የሰዎችን ደስታና ሃዘን መካፈልና ለሰዎች በችግራቸው ጊዜ የአቅማችንን ያህል ማድረግ አብዛኞቻችን ያስደስተናል፤ እርካታም ይሰጣል። ይሁን እንጂ አንዳንዴ ሰዎች በይሉኝታ ሲታሰሩና ከፍላጎታቸው እና ከአቅማቸው በላይ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እንዲሁም ሃሳባቸውን ለሌሎች ሰዎች ደስታ ሲያውሉ ይታያል። ይሉኝታ ሰዎች ‹ምን ይሉኛል› በሚል ሰበብ፤ የራስን ፍላጎት በመግታት ሌሎችን ለማስደሰት መጣር፤ ሌሎችን ማስቀደም ማለት ነው። ይሉኝታ የሚያጠቃቸው ሰዎች ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት እና ግዴታ በላይ የሌሎችን ጉዳይ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። ይሉኝታ የራሳችንን ስራና አጀንዳ ወደ ጎን አድርገን ፤ ፍላጎታችን እና ምርጫችን ተጭነን ሌሎችን ለማስደሰት የመፈለግ ውጤት ነው።
ይሉኝታ የሚያጠቃቸው ሰዎች መገለጫ ባህሪያት ብንመለከት ከሌሎች ሰዎች ሃሳብ ጋር ሁሌም መስማማት እንዳለባቸው ሲሰማቸው፣ ሰዎችን ሊያስደስታቸውና ሊያስከፋቸው ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸው ነገሮች ላይ በብዛት መጨነቅ፣ ባያምኑበትም እንኳ ቢሆን ስለሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገር ሲወራ አብሮ ማማት፣ ሰዎች ስለእነሱ ምን ሊያስቡ እና ምን ሊናገሩ እንደሚችሉ ማሰብና መጨነቅ ተጠቃሾች ናቸው። በተጨማሪም የሃሳብ ልዩነቶችንና ግጭቶችን ተጋፍጦ በሃሳብ ከመርታት ይልቅ መሸሽ፤ ሃሳቦች ሳይብላሉ ማቋረጥ፣ ሰዎች በውይይት መሃል የተለየ ሃሳብ ሲያነሱ ከሃሳቡ ይልቅ ሰዎች ላይ ማተኮር፣ ሃሳባቸውን ከማንጸባረቅና ላመኑበት ነገር ከመቆም ይልቅ ለቡድን ተጽእኖ እጅ መስጠት፣ ከደንብና መመሪያ መከበር ይልቅ በሰዎች ለመሞገስና ለመከበር ትኩረት መስጠት፣ የፈለገውን ያህል ዋጋ ቢያስከፍልም ሌሎችን ላለማስከፋትና ላለማበሳጨት መጣር፣ አይሆንም የማለት ድፍረት ማጣት እና ለሁሉም ነገር እሺን ማስቀደምም የይሉኝታ መገለጫዎች ናቸው።
ስለ ይሉኝታ እንዳወራ ያስገደደኝ አጋጣሚ ላውጋችሁ። የኮሮና ቫይረስ ወደ አገሪቱ ከገባ ጀምሮ በመንግስትማ በጤና ባለሙያዎችም በኩል ህብረተሰቡ ጤንነቱን እንዲጠብቅ የተለያዩ መመሪያዎች ሲሰጡ ቆይተዋል። ከዚህም ውስጥ እጅን ቶሎ ቶሎ መታጠብ፣ እርቀትን ጠብቆ መቆም ወይም መቀመጥ፣ አለመጨባበጥና ግዴታ ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት ይገኙበታል። ይህንንም ህብረተሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ በመገናኛ ብዙሀንና በአደባባይ ትምህርት ሲሰጥም ሰንብቷል። ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ በገባ ሰሞን ሁሉም ህብረተሰብ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ቢነገረውም፤ ‹‹ ኮሮና ወጣትን አይዝም፣ ኮሮናን በባህላዊ መንገድ መከላከል ይቻላል›› በሚል መንፈስ ግዴለሽነቶች በብዛት ይስተዋሉ ነበር።
