ሀገር አቅኚ መወክረ ሀሳቦች በዘመን ስለተደገፉ አእምሮና ልቦች ሳይሆን ስለሚበልጥ እውነት የሚያወጉ የቁም ነገር መድረኮች ናቸው። ለተሻለ የሀገረ መንግስት ግንባታ የተሻለ ሀሳብ የሚዋጣበት፣ ልዩነቶቻችንን ለጦርነት ሳይሆን ለአዋጭ ሃገራዊ ትርክት የምንጠቀምበት፣ በቆዩና በነበሩ እሴቶቻችን አብሮነትን አዳብረን ስለአንዳንድ አለመግባባቶች መላ የምንዘይድበት የኢትዮጵያውያን የማሰብና የማሰላሰል መድረክ ነው።
እየሆንን ያለነውና እየሆነብን ያለው ግን በተቃራኒው ነው። ሀሳቦቻችን ጥል አዝለው በቀልን ከወለዱ ሰነባብተዋል። ለሸንጎ ያልደረሱ ትንንሽ ጣጣዎች ለአፈሙዝ ሲያበቁን ማየት ምን ነካን? ምን እየሆንን ነው? ከሚሉ ጥያቄዎች በገዘፈ ነገን እንድንሰጋ የሚያደርጉን ናቸው። ከማንም ቀድሞ ባለሀገር የሆነ ሕዝብ፣ ከማንም ቀድሞ መተዳደሪያ ስርዐት የመሰረተ ማንነት፣ ነጻነትና ሰብዐዊነት፣ ሰላምና አስታራቂነት በስሙ የሚገነኑበት ሕዝብ ነበርን አሁን ግን …. ለምን ? ።
አሁን እንደሀገር እየሆነው ስላለው ነገር ለምን ብለን የምንጠይቅበት ወቅት ላይ ነን። መታወቂያችን የነበሩት ሰላምና ፍቅር፤ በእርስ በርስ ትስስር ያበለጸጉን የወንድማማችነት ካባዎቻችን የት ነው ያሉት ? በስመ ሀበሻ የሚጠራ ማንነታችን ጥላቻን በሚሰብኩ በማይረቡ ተራ ስሞች ተቀይሮ መነሻችንን ከልሎብናል። አንድ መልክን ሰጥተው በአንድ አምሳል ያበቀሉን እሴቶቻችን እንድንፈራራ እና እንድንሰጋጋ በሚያደርግ የፖለቲካ እድፍ ቆሽሸው ጥላቻ ነጋሪ ሆነዋል።
ሀገር በሰላም እና በጦርነት ስትታወቅ አንድ አይደለችም። የመጣንበትን ረጅም መንገድ ትላንትና ዛሬ ብለን በሁለት ብንከፍለው የሰላምና የጦርነት ዘመን ብለን እንመድበዋለን። እርግጥ ጦርነት ለረጅም ዘመን አብሮን የመጣ መጥፎ ታሪካችን ሆኖ የሚወሳ ቢሆንም ከአሁናዊ ጀብደኝነታችን ጋር ሲነጻጸር ምን እና ምን ነው የሚያስብል እየሆነ ነው።
ቀደም ሲል በክብራችንና በሉአላዊነታችን ከመጡት የውጪ ኃይላት ጋር ነበር፤ አሁን ግን ነጻ አውጪ በሌለው የእርስበርስ ጦርነት ላይ ነን። ድሮ ለነጻነትና ለመላው የጥቁር ሕዝብ ስንል አትንኩኝ ብለናል አሁናዊ ጀብደኝነታችን ግን ፖለቲካ ወለድ የሀሰት ትርክት ነው። እንዲህ አይነቱ የእርስ በርስ ፍትጊያ ሀገር አቅኚ ምክረ ሀሳብ ያስፈልገዋል።
በሀሳብ የዳበረ ፖለቲካ ሀገርን ያስቀድማል። ሀሳብ ሀገር ይፈጥራል፣ ትውልድ ይቀርጻል በስተመጨረሻም ለእርቅና ለምክክር ደጃፉን የከፈተ ማህበራዊ ልምምድን ይሰጠል። በእኛ አሁናዊና የከርሞ የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ ግን ይሄ አይነቱ ልምምድ የለም። ለምንም ነገር ኃይልን አስቀድመን ከተቻለ በውዴታ ካልተቻለ በግዴታ ነገሮችን በማስፈጸም ልምምድ የመጣን ነው። ይሄ ብልሹ ልማድ አድጎ ፖለቲካው ለሀገር እንዳይጠቅም፣ ፖለቲከኞቻችንም ለትውልድ እንዳይበጁ ከማድረጉ እኩል ደምን በደም አስተሳሰብን አስርጾብናል።
