የተወለዱት ሐረር ከተማ ውስጥ ቢሆንም ከአምስት ዓመታቸው ጀምሮ ያደጉትና የኖሩት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ይገኝ በነበረ ደብረዘይት በተባለ ትምህርት ቤት ተማሩ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው የጥቁር አንበሳ ህክምና ትምህርት ክፍል ገብተውም ለሰባት ዓመታት የህክምና ትምህርታቸውን በመማር በ1985ዓ.ም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰውን ባህሪ ማጥናት ይወዱ የነበሩት እኚሁ ሰው ታዲያ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ካገኙ ከዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ተመልሰው በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በ1999 ዓ.ም ያዙ፡፡ በተጨማሪም ፓቶ ባዮሎጂ የትምህርት ዘርፉ በትሮፒካል ዲዚዝ ማስተርሳቸውን ሰሩ፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ ሳርቤት በሚገኘው መንፈሳዊ ኮሎጅ ገብተው ሥነ-መለኮት (ቲዮዎሎጂ) ማስተርስ ለመማር ይጀምራሉ፡፡ ይሁንና ድንገት ወደ አሜሪካ የሚሄዱበት የግል ጉዳይ ያጋጥማቸውና የሥነመለኮት ትምህርታቸውን ከማስተርስ ወደ ዲፕሎማ እንዲቀየርላቸው በማመልከት ለዚያ የሚያበቃቸውን ትምህርት ተከታትለው ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ፡፡ ለትምህርት ልዩ ፍቅር ያላቸው እኚሁ ሰው አሜሪካም ሄደው ትምህርት መማራቸውን አላቆሙም፡፡ የሥነመለኮት ዲፕሎማቸውን ወደ ማስተርስ ማሳደግ ቻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በተለየዩ ከተሞችና ክሊኒኮች እየተዘዋወሩ በጤና ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ በማህበረሰብ ጤና ስፒሻሊስትነት እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በመንፈሳዊ አገልግሎትና የሥነ መለኮት ትምህርት በመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን አነቃቂ ንግግሮችን በማቅረብና የህብረተሰብ አስተሳሰብን በመቅረፅ ጉልህ ሚና እየተጫወቱም ይገኛሉ፡፡ የህክምና፣ የሥነልቦናና የሥነ-መለኮት ባለሙያ የሆኑት የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ በቅርቡ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አመራር ሆነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል፡፡ ከእንግዳችን ጋር በወቅታዊውና የዓለም መንግስታትንና ህዝቦችን በማስጨነቅ ላይ በሚገኘው ኮቪድ 19 (ኮረና ቫይረስ) ላይና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የህክምና ዶክተር ሆነው ሳለ ወደ መንፈሳዊው ትምህርትና አገልግሎት ውስጥ የገቡበት የተለየ ምክንያት ይኖሮት ይሆን?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ የህይወት ጥያቄዎች ነበሩኝ። በህይወት ውስጥ ስላለው ባዶነት ትርጉም እፈልግ ነበር። ለምን ሰው ተፈጠረ? የህይወትስ ትርጉም ምንድን ነው? እያልኩ ለመረዳት እሞክር ነበር። እነዚህ ጥያቄዎቼ ደግሞ ሃኪም ስሆን የሚመለስልኝ ይመስለኝ ነበር።
ይሁንና ትምህርቴን ሳጠናቅቅ እነዚህ ጥያቄዎች እንደማይመለሱልኝ ገባኝ። እንዳውም የተመረቅኩ ቀን ትልቅ ድብርት ውስጥ ነው የገባሁት። የዚያን ቀን እንዳውም ጥያቄዎቼ ያልተመለሱልኝ መሆኑን ሳውቅ ጠጣሁ። ለካ አንድ ነገር ስትደርሺበት ይቀልብሻል!። ህክምና ከጨረስኩ በኋላ አዳማ ቀን ቢሾፍቱ ደግሞ ማታ እየተዘዋወርኩ እሰራ ነበር። የማድረውም እዛው ክሊኒክ ውስጥ ነበር። በዚህ ስራ ውስጥ እያለሁ ለህይወቴ ጥያቄ ውስጤ ለሚሰማኝ ባዶነት ምላሽ የማገኘው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ እንደሆነ ገባኝ። ይሁንና በዚያ ጊዜ እጠጣለሁ፣ ጫት እቅማለሁ፣ ሲጋራ አጨሳለሁ፣ ናይት ክለብም እሄድ ነበር።
አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜ ሌሊት ተጥቼ አድሬ እሁድ ጠዋት ስነሳ ራሴን ሁሉ ለማጥፋት ፈለግኩ። እናም ከዚያ ህይወት ውስጥ ለመውጣትና የእኔም እውቀት ለውጥ ስላላመጣልኝ በሚገባኝ ቋንቋ ወደፈጣሪ እፀልይ ጀመር። በተጨማሪም አብረውን ይሰሩ የነበሩ የተለየዩ እምነት ያላቸው ሰዎች ሆነ ብዬ አከራክራቸውና እውነታውን ለማወቅ እጥር ነበር። አንዲት የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ባልደረባዬ መፃሃፍ ቅዱስ ሰጠችኝ፣ ሌላዋ ፕሮቴስታንት ባልደረባዬ ደግሞ የመዝሙር ሲዲ ላከችልኝ። የካቶሊክ ክርስቲያን ተከታይ የሆነች ጓደኛዬም ወደ ራሷ ቤተክርስቲያን ወሰደችኝ። ከዚያ መንፈሳዊ ዓለምን ወደድኩት። በጣም መፅሃፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመርኩ፤ መፀለይ አዘወተርኩ። በዚያው ሳላውቀው ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ትምህርቶችን ተምረዋል፤ አሁን በየትኛው የሙያ ዘርፍ እያገለገሉ ነው ያሉት?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የህብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ስለሆንኩኝ ክሊኒክ ውስጥ እንድሰራ አይጠበቅብኝም። ግን የማማከር ስራ እሰራለሁ። አንዳንድ ድርጅቶችን የማማከር አገልግሎት እሰጣለሁ። በምጋበዝበት ቦታሁሉ አስተምራለሁ፤ ስልጠና እሰጣለሁ። መንፈሳዊው አገልግሎትም አለኝ ። በተጨማሪም ራሴን የበጎ ፍቃድ አገልጋይ አድርጌ ለአገርና ለህዝብ ሰጥቼያለሁ።
በነገራችን ላይ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እንኳን መንግስት ጥሪ ሲያደርግ የበጎ ፍቃድ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ተመዝግቤያለሁ። እኔ እንዳውም አሜሪካ በሙያዬ እንዳገለግል ጥሪ ቀርቦልኝ ነበር ፤ እኔ ግን ፍቃደኛ አልሆንኩም። እዚህ ከህዝቤ ጋር ቆይቼ በበጎ ፍቃድ ለማገልገል ወስኛለሁ።
ስለዚህ አገሬ በምትጠራኝ ሁሉ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመስራት ራሴን አዘጋጅቼ ነው ያለሁት። አሁን ደግሞ የእናንተም ድርጅት የቦርድ አባል ሆኜ ተሹሜያለሁ። በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ፐብሊክ ዲፕሎማት ሆኜ የበኩሌን ሚና እየተጫወትኩኝ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ካነሱት አይቀር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አመራር እንደመሆንዎ በድርጅቱ ምን አይነት ለውጦች እንዲመጡ ይሻሉ? እርሶ በዚህ ረገድ ምን አይነት አስተዋፅኦ ለማድረግ አቅደዋል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ስንደረግ እኔ በግሌ በጣም ነው የተደሰትኩት። የተደሰትኩት የተለየ ጥቅም አገኝበታለሁ ብዬ አይደለም።
ነገር ግን ፕሬስ ድርጅት የእነ በዓሉ ግርማ ፤ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ስብሃት ገ/እግዚያብሄርና ጳውሎስ ኞኞ ቤት ነበር። የእነሱ አሻራ ያለበት፤ እነሱ የረገጡትን ቦታ መርገጥ በራሱ ለእኔ ክብር ነው። ከዚያ በተጨማሪ ድርጅቱ የሚያሳትማቸው ጋዜጦች የኢትዮጵያ ማስታወሻ ደብተር እንደሆነ አምናለሁ።
የኢትዮጵያን ታሪክን ለማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ወደ እናንተ ድርጅት መምጣት ያዋጣል ባይ ነኝ። ምክንያቱም የተደራጀ ሰነድ ማግኘት የሚቻልበት ተቋም በመሆኑ ነው።
የታመቀ የአገር ታሪክ ያለበት ስፍራ ነው። በተለይ አዲስ ዘመን ከስያሜው ጀምሮ ታሪካዊ በመሆኑ ለጋዜጣው ልዩ ክብር እንዳለኝ ለመግለፅ እሻለሁ። በመሆኑም ልክ ጥያቄው ሲመጣልኝ በደስታ ነው የተቀበልኩት። ከጠየቅሽኝ ጥያቄ አንፃር በድርጅቱ እንዲመጣ የምፈልገው ለውጥ በተለይም አዲስ ዘመን ጋዜጣ በተለያዩ መንግስታት ስር እንደማለፉ ጥቂት የማይባለው ህዝብ ልክ የመንግስት ልሳን አድርጎ ጋዜጣውን ማየት ፥ የመንግስትን ሃሳብ ብቻ የሚያንፀባርቅ የፕሮፖጋንዳ ማሽን አድርጎ የመቁጠር ነገር እንዳለ እረዳለሁ።
በመሆኑም ይህ ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዲለወጥ እፈልጋለሁ። ባለቤትነቱ የመንግስት ቢሆንም መንግስትንም ሆነ ሌሎችንም የሚተች፤ ህዝብ የእኔ ነው ብሎ የሚያምነው ጋዜጣ እንዲሆን እመኛለሁ። ያ ለውጥ እንዲመጣ ደግሞ የበኩሌን ጥረት ለማድረግ እሰራለሁ።
በተጨማሪም የድርጅቱ ሰራተኞች በአነስተኛ ደመወዝ እየሰሩ መሆኑን አውቃለሁ። እኛም ወደ ድርጅቱ ከመምጣታችን በፊት ድርጅቱ አትራፊ ሆኖ እያለ ነገር ግን ሰራተኞች እየሰሩ ያሉት በጣም በዝቅተኛ ደመወዝ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ስለዚህ የሰራተኞችን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ አምናለሁ። ምክንያቱም ሰራተኞች ተነሳ ሽነት ሊኖራቸው የሚችለው በሚገባው ልክ ሲከፈላቸውና ተጠቃሚ ሲሆኑ ነው።
ሰርተው ሲወጡ አንድ ወር የማያደርስ ደመወዝ ከሆነ የሚከፈላቸው ደስ ብሏቸው ሊሰሩ አይችሉም። ሰራተኞች ደግሞ ደስ ብሏቸው ሲሰሩ ለድርጅቱም መልካም ይሆናል ብዬ አምናለሁ። እናም ያ ለውጥ እንዲመጣ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ወቅታዊ ጉዳይ ስንመለስ አንዳንድ የእምነት ሰዎች የኮረና ቫይረስ መለኮታዊ ቁጣ እንደሆነ ይናገራሉ። እርሶ መለኮታዊ ወይም የፈጣሪ ቁጣ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ለእኔ የፈጣሪ ቁጣ ነው ወይም እግዚአብሄር ያመጣው ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ይሄ የነበረ ቫይረስ ነው። አልፋ ፣ ቤታ፣ ጋማ፣ ቤልታ የሚባሉ የኮረና ቫይረስ አይነቶች አሉ። ከእነዚያ ውስጥ ሰውን የሚጎዱ እንደ ኢንፊውሌንዛ አይነት ኮረናዎች አሉ።
በሌላ በኩል ሰውን የማይጎዱ ዞኖቲክ የሆኑ ግን ደግሞ እንስሳቶችን የሚያጠቁ የኮረና ቫይረስ አይነቶች አሉ። የእነዚህ ቫይረሶች አስገራሚው ነገራቸው የምታውቂው ቫይረስ ዘረመሉን ለውጦ አዲስ ሆኖ መምጣቱ ነው። በነገራችን ላይ ኖቭል የተባለው ኮረና ቫይረስ ራሱን አዲስ አድርጎ በመምጣቱ ነው። በተለያየ ጊዜ በተለያየ መልኩ መጥቷል። አሁን ደግሞ ቻይና ውስጥ ከእንስሳት ጋር የሚሰሩ ሰዎችን አዲስ ሆኖ መጥቶ ያዛቸው።
ከዚያ ወጥቶ ይኸው አሁን ዓለምን አዳርሷል። ስለዚህ እኔ በመፅሃፍ ቅዱስ የማውቀው እግዚአብሄር እንዲህ የሚያደርግ አምላክ አይደለም። ቫይረሶችን እየፈጠረና መድሃኒት የማይገኝለት ቫይረስ እያዘጋጀ አይረጭም!። እኔ የማውቀው አምላክ ከላይ ተቀምጦ «ጣሊያን ይህን ያህል ሰው ሞተ ፤ ስፔን ደግሞ ይህንን ያህል ሰው ተያዘ፤ እሰይ ጉልበቴን አሳየኋቸው» እያለ የሚቆጥርና የሚፎክር አምላክ አይደለም።
ከዚያ ይልቅ ፈጣሪያችንን አድነን፤ ታደገን ማለት መልካም ነው። ግን አንተ አመጣኸው ማለት ግን እንደገና እግዚአብሄርን መበደል ነው የሚሆነው። እሱን ክፉ አድርጎ፤ እሱን ጨካኝና ሰውን በማሰቃየት የሚደሰት አምላክ አድርጎ ማቅረብ እሱን እንደገና መበደል ይሆናል።
ይሁንና የሰው ልጆች ግን ንስሃ እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው። በደል በምድር ላይ በዝቷል፤ እውነት ነው። እግዚአብሄር ሊቀጣን ሲፈልግ ጥበቃውን ያነሳ ይሆናል እንጂ የሰው ልጆችን የማሳደድ ዓላማ የለውም። ከፈለገ እኮ ቫይረስ አያስፈልገውም። አብዛኛውን ምድር በውሃ የተሸፈነ አይደል? የሰው ልጆችን ለማጥፋት ከፈለገ በጣቱ ከልበስ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ስለዚህ የአምላክ ቁጣ ነው በሚለው ሃሳብ አልስማማም።
አዲስ ዘመን፡- በሽታው በሌሎች አገራት ቀድሞ የተከሰተ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ አስቀድማ በቂ ዝግጅት አለማድረጓ ከዚህ በላይ ዋጋ ያስከፍላታል ብለው የሚያነሱ ሰዎች አሉ። ይህ ስጋት ምን ያህል ተገቢ ነው ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብዬ አላምንም። ግን በቂ ዝግጅት ያልተደረገው በእንዝላልነት ወይም በቸልተኝነት ነው ብዬም አላስብም። ለምሳሌ የኢትዮጽያ አየር መንገድን እንውሰድ፤ መጀመሪያ አካባቢ እንደምታስታውሺው «በረራዎች መቆም አለባቸው» የሚሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ።
ግን ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በረራን ብናቆም ምንድን ነው የሚሆነው?። ብንቀጥልስ ምን ሊፈጠር ይችላል? ብሎ ጉዳቱንና ጥቅሙን የማመዛዘን ጉዳይ ነው። ሌላው በምክትል ከንቲባው አማካኝነት እንደተነገረው አዲስ አበባ አትዘጋም ተባለ፤ ለምን ይመስልሻል? ግዴለሽ ስለሆኑ ነው?። አየደለም።
አዲስ አበባን ብንዘጋት ለመከላከል ይጠቅማል። ግን ደግሞ ብዙ ሰው በረሃብ ይሞታል። ምክንያቱም በየቀኑ ወጥቶ ሰርቶ ማደር ያለበት የህብረተሰብ ክፍል በመኖሩ ነው። ከዚያ ወንጀሎች ይበራከታሉ። ሰዎች ሲቸገሩ የሚሆነውን ሲያጣ ከባህሪውን ከእሴቶቹ ወጥቶ ወደ ወንጀሎች ነው የሚገባው። ስለዚህ ሁለቱን ማመዘዘን ያስፈልጋል። እናም በመሪዎች ቦታ ሆነሽ ስታዪው እነዚህን ውሳኔዎች መወሰን ቀላል አይደለም።
