ጽንፈኛ ብሔርተኞች ከአንድነት ኃይሉ ለሚሰነዘርባችው ወቀሳ የሚሰጡት የተለመደ መልስ አለ። “ጭንብላችሁን አውልቁ !” አንዳንድ ጊዜ ይህ አባባል ትክክል ሆኖ ይገኛል። ፀጥ ባለ ባህር ላይ ሁሉም ካፒቴን ጀግና ነው እንዲሉ እውነተኛ ጀግና የሚታወቀው ማዕበል ሲነሳ ነው። በየጊዜው በሚነሱ ማዕበሎች ተፈትነው የወደቁ በርካቶች ሳይፈልጉ ጭንብላቸው ሲወልቅ ተመልክተናል።
ባለንበት ወቅትም ማዕብል ተነስቷል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የዓለም የጤና ድርጅትን መረጃ በመደበቅና ለቻይና በመወገን ከሰውታል። አንዳንድ የሪፐብሊካን ሴናተሮችም ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል። ይህን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ የቆሙ “አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን” የጊዜ ወንፊት ሲያንጓልላቸው እያየን ነው።
አንዳንዱ ከዶክተሩ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ እንደ የሥራ ዕድል ቆጥሮት “ቸነፈር ቸርቻሪው” እያለ መጽሔቱን ይቸረችራል። “በባህሪ ትሁቱ በድርጅት ህ.ው.ሃ.ቱ” ብሎ ከኢትዮጵያዊነታቸው ይልቅ ድርጅታዊ ማንነታቸውን አስቀድሞ ሲያበቃ “ዶክተሩ በኢትዮጵያዊነታቸው አይጠረጠሩም” ይልሃል። ይህን ጊዜ እውነት ግን ቸርቻሪው ማን ነው ? ብለህ ትጠይቃለህ።
ሌላው ደግሞ የዶክተሩን ዘር ማንዘር እየቆጠረ ቡድን ተኮር ጥላቻውን ሲዘራና ቂሙን ሲያወራርድ ቆይቶ “አገራዊ እርቅና ብሔራዊ መግባባት” ያስፈልገናል ሲል ትሰማዋለህ። ኤርትራ መወለዳቸውንና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያዊ አይደሉም ለማለት የሚዳዳውም አለ።
የኢትዮጵያን ስም ጠርቶ የማይጠግብ የአንድነት ሰባኪ ደግሞ ዶክተር ቴዎድሮስ ላይ እየተሰባሰበ ስላለው ሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ የተቃውሞ ፊርማ ከቀናት በፊት እንዲህ አለ “ሊንኩን ለጠየቃችሁኝ ይኸውና ወደ 733,000 እየገሰገሰ ነው። 267,000 ይቀረናል። እኛው እንበቃለን። አንድ ሚሊየን እንድረስና ዓለም እየደረሰባት ላለው ሰቆቃ ቀኝ እጅ የሆነውን ሰው እናስወግድ!” አይገርምም ?
እርግጥ ነው ፊርማውን የሚያሰባስቡት ወገኖች ዶክተሩን የሚቃወሙት ኮቪድ 19 በዚህ መጠን ተስፋፍቶ ጉዳት እንዳያደርስ ማድረግ ይቻል እንደነበር የሚያሳዩ በጥናት የተደገፉ ማስረጃዎችን እያቀረቡ ነው። በዚህ ወቅት አንድ ኢትዮጵያዊ የተቻላቸውን ያህል እየደከሙ ላሉት የአገሩ ምልክት “ምንም ቢመጣ ከጎኖት ነን” በማለት ፈንታ እንዴት 267 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዶክተሩ ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቀውን የተቃውሞ ፊርማ ፈርመው ከኃላፊነታቸው እንዲያወርዷቸው በይፋ ይቀሰቅሳል ? ለነገሩ እንዲህ ያለ ተግባር ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለም። ዶክተር ቴዎድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለመሆን ሲወዳደሩም ተቃውሞ የሚያሰሙና ሹመታቸው እንዲታገድ ፊርማ የሚያሰባስቡ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ እናስታውሳለን። መቼም እጅን በእጅ የመብላት አባዜ ተጠናውቶናል።
ዶክተሩ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ማጀቢያ ሙዚቃ “ኣዲመራ” መሆኑን ስትረዳ የወጀቡ ምንጭ የህውሓት ጥላቻ መሆኑን ይገለጽልሃል። ከአዲስ አበባዎቹ በተጨማሪ አንድ ጉምቱ የኤርትራ ዲፕሎማትና “ኤርትሪያን ፕሬስ” በአሳፋሪ ካርቱን በዶክተሩ ላይ እየተሳለቁ የጻፉትን ስታነብ አሥመራና አዲስ አበባ በሚገባ ተናበዋል ትላለህ።
ሁለቱ አካላት ከአንድ ልቦና አንቅተው የሚናገሩ እስኪመስልህ ድረስ የዶክተሩን ሐጢአት ሲዘረዝሩ በሥርዓተ ነጥብ አጠቃቀም እንኳን ልዩነት አታይባቸውም። እኔ ወያኔ ነኝ ብለዋል፤ ከ13 ዓመታት በፊት 700 ኢትዮጵያውያንን የቀጠፈውን የኮሌራ በሽታ አተት የሚል ስም ሰጥተው አድበስብሰውታል፤ ወላጆች እንዲመክኑ አድርገዋል፤ ብረት አንስተው ወደ ኤርትራ በረሃ የወረዱ ኢትዮጵያውያን ፕሮፖጋንዳ ከመሆን ውጭ የሚያመጡት ነገር የለም ብለዋል፤ በዓለም የጤና ድርጅት ታሪክ የህክምና ዲግሪና ትምህርት የሌላቸው የመጀመሪያው የዓለም ህዝብ ሐኪም ሆነው ራሳቸውን ዶክተር እያሉ እየጠሩ ያጭበረብራሉ፤ ዳይሬክተር በሆኑ ጥቂት ወራት የዚምቧብዌውን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን የድርጅቱ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርገው መርጠዋልና ሌሎችንም ክሶች ያቀርቡባቸዋል።