በየመንገዱ በሚገኙ የእጅ መታጠቢዎች አካባቢ ህብረተሰቡ ተራርቆ ከመታጠብ ይልቅ ተፋፍጎና ተደራርቦ ሳሙና እየተዋዋሰ ሲታጠብም ማየት የተለመደ ነው። ነገር ግን በየአካባቢው የሚገኙት በጎ ፈቃደኞች ሁኔታው ትክክል አለመሆኑን ቢያውቁም በይሉኝታ ሰበብ ዝምታን መርጠው ያልፋሉ። በሌላ በኩልም በሸማች ማህበራት ሱቆች፣ በእህል ማስፈጫ ቤቶች እና ሌሎች ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ ያለ ጥንቃቄ የሚደረጉ ነገሮች ቢኖሩም የፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶችም በዝምታ ሲያልፉ ይስተዋላል።
ሌላው ደግሞ በህዝብ ትራንስፖርት መስጫ መኪናዎች ውስጥ በአሁን ወቅት መጨናነቆች ቢቀሩም ከተሳፋሪዎቹ መካከል ማስነጠስና የማሳል ሁኔታ ሲኖር መስኮት እንዲከፈትና ያስነጠሰው ወይም ያሳለው ሰው አፉን እንዲሸፍን የሚናገር ሰው አይታይም። በተመሳሳይም በመንገድ ላይ በጉንፋን ይሁን በሌላ ምክንያት አፉን ሸፍኖ ሲያስል ወይም ሲያስነጥስ ‹‹እንደሱ አይደረግም›› የሚል ሰውም አይስተዋልም፤ የለምም። ምክንያቱም ይሉኝታ ጠፍሮ ማህበረሰቡን ስለያዘ ነው። ይህ ሁኔታ በመንግስት መስሪያ ቤቶች አካባቢም ይታያል። በቢሮ ውስጥ አንድ ሰው ቢያስነጥስ ወይም ቢያስለው ወዲያው ‹‹ጉንፋን ነው…ብርድ ነው›› ብሎ ሲያስተባብል ‹‹አይ አደለም ሌላም ሊሆን ይችላል ተመርመር›› ብሎ የሚከራከር ሰው አይታይም። ምክንያም በይሉኝታ ተሸብቧልና ነው።
በጤና ጣቢዎችና ክሊኒኮች አካባቢ በተለያየ ህመም ምክንያት የሚመጡ ሰዎች ይበዛሉ። የህክምና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ሲሯሯጡ ይስተዋላል። ነገር ግን አስፈላጊው ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም። ታካሚዎች ለመታከም በሚመጡበት ወቅት ነርሶች የሚገባውን ጥንቃቄ በተለይ አፍ መሸፈኛና የእጅ ጓንት ሲያደርጉ አይስተዋልም። ይህን ሁኔታ ሁሉም የሚያስተውለው ጉዳይ ቢሆንም በ‹‹ምን አገባኝ›› መንፈስና በይሉኝታ ተይዞ ሲናገር አይታይም። በዚህም በሆስፒታሎች አካባቢ የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሆኗል።
በምንኖርበት ሰፈር ይሁን በመስሪያ ቤቶች አካባቢ አብዛኛው ሰው ሲበላም ሆነ ሲያወራ ተጠጋግቶ ነው። አንዳንዴም በወሬ መሀል የእጅ ንክኪዎች አይጠፉም። ይህ ሁኔታ ለበሽታው ተጋላጭነት እንደሚጨምር ቢታወቅም፤ በይሉኝታ ተይዘን እያደረግነው እንገኛለን። ከዚህም ሌላ የገንዘብ አጠቃቀማችን የእጅ በእጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ገንዘብ ስንሰጥም ሆነ ስንቀበል ምንም አይነት ጥንቃቄ አናደርግም። ከሰው ገንዘብ ስንቀበል ወይም ስንሰጥ እጃችንን ሳኒታይዘር ስንቀባ አንታይም።
ከላይ ከተዘረዘሩት ውጪ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች በይሉኝታ ምክንያት ለኮሮና በሽታ ሊያጋልጡን እንደሚችሉ ይታወቃል። በተለይ በገበያ ቦታዎች ላይ አሁንም ድረስ ያለው ግፊያና ግርግር ገደብ ሊበጅለት ይገባል። የፀጥታ አስካባሪዎች በአሁኑ ወቅት ለህዝብ መገበያያ እያገለገለ በሚገኘው ጃንሜዳ ውስጥ ተገበያዩ ርቀቱን ጠብቆ ስራውን እንዲሰራ ከማድረግ ይልቅ እነሱም የግርግሩ ተሳታፊ ሆነው ይታያሉ። በየመንገዱ የህዝቡን ፀጥታ የሚጠብቁ ፖሊሶች ተቀራርበው ተቀምጠው ሲያወሩ ይስተዋላል። ርቀታችሁን ጠብቁ የሚለው አባባል ከመልዕክት ባለፈ ተግባር ላይ ሲውል አይታይም:: ስለዚህ ከዚህ ክትባትም መድኃኒትም ካልተገኘለት ቫይረስ ለመከላከል ይሉኝታን ወደጎን በመተው ራስን፣ ቤተሰብን ብሎም አገርን ማስመለጥ ብልህነት ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
መርድ ክፍሉ