አርክቴከት ቁምነገር ታዬ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸርና አርበን ፕላኒንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአድቫንስድ አርክቴክቸራል ዲዛይን አግኝተዋል። ስለ አዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ እንዲሁም ከከተማዋ ፕላንና እቅድ ጋር በተያያዘ ከመጠን በላይ በመስፋቷና በሚታዩት ችግሮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከእኚህ ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- በአርክቴክቸር ላይ ለምን ያህል አመት ሰሩ?
አርክቴክት ቁምነገር፡- በማስተማርና በመስክ ፕሮጀክቶች በአጠቃይ ለ14 አመት ሰርቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡ -የት የት ሰሩ?
አርክቴክት ቁም ነገር፡- በአዲስ አበባ የተለያዩ ሪል ስቴቶች፣ ትልልቅ ሕንጻዎች፣ እንደ ሕብረት ባንክ የመሳሰሉ ባለ 30 ወለል ህንፃዎች፤ የአዋሽ ባንክ የሐዋሳ ቅርንጫፍን፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቤተመፅሐፍት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም ላሊበላ ከተማ ላይም አንድ ሆቴል ሰርቻለሁ።
ባሕርዳር የአማራ ብድርና ቁጠባ ሕንጻን፣ በሱሉልታ የተለያዩ እንግዳ ማረፊያዎች (ገስት ሀውስ) የመሳሰሉትንና ሌሎችንም ሰርቻለሁ። አርክቴክቸርነት በተግባር ብዙ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ እየተገኘ እያደገ የሚሄድ ሙያ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከአርክቴክቸር አንጻር ዘመናዊ የከተማ ፕላን ምን መሆን አለበት?
አርክቴክት ቁምነገር፡- መጀመሪያ የከተማ ልማት እቅድና ፕላን ሰው ተኮር መሆን አለበት። ሰው ማዕከል ከተደረገ ዲዛይን ሲደርግ ቅድሚያ የሚሰጠው ለምን መሆን እንዳለበት በትክክል ይታወቃል። መንገድ የሚሰፋው ለመኪና ነው ወይስ ለብስክሌት መጠቀሚያ ነው የሚበረታታው? ምንድን ነው? የንግድ እንቅስቃሴዎች በጠቅላላ የሚፈቀዱት ለባለሱቆች ወይስ ለአጠቃላይ ሻጮች? የሚፈለገው ምንን መቆጣጠር ነው? ሕዝቡ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን የመኖሪያ ቤቶች ይሰራሉ፤ በስፋት ይቀርባሉ የሚሉት ጉዳዮች በስፋት መታየት ያለባቸው ናቸው። አማራጮቹ ሕዝብ ተኮር (ሰው ተኮር) ሲሆኑ፣ ለሰው የተሻለ ተስማሚ ምቹ የሆነ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር አንጻር ታሳቢ ይደረጋል።
ቀደም ባሉ ጊዜያት የተወሰኑ የአዲስ አበባ አካባቢዎችን ከመኪና ነፃ በማድረግ በእግር የሚኬድበት ይደረግ በሚል የሚነሱ ሀሳቦች ነበሩ። ይሄ የድሮው አርበን ፕላኒንግ (የከተማ ፕላን) ሀሳብ ላይም የነበረ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ እንቅስቃሴ ይታወቃል። አዲስ አበባ እንደነሐዋሳ እና ባሕርዳር ለጥ ያለች ሜዳ ስላልሆነች ሙሉ እንቅስቃሴን በእግር ወይንም በብስክሌት ለማድረግ ያስቸግራል። ቀድሞ ሲሰራበት ከነበረው በላይ አዳዲስ ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ነገሮች መጨመር ነበረበት፤ እስከ አሁን ድረስ መጨመር ያለበት አልተጨመረም። ወደፊት ግን የበለጠ እየታሰበበት በሂደት መጨመር ያለበት እየተጨመረ ለሰው ምቹ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ የሳይክል እና የእግረኛ መንገዶችን የመሳሰሉ አማራጮችን ማካተት እና ለውጥ ለማምጣት መደረግ የሚገባውን ለማድረግ ያልተቻለው ለምንድነው?
