በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ነፃ የልብ ቀዶ ህክምና ተደረገ

አዲስ አበባ፡– በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ ነፃ የልብ ቀዶ ጥገና የህክምና ማድረጉን የታዝማ የውስጥ ደዌ እና የቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል አስታወቀ፡፡

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው አለማየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ማዕከሉ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በአካባቢው ለሚገኙ የልብ ህሙማን በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ብቻ ነፃ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

ቀዶ ህክምናው በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ሸይኽ ሀሰን ያባሬ አጠቃላይ ልዩ ሆስፒታል በመገኘት መደረጉን ጠቅሰው፤ የቀዶ ህክምናው ከአዲስ አበባ ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ መደረጉን እና በሀገር ውስጥ የህክምና ቡድን ብቻ የተዋቀረ መሆኑ ልዩ እንደሚደርገው አመልክተዋል፡፡

አሁን የተደረገው የልብ ቀዶ ህክምና ከአምስት ዓመት ህፃን ጀምሮ እስከ 42 ዓመት የዕድሜ ክልል ድረስ ለሚገኙ ታካሚዎች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ህክምናው የተሰጠው ልብ እና ሳምባን ተክቶ የሚሠራ መሣሪያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደ ጅግጅጋ በመውሰድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለቀጣይ ተመሳሳይ የልብ ቀዶ ጥገና ለማከናወን እና በልብ ህክምናው ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል። ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በልብ ህክምናው ዘርፍ ብቁ ባሙያዎችን ለማፍራት እና የህክምና መሣሪያ ለመጠቀም ስምምነት መደረጉን አስታውሰዋል።

በሱማሌ ክልል አካባቢው ያለው ማህበረሰብ ወደ አዲስ አበባ እየመጣ አገልግሎቱን ያገኝ እንደነበር አውስተው፤ የክልሉ ጤና ቢሮና የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ከማዕከሉ ጋር በመተባበር አቅማቸው ለማይፈቅድ ታካሚዎች ህክምናውን ባሉበት በነጻ እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቁመዋል። በቀጣይ ተቋሙ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመሄድ ተመሳሳይ ሥራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ቀጣይነት ያለው ቀዶ ህክምና እንዲሰጥ እና ግብዓት ለማሟላት የሚያስፈልግ ወጪ እና የሰው ኃይል ባለሙያ አስፈላጊውን ጥናትና ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህም በጅግጅጋ ከተማ ቀጣይነት ያለው የልብ ህክምና ሥራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

Recommended For You