ከዚህ አኳያ ጥረት ተደርጓል ብዬ አስባለው ። ነገር ግን በቂ ነው ብዬ ግን አላምንም። በሌላ በኩል ጥቂት የማይባለው የህብረተሰብ ክፍል በሽታው እኔን አይነካኝም ብሎ መዘናጋት ይታይበታል። ይህ ደግሞ ትልቅ ችግር እንደሚፈጥርብን አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳሉት አሁንም ድረስ አብዛኛው ህዝብ ዘንድ በሽታውን እንደቀላል የማየትና የመዘናጋት ችግር ይታያል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሚገባው በላይ በመጨነቅ ወደአላስፈላጊ መረበሽ ውስጥ የገቡም እንዳሉ ይታወቃል። እንደባለሙያ እነዚህን ነገሮች እንዴት አጣጥሞ መሄድ ይቻላል ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- በጣም ከተጨነቁት ስነሳ በግሌም ያየኋቸው ከመጠን በላይ የሚጨነቁ ሰዎች አጋጥመውኛል። የሚያስቡት በሙሉ ስለኮረና ብቻ ነው። ይሄ የሚያሳየው አስቀድሞ የስብዕና ቀውስ ያለባቸው መሆኑና ከልክ በላይ የመጨነቅ ችግር እንደፈጠረባቸው ነው። እንዲህ አይነት ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች በጣም ከመጨነቃቸው የተነሳ ሰው ይጨብጡና ሄደው ይታጠባሉ።
ምግብ ሲበሉ አንቺ የማታስቢውን ነገር ያስባሉ። ምግቡን ያዘጋጀው ሰው እጁን ታጥቦ ይሆን? አስሎት ይሆን ብለው ይጨነቃሉ። ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር መብላት እንኳን አትቺዪም። በባህሪም ደግሞ ከመጠን በላይ እንዲህ አይነት ጥንቃቄ የሚያደርጉ አሉ። ለምሳሌ የታጠበ ብርጭቆ አንስተው ብርሃን ላይ የሚያዩና ዳግመኛ የሚያጥቡ አሉ። ለእንደዚህ አይነት ሰዎች የኮረና መምጣት ከዚህ ቀደምም ከነበረባቸው ባህሪ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ጭንቀት ነው የሚፈጥርባቸው። በነገራችን ላይ ችግሮችን የመጋፈጥ አቅማችን እኩል አይደለም።
ለምሳሌ የሞት ቁጥሩ ማደጉን ስንሰማ የመቋቋም አቅሙ ከሰው ሰው ይለያል። ለአንዳንዱ ሰው ከሚቀበለው በላይ ሊሆንበት ይችላል። በእኛ አገር አይበለውና ከፍ ያለ የሞት ቁጥር መነገር ከጀመረ በጣም ብዙ ሰው የአዕምሮ ጭንቀት ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። በተጨማሪም የሞት ፍርሃትም አለ። ይህ የሞት ፍርሃት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል። ልጆች ያላቸው «ልጆቼን ሳላሳድግ ብሞት ልጆቼ ምን ይሆናሉ?» የሚሉ ደግሞ ለራሳቸው ሞት የሚፈሩ አሉ። ይሄ ችግር እንዳውም ብዙ ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም። በመሆኑ የአዕምሮ ሃኪሞች ህዝቡን በዚህ ሰዓት ማረጋጋትና ማፅናናት ይጠበቅባቸዋል።በሌላ በኩል ደግሞ ተገዶ መራራቅ ያልቻለ የህብረተሰብ ክፍል ነው ያለን። ይህም ሲባል አንዱ የስራና የኑሮው ሁኔታችን ለመራራቅ ትንሽ ከባድ ነው። ለምሳሌ አሜሪካኖችና አውሮፓውያኖች ቤታችሁ ተቀመጡ ተባሉ። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቤትና አፓርትመንት ስላለው ቆልፈው መቀመጥ ይችላሉ።
እኛ አገር እኮ ቀን ሰርቶ ማታ 20 ብር ከፍለው አንድ ቤት ውስጥ 20ና 30 ሆነው የሚኖሩ በርካታ ሰዎች አሉ። እናም ቤት ሁኑ ስትያቸው የት ነው የሚቀመጡት? በተጨናነቀ ቦታ የሚሰሩ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። እንዴት ብለን ነው ልናራርቃቸው የምንችለው? ይህ የሚያሳየው በግዴለሽነት ብቻ ሳይሆን የኑሮ ሁኔታው የሚያስገድዳቸው መኖራቸውን ነው።
ስለዚህ ድህነታችን እዚህ ጋር ጎድቶናል። በተጨማሪም ደግሞ ባህላዊ መድሃኒቶቻን ላይ ያለን መታመን ሌላው ችግር ነው። ብዙዎቹ በዝንጅብል፥ በነጭ ሽንኩርት፥ በፌጦና በመሰል ባህላዊ ምግቦችና መድሃኒቶች በሽታውን ማቃጠል እንደሚችሉ ያምናሉ። እነዚህ ነገሮች ናቸው እያዘናጉን ያሉት። ይጎዱናል።
ጠንክሮ ከመጣ ደግሞ ከባድ ነው። በሌሎች አገሮች እንደምናየው የሰው ልጅ መቀበሪያ እንኳን የተቸገረበት ሁኔታ ነው ያለው። እንዚህን ሁኔታዎች ስታዪ «ለካ ሞቶ መቀበርም ወግ ነው» እንድትይ ያሰኝሻል። ይሄ ጊዜ ያሳየን እሱን ነው። ለካ ሰው ሞቶብን አልቅሶ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ መቅበርም ትልቅ እድል ነው!። ይህንን እንኳን ያሳጣን በሽታው ነው ያመጣብን ።
