የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ እያስገነባ ያለው የካንሰር፣ ልብ፣ የአንጀትና የጨጓራ ህክምና ማእከላት ፕሮጀክት ከሚይዛቸው የአልጋዎች ቁጥር በመነሳት 555 የሚል ስያሜ ይዞ እ.ኤ.አ በ2015 የግንባታ ኮንትራት ውሉ ጀምሯል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጀመር በመጀመሪያው ውል ላይ የካንሰር ህክምና ማእከሉ በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚሰራና ምድር ቤቱን (ቤዝመንት) ጨምሮ ከመሬት በላይ ባለ ስምንት ወለል ህንፃ እንዲሁም በአንድ ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ ከመሬት በላይ ባለ አራት ወለል ህንፃ የልብ ህክምና ማእከል እንዲሰራ ታስቦ ነበር፡፡ ይሁንና በውሉ መሰረት ወደ ስራ ሲገባ ሆስፒታሉ ህንፃዎቹ ለመገንባት የሚያስችለውን ሰባ ከመቶ የሚሆነውን ቦታ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመረከብ ስራውን ለማከናወን ከስምምነት ላይ በመድረሱ የኮንትራት ውሉን ለማሻሻል የግድ ብሏል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የምህንድስና እና ግንባታ ዳይሬክቶሬት የካንሰር፣ ልብ፣ አንጀትና ጨጓራ ህክምና ማእከላት ፕሮጀክት አስተባባሪ ኢንጂነር ሞቲ አሰፋ እንደሚገልፁት፣ ፕሮጀክቱን ለመጀመር በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመስጠት ቃል የገባው መሬት በአብዛኛው ህንፃዎች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከኢንስቲትዩቱ በኩል ቦታው እንዳይነካብኝ የሚል ጥያቄ መጥቷል፡፡ በዚህም በድጋሚ ከኢንስቲትዩቱ ጋር መደራደርና ቦታዎቹን ማመቻቸት አስፈልጓል፡፡ በዚህ ሂደትም ፕሮጀክቱ አንድ አመት ከሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ተጓቷል፡፡
እንደ ፕሮጀክት አስተባባሪው ገለፃ፤ ከኢንስቲትዩቱ የተገኘውን መሬት ህንጻዎችን በማይነካ መልኩ ለመጠቀም ከኢንስቲትዩቱ ፊት ለፊት የሚገኘውን ቦታ ለማስተካከልና ለግንባታ ዝግጁ ለማድረግ የህንፃ ግንባታውን ዲዛይን የመከለስ ስራ ተጀምሯል፡፡ በመሆኑም በቦታው ላይ የአንድ ሺ 500 ካሬ ሜትር ህንፃ ብቻ ገንብቶ ማለፍ ተገቢ ባለመሆኑ የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር ስራውን አሳድጎ እንዲሰራ ከግዢዎች ኤጀንሲ ፍቃድ ተጠይቋል፡፡
ከኤጀንሲው ፍቃድ በመገኘቱ የካንሰር ህክምና ማእከሉ ባለ ሁለት ምድር ቤት (ቤዝመንት) እና ከመሬት በላይ ስምንት ወለል ህንፃ በስድስት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ፣ የልብ ማእከሉ ምድር ቤት (ቤዝመንት) እና ከመሬት በላይ ባለ ስምንት ወለል በሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እንዲሁም የአንጀትና የጨጓራ ህክምና ማእከሉ ምድር ቤት (ቤዝመንት) እና ከመሬት በላይ ባለ ስምንት ወለል በአንድ ሺህ 400 ካሬ ሜትር ላይ ተሻሽለው እንዲገነቡ ዲዛይናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በግንቦት ወር 2016 በይፋ ተጀምሯል፡፡
የፕሮጀክት አስተባባሪው እንደሚገልፁት፤ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ህንፃዎች በእኩል የግንባታ አፈፃፀም ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ የፋይናንስ አፈፃፀማቸው 40 ከመቶ ደርሷል፡፡ የስትራክቸራል ስራዎችን በሚመለከትም የ 13 ሚሊዮን ብር የኮንክሪት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌሎች የኮንክሪትና የስትራክቸራል ስራዎች ሙሉ በሙሉ አልቀዋል፡፡ የብሎክ ስራ 89 ከመቶ ደርሷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የልስን፣ የስክሪድ በተጓዳኝ ደግሞ የአልሙኒየም ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማጠቃለል (ፊኒሺንግ) ስራዎች በተለይም የልብ ህክምና ማእከሉ ላይ የጂፕሰም ብሎክ ፓርቲሽንና የስክሪድ ስራ ተጠናቆ የጂፕሰም ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
