ለጽሁፌ መነሻ ሃሳብ ይሆነኝ ዘንድ “የሚያበላህ ይቆጣጠርሃል! “He who feeds you, controls you!” የሚለውን የቀድሞውን የቡርኪኖፋሶ ፕሬዚዳንት ካፒቴን ቶማስ ሳንካራ የምንጊዜም ምርጥ አባባል ወስጃለሁ፡፡ ይህ የቶማስ ሳንካራ ንግግር አፍሪካ ውስጥ ያለውን እውነታ እስካሁን በተጨባጭ የሚያመላክት ነው፡፡
አብዮተኛው ቶማስ ሳንካራ የአፍሪካን ኢንዲፔንደንስ ፓርቲን ወክሎ እ.ኤ.አ ከ1983 እስከ 1987 የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ አምስተኛው ፕሬዚዳንት ሆኖ አገልግሏል፡፡ ለሀገሩ ያለውን ታማኝነት እና ፍቅር እስከ ሞት በዘለቀ መስዋእትነቱም አስመስክሯል፡፡ የሀገሪቱን ጦር በመቀላቀል እ.ኤ.አ ከ 1966 ዓ.ም አንስቶ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ አገልግሏል፡፡
እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ታይቶ የጠፋው ቶማስ ሳንካራ የቡርኪናፋሶ ታላቅነት እንዲረጋገጥ በነበረው ጥልቅ ምኞት ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ሪፎርሞችን ጨምሮ በርካታ የለውጥ አስተሳሰቦችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ገና በ33 ዓመቱ ወደ ሥልጣን የወጣው ሳንካራ፣ በዓመቱ የሀገሩን መጠሪያ ስም ከአፐር ቮልታ ሪፐብሊክ ወደ ቡርኪናፋሶ ቀየረ፡፡ ይህም ለጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ሀገሩ ቡርኪናፋሶ ራሷን የቻለች መሆን እንዳለባት ያመነው ቶማስ ሳንካራ፣ “የሚያበላህ ይቆጣጠርሃል!” በሚለው የለውጥ ሃሳቡ ርዳታን እና ከመጠን ያለፈ ብድርን ተከትሎ የሚመጣው እጅ ጥምዘዛ የሀገር እና የሕዝብን ፖለቲካዊ ነጻነት እንደሚፈታተን ለማስረዳት ሞክሯል፡፡
ራስን መቻል፤ በተለይም በምግብ ራስን የመቻል ጉዳይ የፖለቲካ ነጻነትን ምሉእ ለማድረግ ትልቅ አቅም መሆኑን በመግለጽ፤ ሀገሩ በምግብ እህል እራሷን መቻል እንደሚኖርባት በስፋት ለማስገንዘብ ሞክሯል። አስተሳሰቡን መሠረት ያደረጉ የለውጥ ሥራዎችንም ሠርቷል ።
ይህ አፍሪካዊ የለውጥ ሃዋርያ፤ ያሰበውን ማሳካት ባይችልም፤ እንደ አንድ የለውጥ መሪ በወቅቱ ያነሳው ይህ ሃሳብ ዛሬ ድረስ ትልቅ የፖለቲካ እውነታ ተደርጎ ይወሰዳል። ጉዳዩ በምግብ እህል እራሳቸውን ላልቻሉ ሀገራት እስካሁን ፈተናም ሆኖ ቀጥሏል። ለበለጸጉ ሀገራትም ያሻቸውን የማዘዣ እና የማስፈፀሚያ ካርድ ሆኖ እስከ ዛሬ ዘልቋል፡፡
ለመሆኑ ራስን በምግብ መቻል /Food and Nutrition Security/ ማለት ምን ማለት ይሆን?
በምግብ ራስን መቻል የሚባለው ፅንሰ ሃሳብ የተፈጠረው እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ አጋማሽ እንደሆነ የዓለም አቀፉ የምግብ እና የግብርና ድርጅት ፋኦ (FAO) መረጃ ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ በ1974 ዓ.ም የዓለም የምግብ ድርጅት ስብሰባ ‘ዎርልድ ፉድ ሰሚት’ የመጀመሪያ ትኩረት በመጠን እና በአቅርቦት ላይ ነበር። በምግብ ራስን መቻልን ሲተረጉመውም፣
“Availability at all times of adequate world food supplies of basic foodstuffs to sustain a steady expansion of food consumption and to offset fluctuations in production and prices.”
በግርድፉ ወደ አማርኛ ስንመልሰው “በሁሉም ጊዜ የምናገኘው በቂ ዓለም አቀፍ የምግብ አቅርቦት ለዘላቂ የምግብ ፍጆታ ስርጭት እንዲሁም ለምርት እና ዋጋ መዋዠቅ መፍትሄ፡፡” ሲል ፈቶታል ይለናል፡፡
ይህ ትርጓሜ እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን በተለይም እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም በከፍተኛ ደረጃ ተፅእኖ ፈጣሪ የነበረውን “Poverety and Hunger” /ድህነት እና ረሃብ/ የተሰኘውን የአለም ባንክ ሪፖርት ተከትሎ “Access of all people at all times to enough food for an active, healthy life”. “ጤናማ ለሆነ ሕይወት ለሁሉም ሰው የሚያስፈልግ የምግብ አቅርቦት” በሚል አዳብሮታል፡፡
በአባወራ ደረጃ የሚወርደው በምግብ ራስን የመቻል እሳቤ፤ ሰዎች በቂ ምግብ ለማግኘት አካላዊ፣ ማህበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት እስካለባቸው ድረስ በምግብ ራስን መቻል የሚባለው ጉዳይ ተጨባጭ አይሆንም ሲል ያትታል፡፡ አተገባበሩ ላይ ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል ደግሞ ኢኮኖሚያዊውን የምግብ
መልክ ገልጠን የታዳጊ ሀገራትን ተጨባጭ መረጃዎች እንቃኝ፡፡
የምግብ ወጪያች ከአጠቃላይ ወጪያችን ምን ያህሉን ይሸፍናል?