የሚበጀን ደምን በደም ሳይሆን ደምን በእርቅ ነው። እርቅ ደም ያድርቅ በሚል ማህበራዊ ስነቃል በሸንጎና በሽምግልና በዛፍ ጥላ ስር ተጠልለን፣ በነጭ ቡሉኮ ጭራችንን ግራና ቀኝ እያወናጨፍን፣ በዳበረ የአንተም ተው አንተም ተው ወግ ጥልና ጸቦችን አብርደን ብርቱ ማህበራዊ ስርዐትን አንጸናል።
በታላቁ አባት በፈጣሪ ስም‹ ይቅር ለእግዜር› በሚል አስታራቂ ምሬት ጥላቻዎቻችንን ወደፍቅር ቀይረን አብሮነታችንን አስምረናል። ዛሬ ላይ እነዛ የሀገር ጌጥ፣ የትውልድ መልኮች የት ጠፉ ብለን ስንጠይቅ አንድም ዘረኝነት ሸሽጓቸዋል አንድም ፖለቲካው አጥቁሯቸዋል። ሌላ ምክንያት ካስፈለገም ለጥላቻና ለእርስ በርስ ውንብድና የሚወግኑ ክፉ ትርክቶች አወይበዋቸዋል።
ወደነበርንበት የዛፍ ጥላ ስር መመለስ፣ ወደነበርንበት የእርቅ ማዕድ ማስተዋላችን፣ በይቅር ለግዜር ስም ጥላቻዎቻችንን የመሻራችን ማህበራዊ ልምምድ ሀገር የምትፈጠርበት፣ አንቂ ምክረ ሀሳቦቻችን የሚያቆጠቁጡበት እንዲሁም ከእርስ በርስ ፉክክር ወደእርስ በርስ ምክክር የምንመጣበት የአዲስ አስተሳሰብ መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን በጽኑ አምናለው። አሁን ላሉብን ዘርፈ ብዙ የውስጥና የውጪ ችግሮች በሀሳብ የተሞላ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ያስፈልገናል።
በሀሳብ ባልበረታ ማንነት መሀል ሆነን ትላልቅ ሀገራዊ ራዕዮችን ብናርይ ትርጉም የለውም። ሀገራት በኢኮኖሚና በስልጣኔ በርትተው የሚታዩት ሀገር ቀራጭ የሆነውን ፖለቲካ በሀሳብ መምራት ስለቻሉ ነው። ሀምሳ እና ስልሳ ዓመታትን ያለማቋረጥ ጦርነት ያካሄድን ሀገራት ነን። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ምን እንዳጣን እንኳን ለማሰብ ጊዜ አጥተን በተመሳሳይ ጥፋት ውስጥ ነን። ማሰብ የሚለው ልዕለ ኃይል ዋጋ ያለው ሆኖ የሚገለጠው እንዲህ ባለው አጥፊ ታሪክ በኩል ነው።
እስኪ ለአፍታ ወደጦርነት የወሰዱንን የፖለቲካ ንትርክም ሆኑ የሀሰት ትርክቶች እንቃኛቸው። ችግሮቻችንን በውይይት ፈተናቸው ቢሆንና ለእርቅና ለወንድማማችነት ቅድሚያ ሰጥተን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ስለሰላም እንጂ ስለጦርነት የምናወራ ባልሆንን ነበር። በጊዜ ያልተደፈኑ ትንንሽ ክፍተቶች መቼም የማይጠራ ክፉ ታሪክ የሚወለድባቸው ማህጸኖች ናቸው። ቀዳዳዎቻችን ተደፍነው ቢሆንና ነገን አርቆ በሚያይ ልበ ብርሀን ስልሳሌ ስር የቆምን ቢሆን ኖሮ ይሄን ሁሉ የጦርነት ዋጋ ባልከፈልን ነበር።
