ገና በ16 ዓመቷ ገቢ ለማግኘት ትውተረተር የነበረችው ሰላማዊት ዘውዴ፣ ታታሪነት መለያዋ ነው። ህልሟ ሃብታም መሆን ብሎም የራሷን ቤት በራሷ አቅም መገንባት ነበር። አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ተወልዳ ያደገችዋ ሰላማዊት፣ ሃብታም የመሆን ፍላጎቷ እንደሌሎቹ አቻዎቿ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ጨርሳ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ስራ እስከመያዝና ለትልቅ ቦታ እስከመታጨት አላደረሳትም።
እንደአሁኑ የቻይና ጫማ አገሩን ከማጥለቅለቁ በፊት፤ ሰው እየቀጠሩ ሰባተኛ፣ አውቶቡስ ተራ እና መርካቶ በየጉራንጉሩ ጫማ የሚያሰሩ አምራች ነጋዴዎች ዘንድም የስምንተኛ ክፍል ፈተናዋን እንዳጠናቀቀች ተቀጥራ በጫማ ሥራ ላይ ተሰማራች። የልጅነት ፍጥነቷ የቆዳ ቆረጣን አልፋ፤ ቆዳ መላጨትንና ማሳሳትን ዘላ አዘጋጅ አደረጋት። ከእርሷ ቀጥለው ወንዶች ቆዳ ወጥረው፣ ገርዘው፣ አልብሰው ከሶል ጋር የሚያጣብቁት ሥራም ለእርሷ አያዳግታትም። በየሳምንቱ የሚካሄደው የጫማ ሰሪነት ቅጥር አንዳንዶች አልፎ አልፎ ስራ የሚያጡበት ቢሆንም፤ እርሷ ግን ተፈልጋና ተለምና የምትቀጠርበት የስራ ዘርፍ ሆነ።
በየሳምንቱ የሚከፈላትን ገንዘብ አጠራቅማና እቁብ ገብታ ተቀጥራ ትሰራ የነበረውን ጫማ በራሷ ሰርታ መርካቶ የሚገኙ የጫማ ሱቆች እንዲረከቧት አቀደች። መሰረታዊ የሆነውን የጫማ መወጠሪያ ሞዴል ገዛች። በአራት ሺህ ብር የቆዳ መስፊያ መኪና፣ የጫማ ሶልና ቆዳ እንዲሁም ማስቲሽና ሌሎች ጫማ ለመስራት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን አሟላች። ነገር ግን እርሷን ቀጥረው እንደሚያሰሩት ሃብታሞች ሰራተኛ ቀጥራ በየሳምንቱ ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችል አቅም አልነበራትም። ከስራ መልስ ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ብቻዋን እየሰራች ጫማ ማምረት ጀመረች።
የጫማ ስራውን ብቻዋን ስትከውን እንደአሰበችው ቀላል ሆኖ አላገኘችውም። በቂ ገንዘብ የሌላት መሆኑና በትርፍ ሰዓት መስራቷ ብዙም ውጤታማ አላደረጋትም። ትልቁ ፈተና ደግሞ ጫማዎቹ ከተሰሩ በኋላ ተረካቢ ነጋዴ ማግኘት አለመቻሏ ነበር። ባለሱቅ የጫማ ተረካቢዎች ቢገኙም ምርቱ ገበያ ላይ እስኪታወቅ ጫማውን የሚረከቡት በዱቤ ነበር። ዱቤውን የሚከፍሉት ደግሞ ጫማው ከተሸጠ በኋላ ባሻቸው ጊዜ መሆኑ ተስፋ አስቆረጣት።
