ከስኬት ጫፍ የደረሰ ብርታት

በርካቶች በተስፋ መቁረጥና ቸልተኝነት ዓላማቸውን ከግብ ሳያደርሱ ከመንገድ ይቀራሉ። ጥቂቶች ደግሞ ጥቂት ሃሳብና ዕቅድ ብቻ በቂያቸው ነው። አንድን ጉዳይ ቁምነገር ካሉ ወደኋላ መመለስን አያውቁም። በያዙት መንገድ ቀጥለው ከስኬት ጫፍ ይደርሳሉ። ይህ ብርታትም ለብዙኃን ተምሳሌት ሆኖ ተሞክሯቸው ለሌሎች ይተርፋል።

ኮማንደር መስከረም ብሩ ይባላሉ። በርካቶች ከስማቸው ቀጥሎ ጥንካሬያቸውን ሲያደንቁ ይሰማል። በሕይወት ውጣ ወረድ የገጠሟቸውን ፈተናዎች በድል መወጣታቸው ከበርካቶች ዘንድ አድናቆት አትርፎላቸዋል። በሥራ በትምህርት ፣ በልጆች አስተዳደግና በቢዝነስ ዘርፍ ስኬታማ ከሚባሉ ጠንካሮች መካከል አንዷ ናቸው።

ኮማንደር መስከረም ከዛሬ 38 ዓመት በፊት በፖሊስነት ሲቀጠሩ ዋንኛ ዓላማቸው ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣት ነው። እንዳሰቡት ሆኖም ወታደራዊ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ብዙ የለፉበትን ሙያ ተቀላቀሉ። አጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ ሥራቸውን የጀመሩት በፖሊስ ሆስፒታል ጤና ረዳት ሆነው እንደነበር ይናገራሉ።

ኮማንደሯ ከሁለት ዓመት በላይ በሙያው ሠልጥነው ብቁ ሲሆኑ፤ ለሦስት ዓመታት ያህል በሥራው ላይ መቆየታቸውን ይገልጻሉ። በወቅቱ ሥራውን በሚመጥን አግባብ በቂ ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር። እሳቸው ግን ጅማሬያቸው በእዚህ ብቻ መቆም እንደሌለበት ከራሳቸው መከሩ። ምክራቸው ወደ ድርጊት ሲቀየር ደግሞ አፍታ አልቆየም። የጤና ረዳትነት ደረጃቸውን አሳድገው በነርሲንግ ለመሠልጠን መማር እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ከእዚህ በኋላ ኮማንደሯን ከፍጥነታቸው የሚገታ አልተገኘም። ለተከታታይ አስራ ሦስት ዓመታት ያለማቋረጥ በትምህርት ዓለም መቆየታቸውን ይገልጻሉ። ይህ ቆይታ የዓመታት ቁጥር ብቻ አልሆነም። በእነዚህ ጊዜያት መሐል መደበኛ ሥራቸውን እየተወጡ ልጆች የማሳደግ፣ ቤተሰብ የመምራት ኃላፊነትን በድል ተወጥተዋል።

ገና በአፍላነት ዕድሜ የመሠረቱት ትዳር የራሱ ግዴታ አለው። እሳቸው በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ መቆየት አለመፈለጋቸው ከቀለም አዋህዷቸዋል። ቀን ሲሠሩ ውለው ምሽቱን ትምህርት መከታተል ሌላ ተጓዳኝ ተግባራቸው ነው።

መምህሩ ባለቤታቸው የልባቸውን ለመሙላት ፊት እንዳልነሷቸው የሚናገሩት መስከረም፤ በስኬታቸው ሁሉ የእሳቸው መልካምነት እንዳልተለያቸው ሲገልጹ፤ ከታላቅ ምስጋና ጋር ነው። በሰርተፊኬት የጀመረው የኮማንደሯ ትምህርት በአስራ ሦስት ዓመታት ቆይታ ዲፕሎማና ዲግሪ እያለ ቀጠለ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ኢንጂነሪንግ ከተማረው የመጀመሪያ ልጃቸው ጋር በመመረቅ ስኬታቸውን አጣጣሙ።

በሚሠሩበት ሙያ የላብራቶሪ ቴክኒሻን መሆናቸው ደረጃቸውን ከፍ አደረገው። እንዲህ መሆኑ ብቻ ግን “ይበቃኛል” ለሚል ውሳኔ እንዳላደረሳቸው ይናገራሉ። ኮማንደሯ ዕድሜያቸው እየገፋ ቢሆንም ከጅማሬያቸው መመለስን አልፈለጉም። የነገ ሕይወታቸውን የሚደግፍ ትምህርት መቀጠል እንዳለባቸው አስበው ከውሳኔ ደረሱ። ያሰቡት አልቀረም ።የሁለተኛ ዲግሬ (ማስትሬት ) ትምህርታቸውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ቀጥለው ከሦስተኛ ልጃቸው ጋር በእኩል ተመረቁ።

