በዋናነት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ትልልቅ ከተሞች የሚታየው ህንፃ ከቀን ወደቀን በቁጥርም በቁመትም እየጨመረ ስለመሆኑ ይነገራል። በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች ብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ፍጥነታቸውም ‹‹በቅለው ነው እንዴ ያደሩት›› በሚያሰኝ ሁኔታ ከማስገረማቸውም በተጨማሪ ወዲያው ደግሞ ለኪራይ ራሳቸውን ሲያዘጋጁ መስተዋሉም ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ሆኗል። በእርግጥ የእነዚህ ህንፃዎች እንደ አሸን መፍላት የከተማነት መገለጫ ነውን ስንል በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከሰጡት ባለሙያዎቹ መካከል አንዱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ኮሌጅ ትምህርት ቤት መምህርና የአርክቴክት ባለሙያ ዶክተር ዘገየ ቸርነት እንደሚሉት ከሆነ፤ በተለይ በአዲስ አበባ የህንፃ ግንባታው እንደ አሸን የፈላ መሆኑ እውነት ነው። ይህ የሚያሳየው በአንድ በኩል አቅም ያላቸው ሰዎች የመኖሪያ ቤት እጦት እንዳያጋጥማቸው ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ከተሜነትንና የከተማ እድገትን በሙላት ይገልፃል ለማለት አያስችልም።
‹‹ስለከተማ ያለን አስተሳሰብ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነና እንደ አገርም ገጠሬዎች ስለሆነን አብዛኛዎቻችን የከተማ እድገት የምንለካው በሚታይ ነገር ነው ›› የሚሉት ዶክተር ዘገየ፣ ‹‹ይህ የሚታይ ነገር ደግሞ የሚያንፃባርቅ ህንፃ እና አስፓልት ነው። ሌላው ቀርቶ ስንሰራ እንኳ የማይታየውን መሰረታዊ የሆነውን የመሰረተ ልማት ላይ እንኳን አናተኩርም ›› ሲሉ ይጠቅሱና፤ ‹‹ይህም ማለት ከመሬት በታች ለሚቀበሩት ነገሮች ብዙ ትኩረት አንሰጥም። ስራ የሚመስለን ከላይ ከላይ ያለው ነው›› በማለት ይናገራሉ።
ዶክተር ዘገየ፣ ‹‹የመንገዶችና የህንፃዎች መብዛት በራሱ አንድ ግብ ቢሆንም፤ ከተሜነትን እና የከተማ እድገትን በሙላት ይገልፃል ለማለት አንችልም ›› ይላሉ። በእርሳቸው አገላለፅ ከተማ የሚዳሰስና የማይዳሰስ መዋቅር ያለው ነው። ኢትዮጵያውያን ግን ብዙ ጊዜ የሚያሳስባቸው ከሚዳሰስ መዋቅር ይልቅ የባህሉ፣ የታሪኩና የመሳሰለው የማይዳሰሰው ነው። ያ ነገር ነው ወደ ፊዚካል መዋቅር የሚገለጠው።
‹‹ለዚህ ነው እኛ አርክቴክቶች ስናወራ ብዙ ጊዜ የከተማ ፊዚካል ስትራክቸር ስለማህበረሰቡ ምንነትና ማንነት ያለመዋሸት ያሳብቃል የምንለው። አርክቴክቸር ስለማንነታችን አሳባቂ ነው። አሁንም ከተሞቻችን ሲታዩ ይህንኑ የሚያሳብቁ አይነት እንደሆኑ የሚታወቅ ነው።›› ይላሉ።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የሕንፃዎች መብዛት አንዳንድ ጥያቄዎችን ይመለሳል። ለአብነትም የመጠለያ ቤት ፍላጎትን ሊያሳካ ይችላል፤ እንዲሁም ደግሞ የመንገዶች መብዛት የትራንስፖርት ስርዓትን ያመላክታል። በሌላ መንገድ ደግሞ በማስተዋል ሲመረመር የሕንፃዎች እንደ አሸን መብዛት የሚያሳብቀው ሌላ ነገር ደግሞ ያመለክታል። እንደሚታውቀው ህንፃ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራው ከቤት ፍላጎት ብቻ የመነጨ በመሆኑ አይደለም። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቤት መግዛት አይችልም። ለምሳሌ የሚሰሩ ሪል ስቴቶችን የሚገዛው ዳያስፖራው ነው ቢባል፤ እሱ የሚገዛው በይበልጥ ገንዘብን ለማስቀመጥ አሊያም ገንዘቡን ለማሸሽ እንዲረዳው ነው።