አርክቴክት ቁምነገር፡- አዲስ አበባ ስትቆረቆር ጀምራ ወጣገባና ዳገት የሚበዛባት ከተማ ናት። ይህን ደግሞ ምቹ ለማድረግ ቀላል አይደለም፤ ከባድ ነው። እኔ አሁን ጠዋት እየተነሳሁ ብስክሌት እጠቀማለሁ። ሐዋሳ፣ ደብረብርሃን፣ አዳማ ወይም ባሕርዳር ሄጄ ብስክሌት እንደምጠቀመው አዲስ አበባ መጠቀም ግን አልችልም። ሜዳ ሜዳውን እየፈለግኩ ካልሄድኩ በስተቀር፤ ዳገታማና ተራራ ሲሆን፣ የበለጠ ጉልበት ይጠይቃል። ብስክሌት ይዞ ተራራ እና ዳገት በሆነ ቦታ ላይ እየነዱ ወደስራ መሄድ አይቻልም። ምክንያቱም ቢሮ ሲደርሱ ካልታጠቡ ሙቀትና ላብ ይዞ መስራት አይቻልም። የመሬት አቀማመጡ ይዞት የሚመጣው ችግር ቀላል አይደለም። ከላይ የሚታሰበውን ወደ ተግባር ለማዋል አንዱ ትልቁ እንቅፋት አቀማመጡ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቱ ከተሞች በተለምዶ አሰራራቸው በሰፈራ መልክ የተመሰረቱ ናቸው። የከተማ ፕላን በተለያዩ የመሬት ገጾች ላይ የሚታቀደው እንዴት ነው?
አርክቴክት ቁምነገር፡- ከከተማ ፕላኒንግ አንጻር ባሕርዳርና ሐዋሳ በተሻለ መልኩ ፕላን ተደርገው የተመሰረቱ ከተሞች ናቸው። የመንገዶች እንቅስቃሴ እንዲሁም ሰው ላይ መሰረት ያደረጉ ፓርኮች አሏቸው። ሌሎቹም የከተሞቹ ስፍራዎች ሜዳማ ስለሆኑ አቀማመጣቸው ለእንቅስቃሴ ቀላል ሊሆን ይችላል። የአዲስ አበባ የከተማ ይዞታ ግን የተለያየ ወጣ ገባ መሆኑ አማራጮችን ለመመልከት ያስገድዳል።
ከፕላኒንግ አንጻር አዲስ አበባ ላይ የበለጠ መሰራት ይኖርበታል ለማለት እንጂ ሙሉ ለሙሉ አይመችም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ተራራ የሚበዛባቸው እነኮሎምቢያን የመሳሰሉ ሀገሮችና እንደ ቦጎታ፤ ሳን ፍራንሲስኮ ያሉ ከተሞች ከአዲስ አበባ ጋር ተመሳሳይ የመሬት ገጽ ያላቸው ናቸው። ቦታዎቻቸው በጣም ተራራ የሚበዛባቸው ናቸው። እነሱ በሀገራቸው ለችግራቸው የሰጡት መፍትሄ የሚገርም ነው። ለምሳሌ ከተራራ ወደ ተራራ የሚሄድ ኬብል ካር (በኬብል የሚሄዱ መኪናዎችን) መጠቀም አንዱ የትራንስፖርት አገልግሎት መንገዳቸው ነው። በኬብል ካር በወፍራም ሽቦ በተገመደ ገመድ ላይ በአየር ላይ የሚሄድ መኪና ከአንዱ የከተማው ጫፍ ወደ ሌላው የከተማ ጫፍ የከተማውን ነዋሪዎች ያጓጉዛል። ይህ አይነቱ አጠቃቀም በከተማው ውስጥ የአየር ብክለትን ይቀንሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ እንደ ባቡር አይነት ማጓጓዣዎች አሉ። እነሱን በማብዛት ሰውን ማንቀሳቀስ ይቻላል። በመሬት ላይ (ምድር) ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ እንዲሁም በዛው መጠን የመኪና ጋጋታና ትርምሱን መቀነስ ይቻላል። ይሄ አይነቱን አሰራር ወደ ኢትዮጵያ ቢመጣ አዲስ አበባ ላይ ከሚዘረጋው የኬብል ካር ማጓጓዣ ከአንዱ የከተማው ጥግ ወደሌላው የከተማው ጫፍ በተዘረጋው መስመር የአየር ላይ ጉዞውን ማቀላጠፍ ይቻላል። በሌላ በኩል ከተማዋን ከላይ ወደታች ከፍ አድርጎ በማሳየት የቱሪስት መስህብ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። እነርሱ በዚህ ዘዴና አሰራር በሚገባ ተጠቅመውበታል።
አዲስ ዘመን፡-ይሄን ለመስራት ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም አይጠይቅም?
