
– በ12 ወራት ከ5ሺህ 295 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል
ጋምቤላ:- በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ የወርቅ ምርት ከስምንት እጥፍ በላይ ማደጉን የጋምቤላ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ ኡጁሉ አስታወቁ።
አቶ ኡጁሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት 650 ኪሎ ግራም ወርቅ ተገኝቷል። ዘንድሮ ክልሉ በ12 ወራት ከ5ሺህ 295 በላይ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል። ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ስምንት እጥፍ የወርቅ ምርት መገኘቱን ያሳያል ብለዋል።
በክልሉ በዘንድሮው በጀት ዓመት 2 ሺህ 850 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት መታቀዱን አውስተው፤ እስከ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 5 ሺህ 295 ነጥብ 87 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን ኃላፊው ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በክልሉ የወርቅ ምርት ላይ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ወርቅ አምራቾች የወርቅ ምርታቸውን በቀላሉ ወደ ብሔራዊ ባንክ በማስገባት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል በወርቅ ማዕድን ማውጣት ላይ የተሰማሩት በጸጥታ ስጋት ምክንያት ከአቅም በታች ሲያመርቱ እንደነበር አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜ ሰላም በመስፈኑ ወርቅ አምራቾች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት እንዲገቡ አድርጓል ብለዋል።
ለአብነትም በ2016 ዓ.ም 650 ኪሎ ግራም ወርቅ መገኘቱን አስታውሰው፤በክልሉ ሰላም በመስፈኑና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በወርቅ ምርት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ገዳሙ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል የነበሩ አዋጆች የማያሠሩ ነበሩ፤ አሁን ላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ በመሆኑ በማዕድን ዘርፉ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በዘርፉ በ795 ሰዎች በላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረ መሆኑን አመልክተው፤ ከእዚህም 22 በመቶ ያህል ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በክልሉ የተገኘው የሰላም ሁኔታ ማህበረሰቡ በሙሉ አቅሙና ትኩረቱ ወደ ልማት እንዲገባ እና የኑሮ መሻሻል ማድረጉን ተናግረዋል። ይህም መጪው ጊዜ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም የሚያመላክት መሆኑን ነው።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም