋ ጉዳት እያነከስን መሆናችንም እርግጥ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ቢያንስ እስከ አሁን የሰሜን አሜሪካውንና የአውሮፓ ሀገራትን ያህል ጉዳቱ አድቅቆን የምንጨብጠውንና የምንይዘውን ስላላሳጣን ፈጣሪን ልናመሰግን ይገባል። የመንግሥታችን ትጋት፣ የመሪዎቻችን ምሳሌነት፣ የጤና ባለሙያዎች ጥረት፣ የባለ ሀብቶችና የሕዝቡ ትብብር ከሃይማኖት ቤተሰቦች መቃተትና የጸሎት ምልጃ ጋር ተደማምሮ የወረርሽኙ ግልቢያ በአጭሩ እንደሚቀጭና የወደፊቱ ሁኔታም የተሻለ እንደሚሆን ተስፋችን እየለመለመ ነው።
ቸነፈሩ በሕይወት፣ በአካል፣ በቁሳዊ ሃብት፣ በማሕበራዊ ተራክቦ፣ በሥነ አእምሮና በስሜታችን ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች አስረግጠው እየነገሩን ነው። በመሆኑም ግላዊና ቡድናዊ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብንና የጤና ባለሙያዎችን ምክር መተግበር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ጭምር ስለመሆኑም ደጋግሞ ተነግሮናል። ትዕዛዞቹንና ምክሮቹን እያንዳንዱ ሰው ሙሉ ለሙሉ እየተገበራቸው ነው ማለት ባይቻልም መረጃዎቹ ግን በስፋት እየደረሱን እንዳሉ እሙን ነው።
ኮሮናን ለማንበርከክ የሚደረገውን ጥረት ማወደስ ብቻ ሳይሆን ከድሉ በኋላ የሀገራችን ገጽታ ምን ሊመስል እንደሚችል ከወዲሁ ማሰቡ የችኩልነት አጉል ምኞት ሳይሆን ቀድሞ ሊታሰብበት የሚገባ ብርቱ ጉዳይ እንደሆነ በግሌ አምናለሁ። ጦርነት፣ ርሃብ፣ የመንግሥት ሥርዓት ለውጥና ቸነፈርን የመሳሰሉ ሀገራዊ ፈተናዎችና ክስተቶች ካለፉ በኋላ ነገሮች በነበሩበት ሊቀጥሉ እንደማይችሉና አዳዲስ ለውጦች መከሰታቸው አንደማይቀር የካሁን ቀድም ታሪኮቻችን ብዙ አስተምረውናል። ለውጡ አሉታዊ ወይንም አዎንታዊ ሊሆን እንደሚችልም መገመቱ አይከብድም። ያለፉት ተሞክሮዎቻችን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን ይህንኑ እውነታ ነው።
ምሳሌዎችን እናጣቅስ፤ የአድዋም ሆነ የፋሽስት ወረራዎች በድል ከተጠናቀቁ በኋላና ሀገር ነጻነቷን በተቀዳጀች ማግሥት በዲፕሎማሲው መስክ፣ በኤኮኖሚው ዘርፍና በማሕበራዊ ግንኙነት ረገድ ከፍተኛ ለውጦች ተከስተው ለትርፍም ለኪሳራም ዳርገውናል። ብዙ ሀገራት ኢትዮጵያን ወዳጅ ለማድረግ መሽቀዳደማቸው፣ በሮቻቸውንም ለሀገራችንና ለዜጎች፣ ለንግድም ሆነ ለትምህርት ክፍት ማድረጋቸው፣ ሥልጣኔያቸውና ሸቀጦቻቸው ሳይቀሩ በሀገራችን ገበያዎች መትረፍረፋቸው ወዘተ. በበጎነት የሚጠቀሱ ትሩፋቶች ነበሩ።