ላቲን አሜሪካ ውስጥ ሰዎች መቀበሪያና ቀባሪ አጥተው በየመንገዱ ሬሳቸው ተጥሎ አይተናል። ጣሊያን ውስጥ ጦሩ ነው እየቀበራቸው ያለው። ተራቸው ደርሶ እስከሚቀበሩ ድረስ ስድስትና ሰባት ቀን የፈጀባቸው ሰዎች አሉ። እኛ ጋር በዚያ መጠን እንዳይመጣ እፀልያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ተቋማት በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቖጠር ህዝብ በዚህ ቫይረስ ሊያዝና ሊሞት ይችላል የሚል ሃሳብ እየሰጡ ነው ያሉት። እርሶ አሁን ያለው ሁኔታን ይህንን ነገር ያሳያል ብለው ይሰጋሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ከቫይረሱ ባህሪ አንፃር አዎ ስጋት አለኝ። አሁን በሚዲያ እየተነገሩን ያሉት ቁጥሮች በጤና ጥበቃ አማካኝነት ከተመረመሩ ሰዎች ብቻ የተገኘ መረጃ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ብቻ ሰው ነው በቫይረሱ የተያዘው ማለት አይደለም። የመመርመር አቅማችን ሲጨምር በበሽታው የሚያዙት ሰዎች እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። እንዳልሽው እየተነበዩ ያሉት ቁጥሮች በጣም ያስፈራሉ።
በአጠቃላይ በአፍሪካ ላይ የሚነገሩት ነገሮች በጣም ያስፈራሉ። በመጀመሪያ እኮ አሜሪካኖችም ንቀውት ነበር። እኛም ጋር አይመጣም ብለው ነበር። 15 እና 20 ሰው ነው ያለን እሱን እናጠፋዋለን ብለው ነበር። አሁን ላይ ግን ከ15 ሺ በላይ ሰዎች ሞተውባቸዋል።
እናም ሳይንቲስቶች የሚሰጡት ግምትና ትንበያ መናቅ አልፈልግም። በአፍሪካም ሆነ በአገራችን ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ህዝብ በበሽታው እንደሚጠቃ እየገመቱ ነው። ከቫይረሱ ባህሪ ብሎም ከአኗኗራችን አንፃር ሊሆን እንደሚችል አስባለው። ግን እንዳይሆን አሁንም ፈጣሪን እለምነዋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከአዲስ አበባ አልፎ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚገኙ መሆኑ ቫይረሱ ከእጃችን ማምለጡን የሚናገሩ ሰዎች አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ልክ ነሽ፤ የተለያየ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡ የሚነገሩትን ትንቢቶችና ግምቶች በጣም ያጠናክረዋል። ሊዛመት የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑንም ያሳያል። የዚህ ቫይረስ ክፋት ደግሞ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የመተላለፍ አቅሙ በጣም አደገኛ መሆኑ ነው።
ከዚህ አንፃር በተለይ የጤና ባለሙያዎችን ስታዪ እስካሁን እንግሊዝ ውስጥ ሁለት ሺ የጤና ባለሙያዎች በዚህ ቫይረስ ተይዘዋል። ጣሊያን ውስጥ 60 በላይ ዶክተሮች ሞተዋል። እናም እያከምሽው የምትያዢው በሽታ ነው። እንዳውም በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገው ዶክተሮች የሚጮሁት ጩኸት አለ።
«በየግላችን መከለከያ ቁሳቁስ ይቅረብልን» እያሉ ነው። ምክንያቱም ህመምተኛው ጋር ሲቀርቡ በጣም መጠበቅ አለባቸው። ይህንን የሚሉት ግን ራሳቸውን ብቻ ወደው አለመሆኑን ልንረዳላቸው ይገባል። በቀላሉ የሚጋባ በመሆኑ ለቤተሰባቸውና በዙሪያቸው ላለው ሰው ሁሉ በማሰብ ነው።
ስለዚህ በየከተማው መግባቱ እነዚያ ሰዎች አብረው ያሳለፉት ሰው ይኖራል። ስለዚህ አስቀድሜ እንዳልኩት ብዙ ብንመረምር ከዚህም በላይ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ልናገኝ እንደምንችል ይታወቃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምልክትቹን ሳያሳይ በሚቆይባቸው 14 ቀናት ውስጥ ጤነኛ መስሎ ለሌሎች ሊያስተላልፍ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።
ከዚህ አንፃር እንደ አገር እንግዲህ ጉዳችንን የምናውቀው ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ነው። መንግስት ይህ ሊሆን እንደሚችል በመስጋት እያደረገ ያለውን ዝግጅት አደንቃለሁ። ምክንያቱም ድንገት ብዙ መታመም ሲጀምር የጤና ተቋሞቻችን የማስተናገድ አቅም ሊሸከመው አይችለውም።
አዲስ ዘመን፡- የጤና ባለሙያዎች የሚያነ ሱትን ስጋት ለመቀነስ መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም አንዳንድ የቤት አከራዮች ግን በተዛባ መረጃ ምክንያት «በሽታ ታስተላልፉብናላችሁ» በሚል ከቤት እስከማበረር የደረሱበት ሁኔታ እንዳለ እንሰማለን። ይህ ሁኔታ ደግሞ የጤና ባለሙያው በሙያው ህዝብን እንዳያገለግል ያደርገዋል ብለው አያምኑም?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ይህ ጉዳይ እጅግ በጣም ልብ የሚሰብርና የሚያሳዝን ነው። ሌላ አገር የሚደረገውን ስታዩ በጣም ነው የምትቀኚው። በእንግሊዝ ስታዩ ለጤና ባለሙያዎቻቸው የጭብጨባ ዘመቻ ሁሉ ነበራቸው። የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ቀይ እያበሩ «የጤና በላሙያዎች ጀግኖቻችን ናችሁ» እያሉ አድናቆታቸውን እየገለፁ ነው ያሉት። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ከሞት ጋር ነው የተጋፈጡት።