ሀገር አቅኙ ምክረ ሀሳቦች በእኔ እበልጥ እኔ ሽኩቻ ውስጥ ሳይሆን በሚዛናዊነት ውስጥ የተቃኙ፣ ነገን ዛሬ በሚሰራ የፖለቲካ እሳቤ እንዲሁም ጦርነትን በሚሽር ሰላም አምጪ የጋራ እሴት ላይ ጥናት የሚያደርግ በውጤቱም ሀገር የሚጠቅም የበጎ ትውልድ መብቀያ ነው። ጠማማውን አቅንቶ፣ ወልጋዳውን ገርቶ የሰላም መንገድ የሚሰጥ አስተሳሰብ ነው። እንዲህ አይነቱ አዲስ ምልከታ ትላንት ላይ ተንጸባርቆ ቢሆን ዛሬ ላይ ስለሰላም የምንጽፍ፣ ስለኢትዮጵያዊነት የምንናገር እንሆን ነበር።
በየትም ይምጣ ከማንጋርም ይሁን ጦርነት በበጎ የሚነሳ ገጽ የለውም። ለዚህ ደግሞ ያለፉና የቅርብ ጊዜ ታሪኮቻችንን ማስታወስ ይቻላል። በነውራቸው አቻ የሌላቸው ትላልቅ የጥላቻ ቁርሾዎች የሚፈጠሩት ጦርነት ውስጥ ነው። ለጊዜው ያሸነፍን ይመስለናል እንጂ ዛሬ ነገ ሲሆን በብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ የሚመጣ ነው። በዓለም ላይ ያሉ በጦርነት የተሳተፉና ዋጋ የከፈሉ ሀገራት ወደ ኋላ ሄደው አንድና ሁለት ነገሮችን እንዲያስተካክሉ እድል ቢሰጣቸው ብዙዎች በማወቅና ባለማወቅ የገቡበትን የጦርነት ታሪክ በሰላም መቀየር የሚመኙ ሆነው ይገኙ ነበር።
የእኛን ሀገር የጦርነት ታሪክ ከሌላው ሀገር ለየት የሚያደርገው ካለፈው አለመማራችን ነው። በጣም ከሚደንቀኝ የፖለቲካ ጨዋታ መሀል አንዱ ካለፈው ተምሮ መጪውን የተሻለ ለማድረግ ጥረት አለመኖሩ ነው። ከጦርነት ወደጦርነት መገላበጥ እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ከመሆኑም በተጨማሪ ለግዙፍ አገርና ለባለታሪክ ሕዝብ የማይመጥን እንዲሁም በትውልድ ነገ ላይ መቀለድ ጭምር ሆኖ የሚታይ አሳፋሪ ድርጊት ነው።
በሀሳብ በልጽጎ ሰላማዊ መሆን ይቻላል እኮ። በሰላም ጎልምሶ ሰላማዊ የመሆን የጥንት ልማድ አለን እኮ። በሰላም ስለሰላም መወያየት ለምን አቃተን? አትጠራጠሩ ያቃተን በሀሳብ መበልጸግ፣ በሀሳብ መራመድ ነው። በሀገር ጉዳይ ላይ ስለሰላም በምክክር ያልነቃ ትውልድ የመፍጠራችን ነገር በፖለቲካው ምህዳር ዙሪያ የሚነሳ ትልቁ ነውራችን ነው። ኢትዮጵያ ከቃል ይልቅ በተግባር የምትገለጽ የድርጊት ውጤት እንጂ አጋጣሚ ስናገኝ በጥሩ ቃላት ፍቅራችንን በመግለጽ የምታበቃ አይደለችም።
