በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቅ ዙሪያ ያለፉት ስምንት ዓመታት ከስምምነት ሊደረስባቸው የሚገቡ ነበሩ። በነዚህ ጊዜያት ሁሉ፤ ግብጾች ስልታዊ በሆነ መልኩ የእነርሱን ጥቅም ብቻ በሚያስጠብቅ መንገድ ለመደራደር ሲጥሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ግን ሁል ጊዜም የነበራትና ያላት አቋም ውሃውን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንጠቀም የሚል ነበር አሁንም እንደዛው። ለአባይ ወንዝ 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታበረክተው ሀገራችን እዚህ ግባ በሚባል መልኩ የወንዙ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች ። በተፃራሪው ደግሞ ለወንዙ ምንም አስተዋጽኦ የሌላት ግብፅ የበለጠ ተጠቃሚ ሆና ኖራለች።
ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ታሪክ እንደሚያስረዳው ቅኝ ገዥዎች ለራሳቸው ጥቅም ያስቀመጧቸውን ኢፍትሀዊ ስምምነቶችን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመጥቀስ እራሷን እንደ ልዩ ባለ መብት በማድረግ ስትከራከር ቆይታለች ዛሬም እየተከራከረች ትገኛለች ። በአባይ ጉዳይ አለቃም ጠበቃም መሆን ያምራታል፤ የተፋሰሱ አገራት ዋና ጠበቃ መስላ ስትከራከር ኖራለች። በ1929 እና በ1959 በቅኝ ገዢዎች የተካሄዱት ስምምነቶች የዚህ ማሳያዎች ሲሆኑ፤ ስምምነቶቹ ኢፍትሃዊ የግብፅን ተጠቃሚነት ብቻ የሚያስጠብቁ ነበሩ።
በኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም እንኳ ግብጻውያን 98 በመቶ ህዝባቸውን በኤሌክትሪክ ሲያዳርሱ ኢትዮጵያ የዜጎቿን 50 በመቶ ኤሌክትሪክ ማዳረስ አልቻለችም። የህዳሴ ግድብ የአገሪቱን የኤሌክትሪ እጥረት ቀርፎና አዳርሶ ለጎረቤት አገራትም ጭምር የሚተርፍ በረከትና የገቢ ምንጭ የሚሆን ነው። ነገር ግን ከፍትሃዊነት ይልቅ አጉል ወገንተኝነት ባደላበት የዓረብ ሊግ ባካሄደው ስብሰባ ከግብፅ ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ለማውገዝ ሞክረዋል። “ውሾቹ ቢጮኹም ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል” እንደሚባለው ግድቡ ግን በመገንባት ላይ ይገኛል። በስብሰባው ላይ የነበረችው ሱዳን ግን ተቃውማዋለች፤ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የቅርብ ተጠቃሚ የምትሆንበት መንገድ በማወቋ ወይም ፍትሃዊነትን በማስቀደም ብቻ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን አስመስክራለች።
ሱዳናውያኑ ከጎረቤትና ከአካባቢው አገራት ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ የአባይ ተፋሰስን ከግጭት ቀጠናነት ይልቅ የዕድገት ማዕከል ለማድረግ በኢትዮጵያውያን እየተከናወነ ያለውን ተግባር እንደሚደግፉ ገልፀዋል። የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅም የአቅማቸውን ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ ማረጋገጣቸውን በመገናኛ ብዙሃን በቅርቡ መገለፁ ይታወሳል።
የአልጀዚራ ዓረብኛ ፕሮግራም ጠቅሶ አዲስ አድማስ በቅርቡ ባስተላለፈው ዜናም በህዳሴው ግድብ ላይ ግብጽ የያዘችው አቋም እንደማያዋጣት የሱዳን ታዋቂ ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት መምከራቸውንና አገሪቱ ኢትዮጵያን ይቅርታ ጠይቃ ወደ ሦስቱ አገራት የድርድር መድረክ እንድትመልስ መጠየቃቸውን ዘግቧል።
በቅርቡ በተካሄደ ድርድር ግብፅ፣ ከህዳሴ ግድቡ የሚለቀቀውን ውሃ ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እንዳያንስ፣ በግብፅ የሚገኘው ትልቁ የአስዋን ግድብ የውሃ መጠን ከባህር ወለል በታች 165 ሜትር ከወረደ በአፋጣኝ ውሃ ከህዳሴ ግድቡ እንዲለቀቅላት፣ የህዳሴ ግድብ ከ12 እስከ 20 ዓመታት ባላነሰ ጊዜያት እንዲሞላ፣ እንዲሁም የግድቡ ሙሌትና የውሃ አለቃቀቅ በየዓመቱ በሚኖረው የድርቅና የአየር ንብረት ሁኔታ ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የሚሉ ነጥቦችን አንስታለች። በዚህ ሂደት የዓለም ባንክና አሜሪካ አዳራዳሪ መስለው ገብተው ኢትዮጵያን ለመጫን ቢሞክሩም ተቀባይነት አላገኙም።
አንድ ቀን በኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ይገደባል የሚል ሥጋት የነበራቸው ግብጾች፤ ብዙ መሰናክሎች ሲፈጥሩ ቆይተዋል። አገሪቱ ግን ቀደም ሲል መዘግየቶች ቢኖሩም አሁን ግድቡን እያጣደፈችው ትገኛለች። ብድርና እርዳታ ሳትሻ የታላቁ ህዳሴ ግድብ 70 በመቶ ማድረስ በራሱ የታሪካዊ ድል መሠረት ነው። የውጭ እርዳታ ብድር እየጠበቁ እጃቸውን አጣምረው ለተቀመጡ የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆን የምንችልበት፣ ድህነትን የምንዋጋበት፣ ልማትንና ብልጽግናን የምናስፋፋበት ሌላ የዓድዋ ድል ተደርጎ የሚቆጠርበት ይሆናል።
ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ የህዳሴ ግድብ በተመለከተ በተዘጋጀ የምሁራን የምክክር መድረክ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደ ማርያም ‹‹የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለእኛ የነብር ጭራ ነውና ይዘነዋል፣ ከሰማይ በታች ባለ ምንም ኃይል አንለቀውም። ምክንያቱም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ከድህነት መውጫና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን፣ የትውልዳችን ትልቅ ታሪክ፣ ትልቅ አሻራና ሌላው ዓድዋችን ጭምር ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል።
ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደ ማርያም አክለውም ‹‹የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የእያንዳንዳችን የግል ጉዳይ ነው፤ ሁላችንም ያገባናል። ግድቡ የእኔ ነው፤ ግድቡ የእኛ ነው፤ የሚል ጠንካራ የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። በመሆኑም ዛሬም እንደ ትናንቱ ሕዝባችን ለፕሮጀክቱ ስኬት አስፈላጊ ዋጋ ሁሉ ለመክፈል በቁጭት ፍላጎቱን እየገለፀ ይገኛል።›› ብለዋል።
ግብጾች የኢትዮጵያን መንግሥትና ህዝብ ሊወጋ የሚችል አካል ሲፈጥሩ፤ መሣሪያ ገንዘብ እና ስልጠና በማመቻቸት ተባባሪዎች ሲሆኑም ኖረዋል። ከ1960ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ ተቃዋሚ ድርጅቶች በማበረታታት እና በመርዳት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ለማዳከም ብዙ ጥረቶችን አድርገዋል። የኢትዮጵያን መንግሥትና ህዝብ ሊወጋ የሚችል አካል ሲፈጠር መሣሪያ ገንዘብ እና ስልጠና በማመቻቸት ግብጾች ተባባሪዎች ናቸው። ይኸውም ኢትዮጵያውያን ርዕስ በርዕስ ሲጋጩ አባይ ያለ ሥጋት ለመጠቀም ያስችለናል ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው።
ደርግ የርዕስ በርዕስ ግጭት ውስጥ ሲገባ እና ጦርነት በሰሜንና በምዕራብ አካባቢዎች ሲወጠር ኢትዮጵያን ለማዳከም ወሳኝ ጊዜ ተገኘ በሚል የሶማሊያውን ዚያድ ባሬን ጦር በመርዳትና በማስታጠቅ የውክልና ጦርነት አካሂደዋል። የተፈራውን የሶማሊያ ጦርነት ወታደራዊው ደርግ በአጭር ጊዜ ስልጠና ድምጥማጡን አጥፍቶ የዚያድ ባሬን ጦርና አጋሮቹን ሐፍረትን አከናንቧል።
ከላይ የጠቀስናቸው የተወሰኑ ግጭቶች መነሻቸው ምንም ይሁን ምንም በውክልና የተከፈቱ ነበሩ፤ ይህም ኢትዮጵያ ከተረጋጋች አባይን ትገድባለች በሚል ፍራቻ ነው። የአገሪቱ ሰላም የሚረጋገጠው የአባይ ወንዝ ሲገደብና ዜጎቻችን ተጠቃሚ መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው። ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ በውክልና ጦርነት ሲከፍቱብን የነበሩት ወዳጆቻችን ተስፋ ቆርጠው ጦራቸውና ገንዘባቸውን በነፃ አውጪዎች ስም ከመርጨት ተቆጥበው ይቀመጣሉ፤ የኢትዮጵያንም በወንዙ የመጠቀም መብት ሳይወዱ በግድ ያረጋግጣሉ። አገሪቱ ዘላቂ ሰላም የምታገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተገድቦ ለዘመናት ሳትጠቀምበት የነበረችውን አባይን የሀገር ሲሳይ ታደርገዋለች።
በግድቦቻችን ኃይል በማግኘት ከራሳችን አልፈን ለጎረቤቶቻችን እንተርፋለን። የዓለም ባንክ ከሦስት ዓመት በፊት ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆነ ዜጋ 44 ሦስት 3 በመቶ ሲሆን፣ የግብፅ ደግሞ መቶ በመቶ ነው። ግድቡ ድህነትን የምንዋጋበት ብልጽግናን የምንቀዳጅበት ነው። ከዚህም በላቀ ማገዶ ፍለጋ በሚል የሚጨፈጨፍ ደን ለማስቆም የሚረዳ ነው። በአባይ ጉዳይ የበይ ተመልካች የማንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ በተዘዋዋሪ ለግብፅም ልማት ነው። ደን ሲለመልም በአገሪቱ በሞቃታማው አየር ምክንያት በትነት የሚባክነው የአባይ ወንዝ አይኖርም፣ ዝናብም ያመጣል ወንዙም ክረምትን ሳይጠብቅ ይሞላል ለግብፅም ተስፋ ነው።
የአልጀዚራ ጋዜጠኛ መሐመድ ቫል በቅርቡ በግድቡ ላይ ባስተላለፈው ዘገባ በግድቡ አካባቢ በእንጨትና በኩበት ጭስ እየተንገላቱ ምግብ ስለሚያበስሉ እናቶች ጎስቋላ ህይወት አሳይቷል። ይህም ግድቡ ለኢትዮጵያውያን ተገቢ መሆኑንም ማስረጃ ነው፤ ጋዜጠኛው እንደዘገበው “ ምናልባትም በትዕግስት ለዘመናት የጠበቁት ኢትዮጵያውያን ከአባይ ወንዝ የትዕግስታቸውን ጣፋጭ ፍሬ የሚቀምሱበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ።”
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
ይቤ ከደጃች ውቤ