ካለንበት ሰጣ ገባ ወጥተን ለሁላችንም ወደሚበጅ የሰላም አንባ ለመድረስ

ትላንት ብለን በምናስታውሳቸው ሀምሳ ዓመታት ውስጥ እንደ ሀገር ሰላም ናፋቂ ህዝቦች ሆነናል:: ለመነጋገር እና ተነጋግሮም ለመደማመጥ የሚያስችል ማህበረሰባዊ ስሪት ማጣታችን ፤ሀይልን ባስቀደመ የፖለቲካ እሳቤ ፖለቲከኞች መቃኘታቸው ፣ ከዛም አልፎ ለእርስ በርስ ግጭቶች መንገድ የሚከፍቱ የጥላቻ ትርክቶች በዝተው መደመጣቸው ሰላምን ነፋቂ አድርገውናል::

በዚህ ጽሁፍ ዓላማ ያደረኩት “እርቅ ደም ያደርቅ“ የሚለውን የአባቶች አነጋገር መሰረት በማድረግ፤ መጪዎቹን ዘመናችንን ብሩህ ማድረግ እንደምንችል ለማሳየት ነው። በእርቅ ቁርሾዎቻችንን ሳናክም እንደበጎ ውርስ ሞትና ጦርነትን ለትውልዱ ማውረስ እንደሌለብን ለማመላከት ነው::

ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ሆን ተብለውም ይሁን ባለማወቅ የተፈጠሩ አራራቂና አቀያያሚ ትርክቶች ተስተካክለው እንደብሔር ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊ፣ እንደባዕድ ሳይሆን እንደወንድማማች የምንተያይበትን የሰላም አውድ መፍጠር የዚህ ዘመን ትውልድ ኃላፊነት ነው::

አሁን ላይ በእርቅ እና በምክክር ወንድማማችነታችንን እንመልስ ብለን ስንነሳ ትውልዱን በእልህ ሳይሆን በይቅርታ ሰላምን ማምጣት እንደሚችል በማስተማር ነው:: በምክክርና በውይይት ካልሆነ በሀምሳ ዓመታት የፖለቲካ ትንቅንቅ ውስጥ ሰብተውና ደልበው የፈረጠሙ የዘረኝነት፣ የጦርነትና የጥላቻ መንፈሶቻችንን ማስወጣት አንችልም::

ጊዜም በውይይት ካልሆነ በሌላ በምንም መንገድ ሰላምን ማምጣት እንዳንችል የሆንበት ነው:: ከምክክር ውጪ ምንም ማድረግ በማንችልበት ዘመን ላይ በጦርነት ዋጋ መክፈል ከምንም የማይወዳደር ራስ ጠልነት ነው:: ለራሳችን ክብርና ዋጋ ከምንሰጥበት አጋጣሚ አንዱ ጦርነትን በውይይት፣ ጥላቻን በፍቅር ማስቀረት ነው::

ብዙሀኑ ሀገራት ራሳቸውን በመውደድና በማፍቀር ጨርቃቸውን የጣሉ ናቸው። እኛ ግን ለማንም ትርፍ በማያስገኝ ጦርነት ውድ ህይወታችንን እናጣለን:: ለብዙ ዓመታት የለፋንበትን ንብረታችንን እናወድማለን:: ጦርነት ለማንም ድል አስገኝቶ አያውቅም:: አክራሪ እና ፅንፈኛ አስተሳሰቦች ማንንም ፊተኛ አድርገው አያውቁም::

ፊተኝነትና ብኩርና ያለው የጋራ እሳቤ በፈጠረው አብሮነት ውስጥ ነው:: ሀገራዊ ድል፣ ህዝባዊ ልዕልና ያለው ብዙሀነትን ባቀፈ የሰላምና የእርቅ መድረክ ላይ ነው:: የደበዘዙ የጋራ ጸዳሎቻችንን በማጥራት፣ የከሰሩ አስታራቂና አዋሃጅ እሴቶቻችን የአብሮነት መንገድን እንዲጠርጉልን ለእርቅ መቀመጥ ፍሬ የምናፈራበት የሰላም መንገዳችን ነው::