እስኪ ወደጦርነት የሚወስዱ የከሸፉና ያረጁ አመለካከቶችን እንተውና ሰላም አምጪ በሆኑ አመለካከቶች ላይ እንቁም። በዓለም ላይ ጦርነት ያልነካቸው ቢነካቸው እንኳን ከአንድ ጊዜ ጥፋታቸው ተምረው ጦርነት በቃኝ ያሉ ሀገራት ሞልተዋል። ለአብነት ሕንድን መውሰድ ይቻላል። ሕንድ ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት በማንም ላይ ጦርነት ከፍታ ማንም ጦርነት ከፍቶባት አያውቅም። ካናዳ፣ አይስላንድ፣ ኒውዝላንድ በሰላማዊነታቸው የሚታወቁ ጦርነት ጠል ሀገራት ናቸው። ሌሎችም በርካታ ሀገራት አሉ ከአውዳሚና አትራፊ ካልሆነ ጥፋታቸው ተምረው ጤነኛና ሰላማዊ ትውልድ መፍጠር ላይ ያተኮሩ።
ብልህ የብልሀት ስሙን ያገኘው ቀድሞ በመንቃት ከሌሎች ጥፋት ስለተማረ ነው። ሞኝ የሞኝነት አስጸያፊ ስያሜውን ያገኘው ከሌሎች አይደለም ከራሱ መማር ስላልቻለ ነው። አንዳንዶች ቀድመው በመንቃት ከሌሎች ጥፋት ተምረው ራሳቸውን ከጥፋት ይታደጋሉ። ሌሎች ከራሳቸው መማር ሳይችሉ በተደጋጋሚ መተላለፍ የማያባራ ሰቆቃን ያደምጣሉ። እኛም እንደሀገር፣ እንደመንግስት፣ እንደዜጋ፣ እንደፖለቲከኛ ከሞኝነት ወደብልህነት የሚያሻግረንን የሀሳብ ልዕልና መውረስ ትላንትን ላለመድገም የመጨረሻ ዋስትናችን ሆኖ የሚጠቀስ ነው።
በአክሳሪ ጦርነት ትላንት የሚቆጨው ትውልድ ያስፈልገናል። አዋራጅ ከሆነ የኃይል አሰላለፍ ወጥተን ስለአንድነት በአንድነት የምንቆምበት የወንድማማችነት ሕብረት በእጅጉ ግድ የሚለን ጊዜ ላይ ነን። በጦርነት ፍልስፍና አንድ ሰው ሲሞት ሀገር እየተሸረፈች ነው። የእርስ በርስ ትንቅንቅ ሲሆን ደግሞ ከዚህም የባሰ ትርጉም ያለው ነው። በእውነቱ ሰላም እንደኛ የናፈቀው ባለመኖሩ አምናለው። ከጦርነት ወደጦርነት በሆነ መገላበጥ ብዙ ዘመንን በከንቱ አሳልፈናል። ከሰላም ወደሰላም የሽግግት ፖለቲካ እንደናፈቀን ስድስት አስርት ዓመታት ጠቡ።
ሀገር አቅኚ ምክረ ሀሳቦች ከእንዲህ አይነት መጠፋፋት የሚታደጉን፣ የጠፋን በካሳ፣ ያዘነን በይቅርታ አሽረው፣ ወደ አንድነት የሚመልሱን የድሮነት አዋጆች ናቸው ብል አላጋነንኩም። ለማይጠቅመን ስንዳክር በብዙ ወደኋላ ቀርተናል። ይሄ ሊያስቆጨን ሲችል ነው ለሀገር አቅኚ ምክረ ሀሳቦች የምንገዛው። ተመልሰን እዛው ከሆንን ከነውሮቻችን መራቅ አስቸጋሪ ነው የሚሆንብን።
ችግሮቻችን ከእኛው ጋር የመሰንበታቸው፣ በአንድ ችግር ሁለት ሶስት ጊዜ ዋጋ የመክፈላችን ምክንያት ሲጠና የምናገኘው ከሀገር አቅኚ ምክረ ሀሳብ ይልቅ በትርኪምርኪ ጉዳይ ላይ ማተኮራችን እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም። ችግሮቻችን ማንም ያልጠነሰሳቸው እኛው አምጠን የወለድናቸው፣ በእኛው እሽሩሩ የጎለመሱ እኛኑ መልሰው እያጠቁን ያሉ ናቸው። ይሄን ተረድተን ለዳግም ጥፋት እድል ሳንሰጥ በተውጣጣ የሀሳብ መዋጮ ለተሀድሶ እንቁም።
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም