የቅኝ ግዛት ውሎችን ወደ መቃብር  የሸኘ ታሪካዊ ስምምነት !

“ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፤ ዓባይ ግብጽን እንጂ ምን ጠቀመ ለሀገሩ ፤ ዓባይ ዘፈን እንጂ አልሆነም እንጀራ፣ ዓባይ ለም አፈሩን ጠርጎ ሲና በረሃን ያበለጽጋል…” እየተባለ በዘፈንም በግጥም በየዘመናቱ ሲተችና ሲወቀስ ኖሯል። ዛሬም ቢሆን ከዓባይ እየተገኘ ያለው ጥቅም ዓባይን በጭልፋ እንደሚባለው ነው።

ሀገራችን ለረጅም ዓመታት የወንዙን ውሃ ለማልማት የተለያዩ ጥረቶች አድርጋለች ፤ ጥረቶቿ ቅኝ ገዥዎች ለራሳቸው ጥቅም ባስቀመጣቸው ኢትዮጵያን ያላካተቱ የክልከላ ውሎች ምክንያት ተግባራዊ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

እነዚህ ለወንዙ ከፍተኛውን ውሃ የምታበረክተውን ሀገራችንን ያላካተቱ የቅኝ ግዛት ውሎች ፤በዓባይ ወንዝ ላይ ለኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚውል ግድብ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጠችበት ጊዜ ጀምሮ ትልቅ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።

በነዚህ ውሎች ምክንያት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለሥራው የሚሆን ብድር ከመከልከል ባለፈ፤ ግንባታውን ለማስተጓጎል ባፉት አስር ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ሲደረጉ ቆይተዋል ። ከጫና ያለፉ ሴራዎች ሲደረጉ ቆይተዋል።

በተለይም በወንዙ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዳይሰፍን ፤ ዘመን ያለፈባቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች የሙጥኝ ያለችው ግብጽ ፤ ኢፍትሃዊነትን በዓለም አቀፍ አደባባዮች ድምጿን ከፍ አድርጋ ስታሰማ ፤ ለያዥ ለገላጋይ በማይመች መንገድ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ተስተውላለች።

የኢትዮጵያ መንግሥትና ኢትዮጵያውያን የወንዙን ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ታሳቢ ባደረገ መንገድ በዲፕሎማሲም ከፍ ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ፤ አንድም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ውሎች ዘመናቸው እንዲያበቃ ፤ በሌላ በኩል የግድቡን ሥራ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

የግድቡን ሥራ በራሳቸው ገንዘብ፣ ጉልበትና እውቀት ተጨባጭ በማድረግ ፤ በወንዙ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን አዲስ የታሪክ ምእራፍ በብዙ ፈተና ውስጥ ሆነው መጻፍ ችለዋል ። ሥራው አሁን ያለው ትውልድ እንደ ትውልድ በአንድ ድምጽ ሆ! ብሎ የሠራው፤ የሀገራዊ የጋራ ትርክቱ አካል ነው።

የአፍሪካ ሀገሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በተለያየ የቅኝ ግዛት ውሎች የታሰሩ ፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ሳይቀር ተጠቃሚ የሚያደርጓቸውን መብቶቻችውን መጠቀም እንዳይችሉ በብዙ ክልከላ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ። በተፈጥሮ ሀብቶቻቸው እንደልባቸው እንዳያዙና እንዳይጠቀሙ በኢ- ፍትሃዊነት የታሰሩ ናቸው። ከእነዚህ ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ካልተያዙ ሀገሮች ብቸኛዋ ትሁን እንጂ የተለያዩ ሕጎች በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መልኩ የቅኝ ግዛት ተጽእኖ አርፎባታል። በዚህም በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የባለቤትነት መብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳትችል ተደርጋ ቆይታለች።

ሀገሪቱ ለናይል ወንዝ ከፍተኛውን የውሃ መጠን ብታበረክትም ፤ ከውሃ ሀብቱ ተጠቃሚ ሳትሆን የበይ ተመልካች ሆና ለዘመናት ቆይታለች። በውሃ ሀብቱ ላይ ምንም አይነት መብት እንዳይኖራትም ባልተስማማችባቸው የቅኝ ግዛት ውሎች ታሥራ ቆይታለች ።

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትና በውሃ ሀብቱ እኩል ባለመብትነት እንዲኖራት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች። በዚህም አሁን ላይ ውጤታማ መሆን ችላለች።

ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በሰላም በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የውጪ ፖሊሲን የምትከተል ከመሆኗም አኳያ ፤ የናይል ውሃን በፍትሀዊነት ለመጠቀም በተፋሰሱ ሀገራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች ።

በርግጥ ሀገሪቱ የዓባይ ግድብን ለመገንባት የተነሳችው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ውሃ ለማሳጣት አስባ ሳይሆን ከ60 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎቿን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ፤ ይህ ደግሞ ከሞራልም ከዓለም አቀፍ ሕግም አንጻር ተቀባይነት ያለው ነው።

ይህንን የዓደባባይ እውነታ በማጣመም ጉዳዩን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ የግብጽ መንግሥት ረጅም ርቀት ተጉዟል ፤ ጉዳዩን ለጸጥታው ምክር ቤት ከ15 ጊዜ በላነሰ አጀንዳ ለማድረግ ሞክሯል ። በጉዳዩ ዙሪያ በያዘችው የዲፕሎማሲው የበላይነት እነሆ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ከመገንባት አልፎ በሁለተኛ ዙር ሃይል የማመንጨት ተግባር ላይ ተደርሷል።

አሁን ላይ ግብጽም ሆነች ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት ምንም አይነት የውሃ እጥረት ሳይገጥማቸው ውሃው ኤሌክትሪክ አመንጭቶ በበቂ ሁኔታ ለታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መድረስ ችሏል። ዛሬም የውሃ መጠኑ ምንም ሳይቀንስ ማግኘትና መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን የናይልን ውሃ በፍትሃዊነት ለመጠቀም ለረጅም ዓመት ሲደረግ የነበረው ትግል የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተግባራዊ ወደሚሆንበት የታሪክ ምእራፍ ተሸጋግሯል። አዲሱ የትብብር ምዕራፍ የተፋሰሱ ሀገራት የወንዙን ውሃ በፍትሃዊነት ለመጠቀም ፣ የውሃውን ደህንነት በጋራ ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ለሁሉም መብት እኩል እውቅና የሚሰጥ ነው ።

በቀጣይ ይሄንን የሚያስተዳድር ኮሚሽንና የጋራ የሕግ ማዕቀፍ ይዘጋጃል። በዚህ የሕግ ማዕቀፍም ሁሉም እኩል መብትና ጥቅም ኖሯቸው በጋራ ሀብቱ የሚለሙበት እድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ፍትሃዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ወደፊት ባስቀደመ መልኩ የወንዙ ውሃ ተጠቃሚ ትሆናለች ።

በስድስት የተፋሰሱ ሀገራት የተፈረመው የትብብር ማዕቀፉ ከዚህ በፊት በናይል ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ላይ የነበረውን በኢ- ፍትሃዊነትን የታሰሩ የቀኝ ግዛት ውሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ የሚያስችል ነው ። በቀጣይም ለስምምነቱ ተግባራዊነት ፊርማቸውን ያላኖሩ ሀገራትም ፤ የቅኝ ግዛት ውሎች ዘመኑን የማይዋጁና የትም የማያደርሱ መሆናቸውን ተገተንዝበው ስምምነቱን በመፈረም ለፍትሃዊነት ያላቸውን ቁርጠኝነት በአደባባይ ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

አዶኒስ (ከሲኤምሲ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You