በራሷ ለመቆም ትውተረተር የነበረችው ሰላማዊት ጫማውን ለብቻዋ መስራቷ የቻይና ጫማ አገሩን ማጥለቅለቁን ተከትሎ አከሰራት። ተመልሳ ወደ ቅጥር ገባች። በ1997 ዓ.ም ደግሞ አዲስ ነገር ብቅ አለ፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ። የአካባቢዋን ወጣቶችና ሌሎች ቤት የሌላቸው የተመዘገቡ ሰዎችን አስተባብራ በእርሷ መሪነት ይደርሰናል ብለው ተስፋ ላደረጉት ቤት በየወሩ መቆጠብ ጀመረች። እስከ 2004 ዓ.ም ግን ቤት ማግኘት አልቻለችም።
ህይወቷ እንደፈለገችው አለመቀየሩ ቢያበሳጫትም ሌላ ሃሳብ ደግሞ መጣ፤ ዕድሜ መገስገስ ይዟልና በጊዜ ትዳር ለመመስረት ወሰነች። ጊዜዋን ስራ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጋ የምትንቀሳቀሰዋ ሰላማዊት፣ እንደሌሎቹ ሴቶች ቤት ያለውና አንቀባሮ የሚያኖራትን ወንድ አልፈለገችም። ይልቁኑ እንእደርሷ ህይወቱን ለመቀየር ከሚውተረተረው ይርሳው አጥናፍ ጋር ተገናኘች።
እንደምኞቷ ቤት ሳትሰራና በዕጣም ቢሆን ቤት ሳታገኝ ትዳሯ በቤት ኪራይ ላይ ተመሰረተ። በ2004 ዓ.ም አንዲት ሴት ልጅ ወለደች። እንደወትሮ መታተሯን ቀጥላለች፤ በዓመቱ ሁለተኛ ሴት ልጅ ደገመች። ሰላማዊት ቤት ብቻ አይደለም የመነገጃ ሱቅ ለማግኘት እጅግ ደክማለች፤ ነገር ግን ሁለቱም አልተሳኩላትም። በተለይ የአገር ውስጥ ጫማ ገበያ ሙሉ ለሙሉ በቻይና ጫማ ገበያ መተካቱና ለምነው ያሰሯት የነበሩ ሃብታም ቀጣሪዎች ሳይቀሩ ወደ ድህነት ቁልቁል መምዘግዘጋቸው በህይወቷ ላይ ተስፋ እስክትቆርጥ ያደረሳት መጥፎ አጋጣሚ ነበር።
አውቶቡስ ተራ የክፍለ አገር ተሳፋሪ አጫጫኝነት፣ አልፎ አልፎ ደግሞ በድለላ ሥራ ላይ የተሰማራው ይርሳውም ሆነ እርሷ ቤት የሌላቸው መሆኑና የስራቸው ቀጣይነት አስተማማኝ አለመሆን ህይወታቸውን ፈተነው። በተለይ ሁለት ልጆችን ያለበቂ ገንዘብ ማሳደግ የሰላማዊትን ኑሮ አከበደው። የጋራ መኖሪያ ቤቱን ተመዝግባ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ክፈዪ የተባለችውን ገንዘብ በመክፈል በአጠቃላይ ለ10 ዓመታት ብትቆይም የግል ቤት ለማግኘት አልታደለችም። በእነዚህ ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን ያየችዋ ሰላማዊት፣ ንግዱ አልሆንልሽ ሲላት ተቀጥራ እየሰራች፤ ደግሞ ገንዘቡ ጠርቀም ሲልላት ወደ ሌላ ንግድ እየተሰማራች፤ ሌሊት ሳይቀር የአልጋ ልብስ እየሰራች ራሷን ለመለወጥ ብትውተረተርም ኑሮዋ አስደሳች አልሆነላትም።