ደግሞም እስከዛሬ አንድ ሃኪም በሰራው ስህተት ብዙ ሃኪሞች እየተወቀሱ ብዙ ነርሶች እየተወቀሱ ሞራላቸው ዝቅ ብሎ ነው የኖሩት። በዚህ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ሃኪምና ሌላ አገር የሚሰራ ሃኪም ኑራቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው። ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ነው የኖሩ ያሉት። እንዲህ አይነቱ ችግር ሲመጣም ከስራ መቅረት አይቻልም። ማንን እንደሚያክሙ ስለማያውቁም ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ።
በተለይ ደግሞ ነርሶች ከበሽተኛው ጋር ተደጋጋሚ ቅርበት የሚኖራቸው በመሆኑ በስፋት እንዳይጠቁ እሰጋለሁ። በመሆኑም ይሄ ለብቻው አሳሳቢ ስለሚሆን ሞራላቸውን እንጠብቅ። አሁን ነው ልናደንቃቸውና ልናበረታታቸው የሚገባው። እንዳልሽው ህብረተሰቡ እነሱን ማግለልና መሸሽ ከጀመረ የስነልቦና ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል። አሜሪካ እኮ በሺ የሚቆጠሩ ፖሊሲች ሲያዙ ሌሎቹ ብዙ ሺ ፖሊሲች «አሞናል» ብለው ቤት መቅረት ጀመሩ። በእኛም አገር እንዲህ አይነት ነገር ሊፈጠር ይቸላል። በአጠቃላይ አከራዮች የህክምና ባለሙያዎች ማገዝ ሲገባቸው ከቤት ውጡልን ማለት በራሱ ልብ ይሰብራል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ መንግስት ከአንዲት የባህል ሃኪም ጋር በመተባበር መድሃኒት የማግኘት ሂደት ላይ መሆኑን መግለፁን ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ተቃውመውታል፤ እርሶ በዚህ አጭር ጊዜ መድሃኒት መግኘት ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- እኔ ይህንን ጉዳይ በሁለት መንገድ ነው የማየው። አንድም ባህላዊውን ህክምና ስናይ የኢትዮጵያ ህዝብ በአብዛኛው የባህላዊ ህክምና ሲጠቀም ነው የኖረው። ሃኪም ወርቅነህ ከመምጣታቸው በፊት እኮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ባህላዊ ህክምና ነበር የሚጠቀመው።
ዘመናዊ ህክምና ከመጣም በኋላ ህክምናው ተደራሽ ስላልነበር 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የባህል ህክምና ሲጠቀም ነው የኖረው። ስለዚህ የባህል ህክምናን አናጣጥልም። አሁንም ቢሆን አብዛኛው ህዝብ ጉንፋንና የተለያዩ ቀለል ያሉ ህመሞች ሲይዙት ነጭ ሽኩርትና ዝንጅብል ነው የሚጠቀመው።
ይህንን ልምዱን አንቃወመውም። ቻይኖችም ቢሆኑ የባህል ህክምና ብዙ ይጠቀማሉ። በሌላ በኩል ከኮረና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ግን መድሃኒቱ ተገኘ ሲባል እኔም ደንግጬያለሁ። አንደኛ በደንብ ሳይታወቅ እንዴት መድሃኒቱ ሊገኝ ይችላል ብዬ ነው። ምክንያቱም በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥበቫይረሱ የተያዘው ሰው 20 ሰው በሚባልበት ሰዓት ነው።
የቱ ጋርና በየትኛው ህመምተኞች ላይ ተሞክሮ ነው ውጤታማነቱ የተረጋገጠው? የሚለው ነገር ትልቅ ጥያቄ ነበረኝ። አንድ መድሃኒት በህክምናው ዘርፍ የሚያልፍባቸው የተለያዩ ሂደቶች አሉት። እናም እኔ መንግስትን መውቀስ ባልወድም ግን ትንሽ ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች ነበሩት። ይህንን ስል ግን አይገኝም ብዬ አይደለም፤ ሊገኝ ይችላል። የእኛን የባህላዊ ሃኪሞች አልንቅም።
ግን ተገኘ ተብሎ የተነገረበት ሰዓትና በዚያ ሰዓት በሽታው የነበረበት መጠን እንደባለ አዕምሮ እንዴት ብለው አገኙ? የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኝ ነበር። በዚያ ሰዓት ደግሞ መግለፁ ደግሞ በቀላሉ መድሃኒት እንደሚገኝ ህዝቡ እንዲያምንና እንዲዘናጋ ያደርገዋል ብዪ ደግሞ ፍርሃት አድሮብኛል።
በጊዜ ሂደት መድሃኒት እንደሚገኝ ግን እኔም አምናለሁ። መድሃኒት ስንል ክትባትም ማለታችን ነው። ግን ጊዜ ይወስዳል። በአሁኑ ወቅት የተለያዩ መድሃኒቶች ሙከራ ላይ እንዳሉም እናውቃለን። ለምሳሌ አሜሪካኖች የወባ መድሃኒት የሆነው ክሎሮፒን ይሰራል፤ አይሰራም እያሉ እየተከራከሩበት ነው። አንዳንዶችም የኤች. አይ. ቪ መድሃኒቶች ሊሰሩ ይችላሉ ብለው ሙከራ ላይ ናቸው።