በአንጻሩም በጦርነቱ ማግሥት ወረራው ያደረሰብንን በርካታ ጠባሳዎች ማስታወሱን እንኳ ለጊዜው ትተን በሀገር ልጆች መካከል ሳይቀር ቁርሾና ቂም፣ የተገፋሁና የቅድሚያ እውቅና ተነፈግሁ ስሜቶች አቆጥቁጠው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ለምሳሌ፤ ከአድዋ ድል ማግሥት አጤ ምኒልክ ወራሪውን ሠራዊት መረብን ሳያሻግሩ በመቅረታቸው ዛሬም ድረስ የዘለቀ ቁርሾ ሥር ሊሰድ ግድ ሆኗል። ከመረብ መለስ የመገታቱ አሳማኝ ምክንያት ቢዘረዘርም ቂሙን ለማለዘብ ሳይቻል ቀርቶ ባስከተለው ጦስና መዘዝ የደረሰውን ሀገራዊ ኪሳራ እናስታውሳለን።
የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራም እንዲሁ በድል ከተደመደመ በኋላ በሕዝቡ ጤናና ኢኮኖሚ፣ በፖለቲካውና በማኅበራዊው መስተጋብር ላይ ብዙ ጠቃሚና ጎጂ አዳዲስ ክስተቶች ተዋውቀው እንደ ባህል መቀጠላቸው ይታወቃል።
ሚሊዮኖችን የፈጀብን የርሃብ ታሪክም ብዙ ጠባሳና ሀገራዊ ማዲያት ጥሎብን አልፏል። ለርሃባችን ማስታገሻ ብዙ ደጋግ ተቋማትና ግለሰቦች የረዱንን ያህል በአንጻሩም ክብራችንና ስብዕናችን በዓለም ፊት ጠልሽቶ እያዋረደን እንደ ጥላ ሲከተለን እንደኖረ የሚዘነጋ አይደለም። ነገሩ “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ብዙ ጉዳዮችን ማስታወስ በተቻለ ነበር።
ከመንግሥታት ሥርዓተ ለውጥ ማግሥትም ቢሆን የሀገራችን መልክና አቋም የተናጋባቸውንና ያሳከሩንን አንዳንድ እንክርዳዶች አስታውሶ ማለፍ ይቻላል። የዘውዳዊ አገዛዙን መንበረ ስልጣን የተቆጣጠረው አምላክ የለሹና ፈጣሪ ምን ግዱ የነበረው ወታደራዊ መንግሥት ከጭካኔና ከግፍ ትሩፋቱ ጎን ለጎን የሕዝቡን “መንፈሳዊ ፀጋ” በመላጨት ከአምላክ ጋር አኳርፎን እንዳለፈ አይዘነጋም። ከአምላክ ጋር ብቻም ሳይሆን ከነባር ማሕበራዊ በጎ እሴቶች ጋርም እንድንፋታ ጭምር ፈርዶብን ግብረገባዊ ሥነ ምግባር ከትውልዱ ስብዕና ውስጥ ተሟጦ እንዲወጣ ያደረገው ለዘር ይሉት ቅርስ ሳያስቀር ነበር። ከሥነ ምግባር ጋር መፋታታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በብዙ የሕይወት ዘርፎች እርስ በእርስ የጎሪጥ እየተያየን ለመኖር እንደተገደድንም አይዘነጋም።
የኢህአዴግ ሥርዓትም እንዲሁ በዘረኝነትና በጎጠኝነት ክበብ ውስጥ አስገብቶን ሲያናክሰን እንደኖረ የትናንት ታሪካችን አንዱ አካል ነው። እርስ በእርስ የተቋሰልንበት ህመም እያመረቀዘና እያገረሸ ያደረሰብን ክፉ ደዌ ገና ፈውስ ስላላገኘ ብዙ ማለቱ እጅግም አይጠቅምም።
ከኮቬድ 19 ወረርሽኝ ድል ማግሥትስ ምን እንጠብቅ?