‹‹ይህ ማለት ገንዘብ ወይም ሀብት ማስቀመጫ ሌላ አማራጭ ስለሌለ የምናውለው ፊዚካል ሀብት ብቻ ላይ ነው። ይህ ደግሞ የሚያሳብቅብን ሌሎቹ ኢንዱስትሪዎቻችን ሌሎቹ የማምረት አቅሞቻችን፣ የኢኮኖሚም ሴክተሮቻችን በጣም ደካማ ስለሆኑ የሀብት ማሸሽያችን እና ማጠራቀሚያችን ህንፃ ብቻ ሆነ።›› በማለት ነው ዶክተር ዘገየ የሚያስረዱት።
ይሁንና እርሳቸው እንደሚናሩት፤ ከጥቂት ዓመት በኋላ እነዚህን ህንፃች የሚከራይ አቅም ያለው መካከለኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለሌለ ባዶ መቅረታቸው አይቀርም። በአንድ ወቅት መቀሌ በሄዱበት ወቅት አንድ ያስተዋሉት ነገር ቢኖር ልክ እንደሌላውም አካባቢ ብዙ የተሰሩ ህንጻዎችን ነው፤ አቅም ስለሌ ግን የሚከራየቸው የለም፤ በተመሳሳይ በአዲስ አበባም እንዲሁ ያላለቁ ቤቶች ይታያሉ፡ እነዚህ ህንፃዎች፤ ለሚያያቸው ሰው የሚያሳብቁት በሽታ አለ። ይህን ለመረዳት ውስብስብ ወደሆነው የህንፃ ስነ ትንታኔ ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ የሚጠቅሱት ዶክተር ዘገየ፣ ነገር ግን ከከተሜነት አንፃር ከተማ ሲስተዋል የኢኮኖሚ መዋቅር ስለሆነ ከዚህ አኳያ እነዚህ ህንፃዎች እንደ አሸን መፍላታቸው የኢኮኖሚ ጥመት እንዳለ የሚያሳይ ሆኖ ነው ያገኟቸው።
‹‹አሜሪካን አገር እኤአ 2008 ላይ የዓለም የኢኮኖሚ አስጊ ሁኔታ የጀመረው በሪልስቴት ነበር። ሰው ያላቅሙ ገዝቶ ገዝቶ መክፈል ያቃተው ወቅት ነበር። ይህ ደግሞ ይዞት የወረደው ባንኩንም ኢንሹራንሱንም ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያም ብትሆን ይህ ጉዳይ ያስፈራታል። ምክንያቱም እንደ አሸን የፈላው ህንፃ ማምረት የማይችል ሴክተር ነው። ለጊዜው ኮንስትራክሽኑ ኢኮኖሚውን አንቀሳቅሷል። ለወጣቱም የስራ እድል ፈጥሯል። ይሁንና ኢንዱስትሪውም አላደገም። ስለዚህ በከተማው የህንፃው እንደ አሸን መፍላት በአንድ በኩል የተወሰነ ነገር ቢኖረውም፤ በሌላ በኩል ግን የሚያስፈራ ነው።››
ዶክተር ዘገየ፣ ‹‹ስለዚህም ከተማ የሚለውን ነገር የምንረዳበት መንገድ የተንሻፈፈ ነው የምንለው ለዚህ ነው።›› ሲሉ ይናገሩና፤ ‹‹በመሆኑም መንሻፎቻችንን ሁሉ እንደ እድገት መቁጠር ስህተት ነው።›› በማለት ነው የሚያስረዱት። እንዲህም ሲባል ግን ሁሉም ነገር ስህተት ነው ለማለት እንዳልሆነም መገነዘቡ ተገቢ እንደሆነ ያመለክታሉ።
የኢኮኖሚና የእድገት አካሄድ ሚዛኑን የጠበቀ ካልሆነ አንዱ ሌላውን ሊያጠፋ እንደሚችልም ተናግረው፤ ‹‹አሁን ኮንስትራክሽኑን ማቆም አንችልም፤ ምክንያቱም ብዙ ህዝብ በስራው ዘርፍ ቀጥሮ የያዘልንን እሱ ስለሆነ ነው።›› ብለዋል። እሱ ከቆመ በርካታ ወጣት ስራ ፈት ይሆናልና ማቆም የሚቻለው በሂደት እንደሆነ አስረድተዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ አማካሪ አቶ ሄኖክ ባለሟል በበኩላቸው፤ የህንፃዎች መብዛት ከተማነትን በደንብ የሚያሳይ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ቀደም ሲል ወደጎን ይሰፋ የነበረው ከተማ አሁን አሁን ደግሞ ወደ ላይ እያደገ መምጣቱን እንደሚያመለክትም ያስረዳሉ።
