በክልሉ ከ800 ሺህ በላይ ጎብኚዎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፡- በሲዳማ ክልል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ800 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን መጎብኘታቸውን የክልሉ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡

የሲዳማ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሩብ ዓመቱ 800 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እና 5 ሺህ የውጭ አገር ጎብኚዎች የክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

እንደ አቶ አበበ ገለጻ ፤ በሩብ ዓመቱ ከጎብኚዎች በተለያየ መልኩ የተገኘ 750 ሚሊዮን ብር ኢኮኖሚው ላይ ፈሰስ ተደርጓል፡፡

የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር በቀጣዮቹ የበጋ ወራት እየጨመረ እንደሚሄድ እንደሚጠበቅ ገልጸው የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ግን በተመሳሳይ ሊቀጥል እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ሶስት ሚሊዮን ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዓመቱ ሁለት ነጥብ 5 ቢሊዮን ብርም ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉንም አክለው ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት ቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ የቱሪስት መዳረሻዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና የቱሪስት የቆይታ ጊዜን ለመጨመር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያሉት ሶስት ትልልቅ የቱሪስት መዳረሻዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ተጨማሪ መዳረሻዎችን ለመጨመር ከሃዋሳ ከተማ በስተደቡብ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ገራምባ በሚባል ቦታ ላይ ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ብቸኛው ፓርክ የሆነውን ሎክ አባያ ብሔራዊ ፓርክን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ሳፋሪ ሎጅ እየተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በክልሉ አምስተኛው የቱሪዝም መዳረሻ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ሁለቱም በግንባታ ላይ የሚገኙት የቱሪዝም መዳረሻዎች በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቁም ገልጸዋል፡፡

ከመዳረሻ ልማት ጎን ለጎን ነባር የቱሪስት መዳረሻዎች ላይ እሴት የመጨመር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረው፤ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥራት፣ በብቃት እና በቁጥርም በብዛት እንዲደራጁ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝሙን ሀብት የማስተዋወቅ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው፡፡

የሲዳማ ክልል በተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑን አመልክተው፤ ሁሉም ሰው ወደ ክልሉ በመምጣት ክልሉን እንዲጎበኝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You