ተስፋ ሰጪው የጥጥ ምርምር

ዜና ሐተታ

የጥጥ ምርምር በኢትዮጵያ ስድስት አስርት ዓመታትን እንዳስቆጠረ የጥጥ ተመራማሪዎች ያነሳሉ፡፡ የጥጥ ሰብል በከፍተኛ ሁኔታ በተባይ ተጠቂ በመሆኑ የምርት ሂደቱ ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚሻም ያስረዳሉ፡፡ ጥጥን ከተባይ ለመከላከል በምርት ወቅት እስከ አምስት ጊዜ ድረስ የኬሚካል ርጭት ይደረጋል። ይህም ለከፍተኛ የሰው ኃይል እና የገንዘብ ወጪ መዳረጉን ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ለመላው ሀገሪቱ የጥጥ ዘር አቅራቢ ሲሆን፣ ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ በመስኖ እየታገዘ የምርትና ጥራት ደረጃቸው የተሻሻሉ የጥጥ ዘሮችን ለተጠቃሚዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አለማየሁ እንዳሉት፣ ወረር ግብርና ማዕከል በአካባቢው እየለማ የነበረውን ጥጥ በተሻሻሉ የግብርና ቴክሎጂዎች ለመደገፍ ታስቦ በ1956 ዓ.ም ነው የተቋቋመው። ማዕከሉ የጥጥ ምርትን ዓላማ አድርጎ ይቋቋም እንጂ፣ በጊዜ ሂደት በተፈጥሮ ሀብት አያያዝና ሌሎችም የምርምር መስኮች ላይ በርካታ ሥራዎችንም ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በማዕከሉ በጥጥ ላይ ሲካሄድ የነበረው ምርምር በዋናነት የምርት መጠንን ለመጨመር ትኩረት ያደረገ መሆኑን አስታውሰው፤ በኋላ ላይ ወደ ምርት ጥራት ምርምር መሸጋገሩን ይገልጻሉ፡፡

በምርምር ማዕከሉ የጥጥ ምርምር ፕሮግራም ራሱን ችሎ የተቋቋመው በ1981 ዓ.ም መሆኑን አንስተው፤ ከፕሮግራሙ መቋቋም በኋላ የኢንዱስትሪ ሰብሎች ምርምር ፕሮጀክትን በመጀመር የጥጥ ዘረመሎችን መጨመር፣ የምርት ብክነትን ማጥናትና መፍትሔ ማፈላለግ፣ የጥጥ ጥራትን መጨመርና አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ የተባይ መከላከያዎች ለማምረትን ዓላማው አድርጎ ሲሠራም ቆይቷል፡፡

ፕሮጀክቱ በመስኖና በጥጥ በሚለሙ የሀገራችን አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ በድምሩ 43 የተሻሻሉ የጥጥ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት በአብዛኛው ተጠቃሚው ጋር እንዲደርሱ አድርጓል ይላሉ። ከተሻሻሉ የጥጥ ዝርያዎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት በመመረት ላይ ያሉት ውስን ስለሆኑ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ፣ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ አራት ዝርያዎችን ከምርምር ማዕከሉ ማውጣት ተችሏል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ዳይሬክተሩ እንደሚጠቁሙት፤ በአጠቃላይ በሰብሉ ላይ በተደረጉ ምርምሮች በ1960ዎቹ በሄክታር 18 ኩንታል የነበረውን የምርት መጠን በአሁኑ ሰዓት ወደ 54 ነጥብ 3 ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡

የጓይ ትል የሚያስክትለውን የምርት መቀነስና ለኬሚካል ግዢ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ የሚያስችሉ ቢፒ ጥጥ የተሰኘ ዝርያን ከውጭ አስገብቶ ማላመድም የተቻለ ሲሆን፣ ሌሎች ዝርያዎችንም በማፍለቅ በግምገማ ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

በጥጥ ላይ የተደረጉ ምርምሮች ረጅም መንገድ የተጓዙና ሰፊ ለውጥም የተገኘባቸው ቢሆኑም ሰብሉ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ያገኘ አለመሆኑ፣ የጥጥ ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥ የጥጥ ምርትን ከመጠቀም ይልቅ ከውጭ ማስገባት ላይ እንደሚያተኩሩ የተናገሩት የማዕከሉ ዳይሬክተር፣ የጥጥ ምርት ፍላጎት አለመኖር ምርቱ እንዳይጨምር እንቅፋት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ጥጥ ገበያ ከማጣቱ የተነሳ በያማሳው ላይ ገበያ ያጡ ትልልቅ የጥጥ ክምሮች እንደሚስታወሉም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በሀገራችን ለጥጥ ምርት ምቹ የሆነ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም ከዚህ ውስጥ ጥቅም ላይ ማዋል የተቻለው አራት ከመቶ እንኳ የማይሞላ 101 ሺህ ሄክታር ብቻ።

ኢንዱስትሪዎቻችን ኢትዮጵያ ጥጥ የማምረት አቅሟ እስክምን ድረስ ነው? የሚለውን ግንዛቤው ያላቸው አይመስልም ያሉት ዳይተሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ አምራችን ከምርት ፈላጊው የሚያቀራርብ አካልና አሠራር ይፈልጋል ሲሉ ያስረዳሉ።

መንግሥትና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የግብርና ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተቀራርበው መሥራት ቢችሉ የጥጥ ምርትን ለሀገራችን ጨርቅ አምራች ኢንደስትሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ልክ ወደ ውጪ እንደምንልካቸው ቡና እና መሰል ምርቶች ሁሉ ወደ ውጪም በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት ይቻላል ይላሉ፡፡

የዘርፉ ተመራማሪ አቶ ዶኒስ ጉርሜሳ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከሁለት ወራት በፊት በመልካ ሰዲ ብሔራዊ የጥጥ ምርምር የመስክ ቀን ሲያካሂድ እንደተናገሩት፤ የመልካ ሰዲ የጥጥ ምርምር የሙከራ ማሣ በሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ላይ የሚደረግ ሙከራ ነው።

በባዮቴክኖሎጂ የታገዘውና በሌሎች ዓለማት ውጤታማ በመሆኑ የተመሠከረለት የቢቶ ኮተን ዘር እና በማዕከሉ በምርምር ላይ የሚገኘው ምርምር ለበሽታ እና ለጥጥ ተባይ እስከ አምስት ጊዜ በተደጋጋሚ የሚረጨውን የኬሚካል ርጭት የማይፈልግ መሆኑን ይገልጻሉ።

የጥጥ ተባይን ለመከላከል በተደጋጋሚ የሚደረገው የኬሚካል ርጭት የሰው ኃይል እና የኬሚካል ዋጋ ከፍተኛ ወጪ መሆኑን የዘርፉ ተመራማሪ አንስተው፤ ምርምሩ ተስፋ ሰጪ ውጤት የተገኘበት መሆኑን ነው ያነሱት።

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You