በ2007 ዓ.ም ግን አዲስ ነገር መጣ። ሰላማዊት የቤት ዕድለኛ ሆነች። ባለአንድ መኝታ ቢሆንም ስልሳ ስድስት ካሬ ሜትር አንደኛ ፎቅ ላይ የካ አባዶ አካባቢ ዕጣ ወጣላት። ነገር ግን ቅድመ ክፍያውን መክፈል ደግሞ ምጥ ሆነ። እንደምንም ዘመድና ባዳ አግዟት እርሷም ራሷን ለመለወጥ ስትል ያጠራቀመችው ገንዘብ ታክሎበትና ባለቤቷም የተቻለውን ሁሉ ሰብስቦ ቅድመ ክፍያው 48 ሺህ ብር ተከፈለ። ነገር ግን ቤቱን ስትረከብ የፀዳ ባለመሆኑ እንደገና ሌላ ወጪ ጠየቀ። ገንዘብ ተበድራ ራሷም በየጊዜው እየሰራች ባለቤቷም እየተሯሯጠ የሚያገኘው ታክሎበት በቀን ሰራተኛ መሰራት ያለበትን ሳይቀር ራሷ እየሰራች ቤቱን አፀዳች። ሁሉንም አበጃጀች። ኮርኒሱን በጅብሰም አሳምራ ቀለም አስቀባች፤ ይህ ሁሉ የሆነው በብድር ገንዘብ ሲሆን፣ ያሰማመረችውም ‹‹ሰርቼም ሆነ ቤቱን አከራይቼ›› እከፍላለሁ በሚል ነበር።
ምንም እንኳ የደረሳት ቤት ስታፀዳው የበለጠ ቢያጓጓትም ከመኖር ይልቅ ማከራየት እንዳለባት አስባ ደላሎች ተከራይ እንዲያመጡላት ነገረች። ብዙ የተደከመበትና ወጪ የወጣበት ቤት ከቅድመ ክፍያው ሌላ ለ19 ዓመታት በየወሩ አንድ ሺህ 850 ብር የሚከፈልበት መሆኑ በራሱ ለሰላማዊት እጅግ ከባድ ነበር። የቤቱ ኪራይ በየወሩ የሚከፈለውን ዕዳ እንኳ የሚሸፍን አልሆነም። በተጨማሪ በደላሎቹና በተከራዩ ወትዋችነት በአንድ ወር ሺህ 800፤ ለስድስት ወር 10ሺህ 800 ብር ቀድሞ ተሰጣት። ከዛው ላይ የደላላ ክፍያ ተቀንሶለት የተወሰነ ዕዳ ተከፍሎለት እጅግ የተቸገረችበትን የቤተሰቧን ልብስ የሚያጥብላትና ሥራ የሚያቃልልላትን ማጠቢያ ማሽን ከገዛች በኋላ ገንዘቡ አለቀ።
ለስድስት ወራት በብዙ ስቃይ በየወሩ ለዕዳው ገቢ መደረግ የነበረበትን ገንዘብ ገቢ እየደረገች ቆየች። ከስድስት ወር በኋላ አንድ ዓመት እስኪሞላ ገንዘብ ላለመጨመር ውል በመግባቷ በየወሩ 50 ብር እየጨመረች አንድ ሺህ 850 ብር ዕዳ መክፈል ቀጠለች። ከዓመት በኋላ የቤት ኪራዩን ዋጋ እየጨመረች ሁለት ሺህ 500፣ አሁን ደግሞ ሶስት ሺህ 500 ብር ድረስ ብታስከፍልም፤ ለቤቷ ባይተዋር ነች። ልትኖርበት ብትፈልግም በየወሩ የሚያስፈልገውን የወር ክፍያ ፈፅማ መርካቶ ድረስ የትራንስፖርት እያወጣች ኑሮዋን ለማሸነፍ ‹‹ያዳግተኛል›› ብላ በመስጋቷ፤ ሰባተኛ አካባቢ እርሷ ከባለቤቷ እና ከልጆቿ ጋር ዛሬም በአንድ ክፍል ቤት ውስጥ ትኖራለች። ዛሬም ባማረው ቤቷ መኖርን ትሻለች። ነገር ግን እጇ በማጠሩ ለቤቷ ባይተዋር ሆናለች።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
ምህረት ሞገስ