“ያስጨነቅኸኝ ለመልካም ሆነልኝ” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፤ ቀደምት ክስተቶች ብዙ አስተምረውናልና የኮረና ቫይረስ ድል ተመትቶ “ጉሮ ወሸባዬን” ባቀነቀንን ማግሥት ከጉዳቱ ይልቅ በርካታ በጎ ትሩፋቶች እንደሚገጥሙን የግል እምነቴ ከፍ ያለ ነው። ጥቂት ሃሳቦችን ፈነጣጥቄ ለዝርዝር ትንተናው በተከታታይ የጋዜጣው እትሞች ላይ “ነጻ ሃሳቤን” በስፋት ለማቅረብ እሞክራለሁ።
በማኅበራዊ የኑሮ ዘይቤያችን ላይ ለውጥ ይኖራል፤
የኮረና ቫይረስ ክስተት ብዙ አስተምሮናል። ብዙ እውቀቶችንም እንደምንገበይበት ይጠበቃል። በየአካባቢያችን የሙጥኝ ብለን እንደ ልማድ የያዝናቸው “የግልና የቡድን” አባካኝ “ባህሎቻችን” እንደሚለዝቡ በቅድሚያ አስታውሼ ልለፍ። በተለይ የተንዛዙት የሠርግ፣ የሀዘን፣ የቀብር እና በርካታ የማኅበራዊ ኩነቶቻችንና መሰባሰቦቻችን መድረካቸው እንደሚጠብና ታዳሚው እንደሚመጠን ከሩቁ ጠርጥሬያለሁ። ለጉራና ለትምክህት እየተባለ ታዳሚዎች የሚንጋጉበትና ለሌላ በጎ ዓላማ መዋል የሚገባው ሀብት በከንቱ መፍሰሱም ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ያገኛል ባይባልም “ውሃ ልኩ” እንደሚስተካከል ግን ተስፋ አደርጋለሁ። የተመጠነ ታዳሚ፣ የተመጠነ መስተንግዶ፣ በተመጠነ ጊዜ “ጣጣችንን” ቀልጠፍ አድርገን የምንወጣው እንደሚሆንም ግምቴ ጠንካራ ነው። በግለሰብም ሆነ በቡድን ደረጃ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ “የአምልኮ መልክ ኖሮን ኃይሉን ከካድነው አምላክ” ጋርም እርቅ ፈጥረን ወደ ህሊናችን መመለሳችን እየፈጠነ ነው ባይ ነኝ። ምልክቶቹ በስፋት እየተስተዋሉ ነው።
ተዘርፎም ሆነ ተሰርቶ በተገኘ ሀብት ራስን እያቀማጠሉ ለቁርስ ዱባይ፣ ለምሳ ፓሪስ፣ ለራት ሮም፣ ለቀለበት ኒዮርክ ወዘተ. እየተባለ የሚቀበጥበት የቅንጦት ጉዞ ሙሉ ለሙሉ ባይጠፋም በድርበቡ ሊስተካካል እንደሚችል እገምታለሁ። የስደት ታሪካችን፣ የባዕድ ሀገራት ናፋቂነታችንን በተመለከተም ከህልማችን ባንነንና ቀልባችንን ሰብስበን “እኔም ሀገር አለኝ!” ዝማሬያችን የሚገን ይመስለኛል። ከድህነት ሸሽተን ያመለጥን ቢመስለንም እዚያም ቤት “የሚግለበለብ እሳት” እንደሚንቦገቦግ አይተናልና። የሰው ሀገር የሰው መሆኑ ብቻም ሳይሆን ለቀብር እንኳ አንድ ክንድ መሬት ተነፍጎ በድን ሲንከራተትም አስተውለናል። ይህንን ያየ ዓይን ነገም ውቂያኖስ ይብላኝ፣ የምድረ በዳ ወጀብ ይከንበልብኝ ብሎ በሕይወቱ ፈርዶ እግሩን ለስደት ቢያፈጥን ውጤቱን ስላየው “እኔን ያየህ ተቀጣ” ለሚል ወግ መብቃቱ በራሱ ያጠራጥራል።
“ድንጋዩ አደናቅፎህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንቅፋት ቢመታህ ስህተቱ የድንጋዩ ነው፤ ለሁለተኛ ጊዜ ያው ድንጋይ ቢያደናቅፍህ ግን እንቅፋቱ ድንጋዩ ሳይሆን አንተ ነህ” እንዲሉ። ባይመችም ሀገር፤ እንደሚመች ማድረግም የእያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ ነው። መንግሥትም ስደትን ለማስቀረት ከመቼውም ጊዜ ባላይ ተግቶ መሥራት ይኖርበታል። በተለይ ውስብስቡ ቢሮክራሲ ካልተበጣጠሰ በስተቀር ዜጎችም ሆኑ ሀገር ጤና የምናገኝ አይመስለኝም።
በሀገራችን የሚታየው የፖለቲካ መጠላለፍ፣ በመናገር ብዛት አዋቂ መስሎ መታየት፣ በውጭ ሀገራት ኖሮ የመጣ ሁሉ የተሻለ እንደሆነ አድርጎ መቁጠር ቀን የጨለመበት ፋሽን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ። “ዕድሜ ለኮሮና!” ኃያላን ሀገራት ሲርበተበቱና ሲንቀጠቀጡ፣ ባለኃብቶች ገንዘባቸው አላድን ሲላቸው፣ ዝነኞች ምስኪንነታቸው ሲገለጥ ስላስተዋሉ “እኔ እኮ!” እያሉ ቢፎልሉ ነዎሩ ባይ ስለማግኘታቸው እጠራጠራለሁ።
ዘርና ሃይማኖት፣ ቋንቋና ብሔር፣ የሰሜናዊነት፣ የምስራቃዊነት፣ የደቡባዊነትም ሆነ የምዕራባዊነት የክልልነት ፉከራና ትምክህት ከኮሮና ቫይረስ ክፉ ዓይን ሊተርፍ እንዳልቻለም አስተውለናል። ዱላው ያረፈው በሁሉም ዜጎች ላይ ነው። ይህ የወረርሽኝ ቁጣ አልፏቸው በሽልም የወጡ አንዳንድ የሀገራችን ፖለቲከኞችና “አክቲቪስቶች” ነን ባዮች እንደገና ወደ ድንቁርነታቸው ተመልሰው አንገታቸውን በማደንደን በቋንቋና በዘር ወረርሽኝ የሚያነካክሱን ከሆነ እጅ ከወርች አስረን ወደ ህክምና ኳራንቲን እናስገባቸዋለን እንጂ ከዚህ በኋላ “የጥፋት ሆያ ሆዬ!” ሲያስጨፍሩን “ሆ!” እያልን በማዳመቅ ቆመጥና ቆንጨራ ይዘን ለክፉ ሥራቸው ልናጅባቸው አደባባይ አንወጣም። በእንቶ ፈንቶ ትርክታቸው እያማለሉ “ተረት ተረት” ሲያወሩልንም “የላም በረት” በማለት በበረታቸው ውስጥ አንገባም። ይልቁንስ ባለ ብዙ ብሔሯን ሀገራችንን፣ ባለ ብዙ ቋንቋ ሕዝባችንንና ባለ ብዝሃ ባህል ኢትዮጵያችንን በጋራ አቅፈንና ደግፈን ወደ ክብር ማማ ከፍ እናደርጋታለን እንጂ ማንም ይሁን ማን በስመ ፖለቲካ ሲያሳብደን ከንፈን ጨርቃችንን አንጥልም። “እንገነጠላለን! እንለያለን!” እያሉ የበቀቀን ጩኸት ለሚያሰሙ ራስ ወዳዶችና ሟርተኞች ለመገበርም አልፈን አንሰጥም።
ኢኮኖሚያችንም ሆነ የሙጥኝ ብለን ያቀፍናቸው በርካታ ባህሎቻችንና ማሕበራዊ ተራክቧችን ከኮረና የድል ማግሥት ጀምሮ በብዙ መልኩ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልካቸው ሊለወጡ እንደሚችሉ በበቂ ማሳያዎች ማመልከት ቢቻልም ዝርዝሩን በይደር አስተላልፌ እንደ ሥጋት የጠረጠርኩትን አንድ መጻኢ ክስተት ብቻ ከታሪክ ማነጻጸሪያ ጋር እያስተያየሁ ግምቴን አቀርባለሁ።