አርክቴክት ቁምነገር፡- እነዚህና ሌሎችም አማራጮች ስላሉ ለችግሮች መፍትሄዎች መኖራቸውን ለማመላከት ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ እንደ አዲስ አበባ አይነት የመሬት አቀማመጥ ያላቸው አካባቢዎች የወሰዷቸውን መፍትሄዎች ለማሳየት ነው።
አዲስ አበባ ለመኖሪያ፣ ለባይስክሊንግ፣ ከብክለት በጸዳ ሁኔታ ለመኖር እንዲሁም ሰው ተኮር ለሆነ የከተማ ፕላን አትመችም ለማለት ሙሉ በሙሉ አንደፍርም። ለሚታዩት የቀደሙ የከተማዋ ችግሮችም ቢሆን መፍትሄ የሚሆኑ ሰፊ አማራጮች አሉ።
በቀድሞው ጊዜ ዚግዛግ የሆኑ መንገዶች ዶንኪ ፓዝ ይባላሉ። ድሮ አዲስ አበባ ስትቆረቆር ወይንም ትልልቅ ባለስልጣናት የነበሩት ፊታውራሪዎች እና ሌሎችም ሲሰፍሩ መንገዶችን ያወጡ የነበሩት አህያ በሄደበት መንገድ ተከትለው ነበር። እነዛ ነገሮች የእድገት መስመሩን ትንሽ አበላሽተውታል። ምክንያቱም ቧንቧ ሲዘረጋ በአንዱ ባለስልጣን በኩል እንዳይታለፍ ተብሎ ተዟዙሮ ይኬዳል። መንገዱን መቁረጥ ሲቻል ረዥም መንገድ ይኬዳል። ይህ ደግሞ ሀብት ያባክናል። ርቀቱ በጨመረ ቁጥር የውሀ ግፊቱን መጠን የበለጠ መጨመር የግድ የሚል እና የበለጠ ዋጋ ያስጨምራል።
በደንብ ዘልቆ ሲታይ የሚገኙ ዝርዝር ጉዳዮች አሉ። ወጣ ተብሎ ሲታይ ከተማዋን አሁን ባለችበት ደረጃ እንዴት ማሻሻል ይቻላል? ሲባል አንዱ ትልቁ ችግር የመኖሪያ ቤት ነው። አንዳንድ እየተሰጠ ያለው የመፍትሄ መንገድ በጣም ስህተት ነው። ለምሳሌ ኮዬ ፈጬ ላይ ተሄዶ የጋራ መኖሪያ ቤት ከተሰራ በኋላ እንደገና ከጫፍ ለቡ ላይ ይሰራል፤ አቃቂ ላይም እንዲሁ ይሰራል። ጫፍ ጫፍ እየተሄደ መሰራቱ የአዲስ አበባን ከተማ በጣም በመለጠጡ ውሃ እና ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ችግር ፈጥሯል።
ከተማው በተለጠጠ ቁጥር ችግሮች ይበዛሉ። እጅግ ተራርቀው ለሚኖሩት ሰዎች መሰረተ ልማትን ለመድረስ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ይሆናል። እንዲህ አይነት የሚለጠጡ እድገቶችን መቆጣጠር ያስፈልጋል። አኗኗራችን እንደ ሰለጠነ ሀገር መቀየር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ መቀየር ያለበት እንዴት ነው?
