ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በታሪካቸው ከፍላጎታቸው ጋር የሚስማማ የፖለቲካ ወይም የአገዛዝ ሥርዓት ኖሯቸው እንደማያውቅና ከዚህ ጋር ተያይዞም በየዘመናቱ የነበሩ መንግስታት ያለፉባቸውን መንገዶች መዳሰሳችን ይታወሳል:: ዛሬም ተከታዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል::
ሰዎች ማንነታቸውን ገዢዎች ወደ መረጡላቸው ማንነት እንዲለውጡ ለማድረግ ሥርዓቶች ይፋዊና ስልታዊ ጫና ተጠቅመዋል:: በአመለካከትና በርዕዮተዓለማዊ ሥርዓታቸው ውስጥ በብሔር-ብሔረሰብ ማንነታቸው፤ በእምነታቸው፤ በፆታቸው፤ በሙያቸውና በመሳሰሉት ከፍና ዝቅ የሚያደርጉ ወይም የሚያበላልጡና የሚያቃርኑ እሴቶችን ቀርጸዋል::
ይህ አንዱን የሚያኮራና ሌላውን የሚያሸማቅቅ ነበር:: የየሥርዓቱ ገዢ መደብ ባንድ በኩል ለራሱ ማንነት የሚደምቅና የሚያስከብር በሌላ በኩል በሌላው ማንነት ላይ የሚያሳፍርና የሚያስቀይም ቀለም ይቀባል:: ለሌሎች ያለ ሥራቸውና ያለ ስማቸው ስም ሰጧቸው:: የሰው አእምሮ ተፈጥሮ ያልፈጠረውን ልዩነት ፈጠረ:: ለአንድ ወገን ልዩነቶች ጸጋ መሆናቸው ቀርቶ እርግማን ሆነ፤ ለሌላው ወገን አንድነት ኃይል መሆኑ ቀርቶ ክፋት ሆኖ ታየ:: አንዱን በማቀፍ ሌላውን ለመግፋት በሐሳብ የተዘረጋው ይህ ጠባብ የልዩነት መስመር ቀይ መስመር በመሆን ዜጎችን ከፋፈለ:: ሀገሪቱ ግዙፍ ናት፤ ሕዝቡም ሰፊ ነው::
የሥርዓቱ ማሕበራዊ መሠረትና ፍላጎት ግን የሰፋ አድማስ አልነበረውም:: በትክክል የሚወክለው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሳይሆን የጥቂት ግለሰቦችን ፍላጎትና ጥቅም ነው:: እዚህ ጋር አንድ የዓፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ቱባ ባለሥልጣን «ሕዝብን የምንገዛው አንድ ምዕተ-ዓመት ወደ ኋላ አስቀርተን (መልሰን) ነው» የሚል አስተያየት እንደሰጡ ይነገራል:: ይህ አስተያየት የነበረው ጭቆና ምን ያህል አፋኝ እንደነበረ በትክክል ይገልጻል:: በሀገሪቷና በሕዝቦቿ ቁመና ልክ የሚለካ የፖለቲካ አስተሳሰብና እምነት አልነበረም::
የሁሉንም ድምጽ መስማት ወይም ማዳመጥ፤ የሁሉንም ፍላጎትና ጥያቄ ማወቅና መመለስ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓትና አቅም መፍጠር አልተፈለገም:: የገዢዎች ገዢ ሐሳብ የገዥዎችን ፍላጎት ማስተዳደር እንጂ ዜጋን መንከባከብና ሀገርን ማሳደግ አልሆነም:: ዜጋን መቆጣጠር፤ አስተሳሰቡንና እንቅስቃሴውን መገደብ የገዢዎች ዋና ሥራ ሆነ:: በእርግጥ መሪዎች ስለሀገር ዕድገትና ልማት በቁጭት ሲናገሩ እንሰማቸዋለን:: ሀገር የሚያለማውን ሕዝብ ግን ያፍናሉ::
ሕዝብን፤ ዜጎችን ወደ ታች በመጫን ሀገርን ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች ባሏት ሀገር ውስጥ መንግሥት የሁሉንም ፍላጎትና መብት፤ ክብርና ጥቅም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ይጠበቅበታል:: ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ በየቦታው የሚነሱትን ችግሮች ማፈን የሚያስችል