ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ይፋ ካደረገችበት ጊዜ ጀምሮ በመንግስት የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል። ሁኔታውን በመገምገምም አሁንም እስከ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደረሱ እርምጃዎች መወሰዳቸው ቀጥሏል። የጥንቃቄ እርምጃዎቹ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስና በስጋቱ ምክንያት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ህይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ማድረግን ታሳቢ አድርጎ እየተወሰደ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው። ለህዝብ ከቆመና ከወገነ መንግስትም የሚጠበቅ ነው። ከጤና ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሰረት እስከ ሚያዝያ 03 2012 ዓ/ም ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሠዎች ቁጥር 69 ደርሷል፡፡ በርካቶች በለይቶ ማቆያ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ሶስት ሰዎች በቫይረሱ የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ኮቪድ 19 ቫይረስ በኢትዮጵያ ጥላውን ያጠላባቸው ዘርፎች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ በተለይም የአገልግሎት ዘርፉ የተጎዳ ሲሆን፤ ከበዓል ጋር የተያያዙና ሌሎችም ሁነቶችን በማሰናዳት ተዋጥቶላት የነበረችው አዲስ አበባ፤ ከፍተኛ ገቢ የምታጣ ይሆናል፡፡ የዚህ ዘርፍ ትልቁ ክፋይና ዋልታ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቫይረሱ ከተስፋፋ በኋላ በመጀመሪያ ወደ 30 ቀጥሎም ወደ 80 አገራት ያደርግ የነበረውን በረራ አቁሟል፡፡ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ባለውለታ ነው የሚባልለት አየር መንገዱ፤ የ550 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደደረሰበትም በቅርቡ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መጋቢት 11 በሰጡት መግለጫ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጫና ማስከተሉንም አስታውቀዋል። ለአብነትም አየር መንገዱ በቫይረሱ መቀስቀስ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ማጣቱን ተናግረዋል። የወጪ ንግድ ዘርፉን በተለይም የአበባ እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ተቀባይ አገራት ምርቶቹን መቀበል በማቆማቸው ዘርፉ መቀዛቀዙንም እንዲሁ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የንግድ እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የምርት እጥረት እንዲገጥም ሊያደርግ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ናቸው፡፡ ይህም የዋጋ ንረትን ያስከትላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል፡፡
በትናንሽ ዘርፎች ላይ የተስተዋለውም ጫና በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን የሚጎዳ ነው፡፡ ዜጎች ካለ እቅዳቸው ቫይረሱን ለመከላከል ሲሉ ከቁጠባቸው ገንዘብን በማውጣት ግዥዎችን ይፈፅማሉ፡፡
አገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል የመደበችው አምስት ቢሊዮን ብር የመንግስትን ወጪ ከፍ ያደርጋል፡፡ ይህን ለመሸፈን የሚወሰደው እርምጃ ከሁለት አሀዝ ከፍ ያለውን የዋጋ ግሽበት ሊያሳድግ ይችላል የሚል ስጋትንም ደቅኗል፡፡ በሌላ ጎን ገንዘቡ (ለቫይረሱ መከላከያ የተመደበው) ፤ ቫይረሱ ባይከሰት ለሌላ ግልጋሎት ቢውል ሊያስገኝ የሚችለው ጠቀሜታ ትልቅ እንደነበር አይጠረጠርም፡፡ ይሁንና ከምንም ነገር በላይ የዜጎች ህይወት ቅድሚያ ይሰጠዋልና መንግስት ይህን ከግምት አስገብቶ የወሰደው እርምጃ የሚመሰገን ነው።
መንግስት ባለው አቅም በአንድ ወገን ወረርሽኙን ለመከላከል በጽናት እየሰራ በሌላ እጁ ደግሞ ኢኮኖሚው በጣም እንዳይጎዳ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። በተለይም ባለሀብቶች በተቻለ መጠን ከምርት እንዳይስተጓጎሉና ከባንክና ከግብር ጋር በተያያዘ ያለባቸው ጫና እንዲቀንስ አበረታች እርምጃዎችን ወስዷል። ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እና በአፍሪካ የሚያስከትለውን ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ለመቀነስ የሚያስችል ባለ ሶስት ነጥብ የድጋፍ ምክረ ሃሳብ ለቡድን 20 አባል ሀገራት አቅርባለች፡፡
በአጠቃላይ ኮሮና በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ሊያሳርፈው የሚችለው ጠባሳ እስካሁን ይህ ነው ተብሎ በአሀዝ ባይገለፅም፤ ከፍተኛ እንደሚሆን ግን ከወዲሁ ተሰግቷል፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው ደግሞ በመንግስት፣ በባለሀብቱና በህዝቡ የተቀናጀና የተናበበ እርምጃ በመሆኑ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በማጤን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5/ 2012