አርክቴክት ቁምነገር፡- መሀል ከተማው በቁመት በጣም መርዘም መቻል አለበት። ከተማው ወደ መሀል ከተሰበሰበ እና ከረዘመ አንደኛ የመሰረተ ልማት የ(ኢንፍራስትራክቸር) ወጪ ይቀንሳል። ትቦዎች ከርቀት አይዘረጉም። እዚሁ በቅርብ ተደርጎ ውሃ እና ኤሌክትሪክ የሚሰጥበት ሁኔታ ይስተካከላል።
ይሄ ሲሆን ሰው ለስራ ብሎ ረዥም መንገድ መጓዙን ይቀንሳል፤ ከለገጣፎ ቦሌ፣ ሜክሲኮ ወይም ጦር ኃይሎች ድረስ ሰው አይጓዝም። አንድ ሰው የሚጓዝበት ርቀት ከተቀነሰለት የቤተሰብ ወጪ ቀነሰ ማለት ነው። ይህ ማለት መቆጠብ እንዲቻልና የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖር ያግዛል ማለት ነው። በከተማ ውስጥ የአየር ብክለቱን መጠን ይቀነሳል።
ሰው መኖሪያና የስራ ቦታው በጣም ከተራራቀ የግድ መጓጓዣን ይጠቀማል። የህዝብ (ፐብሊክ) ትራንስፖርት ሲጠቀም ደግሞ በትንፋሽ የሚተላለፉትን ቲቢን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎች ይጋለጣል። የበሽታው ስርጭት ይባባሳል። አሁን እንደሚታየው የኮቪድ 19 አይነት የጤና ቀውስ ሲመጣ ደግሞ የበለጠ ችግር ይኖራል።
ኮሮኖ ቫይረስ ከመምጣቱ በፊት ሰው በእግሩ መሄድ በሚችልበት ርቀት ሳይቀር ፐብሊክ ትራንስፖርት ተጠቅሞ እንዲንቀሳቀስ ቢደረግ መልካም ነበር። ከተማን መለጠጥ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ችግርን የሚጨምር ነው። ሰዎችን በማቀራረብ ወደ መሀል ሰብሰብ በማድረግ ከተማዋ ጠበብ ብትል፤ የከተማው አስተዳደር ማቅረብ የሚችላቸውን የከተማ መሰረተ ልማት ወጪያቸውን ይቀንስላቸዋል። በእግር መሄድና መንቀሳቀስ ይቻላል። በዚህ መልኩ ለሕዝቡ የተሻለ አኗኗር ይፈጠራል። ከከተማው ወጣ የሚለውን አካባቢ ለሕዝቡ መዝናኛ ማድረግ ይቻላል።
ሰው በእግሩ እየተናፈሰ የሚሄድበትን አረንጓዴ አካባቢ፣ የብስክሌት መሄጃ መንገዶችን፣ የውሃ ማቆሪያዎች (አርቲፊሻል ሀይቅ) መፍጠር ይቻላል። ሰው እዛ አካባቢ ነፋሻ አየር እያገኘ ልጆቹን ብሎም ቤተሰቡን ይዞ ቁጭ ብሎ መዝናናት ይችላል። ይህ ማለት የተሻሉ ቦታዎች ተፈጠሩ ማለት ነው።
በከተማዋ ዳርቻ ያሉ ቦታዎች እንደዚህ መሆን ሲገባቸው አሁን ግን እያደረግን ያለነው መኖሪያ ቤቶችን አራርቀን እየሰራን መሀል ላይ ሊኖር የሚገባውን ሰዋዊ መሰረቶችን እያሳጣን ነው።
አዲስ ዘመን፡-ከከተማው በጣም ርቀው ከተሰሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉ ሰራተኞች ሊነጋጋ ሲል ይነሱና ከቤቱ ወጥተው ማታ ደግሞ በውድቅት ይመለሳሉ፤ ሌላ አማራጭ የለውም። ይሄም በቤተሰብና በማሕበራዊ ሕይወት ደረጃ ሰፊ መራራቅ መፍጠሩ ይነገራልና ጉዳዩን እንዴት ያዩታል ?
አርክቴክት ቁምነገር፡- ትክክል ነው። በዛ ርቀት ተጉዞ ጠዋት ወጥቶ ማታ ሲገባ/ስትገባ ይደክመዋል፤ ይደክማታል። ልጆቹን መንከባከብ፤ ማስጠናት አይቻልም። ሌሊት ለስራ መውጣት እንደሚገባ ሲታሰብ ደግሞ በጊዜ መተኛት እንደአማራጭ ይወሰዳል። ይሄ ሁኔታ በመጨረሻ ማሕበራዊ ቀውስ ያስከትላል።
አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ አቅጣጫዎች ከከተማዋ የራቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንዲሰሩ ሲታቀድ አርክቴክቸሮች፣ የከተማ ፕላንና እቅድ ላይ የሚሰሩ ጉዳትና ጥቅሙን የሚመዝኑ ሰዎች አልነበሩም ማለት ነው?