ጦርነት የሞት አዋጅ ነው:: በዚህ አዋጅ ውስጥ ሰላም አለ ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው:: ቀድሞውኑ ማንም ጠብቆ አያውቅም:: ወደጦርነት የሚሰማራ ሁሉ ለመግደልና ለመሞት ነው:: በምክክር ነገሮችን ማስተካከል እየተቻለ በሀገርና ትውልድ ላይ መርዝ ለመርጨት መሰናዳት መቼም ቢሆን አዋቂነት አይሆንም::

ጦርነት ውርስ ነው:: ዛሬ ላይ የሚያባራ አይደለም:: እንደሰደድ እሳት ወደነገ ርቆ የሚንጠራራ የሞት ቅርስ ነው:: ሰው እንዴት ሞትን ለትውልድ ያወርሳል? እንደምን መከራን ለመጪው ያስቀምጣል? ስለምን ጥላቻና በቀልን ለልጅ ልጆቹ ያስታቅፋል? ከትላንት በወረስነው የፖለቲካ ውርስ እየተሰቃየን እንዳለን ሁሉ ዛሬ ላይ በምንሆነው ነገር ለነገው ትውልድ መከራን እያስቀመጥንለት ነው::

ጦርነት ማለት ‹ነገን ዛሬ ላይ ቆሞ እንደማውደም› ነው:: እውነት ነው ነገን ዛሬ ላይ ማውደም ከመሆን ውጪ ምንም ሊሆን አይችልም:: ባደረግናቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች ነጋችንን እያወደምን እንደሆነ እናውቃለን? ነገ ማለትስ ለኛ ምን ማለት ነው? ነገ ማለት ትውልድ ነው፣ ነገ ማለት የትውልድ ህልምና ራዕይ ያለበት፣ የሀገር ተስፋ የተቀመጠበት ካዝና ማለት ነው:: ዛሬ ላይ በእልህ ይህን ህልምና ተስፋ ካጠፋን ምን ነገ ይኖረናል?

ነገን ዛሬ እንስራ በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ ውስጥ ብዙ ትግሎችን አድርገናል፤ አሁንም በዛ መሪ ሀሳብ ውስጥ በርካታ በጎ ህልሞችን እያለምን እንገኛለን:: ይህም ሆኖ ግን አክራሪ እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች በሚፈጥሯቸው ጦርነቶች ነገን እያወደምን ነው ። ዛሬ ላይ ይህንን እውነታ መረዳት ካልቻልን ችግሩ አብሮን መዝለቁ አይቀርም።

ነገ የዛሬ መልክ ነው፣ መጪው , የአሁን ጽንስ ነው..ዛሬ የምንሆነው ሁሉ ወደነገ የሚሄድ ነው:: በዚህ መልኩ ነገ አይሰራም:: ነገ የሚሰራው ሰላም ሰባኪ በሆኑ አንደበቶች፣ ለእርቅና ለአብሮነት በበረታ አዕምሮና ልብ በኩል ነው:: መጪው የሚቀናው ኢትዮጵያን ለሰላም ሰላምን ለኢትዮጵያ ስናሰናዳ ነው:: በትውልዱ መሀል ኢትዮጵያዊነት ሲጸና ነው:: በከረረ ፖለቲካ፣ በጠብ ጫሪ ንትርክ ነገ ይወድማል እንጂ አይሠራም::

እየሄድንበት ባለው ሰላም አልባ መንገድ ራሳችንን እየጎዳን ነው:: ሰላም እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እናውቃለን፤ ስለሰላም ብዙ ንግግሮችን እናደርጋለን፤ ለሰላም ዋጋ ስንከፍል ግን አንታይም:: ነገን ዛሬ እንስራ፤ ለትውልዱ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን እናስቀምጥለት ስንል ህዝባዊ ንቅናቄ እናደርጋለን እንደሀሳባችን እውነት መር በሆነ ክዋኔ ስንሰለፍ አንታይም::

የሆነን የአንድ ዘመን ክብርና ማንነትን ነበር ብሎ ማውራት እጅግ ያማል:: ሰላም አጥተን፣ አንድነት ርቆን አሁን ላይ ነበር ብለን እያወራን ነው:: በሰላም ለሰላም የቆሙ ህዝቦች፣ በአንድነት ለአንድነት የተሰለፉ ልቦች ዛሬ በእኔነት ጠይመው እዛና እዚህ በቡዳኔ ቆመው ማየት ያማል::

