መገኛው የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ነው፤ ስሙንም ከከተማዋ መጠሪያ የወሰደ ሲሆን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመባል ይታወቃል። በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ታሪክም ውስጥም በአንጋፋነቱ ይታወቃል፤ ትልቁ የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው። በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ታሪክም ውስጥ ተጠቃሽ ነው። አንጋፋዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ባለታሪኮች የዚህን ተቋም ደጃፍ የጎበኙ ናቸው።
መሠረቱ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1942 ዓ.ም. መጣሉን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ የማስተማር መርሃ ግብሩን በ33 ተማሪዎች የጀመረ መሆኑም ይጠቀሳል።
ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመባል ይታወቅ ነበር፤ በኋላም ‹‹የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በወታደራዊው ደርግ መንግሥት ወደ ስልጣን በመጣ ማግስትም አሁን የሚጠራበትን ስሙን ‹‹አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ›› የሚለውን ስያሜ አግኝቷል።
በአገሪቱ አንጋፋና የመጀመሪያው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጀምሮ የትምህርት፤ የምርምርና የማህበረሰባዊ አገልግሎት ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ቀዳሚ የምርምር ተቋም ለመሆን የሰነቀውን ራዕይ ከማሳካት አንፃር ባደረገው እንቅስቃሴ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞቹንና የቅበላ አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የአገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር አቅም ለመፍጠር በሚያስችለው ቁመና ላይ እንደሚገኝም ይነገርለታል።
ይህ ዩኒቨርሲቲ ዋና አስተዳደሩን ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዋናው ግቢ ያደረገ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ እንዲሁም በደብረ ዘይት በስሩ የተለያዩ ፋኩልቲዎች እና ኢንስትቲዩቶች እንደያዘም ይታወቃል።
ዩኒቨርሲቲው በ2019 ዓ.ም ቀዳሚ ከሆኑ 10 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆን ራዕዩ መሆኑን እና ብቁ ምሩቃንን በማፍራትና ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ እንዲሁም ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎቶችን በመስጠት የሀገሪቱን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ልማት ማፋጠን ዋና ተልዕኮው መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው ድረ ገፅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
አስቴር ኤልያስ