እንደ ባዮሜድ ሴንትራል የቅርብ ወራት መረጃ በታዳጊ ሀገራት በተለይም ከሳህራ በታች ባሉ ሀገራት የምግብ ወጪ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይኸውም ከ65% በመቶ እስከ 70% በመቶ የሀገራቱን የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) እንዲሁም 70% በመቶ የሚሆነውን የአንድ ቤተሰብ ወጪ ይሸፍናል፡፡
ሌላኛው የሳህል ቀጣናን እና የአፍሪካ ቀንድን የሚዳስስ የዓለም ባንክ ዘገባ ደግሞ በቡርኪናፋሶ፣ በቻድ እና በማሊ አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ ሰዎች በራሽን እንደሚደገፉ ሲገልፅ፤ እ.ኤ.አ ከ2017 አስከፊ ረሃብ በኋላ በተደረገላት ድጋፍ ሶማሊያ ቤተሰቦች በቀን ለሁለት ጊዜ መመገብ በማስቻል ለውጥ ማስመዝገቧን ይገልፃል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ሰላሳ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች በአስከፊ ሁኔታ የምግብ ዋስትና የሌላቸው መሆኑን የሚያስነብበው ዘገባው፣ ኬንያ እና ሶማሊያን የመሳሰሉ የቀጣናው ሀገራት ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ አይተውት የማያውቁት አይነት ድርቅ እንዳጋጠማቸው ይጠቁማል፡፡
በዚህ ተጨባጭ እውነታ ስር የምትካተተው ኢትዮጵያም ስምንት ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ በምግብ እና በገንዘብ ድጋፍ ስር እንደሚገኙ የዓለም ባንክ ዘገባ ገልፆ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በስፋት እያከናወነችው ያለውን በራስ ጥረት ምግብ የማምረት እና የአረንጓዴ ዐሻራን አይነት ስኬታማ ጉዞ ለሁሉም ቀጣናዎች መፍትሄ ነው ሲል ያስቀምጠዋል፡፡
ይህንኑ ነጥብ የሚደግፈው የዓለምአቀፉ የምግብ ፕሮግራም (WFP) ዘገባ፣ ለኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አሁንም ዋና ትኩረቷ እንደሆነ በማስታወስ፣ በአሁኑ ጊዜም ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ያልተስተዋለ አመርቂ ሥራ በድህነት ቅነሳ እና በመሠረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ሰርታለች ሲል አስነብቧል፡፡
ይህንን ጥረት አስቀጥለን በቅርቡ ሀገራችንን ከምግብ ርዳታ ጥገኝነት የምናላቅቅበት መንገድ ላይ እንዳለን መስካሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለተከታታይ ዓመታት የተሰራባቸውን የኩታ ገጠም የእርሻ ዘዴ ተጠቃሚ አካባቢዎች ሳንዘነጋ፣ ከሰሞኑ በሐረሪ ክልል ያስተዋልነው ፈጥኖ ደራሽ የማሽላ ምርት እንዲሁም ተስፋ ሰጪው የአማራ ክልል የሩዝ ምርታማነት የያዝነውን መንገድ ውጤታማነት ያመላክታል፡፡
በቤተሰብም ደረጃ ቢሆን እንዴት አድገን ራሳችንን ከምግብ ጥገኝነት እናላቅ? ብለን ብንጠይቅ ብዙዎች የሚሰጡን ምላሽ ምግብን በተቻለ መጠን፣ በተገኘ አስቻይ ክፍት ቦታ ሁሉ ማም ረት እንደሚገባን ነው፡፡
በዚህ ረገድ ከጤናችን አንስቶ እስከ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መቋቋሚያነት ድረስ የተዘረጋው መፍትሄ፣ ቢያንስ ለራሳችን የሚሆን የጓሮ አትክልት ማምረት መጀመራችን እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይህም በጓሯችን፣ በእጃችን የሚገኝ ወርቅ መሆኑን ተገንዝበን ለተሻለ የነገ መዳረሻ ታላቅ የግብርና አብዮት ከየቤታችን መጀመር እንደሚገባን የሚያመላክት ነው፡፡
እንደ ሀገር ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን ታላቁ ቶማስ ሳንካራ እንዳለው “የሚያበላህ ይቆጣጠርሃል” ነውና፣ እጣ ፈንታችን፣ በሌሎች በርዳታ ስም ያሻቸውን እንዳሻቸው ከሚዘውሩ ‘የጠገቡ’ ሀገራት እጅ ላይ እንደሚወድቅ ለመገመት የሚከብድ አይደለም፡፡
ዮናታን ጠለለው ብዙነህ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2017 ዓ.ም