ስምምነቱ አመቺ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመዘርጋት ያስችላል

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከጃፓኑ ዶዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ካምፓኒ ጋር ያደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ ዘላቂና አመቺ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የዶዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዩማ ሳኪ የመግባቢያ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፤ ስምምነቱ የድርጅታቸው አጠቃላይ ራዕይ ከሆነው የገቢ ዋስትናን ከማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚን ከመምራት፣ ለማህበረሰቡ መሠረታዊ ምርትና አገልግሎት ከማድረስ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረጉ ቢዝነሶች ላይ ኢንቨስት ያደርጋል ያሉት ዶክተር ብሩክ፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ታሳቢ ያደረጉ ሀገራዊ ስትራተጂዎችን ለማስፈጸም የሚረዱና ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሥራ ሃሳቦችን እንደሚያበረታታም ጠቁመዋል።

አክለውም፤ ትብብሩ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ የሚሰሠሩ ሞተር ብስክሌቶችን በስፋት በማቅረብ በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የትራንስፖርት ሥርዓቱን ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ታዳሽ ሃይል ላይ የተመሠረተ የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት የካርበን ልቀትን በከፍተኛ መጠን እንደሚቀንስ የገለጹት ዶክተር ብሩክ፤ ስምምነቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡

የዶዳይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዩማ ሳኪ በበኩላቸው፤ አጋርነቱ የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ዘርፍ ወደ ኤሌክትሪከ ተኮር ተሽከርካሪዎች ለመቀየር ወሳኝ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኩባንያው በቀጣይ በ12 ወራት ውስጥ እስከ 100 የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን በመትከል፤ የአጠቃቀም መረጃ በመሰብሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ ዩማ ሳኪ አመላክተዋል።

በሶስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ተደራሽ ማድረግም ዓላማችን ነው ያሉት ዩማ ሳኪ፤ ዶዳይ አስተማማኝ የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሠረተ ልማቶችን በማቅረብ የኢትዮጵያን የከተማ ትራንስፖርት ገጽታ ለመለወጥ ያለመ ኩባንያ ነው ብለዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You