ብዙሀነትን በአብሮነት ያጸኑ፣ በመከባበርና በመቻቻል ለዓለም ምሳሌ መሆን የቻሉ የይቅርታ ፈሮች ዛሬ በብሄር በልጽገው ኢትዮጵያዊነትን ሲሽሩት ማየት ያስቆጫል:: መልኮቻችንን ወደዛሬ መልሰን ዳግም የሰላም ህዝቦች ከመሆን ውጪ ትላንትን መዘከሩ ትርጉም አይኖረውም:: በውይይት ልዩነቶቻችንን አጥበን ነበር ብለን የምናወራውን ክብራችንን ወደዛሬ ማምጣት ይቻለናል::

ለዚህ አይነቱ ህዝባዊ መሻት ሀገራዊ ምክክር በሰፋና በገዘፈ የአብሮነት ዓላማ ዝግጅቱን አጠናቆ እየጠበቀን ነው:: ብሄራዊ ምክክርን ለብሄራዊ ተግባቦት በመጠቀም ሀገራችንን ነጻ ማውጣት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው:: ሜዳውና ፈረሱ ተዘጋጅቶልናል ጋላቢ መጠበቅ አይጠበቅብንም:: በላመና በላቀ አስታራቂና አቀራራቢ ሀሳብ ሰላም ለማውረድ ምቹ ሁኔታ ላይ እንገኛለን:: እድሎቻችን ፍሬ አፍርተው ድህነት እንዲሰጡን ለሁለንተናዊ እርቅ ይሁንታ ማሳየት ይጠበቅብናል::

ዓመታትን በወሰደ ቅድመ ዝግጅት መነሻውን ሀገር መድረሻውን አብሮነት አድርጎ የተጀመረው ብሄራዊ የእርቅ መድረክ በሀሳብ ፍጭት ኢትዮጵያን ሊታደግ እንሆ ደጃፉን ከፍቷል:: እንደሀገር የወደቁብንን የዘረኝነት ቀንበሮች ለማለዘብ፣ ነጣጣይ ትርክቶችን በብዙሀነት ለማከም ከፍ ሲልም በማይደገም ህዝባዊ እሳቤ ሀገር ለማጽናት እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ ያለዋዛ መጠቀም ያስፈልጋል::

በየትኛውም የዓለም ክፍል ችግሮች ይፈጠራሉ የእኛን ሀገር ችግር ለየት የሚያደርገው ችግር የመፍጠራችንን ያክል መፍትሄ ለማምጣት አለመተባበራችን ነው:: እንዲህ አይነቱ ልምምድ የቆዩ ችግሮች በጊዜ መ መ ቆ ጨ ት ሲገባቸው አዲስ ችግሮችን እንዲፈጥሩ እድል በመስጠት የከፋ ችግር ሲያደርስ ቆይቷል::

የመጣንበት የኃይል አሰላለፍ ከጦርነት በኋላ ሰላምን አምኖ የተቀበለ ነው:: ከጦርነት በኋላ ሰላም ለማንም የማይበጅ፣ ብዙ ነገሮችን የሚያበላሽ ድርጊት ነው:: እየመከርን ያለነው ከጦርነት በፊት ሰላም እንዲመጣ፣ ሳንሞትና ሳንገዳደል በእርቅ ተግባቦትን ለመፍጠር ነው:: እየደከምን ያለነው ልዩነቶቻችን ሰፍተው እንዳያገፋፉን፣ በኃይል ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት መሸነፍን ባህል ለማድረግ ነው::

ብኩርና ከህዝብ ጋር ተራምደው የሚደርሱበት እንጂ በአክራሪ እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ተራምደው የሚደርሱበት አይደለም:: ማንም በነዚህ አስተሳሰቦች ተራምዶ ሩቅ አልደረሰም:: ማንም ለብቻው ተጉዞ ለክብር አልበቃም:: ትርፋችንና ክብራችን ያለው ሀገር በቀደመችበት ፖለቲካና ህልማችን በኩል ነው:: ወደኋላ የተጓዝነው ሀገር በሌለችበት የብቻ ሩጫ ትንቅንቅ ስለያዝን ነው:: የተገፋፋነው ብዙሀነት በሌለው እኔነት ውስጥ ስለጎለመስን ነው::