በጃፓን የሚገኙት የኤርትራ አምባሳደር በቲውተር ገፃቸው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቻይና ሰንደቅ ዓላማ አይናቸው ተሸፍኖ የሚያሳይ ምስል ለጥፈው አብጠልጥለዋቸዋል። በአሥመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለዚህ የአምባሳደሩ ድርጊት ከኤርትራ መንግሥት ማብራሪያ መጠየቅ አለበት።
በኢትዮጵያ ስም የሚነግድ ካልሆነ በስተቀር በዓለም መድረክ የአገሩ ስም ደጋግሞ በበጎ እንዲነሳ ምክንያት የሆኑን ሰው ስም ለማጠልሸት የሚነሳ አገሩን የሚወድ ዜጋ አይኖርም። ዶክተር ቴዎድሮስ የኃላፊነት ቦታውን የያዙት በኢትዮጵያ ስም ነው። ስኬታቸው የኢትዮጵያ ስኬት፤ ውድቀታቸውም የኢትዮጵያ ውድቀት ነው። ምርጫው ሲካሄድ ተፎካካሪዎች ሲጠሩ የነበረው በአገራቸው ስም ነው። ሰዎቻችን እንዲህ ካለው የዓለም መድረክ እንዲርቁ በፈቀድን ቁጥር ዲፕሎማሲያዊ ዓቅማችን ተዳክሞ የኢትዮጵያ ተሰሚነት ይበልጥ ይቀንሳል።
የዓለም የጤና ድርጅት ቻይና ውስጥ ለተከሰተ በሽታ አሜሪካንን መጎብኘትና ከዋሽንግተን መረጃ መሰብሰብ አይጠበቅበትም። ከቻይና ጋር የተፈጠረው ግንኙት የበሽታው ማዕከል ከመሆኗ ጋር የተያያዘ ነው። የትራምፕ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ፕሬዚዳንቱ ጣታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ላይ የሚጠቁሙት ድርጅቱ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የሰጠውን ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ቸል ብለው አገራቸውን የከፋ ጉዳት ላይ መጣላቸው ከሚያመጣባቸው ተጠያቂነት ለመሸሽ ነው። እርሳቸው ያኔ በየካቲት ወር ማስጠንቀቂያው ሲሰጥ ማስጠንቀቂያውን ከማጣጣል ይልቅ አሼሼ ገዳሜ ለሚለው ሕዝባቸው በቅጡ አስገንዝበውት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከ23ሺ በላይ ዜጎቻቸው ትቢያ ባልሆኑ ነበር።
የቀድሞዋን ቻይናዊት ዳይሬክተር ዶክተር ማርጋሬት ቻንን ለመተካት ያደረጉትን ወድድር በከፍተኛ ድምፅ በማሸነፍ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ቦታን ከተረከቡ ሦስት ዓመት ሊሞላቸው አንድ ወር የቀራቸው የዶክተር ቴዎድሮስ ዓለም አቀፋዊ ሚና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ ትርጉም አለው። ለዚህ ነው ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት፣ የአፍሪካ ሕብረትን የሚመሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ፣ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ንኬንጋሶንግ፣ የርዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና ሌሎችም በጠንካራ ቃላት ድጋፋቸውን የገለፁላቸው።
ዶክተር ቴዎድሮስ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ፣ የጤና ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት በተለይ በጤናው ዘርፍ ውጤት ያስመዘገቡ፤ የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ያልተነከሩ ፤ አገራቸውንና ህዝባቸውን የሚወዱ እጅግም ሰው ሰው የሚሸቱ ትሁት አገልጋይ እንደነበሩ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። ሌላው ቢቀር ይህ ስብዕናቸው ከክፋት ሊከለክለን ይገባል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት በኢትዮጵያ ለተከሰተው የኮሌራ ወረርሺኝ ደካማ ምላሽ በመስጠታቸው ምክንያት የደረሰውን ጉዳትና ደርጅታቸው ህ.ው.ሓ.ት የፈፀማቸውን ጥፋቶች ዛሬ ሌሎች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጣታቸውን ሲጠቁሙባቸው እየዘረዘርን ለወቀሳ መነሳት አይገባም።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ለዶክተሩ ያላቸውን ድጋፍ መግለፃቸው የሚያስመሰግን ተጠባቂ ተግባር ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2012
የትናየት ፈሩ