አቅም መፍጠር ግድ ይሆንበታል:: የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት በአግላይነቱ ሁሌም ትርምስ የማይለየው ነበር:: በግለሰብ ወይም በጥቂት ግለሰቦች ስብስብ ወይም ማዕከልነት ተፈጥሮ የሚንቀሳቀስ የትኛውም የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓት በባሕርይው አግላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ችግርን የመረዳትና የመፍታት፤ ከጊዜ ጋር የሚሄድ አስተሳሰብና አመለካከት የመቅረጽ አቅም አልነበረውም:: በዚህ ሰበብ ሥርዓቶች በዋነኛነት ተጠምደው የኖሩት ሀገርን በማልማት ወይም በማሳደግ፤ የሕዝብን ሕይወትና ኑሮ በማሻሻል ላይ ሳይሆን በአገዛዝ ሥርዓቱ ጥበቃ ላይ ነው:: ለጥበቃው የነበራቸው አቅም ራሱ በሴራ፤ በግድያ፤ በአፈና፤ በእስርና በግዞት ላይ የተመሰረተ ነው::
ርዕዮተዓለም የሕዝቦችን የልብና የሥነ-ልቡና ስብራት የሚጠግን ወይም የሚፈጥር፤ የሕዝብን ጤናማ ግንኙነት የሚመርዝ ወይም የተመረዘውን ግንኙት የሚያሽር ነው:: የሚቀረጸውና የሚደራጀው ሀገርን በሚመራው የፖለቲካ ሥርዓት ባሕርይ ነው:: ጨቋኝ ሥርዓቶች ዜጎችን የሚከፋፍልና የሚያቃርን ርዕዮተዓለም ይጠቀማሉ:: በሰዎች መካከል ያለው የልዩነት ግድግዳ በመጀመሪያ የሚጠነሰሰው በግለሰብ ወይም በተቧደኑ ግለሰቦች አእምሮ ውስጥ ነው-አንዱን ለማቀፍ ሌላውን ለመግፋት፤ አንዱን ወደ ውስጥ ለማስገባት ሌላውን ወደ ውጭ ለማስወጣት:: አንድ ፀሐፊ በትክክል እንደገለፀው «የቁሳቁስ አጥሮች የሚሰሩት የአእምሮ አጥሮች ሲታነፁ ነው::
በእርግጥ የእውነተኛ ችግሮች ምንጭ የአእምሮ አጥሮች ናቸው:: ከፍርሃት ወይም ከዘለፋ፤ ከዘረኝነትና ከሃይማኖቶች አለመቻቻል … የሚነሳ ጥላቻና የጠላትነትስሜት በሕዝቦች መካከል የመለያ አጥርን ገንብቷል፡፡» የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ እስካከተመበት የዓጼ ኃይለሥላሴ መንግስት ድረስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓቶች ርዕዮተዓለም መሠረት በዋናነት ሥነ-መለኮታዊ ነው:: ቤተ-እምነቶች በተለይም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዓፄያዊ ሥርዓቶች እንደ አንድ ርዕዮተዓለማዊ ተቋም ስታገለግል ነበር::
ዓፄያዊ ሥርዓቶች የሚሰሩት መልካም ነገሮች እንዳሉ ሆነው የፈፀሟቸው ሌሎች መልካም ያልሆኑ ብዙ ነገሮች ነበሩ:: ይሁን እንጂ ርዕዮተዓለማዊ ተቋማት ዓፄያዊ ሥርዓቶች መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን እንዳላቸው ያስተምሩ ነበር:: እነርሱን ለገዢነት የመረጣቸው፤ ሕዝብን ለተገዢነት የፈጠረው ዓለምን የፈጠረው አምላክ መሆኑን መስክረዋል:: ይህን እምነት በሕዝብ ሕይወት ውስጥ ለማስረጽ ሲባል የተቻለው ጥረት ሁሉ ተደርጓል:: ነገሥታት የማይከሰሱና የማይገሰፁ ሰዎች እንደሆኑ ሰብከዋል:: ከነተረቱ «ሰማይ አይታረስ፤ ንጉስ አይከሰስ» ይባል ነበር::