አርክቴክት ቁምነገር፡- አልነበሩም ማለት አይደለም። ለምሳሌ አመለካከቶችን ከፖለቲካ አንፃር እንደሚወስዱት ሰዎች እንየውና ሶሻሊዝምና ተቃራኒው ካፒታሊዝም አለ። ሶሻሊዝም ‹‹ለሁሉም ነገር መፍትሄ ነው›› ብለው የሚያምኑ ሰዎች ነበሩ። ያን ይዘው እስከ ጥግ ወስደው የመሳሪያ ኃይል ተጠቅመውም ቢሆን ለማሳመን ለማስረጽ ሞክረው ነበር።
አርክቴክቸር ሙያውም ላይ ስትመጣ እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ ሰዎች ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። ወደፊትም ይኖራሉ። የአስተሳሰብና የአመለካከት ነጻነት መሰረታዊ ሰብአዊ መብት ነው። ይሄን አከብራለሁ። አንደኛው አስተሳሰብ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ ሰብ አርባን ዴቨሎፕመንቶች አሉ። ከዋናው ከተማ ውጪ ትንንሽ ከተሞችን ራቅ እያደረጉ ይፈጥራሉ። እነዛ ሰዎች ከከተማው ከራቀው ቦታ መሀል ከተማ ወደሚገኘው ስራቸው በግል መኪናቸው ይገባሉ። ያንን የሚያደርጉት ይሄን አይነቱን አስተሳሰብ አዲስ አበባ ውስጥ ለምን አናመጣም የሚሉ ሰዎች ናቸው።
ሲሲዲ የሚባል ሪል ስቴት ወደ ለገጣፎ አካባቢ አለ። እዛ ያለው በጣም የሚገርም ማሕበረሰብ ነው። ማሕበረሰቡ በአንድ ሰፊ ግቢ የራሱ መግቢያ፣ መውጪያና መቆጣጠሪያ ያለው በሚገባ በግምብ የታጠረ አጥር ዙሪያውን ያለው ሲሆን፣ ሌላ ሰው እንዳይረብሸው ተደርጎ የተሰራ የውስጡ ሰላም ፍጹም አስተማማኝ የሆነ ነው። እዚህ ሰፈር ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች የሚሰሩት እዛ አካባቢ አይደለም። በየቀኑ የሚሰሩት አዲስ አበባ መሀል መጥተው ነው። እያልኩ ያለሁት እንዲህ አይነት ልማቶች አያስፈልጉም አይደለም። ሰው እንደ ምርጫው በነጻነት መኖር መቻል አለበት።
ይህን መሰል ልማቶች የሚመጡት ሀሳቡ ካላቸው ሰዎች ነው። ለተግባር መነሻ የሚሆኑት ንድፈ ሀሳቦች (ቲዮሪዎች) ናቸው። እንደነዚህ አይነት የንድፈ ሀሳብ እሳቤዎች (ቲዮሪዎች) ሰብ አርበን ዴቨሎፕመንትን የሚያቀነቅኑ ናቸው። አሜሪካ ወይም ሌላው አገር ላይ ያሉት ልማቶች ተሞክሮዎች አውሮፓ እንኳን ብዙ የሉም። እነዚህ ሰዎች በሚፈጥሯቸው መንደሮችና በዋናው ከተማ መሀል ራቅ ያለ ከፍተት ስላለ በመሀል ላይ የሚፈጠረውን ጉድለት ለመሙላት ሲባል መንግስት ጠብ ጠብ እያደረገ መስሪያቤቶችን በመሀከል ሲያስገባ ሰው ሲሰፍር የጋራ መኖሪያ ቤት ሲገነባ በሂደት ሩቅ መስለው ይታዩ ከነበሩት ጋር ሊገጥም ይችላል።
ከአዲስ አበባ እስከ ለገጣፎ ባለው ርቀትና መስመር ላይ እጅግ ብዙ ልማት አለ። ሰዎች 150 ፣ 300 ካሬ ሜትር ገዝተው እየገቡ፤ የጋራ መኖሪያ ቤት እየተሰራ፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደዛው አካባቢ እየተከፈቱ ሲሰሩ ንግዱ ሲስፋፋ፤ ወደ ኮተቤና አቃቂም እያለ ሌላም ዘንድ ሲሰሩ መስመሩ እየገጠመ ነው። ይህ ውሎ አድሮ በኋላ ተመልሶ ከፍተኛ ጫና የሚያመጣው በከተማ አስተዳደሩ ላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መፍትሄው ምን መሆን አለበት?