የፋሽስት ኢጣሊያ ወረሪ ሠራዊት ሽንፈቱን ተከናንቦ ከሀገር እንደተባረረ አንድ አደገኛ የመከፋፈል እንቅስቃሴ በአርበኞቻችን መካከል ተስተውሎ ነበር። የመከፋፈሉ ዋና መንስዔ የነበረው ለሀገራዊው ድል መገኘት ተቀዳሚዎቹ ፊትአውራሪ አርበኞች እነማን ናቸው? በሚለው ጥያቄ ላይ የተሰጠው ንጉሣዊ መልስ ነበር። ዕውቅናና ሽልማት በአንደኛ ደረጃ፣ በሁለተኛ ደረጃና በሦስተኛ ደረጃ የሚገባው ለማን ነው? በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መግባባት በመታጣቱም አደገኛ ሁኔታ ተከስቶ ነበር። ይህንን ታሪክ ከአሁን ቀደም በአንድ ጽሑፌ ውስጥ መጥቀሴን አንባቢያን ያስታውሱ ይመስለኛል።
የአንደኛ ደረጃ የኒሻንና የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን የሚገባቸው ንጉሡን ጨምሮ “ስደተኛ አርበኞች” ናቸው የሚሉ ወገኖች በአንድ ወገን፣ እኛን ማን ቀድሞን ባዮቹ ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው የተፋለሙት ዋነኞቹ አርበኞች ደግሞ በሌላ ወገን፣ የለም ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ ለድሉ አስተዋጽኦ ያደረግነው እኛ ነን የሚሉ የውስጥ አርበኞች በሦስተኛ ወገን ተሰልፈው “ቀዳሚው ተመስጋኝ እኔ ልሆን ይገባል” በማለት ለእርስ በእርስ ፍልሚያ ነፍጣቸውን እስከ መወልወል ደርሰው ነበር።
የሆነው ሆኖ በብዙ ውይይትና ክርክር በእንግሊዝ የቃል ኪዳን ጦር እየታገዙ ወደ ሀገር የገቡት ንጉሡና ሹማምንቶቻቸው ለሽልማቱ ተቀዳሚ እንደማይሆኑ ከስምምነት ላይ በመደረሱ እነርሱ በሁለተኛ ደረጃ፣ ዋናዎቹ የጦር ሜዳ ጀግኖች አርበኞች በአንደኛ ደረጃ፣ የውስጥ አርበኞች በሦስተኛ ደረጃ እውቅናና ሽልማቱ ስለደረሳቸው ጠቡና ሙግቱ በዚሁ ሊጠናቀቅ ችሏል።
የጸሐፊው ወቅታዊ ስጋትም ከዚህ ጥንታዊ ታሪክ ጋር ይቀራረባል። ነገ ተነገወዲያ ኮቬድ 19 ታሪክ ሆኖ ፍልሚያው በድል ሲጠናቀቅ “ማን ነበር ተቀዳሚው ተፋላሚ? ማንስ ነበር ተከታዩ? ማን ነበር የሰለሰው? ማንስ ከማን ቀጥሎ እውቅናና ሽልማት ሊሰጠው ይገባል?” በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ መሳሳብና መጎሻሻም እንዳይፈጠር ስጋቴ ጠንካራ ነው። ሽልማቱ የግድ የወርቅ ኒሻን ወይንም የብር ዋንጫ ላይሆን ይቻላል። የቃል ንግግርና የጽሑፍ አፍ እላፊም ቢሆን ውጤቱ ላያምር ይችላል። ይህንን መሰሉ ክስተት የሰዎች ሁሉ የጋራ ባህርይ ስለሆነ “በኮሮና ቫይረሱ ፍልሚያ ውስጥ የአቅሙን ያህል ሳያበረክት የቀረ ማን አለና ይሄ ጥያቄ ይጠየቃል? በስመ አብ!” ብለን ብናማትብም የዋህነት ካልሆነ በስተቀር ክርክሩ ብዙም ውሃ የሚቋጥር አይሆንም። መጠየቁ የግድ ስለማይቀር።