ሕጎቻቸውና ትዕዛዞቻቸው፤ ሥልጣናቸውና ውሳኔያቸው የማይጣሱና የማይቀለበሱ ናቸው የሚል እምነት በብዙዎች ውስጥ እንዲፈጠር አድርገዋል:: ነገስታት የፈጣሪን ሕግጋትና ትእዛዛት በመሬት ላይ እንዲያስፈጽሙ ሥልጣን የተሰጣቸው ስለሆኑ ፍትህን ሳያጎድሉ እንደሚሰሩ አስተምረዋል:: የሚወስኑት ውሳኔ፤ የሚሰጡት ትዕዛዝና የሚወስዱት እርምጃ ፈጽሞ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ተብሎ እንዲታመን ደክመዋል:: የነበረውና የሆነው እውነት ግን ከዚህ ይለያል:: ለዚህ ነው ካርል ማርክስ ርዕዮተዓለም የውሸት ንቃተ-ሕሊና ነው ያለው::
የርዕዮተ ዓለም አንዱ አካል ግብረገብ ነው:: የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓቶች የነበራቸው የግብረገብ አቅም ደካማ ነው:: ግብረገብ የጎደለው ፖለቲካ በሕዝብ የሚታመንና የሚከበር አይደለም:: በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና መተማመኛ የሕዝብ ድጋፍ ሳይሆን በሕዝብ ላይ የሚያነጣጥር የታጠቀ ሠራዊትና ፖሊስ ነው:: በእርግጥ በዚህ ሊፈሩ ይችላሉ:: ሊከበሩ ግን ፈጽሞ አይችሉም:: መፈራትና መከበር የተለያዩ ናቸው:: ፍርሃት የሚመጣው ከሚገባቸው አክብሮት ሳይሆን ከኢግብረገባዊና ኢሥነምግባራዊ ድርጊታቸውና ባሕርያቸው ነው:: መከበር የሚገኘው ግን ከፍቅርና እውቅና፤ ከመተማመንና ከአብሮነት ነው::
በጎ ድርጊትና ባህርይ ያስከብራል እንጂ አያስፈራም:: መጥፎ ድርጊትና ባሕርይ ለቅለትና ጥላቻ የሚዳርግ እንጂ መከበርን አያመጣም:: የኢትዮጵያ መሪዎች ምናልባት የተፈጥሮ ሞት እስኪገላግላቸው ድረስ ሥልጣን ላይ መቆየት የሚፈ ልጉት ለሥልጣን የተለየ ፍቅር ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ፍርሃትም ስለነበረባቸውም ነው:: ጭካኔያቸው የሚመ ነጨው ከፍርሃትና ከአላዋቂነታቸው ይመስላል:: በዚህ ጭካኔያቸው በርካታ ዜጎችን በግልጽና በስውር አጥፍተዋል:: ጀግና ለስልጣን ብሎ ወገንን አያጠፋም:: ተቀናቃኝን አቅም ማሳጣት የሚፈለግ እንኳ ቢሆን በሥራ በልጦ በመገኘት እንጂ እስከወዲያኛው እንዳይኖሩ በማድረግ አይደለም::
ሴራና ፍርሃት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ደም ሥሮች ሆነው የቆዩት ለዚህ ነው:: እስካሁን የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተፈጥሮ ችግር አለበት (የተመሠረተበት ፍላጎት ትንሽ ነው፤ ርዕዮተዓለሙ አካታች አይደለም፤ ባርይው ገታራ ነው):: የሚፈጠረው፤ የሚንቀሳቀሰውና የሚተገበረው በሴራ ወይም በሸፍጥ ነው:: የሚመሰረተው በሠፈር በተውጣጡ ጥቂት ሰዎች ሴራ ስለሆነ ማሕበራዊ መሠረቱ ጠባብ ነው:: እዚህ ጋር ሁለት ጉድለቶች ይታዩናል:: አንደኛው የፖለቲካ ሥርዓቱ የሚንቀሳቀሰው ባብዛኛው የጥቂቶችን ፍላጎት ለማስፈፀም ስለሆነ ለብዙኃኑ አግላይ መሆኑ ይታወቃል::
በዚህም ምክንያት ካልተወከለው የሕዝብ ፍላጎት ጋር ይጋጫል:: ሁለተኛ የሥርዓቱ ግትር ባሕርይ ማሕበራዊ መሠረቱን ማስፋት አላስቻለውም:: አግላይ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ሥርዓት የሚፈልገውን ያህል አቅም የማግኘት ዕድል የለውም:: ሌሎችን ማግለል መቻሉን እንጂ ለራሱም የሚገለል መሆኑን አይረዳም:: ጠንካራ መንግሥት ሆኖ ጠንካራ ሕዝብና ሀገር መምራት የሚያስችል መሠረት አይፈጥርለትም:: ራሱን እንደ መንግሥት መቀጠል የሚችለው በጉልበትና በአፈና ነው:: ሕዝብን በማፈን የሚያዳክም መንግሥት በዚያው ልክ ራሱንም ያዳክማል፡፡ መሪዎችና አመራራቸው ከሚገዙት ሕዝብ ጋር በጉልህ የሚንቀሳቀሱት የውጭ ጠላት ወይም ወረራ ሲያገጥም ብቻ ነው::መሪዎች የሕዝብን አስፈላጊነትና ኃያልነት የሚረዱት ይኸኔ ነው::
ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የምትለይበት ታሪክ አላት:: የአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ በቀኝ ገዢዎች ስር በወደቁበት ጊዜ የራሷን ነፃነት አስከብራ የቆየች ብቸኛ ሀገር ነች – ኢትዮጵያ::የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ሁለት ጊዜ ከባድና የተሟላ ዝግጅት የነበራቸው ወረራዎች ፈጽመውባታል:: ሁለቱንም በድል ተወጥታዋለች:: በሀገርም ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ሲታይ ይህ ድል ብዙ ነገሮችን ይናገራል:: ኢትዮጵያ አልሰለጠነችም፤ በኢኮኖሚ አልበለፀገችም፤ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል በወጉ አላደራጀችም፤ በዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ የጦር መሣሪያ አልነበራትም፤ የሕዝቦቿ ውስጣዊ ግንኙነትና አደረጃጀት ጠንካራ ሀገራዊ አቅምና ብሔራዊ ስሜት አልፈጠረም::
በዚህ ላይ ጥቁር አፍሪካዊት ናት:: ይሁን አንጂ ይህቺ ሀገር በኢኮኖሚ የደረጀችውን፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚታገዝ የጦር መሣሪያና የጦር ሠራዊት የነበራትን ነጭ አውሮፓዊቷን ኢጣሊያን በዓለም ታሪክ ፊት፤ ያውም ሁለት ጊዜ፤ ያውም ለሁለተኛ ጊዜ ወረራ ለ40 ዓመታት ስትዘጋች የቆየችውን ኢጣሊያን ድል አድርጋ ነፃነቷን አስከብራለች:: በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል በነበረው የዕድገት፤ የሥልጣኔ፤ የአደረጃጀትና የኃይል ልዩነት አንጻር ኢትዮጵያ ያልታሰበ ድል፤ ይገኛል ተብሎ የማይገመት አሸናፊነት አገኘች:: በጊዜው ይህን የመሰለ ድል ያጣጣመ ሀገርና ሕዝብ መኖሩን እጠራጠራለሁ::
ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ዳግመኛ ወርራ ለማንበርከክ በቁጭት ስትዘጋጅ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አይደለም ለጦርነት መዘጋጀት ለዕለት ጉርስ የሚሆን የኢኮኖሚ አቅም እንኳ አልፈጠሩም:: ይሁን እንጂ ድሉ የጉልበተኛዋ ኢጣሊያ መሆኑ ቀርቶ የእውነተኛ ኢትዮጵያ ሆነ:: ይህ ድል የጎዳው ኢጣሊያን ብቻ አይደለም:: በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በዓለም ላይ የበላይነትና የገዢነት መንፈስ ያደረባቸው ነጮችን ሁሉ ነው:: የሁለቱም ድሎች ወሳኝ ኃይል የተፈጠረው ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ነው:: የመሪዎች ድርሻ የሚናቅ ባይሆንም በሰላም ጊዜ ቦታ ያልነበራቸው፤ መብትና