ሃሳብን በተግባር የገለጡ የቴክኒክ አሠልጣኞች

ትምህርት ሕይወት የሚኖረው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተጨበጠው እውቀት በተግባር ሲተረጎም ነው። በተለይም የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶች በባሕሪያቸው ተግባራዊ ልምምዶችን የሚፈልጉና በፈጠራ ውጤቶች የታጀቡ በመሆናቸው በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን ማስተዋወቃቸው ይጠበቃል። መምህር ያሬድ በለጠ በአሰላ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል አሠልጣኝ ነው። ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን የውሃ ፕላስቲክ ክዳኖችን እና ጀሪካኖችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የአበባ መትከያ፣ አዝራር፣ ቁልፍ መያዣ ፣ጆሮ ጌጥ እና የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃዎችን ለማምረት የሚያስችሉ ሁለት ማሽኖች መሥራታቸውን ይናገራል።

መምህሩ የሥራውን ሂደት ሲያስረዳ፤ “በየአካባቢው የሚጣሉ የውሃ መያዣ ላስቲክ ክዳኖችን እንዲሁም፤ ጀሪካኖችን ከተለያዩ ቦታዎች ሰብስቦ በማሽን መፍጨት የመጀመሪያ ተግባራችን ነው። ከእዚያም የተፈጨውን ላስቲክ አቅልጠን የተለያዩ ቅርጽ ማውጫዎችን በመጠቀም ከአዝራር ጀምሮ የተለያዩ መገልገያ እቃዎችን እናመርታለን።”

አብዛኛውን ጊዜ የፕላስቲክ ቁሳቁሶች በየመንገዱ ስለሚጣሉ አካባቢን ሲበክሉ ነው እንጂ መልሰው ጥቅም ላይ ሲውሉ አይስተዋልም የሚለው አሠልጣኙ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ እና ገቢ ለመፍጠር ማሽኑን ለመሥራት እንደተነሳሱ ያብራራል። በእዚህ መንገድ ማሽኑን ሠርተው ሥራ ላይ ማዋል እንደቻሉ ያስረዳል።

 

ማሽኑ የአካባቢ ጽዳት ለማስጠበቅ እየረዳ እንደሚገኝ እና ሥራ አጥ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲሠሩ እድል የሚፈጥር ስለመሆኑም አንስቷል። በአሁኑ ጊዜም ሰባት የኮሌጁ ሠልጣኝ ተማሪዎች ግቢ ውስጥ የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቷቸው ተደራጅተው በማሽኑ እየሠሩ እንደሚገኙም ይገልጻል።

በተጨማሪም የአሰላ ከተማ አስተዳደር በሴፍቲኔት ለሚሠሩ ሴቶች መጥረጊያ እየገዛላቸው እንደሆነና የተለያዩ ተቋማት የአበባ መትከያ እቃ እየገዟቸው እንደሚገኙ አሠልጣኙ ያስረዳሉ፤ በቀጣይም ማሽኑን በስፋት በማምረት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ይናገራል።

መምህርት ትዕግስት አየለ በኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል አሠልጣኝ ስትሆን፤ ከባልደረቦቿ ጋር በመሆን የአግሮ ፕሮሰሲንግ ትምህርት ክፍል አሠልጣኞች ባመነጩት ሃሳብ መሠረት አትክልት እና ፍራፍሬ ለማድረቅ የሚያገለግል እንዲሁም፤ ዳቦ የሚጋግር “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ በአንዴ ሁለት ተግባራት ማከናወን የሚችል ማሽን መሥራት እንደቻሉ ትናገራለች።

እንደ ሀገር ብዙውን ጊዜ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ማሽኖች የሉም የምትለው ትዕግስት፤ “በእዚህ መሠረት በኮሌጁ አግሮ ፕሮሰሲንግ ትምህርት ክፍል የሚያሠለጥኑ መምህራን ሃሳቡን አመንጭተው ለማኑፋክቸሪንግ ትምህርት ክፍል አመጡልን፤ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ለመሥራት ቻልን።” ስትል ትገልጻለች።

ብዙ ጊዜ ዳቦ የሚጋግሩ ትላልቅ ማሽኖች አሉ፤ ነገር ግን በተመሳሳይ ሰዓት ዳቦ እየጋገረ ፍራፍሬዎችን የሚያደርቅ ማሽን የለም የምትለው አሠልጣኟ፤ የማሽኑ መነሻ ሃሳብ ይህን ክፍተት ከመሙላት አንጻር መሆኑን ታስረዳለች።

“ማሽኑ አምስት ክፍሎች ስላሉት ዳቦ እየጋገርን በሌላ በኩል ደግሞ ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ቲማቲም እና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችን ለማድረቅ ያስችላል። ከደረቀ በኋላ በዱቄት መልክ በማዘጋጀት የብርቱካን ፣ የማንጎ ሻይ ለማፍላት ያስችላል። ቲማቲም በእርጥብ ሲሆን በቶሎ ስለሚበላሽ አድርቆ በዱቄት መልክ ለማዘጋጀትም ይረዳል” ስትል ትገልጻለች።

በቀጣይ የማሽኑን መጠን ጨምሮ የመሥራት ሃሳብ እንዳላቸው በመግለጽ፤ ኮሌጁ ማሽኖችን እየሠራ ለሥራ ፈጣሪዎች መሸጥ ስለሆነ ተግባሩ፤ ማሽኑን በተለያየ መጠን በማምረት ለሥራ ፈጣሪዎች የማስተላለፍ እቅድ እንዳላቸው መምህርት ትዕግስት አመልክታለች።

በመጀመሪያ የወደቁ ቁሳቁሶችን በመልቀም ለሚሸጡት ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማሽኑን ተጠቀመው ፕላስቲኮችን ለመልሶ ጥቅም ለሚያውሉ ግለሰቦች የሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑን ያመላክታል።

ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ማሽኑን እንደሠሩ የሚናገረው ያሬድ፤ እነዚህም የማሽኑን ዲዛይን የሠሩ ፣ ከዲዛይን በኋላም ማሽኑን ወደ ተግባር የቀየሩ እና ከእዚያም በመገጣጠም ሥራ ላይ የተሳተፉ እንደሆኑ ያስረዳል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You