እስካሁን ባለው የፕሮጀክቱ አፈፃፀም 580 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ከግዢዎች ኤጀንሲ ፍቃድ በሚወሰድበት ጊዜ አዳዲስ የዲዛይን ለውጦችና ማሻሻያዎች ሲመጡ የታሰቡ ስራዎች ነበሩ፡፡ ይኸውም ፕሮጀክቱ ሲታለም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች በሌሎች ተቋራጮች እንዲሰሩ ታቅዷል፡፡ በዚሁ መሰረት እነዚህ ሰራዎች የሚሰሩባቸው ደረጃዎች ላይ እየተደረሰ በመሆኑ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዲዛይን ተጠናቆ ወደ ጨረታ ሂደት ላይ ደርሷል፡፡ የፕሮጀክቱ የፊዚካል አፈፃፀምም 60 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡
በፕሮጀክቱ ሂደት በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች ከውጭ አገር ለሚገቡ እቃዎች በተለይም የኤሌክትሪካል፣ የሳኒተሪና ሌሎች የፊኒሺንግ እቃዎች የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት የማቴሪያል ማፅደቅና የማምጫ ጊዜ ወጥቶላቸው እቃዎቹ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት የፖርስሊን፣ የኢፖክሲን፣ የእንጨት በሮች፣ የኤሌክትሪክና የሳኒተሪ ፊዲንጎችን ኮንትራክተሩ ከውጪ አገር አስገብቷል፡፡ እነዚህ ስራዎች አሁን የሚሰሩ ባይሆንም ችግር በሚደርስበት ጊዜ እቃዎቹ ቀርበው ወደገጠማ ለመግባት በማሰብ ነው፡፡ የፊኒሺንግና የኤሌክትሪክ ስራዎችና ሌሎች ኮንትራክተሮች የሚሰሯቸው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ደግሞ በቀጣይ የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ፕሮጀክት አስተባባሪው እንደሚሉት፤ ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ የደህንነት እቃዎች የተሟሉ ቢሆንም በተለይ በቀን ሰራተኞች በኩል የደህንነት ማቴሪያሎቹን በአግባቡ ባለመጠቃማቸው መጠነኛ አደጋዎች አጋጥመዋል፡፡ ይህም በፕሮጀክቱ ሂደት ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይሁንና በግንባታ ሳይቶች ላይ የደህንነት ተቆጣጣሪዎችን በመመደብ ችግሮቹን ለመቅረፍ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአገር ውስጥ የሚመረቱ የግንባታ መሳሪያዎች በተለይ ደግሞ ብሎኬት በላብራቶሪ ፍተሻ ወቅት አብዛኛዎቹ ከተቀመጠው የጥራት ደረጃ በታች መሆንም ሌላኛው ያጋጠመ ችግር ሲሆን፣ ይህንኑ ችግር ኮንትራክተሩ ራሱ በጥራት እንዲያመርት ወይም ከንኡስ ተቋራጮች ጋር እንዲሰራ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ ከዲዛይን ጋር በተያያዘም ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን ከሃኪሞችና አገልግሎቱ ከሚሰጡባቸው ክፍሎች ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ በ 12 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ አስመላሽና ልጆቹ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደረጃ አንድ ህንፃ ተቋራጭና አትኮን ኢንጂነሪንግ አርክቴክቸር ኮንሰልታንሲ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አማካሪ ድርጅት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ በትክክለኛው የኮንትራት ስምምነት መሰረት ግንባታው 920 ቀናትን እንደሚፈጅ ከሆስፒታሉ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለማእከላቱ ግንባታ የተያዘው የገንዘብ መጠንም 987 ሚሊየን ብር ቢሆንም፤ ተጨማሪ የማሻሻያ ስራዎች በመምጣቻው ግንባታው አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅም ታውቋል፡፡
የኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ የመንገድ፣ ጄኔሬተሮች፣ ትራንስፎርመሮችና ሌሎች ስራዎችን አካቶ በሚጠናቀቅበት ጊዜም እስከ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ሊፈጅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ጊዜም የዘገየበትን ቀናት ጨምሮ ሁለት ሺህ 234 ቀናት እንደሚሆንና በዚሁ መሰረት ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በጥር ወር 2020 ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
አስናቀ ፀጋዬ