ክብር የተነፈጉ፤ መገፋትና መታፈን፤ ሥቃይና ሞት የደረሰባቸው ጀግና ኢትዮጵያውያን ነበሩ ለሀገራቸው የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ያስመሰከሩት:: የቁርጥ ቀን ሲመጣ በጨቋኝ ገዢዎች ላይ አላኮረፉም፤ ጥሪያቸውን ከማክበር አልታቀቡም፤ አጋጣሚውን ተጠቅመው እንበቀል አላሉም-ግንባራቸውን ሳያጥፉ በጦሩ ግንባር ተገኝተው ወራሪውን ጦር አንበረከኩ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንጊዜም ለመሪዎቹ ቀና ነው:: መሪዎቹ ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቀና አይደሉም::ከድል በኋላ ለራሳቸው ሞተው እነርሱን ለኩራት ያበቋቸውን ሕዝቦች ወደ ነበረው የጭቆና ሥርዓቶቻቸው መለሷቸው:: ቀን አይቶ ያልከዳቸውን ሕዝብ ከዱ:: ከዚህ የድል ጋር ተያይዞ መነሳት የሚኖርበት አንድ የሚያስቆጭ ነገር አለ:: ይህ ድል የሚያስደስታትን ያህል ኢትዮጵያን የሚያሳፍራት ይመስለኛል:: እስከ ዛሬ ድረስ የድህነት ሰለባ ነች:: ይህ ለጀግና ሕዝብና ሀገር አይመጥንም:: ያን ግዙፍ ታሪክ ያሳንሳል፤ ያን አንፀባራቂ ድል ያደበዝዛል:: ኢትዮጵያ ያገኘችውን ድል እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ነበረባት:: ድልና ቁጭት ባንድ ላይ የማይደክም ጉልበት ሊፈጥሩላት ይገባ ነበር:: ከድህነት ጋር መዋጋት የሕይወት መጥፋት፤ የደም መፍሰስ፤ የአጥንት መከስከስ፤ የሀብት መናጋት አይጠይቅም::
ከዚህ ሁሉ ኪሳራ ነፃ ነው:: ለሀገሩ ነፃነት ሲል ለሕይወቱ ያልሳሳ ሕዝብ ለሀገር ልማት ለሚውል ጉልበትና ዕውቀት እንደምን ሳሳ? ድህነትን መዋጋት የሚጠይቀው በጣም ርካሽ ነገሮች ናቸው-ደግሞም ሁሉም በውስጣችን ናቸው:: እነዚህ ቁርጠኛ አመራር፤ የሰው ጉልበትና ዕውቀት፤ ቅንነትና አስተዋይነት፤ ቁጭትና ትጋት ናቸው:: የቁርጠኛና ብልህ፤ የአስተዋይና በሳል አመራር መታጣት ኢትዮጵያ በወራሪዎችና በቅኝ-ገዢዎች ላይ የተቀዳጀችውን ድል በኢኮኖሚ፤ በማሕበራዊና ባሕላዊ ሕይወት ማስቀጠል ሳያስችላት ቀረ::
የኢትዮጵያ መንግሥታት በሀገራቸውና በሚመሩት ሕዝብ የሚተማመኑ አይደሉም:: በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን በደል ልባቸው ያውቃል:: ስለዚህ ይፈሩታል:: ለሁሉም የጀርባ አጥንት ሆነው በሕዝብ ላይ የማይገባ በደል እንዲያደርሱ የሚረዱአቸው አንዳንድ የውጭ መንግሥታት ናቸው:: የሀገሬው ሕዝብ የሚማረርባቸውን መሪዎች ወደ ቤተ መንግሥታቸው ጠርተው ሽልማት የሚሰጧቸው፤ በማዕረግ የሚያንቆጡቁጧቸው ወይም ክብር ለማይገባቸው የክብር ማዕረግ በመስጠት የልብ ልብ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ የውጭ መንግሥታት ናቸው:: ሌሎች መንግሥታት ለመሪዎቻችን የሚሰጡትን ክብር የኢትዮጵያ ሕዝብ አይጠላም::