አማካሪ አቶ ሄኖክ አክለውም እንደገለፁት፤ በፊት ወደ ጎን በመለጠጥ ሰፊ ቦታ ይፈልጉ የነበሩ አካሄዶች ቀርተው ቦታውን በአግባቡ ለመጠቀምም የራሱን አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛል። ስለዚህ በርካታ ፎቅ መኖሩ ከተሜነትንም የከተማውንም እድገት ያሳያል ማለት ነው።
‹‹ነገር ግን የህንፃዎች መብዛቱ ብቻውን በቂ አይደለም።›› የሚሉት አማካሪው፣ ‹‹ምክንያቱም የምናያቸው ህንፃዎች ብዙዎቹ ኢትዮጵያን የሚያሳዩ እና የሚመስሉ አይደሉም።›› ሲሉ ይናገራሉ። ብዙዎቹ ከተለያዩ አገሮች በተለይ ደግሞ ከአረብ አገራትና ከአውሮፓ የተኮረጁ ናቸው። ብዙ ጊዜ ደግሞ አርክቴክቱን የሚያስገድደው ባለሀብቱ ነው፤ ባለሀብቱ አርክቴክቱ እንዲሰራለት ነው የሚያደርገው ከአንዱ አረብ አገር አሊያም አውሮፓ አገር ያየውን ዲዛይን ነው። ከዚህ የተነሳ በአገሪቱ ካሉ ህንፃዎች ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሉ ትንሽ ናቸው። ህንፃዎቹ የየአገራቸውን ባህልና ወግ የሚያንፀባርቁ መሆን ቢችሉ መልካም እንደነበርም ጠቅሰው፤ ‹‹እንደአለመታደል ሆኖ የእኛ ህንፃዎች ያን ሲያደርጉ አይስተዋልም።›› ብለዋል።
አቶ ሄኖክ እንደሚሉት፤ ይህ አሰራር እንዲቀየር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክፍለ ከተሞችን የሚያስገድድ ማኑዋል አዘጋጅቷል። በተለይ አንድ አካባቢ የሚሰሩ ፎቆች ቢያንስ አካባቢያቸውን እንዲመስሉ ብሎም በቁመታቸውም ሆነ በቀለምና በቅርፃቸው እንዲመሳሰሉ ለማድረግ እየተሰራና ነው። ከዚህ በኋላ የሚሰሩ ህንፃዎች የተለያዩ መሆን የለባቸውም። ክፍለ ከተሞች ‹በዚህ አካባቢ መሰራት ያለበት እንዲህ አይነት ህንፃ ነው› በሚል በተዘጋጀው ማኑዋል መሰረት እንዲሰራ የሚያደርጉ ይሆናል።
ለአብነትም ሲጠቅሱ ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብሄራዊ አካባቢ አንድ ግለሰብ ህንፃ ልስራ ካለ መነሻ ሁኔታውን ከሚኒስቴሩ ይወስዳል። የህንፃው ቁመት፣ ቀለምና ሌሎችም መሆን ያለባቸውን ከግምት በማስገባት ነው መስራት የሚችለው። ክፍለ ከተሞች በዚህ መልኩ አስገዳጅ የሆኑ የከተማ ዲዛይኖች እንዲተገበሩ የሚያደረጉ ይሆናል። ቢያንስ ዝብርቅርቅ ብሎ ይሰራ የነበረውን ህንፃ በተወሰነ መልኩ እንኳ ተመሳሳይነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው እየተሰራ ያለው።
‹‹ልክ በአንድ አካባቢ የሚሰሩ የአውሮፓ ከተማዎችን ብናስተውል በብዙ ነገራቸው ተመሳሳይ የሆኑ ናቸው፤ እንዲሆኑም አስገዳጅ ህግ ስላለም ነው በዛ መልኩ የሚሰሩት። በእኛ ከዚህ በኋላ የሚሰሩ ህንፃዎች በቁመታቸውም ሆነ በቀለማቸው ተመሳሳይ እንዲሆኑ ኃላፊነቱን ለየክፍለ ከተማው ሰጥተን እንዲሰሩ የምናደርገው በዛ መልኩ ነው፤ በእርግጥ ይህ አሁን ላይ ተግባራዊ አልሆነም። ነገር ግን ብዙ ችግሮችና ስህተቶች ስላሉ ከዚህ በኋላ ወደማስገደዱ የሚገባ ይሆናል።›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
አስቴር ኤልያስ