ሙከራ ላይ እያለን ግን አሁን ማለት ያለብን መድሃኒትም የለም ፤ ክትባትም የለም ያለው መፍትሄ እጅ መታጠብ መራራቅ ሰው የተሰበሰበበት ቦታ አለመሄድ ህክምና ባለሙያዎች በሰጡን መመሪያ መኖር ነው። ይህንን ነው በየዕለቱ ለህዝባችን ማስተማር ያለብን።
አዲስ ዘመን፡- የእምነት ተቋማት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ቤተእምነቶቻቸው እንዲዘጋና ምዕመኑ በየቤቱ ጸሎትን እንዲያከናውን አድርገዋል።በሌላ በኩል አንዳንድ የእምነት አባቶች መዝጋት የአምላክን የማዳን ሃይል መገዳደር እንደሆነ ጠቅሰው ይቃወማሉ። ይህንን እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- እኔ የሚቃወሙትንም ሰዎች እረዳቸዋለሁ። ሙስሊሞች ለመስኪዳቸው ያላቸው ፍቅር በጣም ከፍተኛ ነው። ኢራን ውስጥ እኮ መንግስት በትዕዛዝ መስኪድ ሊዘጋ ሞክሮ ችግር ተፈጥሯል። አሁንም የእኛ መንግስት ጥበብ ተጠቅሞ ራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች እንዲዘጉ ባያደርግ ኖሮ ችግር ይፈጠር ነበር። ስለዚህ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመስኪዶች ጋር ያለው ግኑኝነት ጥብቅ ነው፤ እዛ ላይ ሄዶ አላህን እንደሚያገኝ ያምናል። ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ደግሞ ቤተክርስቲያን ሲሄድ ለራሱ የሚሰማው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም እረፍት አለ።
ይህ ስለሆነ ቤተእምነት መዘጋት የለበትም ብለው የሚያምኑ አሉ። ግን ደግሞ በሌላ በኩል ስትመለከቺ ለምሳሌ በእስልምና መስገድ አለ፤ አንዱ የሰገደበት ቦታ ላይ ሌላው ሲሰግድ በቀጥታ ይተላለፍበታል። ለመተላለፍ በጣም ቀላል ነው የሚሆነው። በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም አንዱ የተሳለመበትን ቦታ ሌላው ሲሳለም በቀጥታ ነው የሚተላለፍበት።
ወደ ፕሮቴስታንትም በተመሳሳይ እጅ ለእጅ ተያይዞ ወይም እጅ በመጫን የሚፀለይበት አካሄድ በሽታው እንዲተላለፍ ያደርጋል። ይህ በሽታ ደግሞ ቄስ፥ ሼክና ፓስተር ብሎ አይለይም። አንዱ አገልጋይ ከያዘው ለስንት ሰው እንደሚያስተላልፍ መገመት ይቻላል። ስለዚህ እያዘንንና እያለቀስን እንጂ ደስ ብሎን አይደለም ቤተእምነቶቻችንን የምንዘጋው። በቃ ይዘጋ ተብሎ የሚወሰን ቀላል ውሳኔ አይደለም። ግን የግድ ይህ ጊዜ መታለፍ ስላለበት መዘጋቱ ትክክል ነው ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በነበረው የእምነት ተቋማት የፀሎት መርሃ ግብር ላይ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር ቤተእምነቶች መዘጋት የእምነት አባቶችም ሆነ የህዝቡ ሃጥያት ውጤት ነው የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። በዚህ ሃሳብ እርሶ ይስማማሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ኡመር የተናገሩትን ሰምቻለሁ፤ በጣም ልብ ይነካ ነበር። በአንድ በኩል በመንፈሳዊ አይን ስታዪው እውነት ነው። በመፃሃፍ ቅዱስ ላይ ትንቢተ ሚልኪያስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 ላይ በግልፅ « በመሰዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ፤ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ምነው በተገኘ፤ በእናንተ ደስ አይለኝ «ቁርባንም ከእጃችሁ አልቀበልም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር» ተብሎ ተፅፏል።
ሃጂ ሙፍቲ እንዳሉት እግዚአብሄር ሲቆጣ የቤተ እምነቶችን ደጅ እንደሚዘጋ በግልፅ ተቀምጧል። እናም አምልኮ ቤቶቻችን በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስኪድ የነበሩ ሹኩቻዎችን ስታዪ፥ በዘር መደራጀቱን ስታዪ፥ ይሄ የኦሮሞ ቤተክርስትያን፤ ይሄ የአማራ ቤተክርስቲያን ተባብሎ እርስ በርስ የመጎነተታል፤ ብሎም በገንዘብና በሃጥያት ተጨማልቀን ነበር።
እርሳቸው እንዳሉት ቤተመቅደስ ውስጥ የተጠራቀመ ሃጥያት እንደነበረ ምንም ጥያቄ የለውም። ስለዚህ ይህንን ተጠቅሞ በዚህ አጋጣሚ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ለዚያውም ፋሲካ ቀርቦ እያለ የህማማት ሰሞን ላይ ቤተክርስቲያን ተዘጋ ማለት የፈጣሪ ቁጣ ነው ማለት እንችላለን።