ጦርነት ለማንም መፍትሄ ሆኖ አያውቅም:: የትውልድ ተስፋና የሀገር ብልጽግና በሰላም እሳቤ ውስጥ የሚውለበለቡ ናቸው ሰንደቁን አፍርሶ ልማት የለም:: ዓርማውን አውርዶ ተስፋ የለም:: አስቀድመን በሰንደቁ ላይ የሰላም ዓርማን እንስቀል ያኔ ሁሉም ነገር መልካም ሲሆን እናያለን::

ሁሉም ነገር መልካም ያልሆነው ሰንደቁ ላይ ሰላም ስለሌለ ነው:: ሰንደቁ ላይ መከራና ሰቆቃን፣ ጦርነትና ዋይታን ሰቅለን እንዴት ነው ብርሀን የሚወጣልን? እንዴት ነው በሰማያችን ላይ ጨረቃ የምትፈነጥቀው? ብርሀን እንዲመጣ ወጀቡ ገለል ማለት አለበት፣ ጭጋጉ መጥራት ይኖርበታል::

ያለቅድመ ሁኔታ ሰላም ያስፈልገናል፣ አብሮነት ግድ ይለናል:: እንደሰላም ያሉ በሀገር ግንባታ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው የትስስር ገመዶች በአንድ ወገን የሚጸኑ ሳይሆኑ የሁሉንም ሰው ትብብር የሚሹ ናቸው:: ብሔራዊ ምክክር የህዝብ ድምጽ የሚሰማበት፣ አብሮነት የሚጸናበት በስተመጨረሻም በአንድ አሸናፊ እውነት ኢትዮጵያዊነትን የምንገልጥበት የእርቅና የወዳጅነት መንፈስ ነው::

ሰላምን ለኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያን ለሰላም የሚለው መነሻ ሀሳቤ ሀገራችንን ከጦርነት የምንታደግበት፣ ትውልዱን ከጥላቻ፣ ፖለቲካውን ከአክራሪ እና ፅንፈኛ አስተሳሰቦች ነጻ የምናወጣበት እንዲሁም ለአዲስ ህዝባዊ አስተሳሰብን የምንሰናዳበት የተሀድሶ ምእራፍ ነው:: በመጣንበት መንገድ መሄድ ሳይሆን አዲስ አቅጣጫ መቀየስ ይኖርብናል:: በሀሳብ የዳበረ፣ በውይይት የሰመረ፣ ትላንትን በይቅርታ የሻረ፣ ዛሬን በእርቅ የተቀበለ፣ መጪውን በተስፋ የሚቀበል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚጠሩበት አቅጣጫ ያስፈልገናል::

ጓዳ የተደበቁ የጋራ እሴቶቻችን ወደአደባባይ ወጥተው ኢትዮጵያዊነትን ይናገሩ:: መካሪና አስታራቂ ሆነው ዘመናትን የቆዩ ትውፊቶቻችን ማን እንደነበርን፣ እንዴት እንደነበርን ጽኑ ፍቅራችንን ይመስክሩ:: በፖለቲካ ትርክት የጨቀዩ አብሮነትን የኳሉ የታሪክ ሰነዶቻችን ለወደቀብን ሀገራዊ መከራ መልስ እንዲሰጡን ወደኋላ መለስ እንበል:: በክፉዎች የተደበቁ ተሳስረንና ተጋምደን የመጣንባቸው ህብረ ቀለሞቻችን ማንነታችንን ይግለጡ:: የለበስናቸውን የዘር ካባዎች አውልቀን በጋራ የሰፋነውን የአብሮነት ሸማ ስንከናነብ ያን ጊዜ ነገሮች እንደምንፈልጋቸው መሆን ይጀምራሉ::

በሀሳብ በልጽገን በመከራዎቻችን ላይ የበላይ እስካልሆንን ድረስ፣ በሀሳብ በልጽገን የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር እስካልነቃን ድረስ ከምኞታችን አንደርስም:: ምኞት ምቹ ልብ ይፈልጋል:: ምቹ ልብ ደግሞ ሰላም ያለበት፣ በፍቅርና በይቅርታ የዳበረ ነው:: ካለሰላም የትኛውም ህልም ፍሬ ማፍራት አይችልም:: ካለእርቅ የትኛውም ዓላማ ግቡን መምታት አይሆንለትም:: ካለንበት ሰጣ ገባ ወጥተን ለሁላችንም ወደሚበጅ የሰላም አንባ ለመድረስ ተግባቦትን ተልዕኮው ላደረገ ውይይት ልባችንን ክፍት እናድርግ::

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም

Recommended For You