አርክቴክት ቁምነገር፡- ከተማውን ሰብሰብ ማድረግ መቻል ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የከተማ ኑሮን ሰው ውስጥ ማስረጽ ያለበት የከተማ አስተዳደሩ ነው። የሚቀጥለው ደረጃ ፕላኑ ከተማውን ወደ መሀል ሰብሰብ አድርጎ ወደ ላይ ማሳደግ፤ ረጃጅም ሕንጻዎችን በመገንባት ከተማው ሲሰበሰብ ብዙ ሰዎችን በአንድ አካባቢ ማስፈር ይቻላል።
ይህ ሲደረግ ብዙ ሰዎች ሲሰበሰቡ ዙሪያው ነጻ ይሆናል። ለአንድ ሺህ ሰው አፓርትመንት ከመስራትና ለአንድ ሺህ ሰው ባለ 200 ካሬሜትር ቦታ ከመስጠት ትልቁ ለውጥ የሚያመጣው እና ከተማዋን የሚያሳድገው የትኛው ነው ብሎ ማስላት ይቻላል። አዋጪው አፓርትመንቶችን መስራቱ ነው። ይሄ ሲሆን ሰፊው መሬት ነጻ ይሆናል። ለልጆች መጫወቻ፤ ለአዋቂዎች መሰብሰቢያ፣ መናፈሻ ቦታ፣ ጅምናዚየም፣ ላይብረሪ፣ የኳስ መጫወቻ ወዘተ ከተማ መሀል ማዘጋጀት ይቻላል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባ ሕዝቡ በየጊዜው እየሰፋና እየጨመረ የሄደባት መሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ጥሏታል። ይሄን ሁሉ ሊሸከም የሚችል የውሃ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረብ ተስኗታል። ይሄን ችግር ያከበደው የከተማው መለጠጥና መስፋፋት የህዝቡ መብዛት ነው የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ። እርሶስ በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አርክቴክት ቁምነገር፡- ለምሳሌ እኔ የምኖረው ልደታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነው። የውሃ አገልግሎት እየተሰጠ ቢሆንም፤ 7ኛ ፎቅ ላይ ስላለሁ በቂ ግፊት ስለሌለው ውሃው መውጣት አይችልም። በዛ ምክንያት ሌላውን አካባቢ ለማዳረስ ሲባል፤ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የምንኖረው ሰዎች ተሰባስበን ሌላ ታንከር ገዝተን ፓምፕ አዘጋጅተን ከታች የሚመጣውን ውሃ ሰብስበን እየተጠቀምን ነው። ይሄንን የከተማው መስፋት የፈጠረው ጫና ነው። ሰብሰብ ቢደረግ ወደጎን የሚገፋውን ውሃ በማሳጠር ወደላይ መግፋት ይቻል ነበር። ወደ ጎን ሁለትና ሶስት መቶ ሜትር ከሚገፋ ወደ ከፍታ 70 ሜትር ቢገፋ ቀላል ነበር። እንዲህ አይነት አማራጮችን ማየቱ የተሻለ ነው። የኤሌክትሪኩ ችግር ሀገር አቀፍ ጉዳይ ስለሆነ የሚሻለው መንግስት የሚፈታበትን መንገድ ማየት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመስመሮች ዝርጋታ (ውሃ፤ መብራት፤ ስልክ) ወዘተ ባለቤት አላቸው። ከከተማ ዲዛይንና ፕላኑ ጋር አብረው አይታዩም?
አርክቴክት ቁምነገር፡- ይታያሉ፤ የመብራቱን ችግር በተመለከተ ከመንግስት የሚጠበቀው ዋናው መፍትሄ እንዳለ ሆኖ ሶላር በማድረግ እያንዳንዱ ቤት ከግሪዱ ላይ (ከኤሌክትሪክ መስመር ቋቱ) ላይ የሚወስደውን መጠን እንዲቀንስ ማድረግ ይቻላል። እያንዳንዱ ሰው በኪሎ ዋት የሚፈልገውን ወርሀዊ ፍጆታ ከጸሀይ ብርሀን ከሚመነጭለት ሶላር መጠቀም መቻል አለበት። ይህን ማድረግ ይቻላልም።
በእርግጥ እነዚህ ነገሮች ገና ጥናቶቻቸው ጥርት ብለው አላለቁም። በጥናት ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው። ሰፊ ጥናት አድርጎ አማራጭ ለማቅረብ ጊዜ ሊፈልግ ይችላል። ነገር ግን አማራጮች አሉ። አርክቴክቸር ችግሩን ሊያቃልለው ይችላል። አንዱ ሕንጻ ራሱን እንዲችል ከተፈቀደለት በሶላርም ሆነ በሌሎች አማራጮች ከግሪዱ የሚወስደውን ሃይል መቀነስ ይቻላል። ትርጉም ያለው ለውጥ የሚመጣው ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰሩት ትላልቅ የኃይል ማመንጫዎች ስራቸው ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲችሉ ብቻ ነው።
አሜሪካ የምትተማመነው ሶላር ኢነርጂ ላይ አይደለም። ኤሌክትሪክ የምታመነጨው ከኒውክሊየር ኤነርጂ ነው። ኢንደስትሪዎቿን የምትደግፈው በዚህ ነው። ሶላር ፓነል ፋርም የሚባል አለ። በጣም ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ነው። እንደዛ ካልተደረገ በስተቀር ለኢንዱስትሪዎች ኃይል ማቅረብ አይቻልም። ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የስልጣኔው አካል ናቸው። ከተሞች የሚለወጡት የሚያድጉት ከኢንዱስትሪው ከሚወጣ ግብአት ነው። ከተሞችን በብሔራዊ ደረጃ ሊመጣ ከሚችለው እድገት ጋርም ማሰብ ይገባል።
ለአዲስ አበባ ከሶላር ፓናል ፋርም (በሰፊ የእርሻ መሬት ላይ ከተዘረጋ የጸሐይ ብርሀን ኃይል ማመንጫ) ወይንም ከዊንድ ኤነርጂ (የንፋስ ኃይል) ተጠቅሜ ኃይል አቀርባለሁ ቢባል እነዚህን ለማድረግ የሚያስችለውን ግዙፍ ሀገራዊ ወጪን ማሰብ ይጠይቃል። በኢትዮጵያ አሁን ቴክኖሎጂው የሚሰራበት አይደለም። በሂደት መስራት ይቻላል። ግን ደግሞ በምእራቡ አለም ራሱ ቴክኖሎጂው ገና እድገቱን አልጨረሰም። እዚህ መጥቶ ይመረትበት ቢባል በትናንሽ ደረጃ ሊሰራበት ይችላል። ትልልቅ ከተሞችን ሊደግፍ መብራት ሊያበራ የሚችል አቅም ግን ገና አላደገም፤ ጅምር ነው። እንደዚህ አይነቱን ስራ ለመስራት ባለሙያ ሃብት እና ካፒታልን ማዳበር ያስፈልጋል። እስከዛው በትንሽ ደረጃ መስራት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በእቅድም ሆነ ያለ አቅድ የከተማው ማደግና ከአቅም በላይ መለጠጥ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱን አባብሶታል። ከተማዋ ጨለማን ማሸነፍ ያልቻለችም ነች። ይህን ችግር ለመቅረፍና ከተማዋን በቴክኖሎጂ ጨለማዋን ለመግፈፍ እርስዎ ምን ይላሉ?
አርክቴክት ቁምነገር፤- በዋነኛነት ኢንደስትሪያል የሆኑ ለምሳሌ አዲስ አበባ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ አለ። ከተማው ሲያድግ ትላልቅ እድገቶች አብረው አሉ። የመኖሪያ ቤቶች ለሰራተኞች እየተሰሩ ትላልቅ የኢንደስትሪ ፓርኮችም እየተገነቡ ነው። ለእነዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ የሚቻልበት መንገድ የግድ ከንፋስና ከሶላር ፓነል ፋርም የኃይል ማመንጫ ጋር ብቻ የተያያዙ ላይሆኑ ይችላል። ከአለን የአቅምና የቴክኖሎጂ እድገት አንጻር ማለት ነው። ሀይድሮ ፓወርና የመሬቱን ውስጥ የጂኦ ተርማል የኃይል ምንጭ ለመጠቀም አማራጭ መፈለጉ የተሻለ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፤-ስለሰጡን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን።
አርክቴክት ቁምነገር-እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 6/2012
ወንድወሰን መኮንን