ለሙስሊሞችም መስጂድ መዘጋት ከፍተኛ ተግሳፅ ነው። የሃየማኖት ሰዎች ራሳችንን የምናይበት ጊዜ ነው። ንስሃ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ አገልጋዩም ሆነ ህዝቡ ሊያስብበት ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚያውቁት ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሁሉም ቤተእምነቶች በአንድ ላይ ሆነው ለ30 ቀን የፀሎት ጊዜ ታውጇል። ይህ አዋጅ በተጨባጭ ህዝቡ ከአምላኩ ምህረትን የሚጠይቅበት እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- እንግዲህ የእግዚአብሄር ተግሳፅ የሚጀምረው ከቤቱ ነው። ከሃይማኖት መሪዎች ነው። ከልባቸው ንስሃ ሊገቡና ይቅርታና ምህረት ሊጠይቁ ይገባቸዋል። ምክንያቱም መፅሃፍ ቅዱስ ላይ የምናውቃቸው የሃይማኖት መሪዎች በግንባራቸው ወድቀው ተደፍተው ነው የሚፀልዩት።
በመሆኑም የሃይማኖት መሪዎቹ ለሚዲያ ትኩረት ሳይሆን ከልባቸው በር ዘግተው በፈጣሪያቸው ፊት መውደቅ ይገባቸዋል። ምክንያቱም መጀመሪያ የሚጠይቃቸው እነሱን ነው። ከዚያ ወደ አማኙ ስትመጪ እያንዳንዱ ሰው ራሱን ነው ማየት ያለበት። እኔን ብትመለከችኝ በጣም ብዙ ንስሃ የምገባባቸው ጉዳዮች አሉኝ። ራሴን የማይበት። በተለይ እንደዚህ አይነት የፀሎት አዋጅ ሲታወጅ እንግዲህ እናንተ ፀልዩ ብዬ ለሌሎች አልተውም ራሴን አያለሁ።
ቃሉም እንደሚለው በስሙ የተጠራ ህዝብ ሰውነቱን አዋርዶ ቢፀልይ፤ ፊቱም ቢፈልጉ፤ ከክፉ መንገዳቸው ቢመለሱ፤ እሱ ከሰማይ ሆኖ ይሰማል፤ ምድራችንን ይፈውሳል፤ ሃጥያታችንንም ይቅር ይላል። ስለዚህ ይህ ትልቅ ቃል ነው። በዚህ መሰረት በእግዚአብሄር ፊት ንስሃ መገባቱ የአንድ ወሩ የፆም ፀሎት ጊዜ በጣም ተስማምቶኛል፤ ግን ከልብ መደረግ እንዳለበት አምናለሁ። ህዝቡም ከልብ ተገንዝቦ ማድረግ አለበት። ደግሞም የሚራራ የሚያዝን ሲጠሩት የሚደርስ አምላክ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- ከኮረና መምጣት ጋር ተያይዞ በየመገናኛ ብዙሃኑ ዘር ከዘር እምነት ከእምነት ጋር ሲያጋጩ የነበሩ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ድምፃቸው ጠፍቷል፤ ይህ ሁኔታ ኮረና ጉዳት ብቻ ሳይሆን ጥቅምም አምጥቷል ለማለት አያስደፍርም?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- በአንድ በኩል እንዳልሽው ይህ ቫይረስ የሰው ልጆች የመጨረሻ ምስኪኖች እንደሆንን ነው ያሳየን። በአጠቃላይ ሀብታሙ፥ ደሃው የተማረው ያልተማረው የመጨረሻ አቅመ ቢስ መሆናችን ነው ያሳየው። ምክንያቱም ትላልቅ የተባሉትን አገሮች ሲያንበረክካቸው አይተናል።
በቃ አንችልም ብለው ተስፋ ሲቆርጡ አይተናል። እኛም አገር እኮ እንደከዚህ ቀደሙ ባንኮክ ሄጄ እታከማለው ማለት አይቻልም። የሰው ልጆችን ከሚያንበረክክ በሽታ የሚያድንም የሚፈውስም ሁሉን ቻይ እግዚአብሄር እንደሆነ የታየበት ነው። ይህ እንዲሆን አደረገ ባልልም፤ በዚህ ግን እግዚአብሄር ታላቀነቱ ታይቷል። ሰው ደካማ እንደሆነ ታይቷል። የፖለቲካ ሰዎችም ሁላችንም ራሳችንን እንደምናይ እራሳቸውን ያያሉ ተብሎ ይታመናል።
«ለካ ህይወት እንደዚህ ናት! ለካ የምንጋደልበት ፖለቲካ ይሄ ነው! ለካ የምንጣላባት አዲስ አበባ ይህቺ ናት!» ብለው ያስባሉ። ስለዚህ ፖለቲከኞቻችንና አክቲቪስቶቻችን ቆም ብለው ሰው መሆናቸውን ሊያስቡ ይገባል። ከነበሩበት የተሳሳተ መንገድ ወጥተው ለሰው ሁሉ ፍቅር ሊኖራቸውና ለአገራቸው ሰላም ለማምጣት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
የእንቅስቃሴያቸው መሰረቱ ፍቅር መሆን አለበት። መራር ጥላቻና ተቃውሞቸውን የሚተውበት ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ። በሌላ በኩልም ኢኮኖሚያችን በጣም እየተጎዳ መሆኑን ለመረዳት ኢኮኖሚስት መሆን አይጠበቅብኝም። በአጠቃላይ ግን ይህ ቫይረስ የነበረንን በራስ የመተማመን ሁኔታ መሬት ላይ አውርዶ እንደከሰከሰው እውነት ነው።
ግን እንደመንደርደሪያ ልናየው እንችላለን። በጣም ወደኋላ መልሶናል፤ ግን ሮጠን እንቀድመዋለን ብዬ አስባለው። አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ ላመሰግኖዎት እወዳለሁ። ዶክተር ወዳጄነህ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደ ረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2012
ማህሌት አብዱል