በዞኑ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፡- በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአዳዲስ የግብርና አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ 30 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ የእርሻ መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ሃውልቱ ታደሰ እንዳሉት፤ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል የተቀመጠውን የስንዴ ልማት መርሃ ግብር ለማሳካት እየተሠራ ነው፡፡

ለዚህም በያዝነው የበጋ ወራት 29 ሺህ 748 ሄክታር መሬት ለመስኖ ስንዴ ልማት መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ እስካሁን በተከናወነ ጥረትም 3 ሺህ 652 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር ሥራ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በመስኖ ስንዴ ልማቱ ከ60 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን በመስኖ ልማት አሠራርና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም በየደረጃው ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግሉ 92 አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ አውታሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ 23 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመስኖ ካናል ጠረጋ በማከናወን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም ለመስኖ ልማቱ የሚውሉ አራት ሺህ ነባር የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን አርሶ አደሮቹ ማዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ 249 አዳዲስ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች መቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በሄክታር 32 ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን ዘንድሮ የተሻለ ቴክኖሎጂንና ግብዓትን በመጠቀም በሄክታር ወደ 40 ኩንታል ለማሳደግ ታቅዶ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ መታቀዱን ጠቁመው፤ ከሚለማው መሬትም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይጠበቃል፡፡

በዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ግማሽ ሄክታር መሬት አርሰው ለዘር ሥራ ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እሸቴ ማሩ ናቸው፡፡

በአካባቢያቸው የተገነባውን የመስኖ ካናል በመጠቀም በስንዴ ከሚያለሙት መሬት 20 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጋሻው ሲሳይ በበኩላቸው፤ በኩታ ገጠም እርሻ አንድ ሄክታር ማሳቸውን በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት መሬት የማለስለስ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡

ከሚያለሙት መሬትም 40 ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸው፤ ያመረቱትን ምርት በአካባቢያቸው ለሚገኙ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት በገበያ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን እንዳቀዱም ገልፀዋል፡፡

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ልማት 40 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ በሁለት ዙር አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የምግብ ሰብሎችን ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You