ለምሳሌ፤ “ተገቢውን አመራር ስሰጥ የነበርኩት እኔ ስለሆንኩ ተቀዳሚው እውቅና የሚገባው ለእኔና ለቡድኔ ነው” የሚሉ ወገኖች ወይንም ተቋማት ብቅ ማለታቸው አይቀርም። “እኔ እንዲህና እንዲህ ባላደርግ ኖሮ መች የተሻለ ውጤት ይገኝ ነበር?” ብለው ዘራፍ የሚሉም ይጠፋሉ ተብሎ አይገመትም። እንዲህ አይነቱ ራስን የማስቀደም እሽቅድምድም ለቁርሾና ለቂም፣ ለኩርፊያና ለመገለል እንዳይዳርግ ከወዲሁ አርቆ ቢታሰብበት አይከፋም።
በመጨረሻም፤ እያሽቆጠቆጠን ስላለው ጣጠኛ ሕገ መንግሥታችን ነገ መሻሻሉ ስለማይቀር አንድ ጉዳይ አስታውሼ ልለፍ። እድል ቀንቷቸው በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ኮሚሽን ውስጥ የሚመደቡ አባላትና ይመለከተኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት ማስታወሻውን ቢይዙልኝ አልጠላም። የኮረና ቫይረስ ጉዳይ ብዙ አዳዲስ ክስተቶችን ሰላሳየን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 “የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት” በሚለው አንቀጽ ሥር የሰፈሩት ሦስት ንዑሳን አንቀጽ በደንብ ቢመረመሩ መልካም ነው። እውን የኮቬድ 19 ወረራ ያረጋገጠልን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተጠቀሰውን እውነታ ነው? መጠያየቁ አይከፋም። “መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” የሚለው ድንጋጌ እንደምን ነበር በዘመነ ኮሮና በሀገራችን እየተተገበረ ያለው። ለወደፊቱስ ምን ትምህርት ይሰጠናል? በግሌ የተረዳሁት አንድ እውነት መንግሥት ያለ ሃይማኖት፤ ሃይማኖትም ያለ መንግሥት መደጋገፍ ትርጉመ ቢስ እንደሆኑ በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ችያለሁ። ማሕበረሰብን ከሃይማኖትና ከሥነ ምግባር ማራቅ ትርፉ ምን እንደሆነም ከቀደምቱ ኑሯችን በሚገባ ተምረናል። ስለዚህ ነው ቀድሞ ቢታሰብበት መልካም ነው ያልኩት።
በተረፈ ኮቬድ 19 ተሸንፎ በጦር ሜዳ ፍልሚያው ተጠራርጎ እንደሚወገድ በማመን የሀገሬ መልክ በድሉ ማግሥት ምን ሊሆን ይችል ይሆን የሚል ምኞቴንና ስጋቴን እንዲህ ተመልክቻለሁ። በእርግጠኝነት የማምነው ግን ከኮሮና ቫይረስ መወገድ በኋላ የሀገሬን ፊት የምናስተውለው በገመምተኛ ፊት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። የተሰበረው ተጠግኖ፣ የወደመው ተተክቶ፣ የሀገሬ እንባ ታብሶ፣ በሕይወት ያጣናቸውን ዜጎች እያስታወስን፣ ከህመሙ ያገገሙትን እያቀፍን በሃሴት የምንዘምርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ከትናንትናም ሆነ ከዛሬ ይልቅ ሀገሬ ነገ ደምቃና ተኩላ በዓለም አደባባዮች ፊት እንደምትገለጥ አሜን ብዬ አምኛለሁ። ሰላም ይሁን!!!
አበቃሁ! አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)