እነዚህ የብርታት ዓመታት ለኮማንደሯ በእልህና ጥንካሬ የተሞሉ ነበሩ። እሳቸው እንደሚሉት፤ በአንድ ዓይነት የሥራ ዘርፍ ብቻ መቆየት አለመፈለጋቸው በለውጥ ጎዳና እንዲራመዱ አፍጥኗቸዋል። ይህ እውነታም ከሰርተፊኬት ዲግሪ፣ ብሎም እስከ ማስትሬት አድርሷቸዋል።

ከቀናት በአንዱ ደግሞ ለቤተሰቡ ከአንድ ሰው ልዩ ስጦታ መበርከቱን በትውስታ ያወጋሉ ። ለዓመታት የኖሩባቸው የቤት አከራይ አንዲት ላምን “እነሆ! ሲሉ አበረከቱላቸው። ኮማንደሯ የላሟ በስጦታ መበርከት ከአባወራቸው ጋር ብዙ እንዳወዛገባቸው ያስታውሳሉ። በወቅቱ የእሳቸውና የባላቸው ሥራ መዋልና የልጆቻቸው ተማሪ መሆን ከላሟ ጋር እንዳያመች ሆኖ ፈተናውን አበዛው።

እንዲያም ሆኖ ኮማንደሯ ከቤተሰቡ ለገጠማቸው ፈተና እጅ እንዳልሰጡ ይናገራሉ። ገቢን ለማሳደግ የላሟ መኖር ግድ መሆኑን አሳምነው ሁሉን በፍቅር አሸነፉ። ከሥራ በፊት እሳቸውና ባለቤታቸው ወተት አልበው አዛባ ሲዝቁ ለትንንሾቹ ልጆች ሌላውን ኃላፊነት ሰጡ። ልጆቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ትኩስ ወተት ማመላለስን ለመዱ። ሲመለሱም የወተት ዕቃዎችን ማጠብ ግዴታቸው ሆነ።

ኮማንደሯ በቤቱ የሥራ ባሕል መፈጠሩ ታሪካቸውን እንደለወጠው ይናገራሉ። ዛሬ በስጦታ የመጣችው የአንዲት ላም ታሪክ ተቀይሮ ሃያ ሁለት የወተት ላሞች በበረታቸው ይገኛሉ። የእነሱ በረከት ደግሞ በቁጥር ብቻ አልቀረም። ገቢን አሳድጎ ቤተሰብን አሳድሯል፤ ልጆችን አስተምሮ ለወግ ማዕረግ አብቅቷል።

የልፋት ድካም ጥረታቸው ለውጤት እንዳበቃቸው የሚገልጹት ኮማንደር መስከረም፤ የመጀመሪያ ልጃቸውን በኢንጅነሪንግ አስመርቀዋል። ሁለተኛው ልጃቸው ደግሞ ዶክተር ሆኖ እሳቸው ባገለገሉበት የፖሊስ ሆስፒታል እየሠራ ይገኛል። ሦስተኛዋ ልጃቸው ከዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ምሩቅ ናት። አራተኛውና የመጨረሻው ልጃቸው ደግሞ የአስር ዓመት ሕጻን መሆኑን ይገልጻሉ።

መስከረም፤ ለ38 ዓመታት የሠሩበትን የፖሊስ ቤት ከመስከረም 2017 ዓ.ም ጀምሮ በክብር መሰናበታቸው ግድ ነበር። በበርካታ ውጣ ውረድ የታለፈው የኮማንደሯ ሕይወት ስኬታማ ቢሆንም፤ እሳቸው ግን ርምጃቸውን “በበቃኝ” አልገቱም። ጡረታ ከወጡ በኋላ አዲስ ሥራ ለመፍጠር አቀዱና ተሳካላቸው።

ለንግድ ሥራ የሚሆን ሱቅ መክፈታቸውን የሚገልጹት ኮማንደር መስከረም፤ በዋነኛነት “መስኪ ድፎ ዳቦ”ን በብዛት እያዘጋጁ በመሸጥ እውቅናን አገኙ። ጣፋጩ የአገልግል ምግባቸውም በድግስና ሀዘን ቦታ ሁሉ ተመራጭ ሆነላቸው። ለቤተሰቦቻቸው ጠንካራ የሥራ ባሕልን ያስተማሩት ብርቱ ሴት ዛሬ ልጆቻቸው የትልቅ ድርጅትና የሚያኮራ እውቀት ባለቤት ሆነው ማየታቸው ከልብ እንደሚያኮራቸው ይናገራሉ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You