ከ296 የመንገድ ፕሮጀክቶች 127ቱ ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም

– ከተያዘላቸው በጀት በላይ ተጨማሪ ወጪ የወጣባቸው 180 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ተመላከተ

አዲስአበባ፡– ከ296 የመንገድ ፕሮጀክቶች 127ቱ ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ መረጃ አልተገኘም ሲል የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ የፋይናንስ የሕጋዊነት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፤ የመንግሥት ፕሮጀክት አስተዳደር እና የአመራር ሥርዓት አዋጅ 1210/2012 ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ተደርጓል። በተደረገው የናሙና ኦዲትም የአዋጭነት ጥናት እና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሳይሠራላቸው በጀት ተፈቅዶላቸው ወደ ትግበራ የገቡ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ዋና ኦዲተሯ በናሙና ከታዩ 296 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ አራት ዓመትና ከእዚያ በላይ የዘገዩ እና ከእዚህ ውስጥ 127 ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ መረጃ ያልተገኘላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 52 የመንገድ ፕሮጀክቶች እና 42 የመስኖ ፕሮጀክቶች በድምሩ 94 ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ግምገማ ሳይደረግላቸው ፣ በጀት ተፈቅዶላቸው ወደ ትግበራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

በናሙና ከታዩ አራት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስገነቧቸው ግንባታዎች እና 147 የመስኖ ፕሮጀክቶች ከአንድ ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የዘገዩ መሆናቸውን አመልክተው፤ ከ267 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት የጠየቁ 20 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥም ዘጠኙ ፕሮጀክቶች መቶ በመቶ እስከ 200 በመቶ ተጨማሪ በጀት ያስከተሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

መጀመሪያ ከተመደበላቸው በጀት ከ78 በመቶ እስከ 760 በመቶ ተጨማሪ ተደርጎ ብር 17 ቢሊዮን 254 ሚሊዮን 150ሺህ 104 ተጨማሪ ገንዘብ የጠየቁ የመስኖና በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በእቅድ ከተያዘ በጀት ብር 13 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ተጨማሪ በጀት የወጣባቸው ከ180 በላይ የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸው ጠቁመው፤ ከእዚህ ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ ተጨማሪ ወጪ የወጣላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ዋና ኦዲተሯ አስታውቀዋል።

በናሙና በታዩት በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክቶቹ የተጠናቀቁ እና ሥራ የጀመሩ ቢሆንም፤ ፕሮጀክቶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ ብር 2 ቢሊዮን 964 ሚሊዮን 476 ሺህ 085 በጀት ተመድቦ የተለቀቀላቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች ብር 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን በጀት የተለቀቀላቸው ቢሆንም፤ ገንዘቡ ግን ለፕሮጀክቶቹ ሥራ ያልዋለ መሆኑን አውስተው፤ ከፕሮጀክት ጽንሰ ሃሳብ ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ የሚያዝበት፣ የመረጃ ልውውጥ የሚደረግበት ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትና የመረጃ ቋት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አለመኖሩንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የፋይናንሻል እና የፊዚካል እቅድ መርሃ-ግብር ሳይዘጋጅላቸው በናሙና ከታዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተገኘ መረጃ መሠረት 2013 እስከ 2016 ዓ.ም የተጀመሩ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ስምንት የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 15 የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ 12 የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 10 የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ በድምሩ 45 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶች ያሉበት ሁኔታ በጋራ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በፕላን ሚኒስቴር ተገምግሞ እና የፋይናንሻልና የፊዚካል አፈጻጸማቸው ሳይገመገም ባሉበት ሁኔታ መቀጠላቸውንም ዋና ኦዲተሯ አብራርተዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You