ይሁን እንጂ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ገዳይና ጨፍጫፊ የሆኑ መሪዎችን መሸለም ለአስቀያሚ ሥራቸው እውቅና የመስጠት ያክል መሆኑን ግን ይረዳል:: ያንድ የፖለቲካ ሥርዓት የደም ሥር መዘዋወር የሚኖርበት በተገዢው ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ነው:: ይህን የሚያውቅ መንግሥታዊ ሥርዓት ለራሱ መኖር ብቻ ሳይሆን የሀገርንና የሕዝብን አቅም ማፈርጠም የሚችል ነው:: ይህን መረዳት የማይችል ግን አወዳደቁ የማያምር ብቻ ሳይሆን ሀገርንና ሕዝብን የሚያዳክም ነው፡፡ ዛሬ ጎልቶ የሚታየው የሀገር ሳይሆን የመንደር፤ የቀበሌ፤ የጎጥና የግለሰብ ፖለቲካ ነው::
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በአግባቡ የሚወክል የፖለቲካ ማሕበር መኖሩ ያጠራጥራል:: ለሀገርና ለሕዝብ የሚጨነቁ ዜጎች የሉም ማለት ግን አይደለም:: የሴራና የጠለፋ ፖለቲካ በሚደራው ተንኮል ምክንያት ጎልቶና ደምቆ የሚወጣ ድምጽ ግን የላቸውም:: በቁጥር ከመቶ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን እንዳሉ ይነገራል:: በዚያው ልክ የአስተሳሰብ፤ የአመለካከት ወይም የርዕዮተዓለም ልዩነት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም::
በእርግጠኝነት የሐሳብ ድግግሞሽ ይኖራል::ሁሉም እንደ ፖለቲካ ፓርቲነታቸው ለሥልጣን የሚታገሉ መሆናቸው የሚካድ አይደለም:: በዚህ መልክ ለሥልጣን መፎካከር ግን ለራሳቸው፤ ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ችግር ነው::በዚህ ቁመና ችግርን ማወሳሰብ እንጂ መፍትሔን ማምጣት ያስቸግራል:: ከዚህ አንድ እውነት ማረጋገጥ ይቻላል::
ፖለቲከኞቻችን ዛሬም የሚገኙት ከትናንቱ ቦታቸው ነው:: የመፍትሔ ሳይሆን የችግር አካል ሆነው መቆየትን የመረጡ ይመስላል:: የችግር ቀጠና ውስጥ ሆነው ሌላ ችግር እየጋበዙን ነው::ይህን መረዳት የማይችሉ ከሆነ ፖለቲከኛ መሆናቸውን መጠራጠር ያስፈልጋል:: ትልቁ የሀገራችን ፖለቲከኞች ውድቀት ራሳቸውን የችግሩ አካል አድርገው አለማየታቸው ነው:: ለችግሮች ሁሉ ሌላውን ምክንያት ማድረግ ቀላል ነው:: የሚከብደው የመፍትሔ አካል ካልሆኑ የችግር አካል መሆን የግድ መሆኑን መረዳት ነው:: በተጠቀሰው አሰላለፍ ውስጥ ቆሞ «እኔ የመፍትሔ እንጂ የችግሩ አካል አይደለሁም» ማለት አንድም ጅልነት ነው፤ አሊያም ቅጥፈት ነው::ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባለፉት አራት እና አምስት አስርተዓመታት በፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ቆይተዋል:: አሁንም እዚያው ትርምስ ውስጥ ናቸው:: ሁሌም ከትርምስ ያላለፈ ትርምስ ያተራምሳቸዋል:: ከጥሬነት ወደ ብስለት የማያሸጋግር ትርምስ፤ ሁሌም ፍሬ የማይሰጥ ትርምስ:: የኢትዮጵያን ፖለቲካና ፖለቲካኞች ጊዜ፤ ፈተና፤ ውድቀት፤ ትምህርት፤ ዕድሜና ምክር አያበስላቸውም:: መፈጠርን፤ ማደግን፤ ማርጀትንና በመጨረሻ መሞትን የማያውቅ ፖለቲካ ነው ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው ሲተላለፍ የቆየው:: ለራሱ እንደ ቀጨጨ፤ ሀገሪቱንና ሕዝቧን እንዳቀጨጨ አሁንም ቀጥሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2012
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